Tuesday, March 24, 2026

❖የቃየል መንገድ፤

ከውድቀት በኋላ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በመሥዋዕት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ እናስተውላለን፡፡ ሰው በእግዚበብሔር መልክነት እንደምሳሌው የኖረባቸው ጊዜያት እጅግ የተወደዱና የመለኮትን አሳብ መታዘዝ የታየባቸው ቢሆኑም ሰው እንዲህ ያለውን ቅዱስ ሕብረት ጠብቆ የዘለቀው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡
       እግዚአብሔር ለሰው የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድሞ በመፍጠር ሰውን በተጠናቀቀና በተዋበ ዓለም በማስቀመጥ ምን ያህል አሳቢና አፍቃሪ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ ዳሩ ግን ሰው ከነበጀቱ እንደ ዔደን ገነት ባለው ያማረ ስፍራ መቀመጡ ደግሞም ሊጠቀም የሚችልበት ብዙ አማራጭ መሐል መመላለሱ ፈጣሪውን ላለመበደል አቅም አልሆነውም፡፡ ስለዚህ ባለመታዘዝ ጠንቅ ኃጢአት በአንድ ሰው አዳም ምክንያት ወደ ዓለም ገባ፡፡ ከዚህ የተነሣ ሰው እግዚአብሔር ፊት የሚቆምበት መንፈሳዊ ድፍረትና ተቀባይነት አጣ፡፡
       አዳም ከበደለ በኋላ በመልኩ እንደ ምሳሌው ልጅ በመውለዱ ኃጢአተኝነት ለሰው ሁሉ ደረሰ (ዘፍ. 5÷1)፡፡ ይህ ክፍል እኔ ባልበደልኩትና በስፋራው ላይ ተገኝቼ ባልበላሁት ከአዳም ኃጢአት ጋር ስለ ምን እደመራለሁ? ለሚለው የአንዳንድ ሰዎች ሙግት ከበቂ በላይ ምላሽ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር አዳምን በመልኩ (ጽድቅ፣ ቅድስናና እውቀት) እንደ ምሳሌው (ምድርን መግዛት) እንደፈጠረው ከተረዳን (ዘፍ. 1÷26) ከውድቀት በኋላ ኃጢአተኛው አዳም በመልኩ (ኃጢአተኝነት) እንደ ምሳሌው (ፍርሃት) ልጅ በመውለዱ ኃጢአት በዘር የሚደርስ (orginal sin) ሆኖአል፡፡ 
        አቤልና ቃየልን የምናገኛቸው በዘፍጥረት ምዕራፍ አራት ላይ ሲሆን ርእሳችን የሚገኘው ደግሞ በይሁዳ መልእክት ውስጥ ነው፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍና በይሁዳ መልእክት መካከል የብዙ ዘመናት ልዩነት አለ፡፡ ዳሩ ግን በሁለቱም ዘመናት ውስጥ አንድ መንገድ እንመለከታለን፡፡ ይህም የቃየል መንገድ ነው (ይሁዳ 11)፡፡ የቃየል መንገድ በአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በስህተት አስተማሪዎች ምክንያት ጠላት በስንዴው መካከል ከዘራቸው እንክርዳድ ትምህርቶች አንዱ ነው፡፡ እንደነዚህ ላሉቱ እግዚአብሔር ያለውን መልእክት ሐዋርያው ሲናገር “ወዮላቸው” በማለት ነው፡፡ ይህም የመንገዱን አስከፊነት እንዲሁም የቅጣቱን ክብደት የምንረዳበት እጅግ ግልጥ የሆነ ማሳያ ነው፡፡
        የያዕቆብ ወንድም የይሁዳ መልእክት አንድ ምእራፍ ያለው ቢሆንም በውስጡ የያዘው ትምህርት ግን በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሾልከው ስለ ገቡ የስህተት ትምህርቶች፣ የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ስለሚለውጡ ሴሰኛች፣ ንጉሣችንንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚክዱ ዓመፀኛች፣ ሥጋቸውን ስለሚያረክሱ ግድየለሾች፣ ጌትነትን ስለሚጥሉ ትዕቢተኞች፣ ሥልጣን ያላቸውን ስለሚሳደቡ ሰነፎች እንዲሁም ውኃ ስለሌለባቸው ደመናዎች (የስህተት አስተማሪዎች) በመልእክቱ ውስጥ ከተጠቀሱት አሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ መልእክቱን በማስተዋል ሆነን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ብናጠናው ልባችንን  የሚሞላና ለነፍሳችን የሚረባ ብዙ ትምህርት እንዳለው አምናለሁ፡፡
        “ከብዙ ቀን በኋላም ቃየል ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም (ዘፍ. 4÷4)” የመጀመሪያዎቹ ቤተሰቦቻችን የመጀመሪያ ልጆች ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው ብዙ ብልሽቶች ጽንሰትና ውልደት የሚጀምረው ከላይ ባለበብነው ክፍል ላይ ነው፡፡ በእድሜያችን የምንሠራው በጎም ሆነ ክፉ ተግባር በወደፊቱ ትውልድ ላይ የሚኖረው መልካምም ሆነ መጥፎ ተጽእኖ ግልጽና ብዙ ነው፡፡
        ወንድማማቾቹ በመሠዊያው ፊት መሥዋዕታቸውን ይዘው ሲቀርቡ እነርሱ ብቻ አይደሉም የተለያዩት ከእነርሱ በኋላ የተነሣውም ትውልድ መሠዊያው ፊት ሲደርስ እየተለያየ ነው የኖረው፡፡ ስለመለያየት ስናወራ እነሆ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ ቀራንዮ መስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን ሁለት ወንበዴዎች እናስታውሳቸዋለን፡፡ በመስረቅ ብቻ ሳይሆን በመግደልም ሕብረት አድርገው የኖሩ፤ ፍቅራቸው በክፉ ባልንጀርነት ላይ የተመሰረተ ዓመፀኞች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ራሱን የዘላለም መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው፣ ስለ ሁሉ በሞተው በአንዱ በክርስቶስ ደግሞም ለዘላለም ሞታችን ማርከሻ የዘላለም ሕይወት በሆነው ጌታ መስማማት አልቻሉም፡፡ አንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ሲመሰክር ሌላው ደግሞ እኔነቱንና ትምክህቱን አሳየ፡፡ ይህም ለሁለቱ ባልንጀሮች የአንድና የሁለት ቀን ሳይሆን የዘላለም ልዩነት ሆነ፡፡

❖የገላትያ አዚም፤


          የእግዚአብሔርን ሕልውና የተቀበልንበት መንገድ እምነት ነው፡፡ እርሱን ያየውና የዳሰሰው የለም፡፡ ስለ እርሱ ከሰማነው ቃል የተነሣ ግን ወደ ማመን ከፍታ መምጣ ሆኖልናል፡፡ በእርሱና በእኛ መካከል ያለው መግባባት የተመሰረተው በእምነት ላይ እንደሆነ ለልባችን ማስረገጥ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ በረከት የምንቀበለው የእግዚአብሔርን ሕልውና በተቀበልንበት መንገድ ነው፡፡ ራሱን በማመን ሰጥቶን የእርሱ የሆነውየገን እንደ ትጋታችን መጠን ሊሰጠን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስጦታው ጸጋ (የማይገባ) ነው!
          ሐዋርያው ለገላትያ ሰዎች በፃፈው መልእክት “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች  ሆይ በአይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? (ገላ. 3÷1)” በማለት መጠይቃዊ ተግሳጽ ሲያስተላልፍ እናስተውላለን፡፡ የገላትያ ሰዎች ከሚያስመካው የእግዚአብሔር ጽድቅ ይልቅ በራሳቸው ጥረት የተመኩ ነበሩ፡፡ በሕግና በነቢያት የተመሰከረለትን ነገር ግን ያለ ሕግ የተገለጠውን የመለኮት ጽድቅ በሥጋቸው ውስጥ ካለው ትምክህት የተነሣ ገፍተውት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲያማ ክርስቶስ በከንቱ ሞቶአል? እስኪል ድረስ የሕዝቡ ድንዛዜ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ዋጋ ያሳጣ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ ለእውነት እንዳይታዘዙ ልባቸው ደነደነ፡፡
          ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ (2 ቆሮ. 4÷4) ተብሎ እንደተፃፈ የዲያብሎስ ውጊያ ከአሳባችን ጋር ነው፡፡ አሳባችንን ማሳወር! ሰው ደግሞ ልቡ (አሳብ) ካላየ አይኑ አያስተውልም፡፡ በተለይ በእምነት ውስጥ ስንኖር የዚህ እውነት ተግባራዊነት ግልጽ ይሆናል፡፡ በአንድ ሰው ውስጥ ያለው ትልቁ ሐብት አሳቡ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ የተባለው፡፡ ጉብዝናችንን እግዚአብሔርን ካላሰብንበት ሽምግልናችን የጸጸት ይሆናል፡፡ የምድሪቱ ጩኸት ምንድነው ካልን መልሱ “የአስተሳሰብ ለውጥ” የሚል ነው፡፡ ሐዋርያው የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሲል አእምሮ የሌላችሁ ማለቱ አይደለም፡፡ እየሰማችሁ የማትረዱ፣ እያያችሁ የማትቀበሉ፣ በተገለጠው እውነት የማታምኑ ማለቱ ነው፡፡
          ተግባራዊ ወደሆነው ሕይወታችን ስንመጣ የገላትያ አዚም በግልጥ ይስተዋላል፡፡ አዚም መፍዘዝንና መደብዘዝን የሚያመለክት ቃል ሲሆን ይህም ከድግምት ኃይል ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የሥራ ብዛት፣ የጤና መቃወስ፣ የእድሜ ሕፃንነት ያመጣው መንፈሳዊ ችግር ሳይሆን እግዚአብሔር በልጁ የሠራውን ማዳን ባለማስተዋል፣ ከመንፈሳዊ ጤና ማጣትና በቃሉ ካለማደግ ጨቅላነት የሚመጣ ድንዛዜ ነው፡፡ ይህም የዚህ ዓለም አምላክ በተባለው ሰይጣን አጋዥነት የሚከወን ድርጊት ነው፡፡
         ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናስታውሰው ያዘዘን ሞቱንና ውርደቱን ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ታሪክ መቀየር ያለው እርሱ በመስቀል ላይ ኃጢአታችንን ተሸክሞ የሕግ እርግማን ሆኖ በመሞቱ ነው (ዘዳ. 21÷23)፡፡ እኛ የተዋረድንበትን ቀን ሌሎች አይደሉም እኛው ራሳችን እንኳን ልናስበው አንፈልግም፡፡ ቤታችን ላይ የሚሰቀለው ፎቶ እንኳ ምቾታችንን የሚያሳየው ተመርጦ ነው፡፡ ከስተን ጠቁረን የተነሣነው የት ነው የሚቀመጠው? ጌታ ግን በእጅና በእግሮቹ ላይ ችንካር እንዳለፈ፣ ፊቱ ላይ ምራቅ እንደተተፋ፣ ራሱ ላይ የእሾህ አክሊል እንደደፋ፣ ጀርባው በጅራፍ እንደተገረፈ፣ በየሸንጎው እንደተንገላታ፣ እርጥብ እንጨት ተሸክሞ ተራራው ላይ ደፋ ቀና እንዳለ አስቡት ሲል አላፈረም፡፡
          ለጠፋው መልካችን መልክ የሆነን ባየነው ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደምግባት የለውም ተብሎለት ነው (ኢሳ. 53÷2)፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ስለ መተላለፋችን የቆሰለ ስለ በደላችን የደቀቀ እርሱ ነው፡፡ ከመስቀሉ ጋር የተያያዘው ሕይወት ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ የሰጠው ጌታ ነው፡፡ የምናከብረውም እንደ ወንበዴ የተሰቀለልንን ፃድቅ ክርስቶስን ነው፡፡ በኃጢአት ምክንያት ያጣነው መልካችን ጽድቅ፣ ቅድስና እና እውቀት የተመለሰው ክርስቶስ መልክ ሆኖልን ነው፡፡ እርሱ ደምግባት የለውም ቢባልለትም መልካችን ነውና አናፍርበትም፡፡ በመልኩ የሚያፍር የለምና፡፡
          በኃጢአት ምክንያት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ (ኤፌ. 2÷14) የፈረሰው እርሱን እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ ስላቆመው ነው (ሮሜ. 3÷25)፡፡ ሁላችንም እንደሚገባን በሁለት ሰዎች መሐል ለረጅም ጊዜ ጸብ ቆሞ ከነበረ የሚፈርሰው እርቅ በመካከላቸው ሲቆም ነው፡፡ አለዚያ ቦታው ባዶ ሊሆን አይችልም፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያገኘነው በልጁ በክርስቶስ ክርስቲያን በሆንበት መታወቅ ነው፡፡ ሁላችንም ዳግም የእግዚአብሔር የሆነው በልጁ በክርስቶስ ቤዛነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ መታወቂያችን ነው፡፡ ታዲያ ልጁ የሌለው ሕይወት የለውም ቢባል ምን ይደንቃል?
           ዳሩ ግን ይህንን ሁሉ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነት እንዳናስተውል ደግሞም ለእውነቱ እንዳንታዘዝ በኑሮአችን ውስጥ ልዩ ልዩ አዚም ጋርዶን ይስተዋላል፡፡ ሐዋርያው በፊታችሁ እንደተሰቀለ ሆኖ ይላል፡፡ እለት እለት በፊታችን እናስተውለው ዘንድ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገልን ውለታ በግልጥ ተስሏል፡፡ የእግዚአብሔር ውለታ ደግሞ ወቅት እየጠበቅን የምንዘክረው ሳይሆን በየጊዜው የምናከብረውና ልባችን ላይ ትልቁን ስፍራ የያዘ ሐቅ ሊሆን አግባብ ነው፡፡
            እርሱ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንዴት ራሱን እንዳዋረደ ስናስተውል ክብሬ ብለን አንሟገትም፡፡ እርሱ ሕማማችንን እንዴት እንደተሸከመ ስናስተውል ሕመማችንን ቆጥረን አንማረርም፡፡ እርሱ በመከራ እንዴት እንደደቀቀ ስንረዳ የሰዎች ማሳዘን፣ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ የሕይወት ፈተናችን ሁሉ ይፈወሳል፡፡ ተወዳጆች ሆይ የተሰቀለውን እዩ! ደግሞም ስላደረገው ሁሉ ልባዊ በሆነ መንገድ ስሙን አክብሩ፡፡ 
          በገላትያ ምእመናን ላይ የተስተዋለው አዚም ግን ለዘላለም አይግዛን!!     

❖አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ

‹‹በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም።›› (2 ሳሙ. 14፡25)፤ ‹‹ . . አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።›› (2 ሳሙ. 15፡6)!

           ውበት የሰውን ልብ የመግዛት ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ ውበት በተለያየ መንገድ እንደ መስፈርት ጥቅም ላይ ሲውልም እናያለን፡፡ ሰዎች ለውበታቸው ስፍራ እንደሚሰጡ፤ ብዙ ወጪ እንደሚመድቡ ልናስተውልም እንችላለን፡፡ ውበት ልብን ይሰርቃል፤ ውበት አቋም ያስለውጣል፤ ውበት ለሰዎች ዓይን ርሀብ ጥጋብ ይሆናል፤ ውበት ምኞት በረሃ ላደረገው አእምሮ እንደ ጥሩ ምንጭ ነው፡፡ ይስሐቅ በርብቃ ውበት ከእናቱ ሞት ተጽናንቷል (ዘፍ. 24፡27)፤ ያዕቆብ ስለ ራሔል ውበት ለአጎቱ ለላባ አሥራ አራት ዓመት ተገዝቶአል (ዘፍ. 29፡17)፤ ንጉሥ አርጤክስስ በአመፀኛይቱ አስጢን ፈንታ ለአስቴር ውበት እጅ ሰጥቶአል (መጽሐፈ አስቴር 2፡17)፡፡

          ውበት ሰዎችን ከእውነት ፈቀቅ፤ ከሕሊና ዝቅ ያደርጋል፡፡ ንጉሡ ዳዊት በቤርሳቤህ ውበት ሚዛን ስቶ ነፍስ እስከ ማስጠፋት ደርሶአል (2 ሳሙ. 11፡2-4፤ 14-17)፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ፍቅር የተለበጠው ንጉሡ ሰሎሞን የአህዛብን ጣዖታት ወደ ማምለክ የነዳው የአህዛብ ሴቶች ውበት ፍቅር ነው (1 ነገ. 11፡1)፤ ሳሙኤልን በዓይኑ ፊት ‹‹እግዚአብሔር እንደሚያይ እንዳያይ›› ያደረገው የኤልያብ ውበት ነው (1 ሳሙ. 16፡6)፡፡


          ሶምሶንን ለጥፋቱ የልቡን ሁሉ እንዲገልጥ ያስገደደው የደሊላ ውበት ፍቅር ነው (መሳ. 16፡18)፤ ሕዝቅኤልን የዓይን አምሮት የሆነበት፤ ለተቀሰፈችው ሚስቱ በደረቁ ሀዘን ያስቀመጠው የገዛ አጋሩ ውበት ነው (ሕዝ. 24፡16)፤ አምኖንን ያስተከዘና ለሕመም የዳረገው፤ ሲያልፍም ያረከሰው የእህቱ ትዕማር ውበት ፍቅር ነው (2 ሳሙ. 13፡2)፤ የጲጥፋራ ሚስት በዮሴፍ ውበት ክፉ አስባለች (ዘፍ. 39፡6-10)፤ ውበትን የታከከ ፍቅር ለውድቀት የሆነባቸው ታሪኮች ብዙ ናቸው፡፡ ምድራችን ላይ ውበት ለእግዚአብሔር ክብር ከዋለበት ይልቅ ለአመጽ መሣሪያነት በእጅጉ አገልግሏል፡፡

         ያለፉ ድርጊቶችን ከታሪክ መለስ ብለን ስናገላብጥ በውበታቸው ክፉ ምክርን ያስፈጸሙ፤ መንግሥት ያናወጠ ሴራ ጫፍ ያደረሱ፤ አቅል አስተው ለስሜት የተነጠፈውን ለሞት ሽኝት ያደረጉ ሰዎችን እንደርስባቸዋለን፡፡ ቆነጃጅት እንደ ፍልጥ ሰዎች ለለኮሱት ግጭት ተማግደዋል፤ የባለ ጠጎች ማጫወቻም መጫወቻም ሆነዋል፡፡ ቆንጆ የተፈጥሮ አበባ ገበያ ላይ እንደሚውል፤ ሕሊናቸውን በሸጡና ለዚህም በሚተባበሩ ቆነጃጅት አየር ባየር የሰው ንግዶች ዓለም ላይ ደርተዋል፡፡ ስለ ውበት ብዙ ልንል እንደምንችል እንዳለ ሆኖ ወደ ተነሣንበት ርዕስ እንመለስ፡፡ 

           አቤሴሎም የስሙ ትርጉም ‹‹አባቴ ሰላም ነው›› የሚል ሲሆን፤ ለነቢዩ ዳዊት እጅግ የሚወደው ልጁም ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ስፍራ ደግመን በማናነበው መልኩ የአቤሴሎምን ውበት ‹‹ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር ያልነበረበት›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ስለ ጸጉሩ ውበት እንኳ ‹‹ጠጉሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቆረጠው ነበር፤ ሲቆረጥም የራሱ ጠጉር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር›› (2 ሳሙ. 14፡26) ይለናል (አንድ ሰቅል አስራ ሁለት ግራም ያህል ይመዝናል)፡፡ በዚህ ሁሉ አገላለጽ አቤሴሎም ምን ያህል ውብ እንደ ነበር ልንረዳ ይቻለናል፡፡

         አቤሴሎም የንጉሥ ልጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውበቱ፤ የአባቱን መንግሥት ለመገልበጥና ዙፋን ላይ ለመቀመጥ የእስራኤልን ልብ ለመስረቅ ጠቅሞታል (2 ሳሙ. 15፡6)፡፡ በዚህም ሴራ ለአቤሴሎም ቁስ ሳይሆን ልቡን የሰጠው የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁለት መቶ ነበር፤ እነርሱም የሚሆነውን ነገር ከቶ ሳያውቁ በየዋህነት የተዋበውን አቤሴሎም ተከተሉት (2 ሳሙ. 15፡11)፡፡ አቤሴሎም ሕቡዕ በሆነ ሴራው ከአባቱ ከንጉሥ ዳዊት የሚሸሸውን እና ወደ እርሱ የሚተባበረውን ሕዝብ እያበዛ ሄደ፡፡ አባቱ በዙፋን እያለም በኬብሮን ቀንደ መለከት አስነፍቶ ንጉሥ መሆኑን አወጀ፡፡

        የአቤሴሎም ክፋት አዛኝ ነው፡፡ አካሄዱም ማስተዋል ለሌለው ሰው በቀላሉ ግልጥ አልነበረም፡፡ አቤሴሎም ለእህቱ ለትዕማር የሚቆሮቆር፤ እግዚአብሔር የሾመው ዳዊትን ግን የሚያሳድድ ነበር፡፡ ከአመጸኛነቱ የተነሣ ሰው መጥራ ሲፈልግ እንኳ ‹‹እርሻውን አቃጥሉት›› የሚል ነበር፡፡ አቤሴሎም ወንድሙ አምኖንን ለማስገደል ሁለት ዓመት ከራሱ ልብ ጋር ሴራውን የመከረ፤ ይህንንም ለመፈጸም እንደ ንጉሥ ያለ ግብዣ ያዘጋጀ፤ ለሟች ወንድሙ የሚሰክርበትን ያስጠመቀ ነው፡፡ አባቱን የዙፋን ስደተኛ አድርጎ መካሮቹ በሰገነት ላይ በደኮኑለት ድንኳን ውስጥ ያባቱን ቁባቶች ያስነወረም ነበር፡፡

        የዳዊት መንግሥት ባለበት የእስራኤል ግዛት ውስጥ በወንድሙ ላይ የሞት ፍርድን ያስተላለፈ፤ ወንድሙን ለሞቱ በስካር ያጠገበ ነው (2 ሳሙ. 13፡28)፤ አባቱን ዳዊትን ደግሞ ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ያሳደደ ነው (2 ሳሙ. 15፡30)፡፡ አቤሴሎም የአባቱን ዙፋን ፍርድ በሕዝቡ ዘንድ ያክፋፋ፤ እጁን ዘርግቶ ያስም የነበረ ‹‹በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?›› የሚል ምኞት ያሰከረው ምስኪን ነበር፡፡ አቤሴሎም የዳዊት መካር የሆነውን አኪጦፌልን በማሳመን በንጉሡ በአባቱ በዳዊት ላይ ሴራው ጽኑ ሆነለት (2 ሳሙ. 15፡12)፤ ዳዊትም ከልጁ ከአቤሴሎም ሸሸ (15፡14)፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ በዳዊት ሕይወት የምንመለከታቸው ውድቀቶች እራሳቸውን የቻሉ የምልከታ ምእራፎች መሆናቸው እንዳለ ሆኖ እያየነው ያለነው የአባትነትን ሥፍራ ያላከበረውን የአቤሴሎምን ሕይወት ነው፡፡ ነቢዩ ሳሙኤልን ልኮ ዳዊትን የቀባው እግዚአብሔር ነው (1 ሳሙ. 16፡12-13)፤ የሳሙኤልን ዓይኖች በተመለከተ እግዚአብሔር ሲናገር ‹‹ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል›› አለው (1 ሳሙ. 16፡7)፡፡ አቤሴሎም ከራሱ እስከ እግሩ ነውር እንደ ሌለበት ተነግሮናል፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ልብና ኩላሊትን ይመረምራል (መዝ. 7፡9)፡፡ አቤሴሎም የእስራኤልን ልብ መስረቅ የቻለ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ልብ ግን አላገኘውም፡፡

       እግዚአብሔር ለእርሱ የተዋበ የሆነውን ‹‹እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ›› አለ (ሐዋ. 13፡22)፡፡ ምን ጊዜም እግዚአብሔር ልቡ ያለው እንደ ልቡ ምክር በሆነው ነገር ነው፤ ፈቃዱም የሚከናወነው እንደ ዘላለም አሳቡ ነው፡፡ የሰው ሩጫ የማይቀድመው፤ የሰው ጥበብ የማይጠበበው እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ የአቤሴሎም ውበት እግዚአብሔር የቀባውን ለመሸፈን፤ ሲያልፍም ስፍራውን ለመያዝ የቀናው ቢመስልም የነገሮች መጨረሻ ግን ‹‹እግዚአብሔር አትራፊ ነው›› ይላል፡፡ ለአቤሴሎም ደግሞ እጅግ ኪሳራ!

       በነቢዩ በዳዊት መዝሙር ‹‹ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ።›› (መዝ. 44፡2) የተባለለትን ውብ እናያለል፡፡ መዝሙሩ የቆሬ ልጆች ትምህርት ነውና ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም የጻፈው ቅኔ እንደ ሆነ ልናስብ አንችልም፡፡ ይልቁንም ከትምህርቱ ትንቢታዊ ይዘት የምንረዳው በቀጥታ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት እንድናመራ የሚጋብዘን መሆኑን ነው፡፡

       ‹‹የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፤ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፤ እኛም አላከበርነውም›› (ኢሳ. 53፡1-3)፤ በዚህ የትንቢት ክፍል ከአቤሴሎም የሚበልጠውን፤ ውበቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ የሚያምረውን እናስተውላለን፤ ክርስቶስ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ!

      ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው›› (ዕብ. 4፡15) የተባለለት ክርስቶስ ነው፡፡ አቤሴሎም ውጫዊ መልኩ የሚማርክ እንደ ሆነ ብናውቅም፤ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም የተባለለት ጌታ፤ አብ ደስ የተሰኘበት ውበት ነው (ማቴ. 3፡17)፡፡ በአቤሴሎም ራስ ላይ በአመት አንድ ጊዜ የሚቆረጥ ብዙ ጠጉር የነበረ ሲሆን፤ ክርስቶስ ግን በራሱ ላይ የሾህ አክሊልን የደፋ ነው፡፡ በአቤሴሎም ራስ ላይ ያለው ጠጉር ከሚመዝነው ሰቅል በላይ ኢየሱስ ስለ ሁላችንም ኃጢአት በራሱ ላይ የተጫነው የእሾህ አክሊል እጅግ ይከብዳል፡፡ ክርስቶስ ኃጢአት የሌለበት ንጹሕ ነውና፡፡

      ጌታችን ኢየሱስ ‹‹ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና›› (ዮሐ. 6፡38) እንዳለ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ ነው፡፡ እኔና አብ አንድ ነን (ዮሐ 10፡30) በማለት በምድር ላይ የአባቱን ውበት ያሳየ የመለኮት ሙላት ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ የባሪያን መልክ የያዘ ቢሆንም፤ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገ ቢሆንም፤ በምስሉ እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን ያዋረደ ቢሆንም፤ ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ቢሆንም (ፊል. 2፡7) ከራሱ እስከ እግሩ ነውር የሌለበት ቤዛችን ክርስቶስ እርሱ ብቻ ነው፡፡

       ዓለም እንደ አቤሴሎም ባለ ውበት ብትሽቆጠቆጥ ለክብር የሚጋፉ፤ ለታይታ የሚተራመሱ፤ በሴራ ጉሽ የሰከሩ አደባባይ ናት፡፡ ለእኛ እውነተኛው አቤሴሎም ነውር የሌለበት ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው፡፡ ስለ አቤሴሎም ‹‹በላያችን እንዲሆን የቀባነው›› (2 ሳሙ. 19፡10) በማለት ሕዝቡ በሰልፍ ለሞተው አቤሴሎም ቁጭታቸውን ሲገልጹ እናነባለን፡፡ ክርስቶስን በተመለከተ፤ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?›› ባላቸው ጊዜ ጴጥሮስ ‹‹ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ›› አለ (ሉቃ. 9፡20)፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀባውን ክብርና ስፍራ ማንም ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሊወስድ አይቻለውም፡፡

       አቤሴሎምን ለዚህ ክፋት ምክንያቱ የነበረውንና የሕይወቱን ፍጻሜ እንመልከት፡፡ ‹‹አቤሴሎምም ሕያው ሳለ፡- ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሐውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር›› (2 ሳሙ. 18፡18) የሚል ተጽፎ እናነባለን፤ እንዲሁም ሞቱን ‹‹አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር በበቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ ራሱም በዛፉ ተያዘ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፤ ተቀምጦበትም የነበረው በቅሎ አለፈ›› (2 ሳሙ. 18፡18) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን፡፡

       የአቤሴሎም ፍጻሜ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ አቤሴሎም ከስሙ ጋር የተያያዘ ፍላጎት እንደ ነበረው አስተውለናል፡፡ በርግጥ አቤሴሎም በዚህ ስፍራ እንዳነበብነው ልጅ ያልነበረው አልነበረም (2 ሳሙ. 14፡27)፡፡ ነገር ግን ዙፋኑ የዳዊት ስለ ነበር አቤሴሎምን የራሱ ልጆች እንኳ ከንግሥና ጋር በተያያዘ ሊያስቡት አይችሉም፡፡ ስለዚህ በንጉሥ ሸለቆ ለራሱ ሐውልት አቆመ፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ በሆነው እኛ እንዳንቆም ይርዳን፡፡ አቤሴሎም እንዳሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ እንደዚያ ያለ ሴረኛ በኤፍሬም ዱር ውስጥ ያለ አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ አንጠለጠለው፤ አቤሴሎም ውበቱ ጥፋቱ ሆነበት፡፡

        ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ክብሩ ሳይሆን ስለ ክብራችን ራሱን አዋረደ፤ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መስቀል ላይ ሞተ፡፡ አቤሴሎም ስለ ስሙ በምድርና በሰማይ መካከል በአንዲት ቅርንጫፍ ተንጠልጥሎ በጋሻ ጃግሬዎች ተመትቶ ሞተ፡፡ እርሱም በዱር ባለ በታላቅ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ እጅግ ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ሸፈነው (2 ሳሙ. 18፡17)፤ የአቤሴሎም መታሰቢያው እንዲህ ሆነ፡፡ የተወደዳችሁ ሆይ፤ ክርስቶስ ስለ ሁላችንም መከራን ተቀብሎ፤ ሞቶ ከሞት ተነሥቶአል፡፡ ሁሉን በእርሱ ስም እናደርገው ዘንድ እርሱ ዛሬም ሕያው ነው፡፡

       በራሳችን ስም ለራሳችን የሚቆም ሐውልት የለም፡፡ ‹‹. . እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት›› (ቆላ. 3፡17) እንደ ተባለ፤ ለዚህ ሕያውና የሚሠራ ቃል መታዘዝ ያስፈልገናል፡፡ በብሉይ ኪዳን የተተረከልን አቤሴሎም ዛሬ የለ ይሆናል፤ ዳሩ ግን መንፈሱ ባመኑና በሚያገለግሉ ላይ ይሠራል፡፡ እንዲህ ባለው ርኩሰት ራስን አለማሳደፍ እግዚአብሔር ‹‹እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ፤ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ፡፡›› (መዝ. 2፡6) ያለለትን ልጁን ክርስቶስን በተግባር ማክበር ነው፡፡ ከሰማይ ወደ እኛ የወረደ ውበት፤ በአብ ዘንድ መታያ ውበት፤ በዘመናችን ሁሉ ዝርግፍ ጌጥ፤ በመለኮት ዙፋን ፊት የምንታይበት የውበት ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 8፡29)!