Monday, January 26, 2026

❖ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፦


"በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።"

             (ራዕ.14:13)


" እንግዲህ። በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው።"

(ዮሐ 8:24)


1ኛ፡ ጌታን ያመኑ እርሱ ኃጢአት ሆኖና ኃጢአታቸውን ተሸክሞ ሞቶላቸዋልና ሲያንቀላፉ "በጌታ" 1ተሰ፡4÷14 ላይ ደግሞ "በኢየሱስ" ተብሏል። 


በጌታ ያላመኑ ከነኃጢአታቸው በምድር፣ ለዘላለምም ይሞታሉ። 


2ኛ፡ በጌታ አንቀላፍተን፣ ወደ የትም ሳይሆን ወደዚያው ጌታ መሄዳችንን ስናስብ ነፍሳችን ደስታ ሞላት። 


" ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል።"

(የሐዋርያት ሥራ 7:59)


3ኛ፡ ጉዞአችን ከጌታ ጋር ወደ መኖር  መሆኑን ስናስተውል፣ የተከሰተው ነገር ሌላ ሳይሆን የኑሮ ለውጥ ነው  ብላ ነፍሳችን ሐሴት አደረገች። 


"ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤"

( ፊል.1:23)


> ለክርስቲያን ብቻ ጥቅም (ፊል፡1÷21) እንዲሁም አጋር በሆነው (1ቆሮ፡3÷22) ሞት ትራንስፓርትነት ተሻግሮ፣ ኑሮ በአብ ቤት ከኢየሱስ ጋር፣ ቀድመው ከንቀላፉት አእላፍ ቅዱሳን ጋር!


4ኛ፡ ታዲያ አሁን የገጠመንን እንዴት እንገልፀዋለን ስንል፣ 2ቆሮ፡5 እና 2ጴጥ፡1 ትዝ አሉን። 

የገጠመን  ምንም ሳይሆን በአንድም ይሁን በሌላ የማይቀረው የጊዜያዊው ድንኳን መፍረስ ነው፤ የማይፈርስ ሰማያዊ ክቡር አካል እንደሚጠብቀን ማሰብ ልብን ያሳርፋል::


" ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።"

(2ኛቆሮ.5:1)


5ኛ፡ ከሁሉም በላይ ካመኑት ወገኖቻችን፣ ለዘላለም ላንለያይ እንደምንገናኝ ማወቃችን ደግሞ ሙሉ መተማመን ሰጥቶናል። ጌታ ሊመጣ በደጅ እንደሆነ እናውቃለን። 


(1ኛተሰ. ምዕ. 4)

----------

16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤


17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።


> የጌታ ባንሆን ምን ይውጠን ነበር? የጌታ መሆናችን ስንቱን ነገር ለዋወጠው? 

   ጌታ ሆይ ስምህ ይባረክ!!!