Tuesday, April 7, 2026

❖ሕማማት፦

ሕማማተ ክርስቶስ፡ በጌታችን ኢየሱስ ላይ የተሸረበው ሴራ።
በአራቱ ወንጌላውያን ሐተታ።
*** ማቴዎስ 26:1-5***
" ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ሁሉ ጨርሶ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ "ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንደሚሆን ታውቃላችሁ፥ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል።" በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብ ሽማግሌዎችም ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በተንኰል ይዘው ሊገድሉት ተማከሩ፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ "በበዓል አይሁን" አሉ።
ቅዱስ ማቴዎስ የሕማማቱን ታሪክ የሚጀምረው ጌታችን ኢየሱስ ሊፈጸሙ ባሉት ክስተቶች ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዳለው በማጉላት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ስለሚመጣው መያዙና መሰቀሉ ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ይሰጣቸዋል። ይህ ስለ ሕማማቱ ከተናገራቸው አራት ተከታታይ ትንቢቶች (ማቴ= 16:21፤ 17:22-23፤ 20:18-19) የመጨረሻው ሲሆን፣ ይህም ሕማማቱ የኢየሱስ ሕይወትና ተልዕኮ ዋና አካል መሆኑን ያሳያል።
"ኢየሱስም እነዚህን ቃላት ሁሉ ጨርሶ" የሚለው የመክፈቻ ሐረግ፣ ማቴዎስ በወንጌሉ ውስጥ ዋና ዋና ሽግግሮችን ለመለየት የሚጠቀምበት ነው። ይህም የወንጌሉ ዋና መዋቅር የሆኑትን አምስቱን ታላላቅ ንግግሮች ማጠቃለያ ያመለክታል ( ማቴ=7:28፤ 11:1፤ 13:53፤ 19:1 እንመልከት)።
ቅዱስ ማቴዎስ እዚህ ጋር "ሁሉ" የሚለውን ቃል የጨመረው፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የማስተማር አገልግሎቱን አሁን ማጠናቀቁን ለማመልከት ነው። የኢየሱስ የመጨረሻ ንግግር ስለ ብሉይ ኪዳን ዘመን ፍጻሜ የተናገረው የምጽአት ትምህርት (ማቴ 24-25) ነበር።
ይህ ሽግግር የጌታችን የኢየሱስን የትምህርት አገልግሎት ከሕማማቱ ጋር ያገናኘዋል፤ እንዲሁም በምጽአት ( በ70 ዓ/ም በኢየሩሳሌም ላይ ለፍርድ የሚመጣበት ወቅት) ትምህርቱ ላይ የተገለጸውን የከበረውን የሰው ልጅ፣ ሕማማትን ሊቀበል ካለው መከራ የሰው ልጅ ጋር ጎን ለጎን ያነጻጽረዋል።
ቅዱስ ማቴዎስ በፋሲካ በዓልና በኢየሱስ ሞት መካከል ያለውን ግንኙነት በግልጽ ያሳያል። ይህንን ንጽጽር በጌታችን ኢየሱስ ትንቢት ውስጥ በማስቀመጥ፣ ወንጌላዊው ግንኙነቱ በአጋጣሚ ሳይሆን የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል መሆኑን ያሳያል። የኢየሱስ ሞትና በመጨረሻው እራት የሚታሰበው መታሰቢያው፣ ለአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ እውነተኛው የፋሲካ መሥዋዕት ነው።
የዚህ ድርብ ትዕይንት ሁለተኛ አጋማሽ የጌታችን ኢየሱስን ግልጽ እውቀትና ዝግጁነት፣ ከሴራ አጋዥዎቹ ምስጢራዊነትና ተንኰል ጋር ያነጻጽረዋል። የአይሁድ መሪዎች በጌታችን ኢየሱስ ሕፃንነት ጊዜ ሕይወቱን ለማጥፋት በሄሮድስ ዙሪያ እንደተሰበሰቡ ሁሉ (ማቴ=2:4)፣ አሁንም ጌታችን ኢየሱስን ለመግደል ከሊቀ ካህናቱ ጋር ይማከራሉ። የሊቀ ካህናቱን ስም ቀያፋ ብሎ የጠቀሰው ማቴዎስ ብቻ ነው። ምንም እንኳ መሪዎቹ ብዙ የመንፈሳዊ ተጓዦች ሁከት ሊያስነሱ ይችላሉ በሚል ፍርሃት በፋሲካ በዓል ወቅት ላለማሰር ቢወስኑም፣ የኢየሱስ ትንቢታዊ ቃል ግን ጊዜው የማይቀር መሆኑን አረጋግጧል።
*** ማርቆስ 14:1-2***
በጌታችን ኢየሱስ ላይ የተሸረበው ሴራ፡ በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ሐተታ።
ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቅዱስ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን "በበዓል አይሁን" ይሉ ነበር።
ቅዱስ ማርቆስ የሕማማቱን ታሪክ የሚጀምረው እነዚህን የመጨረሻ ክስተቶች ከአይሁድ የፋሲካ በዓል አውድ ጋር በማያያዝ ነው። በየዓመቱ ፋሲካ የሚከበረው እስራኤላውያን ከባርነት ወደ ነፃነት የወጡበትን ቤዛነት ለማስታወስ ነበር። እንደ ሁሉም የአይሁድ በዓላት፣ ፋሲካም የሚጀምረው ፀሐይ ስትጠልቅ ነበር። በዓሉ ከመጀመሩ በፊት ባለው ከሰዓት በኋላ፣ የፋሲካው በግ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይሰዋል።
በዚያ ምሽት በሚደረገው የፋሲካ እራት፣ የዘፀአት (ከግብፅ መውጣት) ክስተቶች ይተረካሉ፣ ይታሰባሉም። ከግብፅ በችኮላ መውጣታቸውንና በበረሃ የተቀበሉትን መከራ ለማስታወስ፣ ለእራቱና ከዚያ በኋላ ላሉት ሰባት ቀናት የሚበላው እርሾ የሌለበት እንጀራ (ቅዱስ) ብቻ ነበር።
ፋሲካ ከሐሙስ ፀሐይ መግቢያ እስከ ዓርብ ፀሐይ መግቢያ ድረስ የሚከበር በመሆኑ፣ በማርቆስ የዘመን አቆጣጠር መሠረት በጌታችን ኢየሱስ ላይ የታሰበው ሴራ የጀመረው ረቡዕ ዕለት ነው።
ማርቆስ በወንጌሉ ውስጥ የካህናት አለቆችንና ጻፎችን ደጋግሞ ይጠቅሳል። ጻፎች በዚያ ዘመን የነበሩ የሕግ ባለሙያዎችና የሃይማኖት ሊቃውንት ነበሩ። ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር የነበረው ግጭት ከወንጌሉ መጀመሪያ (ማር= 1:22) ጀምሮ እያደገ መጥቶ በሕማማቱ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። የካህናት አለቆች ደግሞ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ሊቃነ ካህናት እንደ አማካሪ ያገለግሉ ነበር። ኢየሱስ ስለ ሕማማቱ በተናገራቸው ትንቢቶች ውስጥ እነርሱን መጥቀስ ጀምሮ ነበር (ማር=8:31)።
በወንጌሉ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ፣ ጌታችን ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ ለሞት አሳልፈው እንደሚሰጡት ዘወትር ይተነብይ ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎቹ ጌታችን ኢየሱስ በሕዝቡ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በመፍራት በበዓሉ ወቅት ላለማሰር ወስነው ነበር። ሆኖም፣ ሁኔታው በእነርሱ ቁጥጥር ሥር አልነበረም፤ ጌታችን ኢየሱስም በትክክል እስራኤል የነፃነት በዓሏን በሚያከብሩበት ዕለት ይሞታል።
*** ሉቃስ 22:1-6***
በጌታችን ኢየሱስ ላይ የተሸረበው ሴራ
ፋሲካ የሚባለው የቅዱስ በዓልም ቀረበ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና እንዴት አድርገው እንዲገድሉት ይፈልጉ ነበር። ከአሥራ ሁለቱም ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ሰይጣን ገባበት፤ ሄዶም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከሰራዊት አለቆች ጋር ተነጋገረ። እነርሱም ደስ አላቸው፥ ብርም ሊሰጡት ተስማሙ። እሺም አለ፥ ሕዝብ በሌለበት አሳልፎ የሚሰጥበትን አመቺ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
እንደሌሎቹ ወንጌላውያን ሁሉ፣ ቅዱስ ሉቃስም የሕማማቱን ታሪክ መቼት በፋሲካ በዓል ወቅት ያደርገዋል። በመጀመሪያ ለየቅል የነበሩት የፋሲካ እና የቅዱስ (እርሾ የሌለበት እንጀራ) በዓላት አሁን እንደ አንድ በዓል ይከበራሉ። ቅዱስ ሉቃስ የጌታችን ኢየሱስን ሕማማት እንደ አዲስ የነፃነት (የቤዛነት) ክስተት እንዲረዱት አንባቢዎቹን አዘጋጅቷቸዋል። በደብረ ታቦር (በተራራው ላይ) ጌታችን፡ ኢየሱስ በተለወጠ ጊዜ፣ ሙሴና ኤልያስ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ሊፈጽመው ስላለው "መውጣቱ" (ዘጸአት) ተነጋግረው ነበር (ሉቃ=9:30)።
ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን ኢየሱስን ለማጥፋት በተሸረበው ሴራ ውስጥ አዲስ ተዋናይን ያስተዋውቃል። ከካህናት አለቆች፣ ከጻፎችና ከይሁዳ በተጨማሪ ስለ ሰይጣን ሚና ይናገራል። ይሁዳ በሴራው ውስጥ ያለው ተሳትፎ ሰይጣን በእርሱ ውስጥ በመግባቱ እንደሆነ ተገልጿል። ሰይጣን እዚህ ጋር የሚኖረው ሚና በምድረ በዳ በነበረው ፈተና ወቅት ተዘጋጅቶ ነበር። ዲያብሎስ በፈተናው ከወደቀ በኋላ፣ "እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ" ( ሉቃ=4:13) ተብሎ ነበር።
አሁን ሕማማቱ ሰይጣን ጌታችን ኢየሱስንና ተከታዮቹን ለማጥቃት የሚያገኘው አመቺ ጊዜ ሆኗል። የሐዋርያትን ተልዕኮ "ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ" (ሉቃ=10:18) በማለት የገለጸው ሉቃስ፣ አሁን የሕማማቱን ታሪክ ኢየሱስ ከክፉ ኃይላት ጋር የሚያደርገው ታላቅ ፍልሚያ አድርጎ ያቀርበዋል።
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ፡ አይሁድ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሸረቡትን ሴራ፡ ሳይገልጽ፡ የሕማማቱን ታሪክ ከታሰረበት ቀን ከረቡዕ ይጀምራል።

Tuesday, March 24, 2026

❖የቃየል መንገድ፤

ከውድቀት በኋላ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በመሥዋዕት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ እናስተውላለን፡፡ ሰው በእግዚበብሔር መልክነት እንደምሳሌው የኖረባቸው ጊዜያት እጅግ የተወደዱና የመለኮትን አሳብ መታዘዝ የታየባቸው ቢሆኑም ሰው እንዲህ ያለውን ቅዱስ ሕብረት ጠብቆ የዘለቀው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡
       እግዚአብሔር ለሰው የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድሞ በመፍጠር ሰውን በተጠናቀቀና በተዋበ ዓለም በማስቀመጥ ምን ያህል አሳቢና አፍቃሪ መሆኑን አሳይቶናል፡፡ ዳሩ ግን ሰው ከነበጀቱ እንደ ዔደን ገነት ባለው ያማረ ስፍራ መቀመጡ ደግሞም ሊጠቀም የሚችልበት ብዙ አማራጭ መሐል መመላለሱ ፈጣሪውን ላለመበደል አቅም አልሆነውም፡፡ ስለዚህ ባለመታዘዝ ጠንቅ ኃጢአት በአንድ ሰው አዳም ምክንያት ወደ ዓለም ገባ፡፡ ከዚህ የተነሣ ሰው እግዚአብሔር ፊት የሚቆምበት መንፈሳዊ ድፍረትና ተቀባይነት አጣ፡፡
       አዳም ከበደለ በኋላ በመልኩ እንደ ምሳሌው ልጅ በመውለዱ ኃጢአተኝነት ለሰው ሁሉ ደረሰ (ዘፍ. 5÷1)፡፡ ይህ ክፍል እኔ ባልበደልኩትና በስፋራው ላይ ተገኝቼ ባልበላሁት ከአዳም ኃጢአት ጋር ስለ ምን እደመራለሁ? ለሚለው የአንዳንድ ሰዎች ሙግት ከበቂ በላይ ምላሽ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር አዳምን በመልኩ (ጽድቅ፣ ቅድስናና እውቀት) እንደ ምሳሌው (ምድርን መግዛት) እንደፈጠረው ከተረዳን (ዘፍ. 1÷26) ከውድቀት በኋላ ኃጢአተኛው አዳም በመልኩ (ኃጢአተኝነት) እንደ ምሳሌው (ፍርሃት) ልጅ በመውለዱ ኃጢአት በዘር የሚደርስ (orginal sin) ሆኖአል፡፡ 
        አቤልና ቃየልን የምናገኛቸው በዘፍጥረት ምዕራፍ አራት ላይ ሲሆን ርእሳችን የሚገኘው ደግሞ በይሁዳ መልእክት ውስጥ ነው፡፡ በዘፍጥረት መጽሐፍና በይሁዳ መልእክት መካከል የብዙ ዘመናት ልዩነት አለ፡፡ ዳሩ ግን በሁለቱም ዘመናት ውስጥ አንድ መንገድ እንመለከታለን፡፡ ይህም የቃየል መንገድ ነው (ይሁዳ 11)፡፡ የቃየል መንገድ በአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በስህተት አስተማሪዎች ምክንያት ጠላት በስንዴው መካከል ከዘራቸው እንክርዳድ ትምህርቶች አንዱ ነው፡፡ እንደነዚህ ላሉቱ እግዚአብሔር ያለውን መልእክት ሐዋርያው ሲናገር “ወዮላቸው” በማለት ነው፡፡ ይህም የመንገዱን አስከፊነት እንዲሁም የቅጣቱን ክብደት የምንረዳበት እጅግ ግልጥ የሆነ ማሳያ ነው፡፡
        የያዕቆብ ወንድም የይሁዳ መልእክት አንድ ምእራፍ ያለው ቢሆንም በውስጡ የያዘው ትምህርት ግን በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሾልከው ስለ ገቡ የስህተት ትምህርቶች፣ የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ስለሚለውጡ ሴሰኛች፣ ንጉሣችንንና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚክዱ ዓመፀኛች፣ ሥጋቸውን ስለሚያረክሱ ግድየለሾች፣ ጌትነትን ስለሚጥሉ ትዕቢተኞች፣ ሥልጣን ያላቸውን ስለሚሳደቡ ሰነፎች እንዲሁም ውኃ ስለሌለባቸው ደመናዎች (የስህተት አስተማሪዎች) በመልእክቱ ውስጥ ከተጠቀሱት አሳቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ መልእክቱን በማስተዋል ሆነን በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ብናጠናው ልባችንን  የሚሞላና ለነፍሳችን የሚረባ ብዙ ትምህርት እንዳለው አምናለሁ፡፡
        “ከብዙ ቀን በኋላም ቃየል ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም (ዘፍ. 4÷4)” የመጀመሪያዎቹ ቤተሰቦቻችን የመጀመሪያ ልጆች ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው ብዙ ብልሽቶች ጽንሰትና ውልደት የሚጀምረው ከላይ ባለበብነው ክፍል ላይ ነው፡፡ በእድሜያችን የምንሠራው በጎም ሆነ ክፉ ተግባር በወደፊቱ ትውልድ ላይ የሚኖረው መልካምም ሆነ መጥፎ ተጽእኖ ግልጽና ብዙ ነው፡፡
        ወንድማማቾቹ በመሠዊያው ፊት መሥዋዕታቸውን ይዘው ሲቀርቡ እነርሱ ብቻ አይደሉም የተለያዩት ከእነርሱ በኋላ የተነሣውም ትውልድ መሠዊያው ፊት ሲደርስ እየተለያየ ነው የኖረው፡፡ ስለመለያየት ስናወራ እነሆ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ ቀራንዮ መስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን ሁለት ወንበዴዎች እናስታውሳቸዋለን፡፡ በመስረቅ ብቻ ሳይሆን በመግደልም ሕብረት አድርገው የኖሩ፤ ፍቅራቸው በክፉ ባልንጀርነት ላይ የተመሰረተ ዓመፀኞች ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን ራሱን የዘላለም መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበው፣ ስለ ሁሉ በሞተው በአንዱ በክርስቶስ ደግሞም ለዘላለም ሞታችን ማርከሻ የዘላለም ሕይወት በሆነው ጌታ መስማማት አልቻሉም፡፡ አንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ሲመሰክር ሌላው ደግሞ እኔነቱንና ትምክህቱን አሳየ፡፡ ይህም ለሁለቱ ባልንጀሮች የአንድና የሁለት ቀን ሳይሆን የዘላለም ልዩነት ሆነ፡፡

❖የገላትያ አዚም፤


          የእግዚአብሔርን ሕልውና የተቀበልንበት መንገድ እምነት ነው፡፡ እርሱን ያየውና የዳሰሰው የለም፡፡ ስለ እርሱ ከሰማነው ቃል የተነሣ ግን ወደ ማመን ከፍታ መምጣ ሆኖልናል፡፡ በእርሱና በእኛ መካከል ያለው መግባባት የተመሰረተው በእምነት ላይ እንደሆነ ለልባችን ማስረገጥ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ በረከት የምንቀበለው የእግዚአብሔርን ሕልውና በተቀበልንበት መንገድ ነው፡፡ ራሱን በማመን ሰጥቶን የእርሱ የሆነውየገን እንደ ትጋታችን መጠን ሊሰጠን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስጦታው ጸጋ (የማይገባ) ነው!
          ሐዋርያው ለገላትያ ሰዎች በፃፈው መልእክት “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች  ሆይ በአይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? (ገላ. 3÷1)” በማለት መጠይቃዊ ተግሳጽ ሲያስተላልፍ እናስተውላለን፡፡ የገላትያ ሰዎች ከሚያስመካው የእግዚአብሔር ጽድቅ ይልቅ በራሳቸው ጥረት የተመኩ ነበሩ፡፡ በሕግና በነቢያት የተመሰከረለትን ነገር ግን ያለ ሕግ የተገለጠውን የመለኮት ጽድቅ በሥጋቸው ውስጥ ካለው ትምክህት የተነሣ ገፍተውት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲያማ ክርስቶስ በከንቱ ሞቶአል? እስኪል ድረስ የሕዝቡ ድንዛዜ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ዋጋ ያሳጣ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ ለእውነት እንዳይታዘዙ ልባቸው ደነደነ፡፡
          ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ (2 ቆሮ. 4÷4) ተብሎ እንደተፃፈ የዲያብሎስ ውጊያ ከአሳባችን ጋር ነው፡፡ አሳባችንን ማሳወር! ሰው ደግሞ ልቡ (አሳብ) ካላየ አይኑ አያስተውልም፡፡ በተለይ በእምነት ውስጥ ስንኖር የዚህ እውነት ተግባራዊነት ግልጽ ይሆናል፡፡ በአንድ ሰው ውስጥ ያለው ትልቁ ሐብት አሳቡ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ የተባለው፡፡ ጉብዝናችንን እግዚአብሔርን ካላሰብንበት ሽምግልናችን የጸጸት ይሆናል፡፡ የምድሪቱ ጩኸት ምንድነው ካልን መልሱ “የአስተሳሰብ ለውጥ” የሚል ነው፡፡ ሐዋርያው የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሲል አእምሮ የሌላችሁ ማለቱ አይደለም፡፡ እየሰማችሁ የማትረዱ፣ እያያችሁ የማትቀበሉ፣ በተገለጠው እውነት የማታምኑ ማለቱ ነው፡፡
          ተግባራዊ ወደሆነው ሕይወታችን ስንመጣ የገላትያ አዚም በግልጥ ይስተዋላል፡፡ አዚም መፍዘዝንና መደብዘዝን የሚያመለክት ቃል ሲሆን ይህም ከድግምት ኃይል ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የሥራ ብዛት፣ የጤና መቃወስ፣ የእድሜ ሕፃንነት ያመጣው መንፈሳዊ ችግር ሳይሆን እግዚአብሔር በልጁ የሠራውን ማዳን ባለማስተዋል፣ ከመንፈሳዊ ጤና ማጣትና በቃሉ ካለማደግ ጨቅላነት የሚመጣ ድንዛዜ ነው፡፡ ይህም የዚህ ዓለም አምላክ በተባለው ሰይጣን አጋዥነት የሚከወን ድርጊት ነው፡፡
         ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናስታውሰው ያዘዘን ሞቱንና ውርደቱን ነው፡፡ ምክንያቱም የእኛ ታሪክ መቀየር ያለው እርሱ በመስቀል ላይ ኃጢአታችንን ተሸክሞ የሕግ እርግማን ሆኖ በመሞቱ ነው (ዘዳ. 21÷23)፡፡ እኛ የተዋረድንበትን ቀን ሌሎች አይደሉም እኛው ራሳችን እንኳን ልናስበው አንፈልግም፡፡ ቤታችን ላይ የሚሰቀለው ፎቶ እንኳ ምቾታችንን የሚያሳየው ተመርጦ ነው፡፡ ከስተን ጠቁረን የተነሣነው የት ነው የሚቀመጠው? ጌታ ግን በእጅና በእግሮቹ ላይ ችንካር እንዳለፈ፣ ፊቱ ላይ ምራቅ እንደተተፋ፣ ራሱ ላይ የእሾህ አክሊል እንደደፋ፣ ጀርባው በጅራፍ እንደተገረፈ፣ በየሸንጎው እንደተንገላታ፣ እርጥብ እንጨት ተሸክሞ ተራራው ላይ ደፋ ቀና እንዳለ አስቡት ሲል አላፈረም፡፡
          ለጠፋው መልካችን መልክ የሆነን ባየነው ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደምግባት የለውም ተብሎለት ነው (ኢሳ. 53÷2)፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ስለ መተላለፋችን የቆሰለ ስለ በደላችን የደቀቀ እርሱ ነው፡፡ ከመስቀሉ ጋር የተያያዘው ሕይወት ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ የሰጠው ጌታ ነው፡፡ የምናከብረውም እንደ ወንበዴ የተሰቀለልንን ፃድቅ ክርስቶስን ነው፡፡ በኃጢአት ምክንያት ያጣነው መልካችን ጽድቅ፣ ቅድስና እና እውቀት የተመለሰው ክርስቶስ መልክ ሆኖልን ነው፡፡ እርሱ ደምግባት የለውም ቢባልለትም መልካችን ነውና አናፍርበትም፡፡ በመልኩ የሚያፍር የለምና፡፡
          በኃጢአት ምክንያት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ (ኤፌ. 2÷14) የፈረሰው እርሱን እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ ስላቆመው ነው (ሮሜ. 3÷25)፡፡ ሁላችንም እንደሚገባን በሁለት ሰዎች መሐል ለረጅም ጊዜ ጸብ ቆሞ ከነበረ የሚፈርሰው እርቅ በመካከላቸው ሲቆም ነው፡፡ አለዚያ ቦታው ባዶ ሊሆን አይችልም፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያገኘነው በልጁ በክርስቶስ ክርስቲያን በሆንበት መታወቅ ነው፡፡ ሁላችንም ዳግም የእግዚአብሔር የሆነው በልጁ በክርስቶስ ቤዛነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ መታወቂያችን ነው፡፡ ታዲያ ልጁ የሌለው ሕይወት የለውም ቢባል ምን ይደንቃል?
           ዳሩ ግን ይህንን ሁሉ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነት እንዳናስተውል ደግሞም ለእውነቱ እንዳንታዘዝ በኑሮአችን ውስጥ ልዩ ልዩ አዚም ጋርዶን ይስተዋላል፡፡ ሐዋርያው በፊታችሁ እንደተሰቀለ ሆኖ ይላል፡፡ እለት እለት በፊታችን እናስተውለው ዘንድ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገልን ውለታ በግልጥ ተስሏል፡፡ የእግዚአብሔር ውለታ ደግሞ ወቅት እየጠበቅን የምንዘክረው ሳይሆን በየጊዜው የምናከብረውና ልባችን ላይ ትልቁን ስፍራ የያዘ ሐቅ ሊሆን አግባብ ነው፡፡
            እርሱ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንዴት ራሱን እንዳዋረደ ስናስተውል ክብሬ ብለን አንሟገትም፡፡ እርሱ ሕማማችንን እንዴት እንደተሸከመ ስናስተውል ሕመማችንን ቆጥረን አንማረርም፡፡ እርሱ በመከራ እንዴት እንደደቀቀ ስንረዳ የሰዎች ማሳዘን፣ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ የሕይወት ፈተናችን ሁሉ ይፈወሳል፡፡ ተወዳጆች ሆይ የተሰቀለውን እዩ! ደግሞም ስላደረገው ሁሉ ልባዊ በሆነ መንገድ ስሙን አክብሩ፡፡ 
          በገላትያ ምእመናን ላይ የተስተዋለው አዚም ግን ለዘላለም አይግዛን!!     

❖አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ

‹‹በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም።›› (2 ሳሙ. 14፡25)፤ ‹‹ . . አቤሴሎምም የእስራኤልን ሰዎች ልብ ሰረቀ።›› (2 ሳሙ. 15፡6)!

           ውበት የሰውን ልብ የመግዛት ከፍተኛ አቅም አለው፡፡ ውበት በተለያየ መንገድ እንደ መስፈርት ጥቅም ላይ ሲውልም እናያለን፡፡ ሰዎች ለውበታቸው ስፍራ እንደሚሰጡ፤ ብዙ ወጪ እንደሚመድቡ ልናስተውልም እንችላለን፡፡ ውበት ልብን ይሰርቃል፤ ውበት አቋም ያስለውጣል፤ ውበት ለሰዎች ዓይን ርሀብ ጥጋብ ይሆናል፤ ውበት ምኞት በረሃ ላደረገው አእምሮ እንደ ጥሩ ምንጭ ነው፡፡ ይስሐቅ በርብቃ ውበት ከእናቱ ሞት ተጽናንቷል (ዘፍ. 24፡27)፤ ያዕቆብ ስለ ራሔል ውበት ለአጎቱ ለላባ አሥራ አራት ዓመት ተገዝቶአል (ዘፍ. 29፡17)፤ ንጉሥ አርጤክስስ በአመፀኛይቱ አስጢን ፈንታ ለአስቴር ውበት እጅ ሰጥቶአል (መጽሐፈ አስቴር 2፡17)፡፡

          ውበት ሰዎችን ከእውነት ፈቀቅ፤ ከሕሊና ዝቅ ያደርጋል፡፡ ንጉሡ ዳዊት በቤርሳቤህ ውበት ሚዛን ስቶ ነፍስ እስከ ማስጠፋት ደርሶአል (2 ሳሙ. 11፡2-4፤ 14-17)፤ ውስጡ በኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ፍቅር የተለበጠው ንጉሡ ሰሎሞን የአህዛብን ጣዖታት ወደ ማምለክ የነዳው የአህዛብ ሴቶች ውበት ፍቅር ነው (1 ነገ. 11፡1)፤ ሳሙኤልን በዓይኑ ፊት ‹‹እግዚአብሔር እንደሚያይ እንዳያይ›› ያደረገው የኤልያብ ውበት ነው (1 ሳሙ. 16፡6)፡፡


          ሶምሶንን ለጥፋቱ የልቡን ሁሉ እንዲገልጥ ያስገደደው የደሊላ ውበት ፍቅር ነው (መሳ. 16፡18)፤ ሕዝቅኤልን የዓይን አምሮት የሆነበት፤ ለተቀሰፈችው ሚስቱ በደረቁ ሀዘን ያስቀመጠው የገዛ አጋሩ ውበት ነው (ሕዝ. 24፡16)፤ አምኖንን ያስተከዘና ለሕመም የዳረገው፤ ሲያልፍም ያረከሰው የእህቱ ትዕማር ውበት ፍቅር ነው (2 ሳሙ. 13፡2)፤ የጲጥፋራ ሚስት በዮሴፍ ውበት ክፉ አስባለች (ዘፍ. 39፡6-10)፤ ውበትን የታከከ ፍቅር ለውድቀት የሆነባቸው ታሪኮች ብዙ ናቸው፡፡ ምድራችን ላይ ውበት ለእግዚአብሔር ክብር ከዋለበት ይልቅ ለአመጽ መሣሪያነት በእጅጉ አገልግሏል፡፡

         ያለፉ ድርጊቶችን ከታሪክ መለስ ብለን ስናገላብጥ በውበታቸው ክፉ ምክርን ያስፈጸሙ፤ መንግሥት ያናወጠ ሴራ ጫፍ ያደረሱ፤ አቅል አስተው ለስሜት የተነጠፈውን ለሞት ሽኝት ያደረጉ ሰዎችን እንደርስባቸዋለን፡፡ ቆነጃጅት እንደ ፍልጥ ሰዎች ለለኮሱት ግጭት ተማግደዋል፤ የባለ ጠጎች ማጫወቻም መጫወቻም ሆነዋል፡፡ ቆንጆ የተፈጥሮ አበባ ገበያ ላይ እንደሚውል፤ ሕሊናቸውን በሸጡና ለዚህም በሚተባበሩ ቆነጃጅት አየር ባየር የሰው ንግዶች ዓለም ላይ ደርተዋል፡፡ ስለ ውበት ብዙ ልንል እንደምንችል እንዳለ ሆኖ ወደ ተነሣንበት ርዕስ እንመለስ፡፡ 

           አቤሴሎም የስሙ ትርጉም ‹‹አባቴ ሰላም ነው›› የሚል ሲሆን፤ ለነቢዩ ዳዊት እጅግ የሚወደው ልጁም ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ስፍራ ደግመን በማናነበው መልኩ የአቤሴሎምን ውበት ‹‹ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር ያልነበረበት›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ስለ ጸጉሩ ውበት እንኳ ‹‹ጠጉሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቆረጠው ነበር፤ ሲቆረጥም የራሱ ጠጉር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር›› (2 ሳሙ. 14፡26) ይለናል (አንድ ሰቅል አስራ ሁለት ግራም ያህል ይመዝናል)፡፡ በዚህ ሁሉ አገላለጽ አቤሴሎም ምን ያህል ውብ እንደ ነበር ልንረዳ ይቻለናል፡፡

         አቤሴሎም የንጉሥ ልጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውበቱ፤ የአባቱን መንግሥት ለመገልበጥና ዙፋን ላይ ለመቀመጥ የእስራኤልን ልብ ለመስረቅ ጠቅሞታል (2 ሳሙ. 15፡6)፡፡ በዚህም ሴራ ለአቤሴሎም ቁስ ሳይሆን ልቡን የሰጠው የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁለት መቶ ነበር፤ እነርሱም የሚሆነውን ነገር ከቶ ሳያውቁ በየዋህነት የተዋበውን አቤሴሎም ተከተሉት (2 ሳሙ. 15፡11)፡፡ አቤሴሎም ሕቡዕ በሆነ ሴራው ከአባቱ ከንጉሥ ዳዊት የሚሸሸውን እና ወደ እርሱ የሚተባበረውን ሕዝብ እያበዛ ሄደ፡፡ አባቱ በዙፋን እያለም በኬብሮን ቀንደ መለከት አስነፍቶ ንጉሥ መሆኑን አወጀ፡፡

        የአቤሴሎም ክፋት አዛኝ ነው፡፡ አካሄዱም ማስተዋል ለሌለው ሰው በቀላሉ ግልጥ አልነበረም፡፡ አቤሴሎም ለእህቱ ለትዕማር የሚቆሮቆር፤ እግዚአብሔር የሾመው ዳዊትን ግን የሚያሳድድ ነበር፡፡ ከአመጸኛነቱ የተነሣ ሰው መጥራ ሲፈልግ እንኳ ‹‹እርሻውን አቃጥሉት›› የሚል ነበር፡፡ አቤሴሎም ወንድሙ አምኖንን ለማስገደል ሁለት ዓመት ከራሱ ልብ ጋር ሴራውን የመከረ፤ ይህንንም ለመፈጸም እንደ ንጉሥ ያለ ግብዣ ያዘጋጀ፤ ለሟች ወንድሙ የሚሰክርበትን ያስጠመቀ ነው፡፡ አባቱን የዙፋን ስደተኛ አድርጎ መካሮቹ በሰገነት ላይ በደኮኑለት ድንኳን ውስጥ ያባቱን ቁባቶች ያስነወረም ነበር፡፡

        የዳዊት መንግሥት ባለበት የእስራኤል ግዛት ውስጥ በወንድሙ ላይ የሞት ፍርድን ያስተላለፈ፤ ወንድሙን ለሞቱ በስካር ያጠገበ ነው (2 ሳሙ. 13፡28)፤ አባቱን ዳዊትን ደግሞ ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ያሳደደ ነው (2 ሳሙ. 15፡30)፡፡ አቤሴሎም የአባቱን ዙፋን ፍርድ በሕዝቡ ዘንድ ያክፋፋ፤ እጁን ዘርግቶ ያስም የነበረ ‹‹በአገር ላይ ፈራጅ አድርጎ ማን በሾመኝ?›› የሚል ምኞት ያሰከረው ምስኪን ነበር፡፡ አቤሴሎም የዳዊት መካር የሆነውን አኪጦፌልን በማሳመን በንጉሡ በአባቱ በዳዊት ላይ ሴራው ጽኑ ሆነለት (2 ሳሙ. 15፡12)፤ ዳዊትም ከልጁ ከአቤሴሎም ሸሸ (15፡14)፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ በዳዊት ሕይወት የምንመለከታቸው ውድቀቶች እራሳቸውን የቻሉ የምልከታ ምእራፎች መሆናቸው እንዳለ ሆኖ እያየነው ያለነው የአባትነትን ሥፍራ ያላከበረውን የአቤሴሎምን ሕይወት ነው፡፡ ነቢዩ ሳሙኤልን ልኮ ዳዊትን የቀባው እግዚአብሔር ነው (1 ሳሙ. 16፡12-13)፤ የሳሙኤልን ዓይኖች በተመለከተ እግዚአብሔር ሲናገር ‹‹ሰው ፊትን ያያል እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል›› አለው (1 ሳሙ. 16፡7)፡፡ አቤሴሎም ከራሱ እስከ እግሩ ነውር እንደ ሌለበት ተነግሮናል፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ልብና ኩላሊትን ይመረምራል (መዝ. 7፡9)፡፡ አቤሴሎም የእስራኤልን ልብ መስረቅ የቻለ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ልብ ግን አላገኘውም፡፡

       እግዚአብሔር ለእርሱ የተዋበ የሆነውን ‹‹እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ›› አለ (ሐዋ. 13፡22)፡፡ ምን ጊዜም እግዚአብሔር ልቡ ያለው እንደ ልቡ ምክር በሆነው ነገር ነው፤ ፈቃዱም የሚከናወነው እንደ ዘላለም አሳቡ ነው፡፡ የሰው ሩጫ የማይቀድመው፤ የሰው ጥበብ የማይጠበበው እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡ የአቤሴሎም ውበት እግዚአብሔር የቀባውን ለመሸፈን፤ ሲያልፍም ስፍራውን ለመያዝ የቀናው ቢመስልም የነገሮች መጨረሻ ግን ‹‹እግዚአብሔር አትራፊ ነው›› ይላል፡፡ ለአቤሴሎም ደግሞ እጅግ ኪሳራ!

       በነቢዩ በዳዊት መዝሙር ‹‹ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል ሞገስ በከንፈሮችህ ፈሰሰ ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ባረከህ።›› (መዝ. 44፡2) የተባለለትን ውብ እናያለል፡፡ መዝሙሩ የቆሬ ልጆች ትምህርት ነውና ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም የጻፈው ቅኔ እንደ ሆነ ልናስብ አንችልም፡፡ ይልቁንም ከትምህርቱ ትንቢታዊ ይዘት የምንረዳው በቀጥታ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት እንድናመራ የሚጋብዘን መሆኑን ነው፡፡

       ‹‹የሰማነውን ነገር ማን አምኖአል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል፤ መልክና ውበት የለውም፤ ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፤ እኛም አላከበርነውም›› (ኢሳ. 53፡1-3)፤ በዚህ የትንቢት ክፍል ከአቤሴሎም የሚበልጠውን፤ ውበቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ይልቅ የሚያምረውን እናስተውላለን፤ ክርስቶስ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ!

      ተወዳጆች ሆይ፤ ‹‹ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው›› (ዕብ. 4፡15) የተባለለት ክርስቶስ ነው፡፡ አቤሴሎም ውጫዊ መልኩ የሚማርክ እንደ ሆነ ብናውቅም፤ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም የተባለለት ጌታ፤ አብ ደስ የተሰኘበት ውበት ነው (ማቴ. 3፡17)፡፡ በአቤሴሎም ራስ ላይ በአመት አንድ ጊዜ የሚቆረጥ ብዙ ጠጉር የነበረ ሲሆን፤ ክርስቶስ ግን በራሱ ላይ የሾህ አክሊልን የደፋ ነው፡፡ በአቤሴሎም ራስ ላይ ያለው ጠጉር ከሚመዝነው ሰቅል በላይ ኢየሱስ ስለ ሁላችንም ኃጢአት በራሱ ላይ የተጫነው የእሾህ አክሊል እጅግ ይከብዳል፡፡ ክርስቶስ ኃጢአት የሌለበት ንጹሕ ነውና፡፡

      ጌታችን ኢየሱስ ‹‹ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና›› (ዮሐ. 6፡38) እንዳለ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመ ነው፡፡ እኔና አብ አንድ ነን (ዮሐ 10፡30) በማለት በምድር ላይ የአባቱን ውበት ያሳየ የመለኮት ሙላት ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ የባሪያን መልክ የያዘ ቢሆንም፤ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገ ቢሆንም፤ በምስሉ እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን ያዋረደ ቢሆንም፤ ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ቢሆንም (ፊል. 2፡7) ከራሱ እስከ እግሩ ነውር የሌለበት ቤዛችን ክርስቶስ እርሱ ብቻ ነው፡፡

       ዓለም እንደ አቤሴሎም ባለ ውበት ብትሽቆጠቆጥ ለክብር የሚጋፉ፤ ለታይታ የሚተራመሱ፤ በሴራ ጉሽ የሰከሩ አደባባይ ናት፡፡ ለእኛ እውነተኛው አቤሴሎም ነውር የሌለበት ከሰማይ የወረደ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነው፡፡ ስለ አቤሴሎም ‹‹በላያችን እንዲሆን የቀባነው›› (2 ሳሙ. 19፡10) በማለት ሕዝቡ በሰልፍ ለሞተው አቤሴሎም ቁጭታቸውን ሲገልጹ እናነባለን፡፡ ክርስቶስን በተመለከተ፤ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?›› ባላቸው ጊዜ ጴጥሮስ ‹‹ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ›› አለ (ሉቃ. 9፡20)፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀባውን ክብርና ስፍራ ማንም ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሊወስድ አይቻለውም፡፡

       አቤሴሎምን ለዚህ ክፋት ምክንያቱ የነበረውንና የሕይወቱን ፍጻሜ እንመልከት፡፡ ‹‹አቤሴሎምም ሕያው ሳለ፡- ለስሜ መታሰቢያ የሚሆን ልጅ የለኝም ብሎ ሐውልት ወስዶ በንጉሥ ሸለቆ ውስጥ ለራሱ አቁሞ ነበር፤ ሐውልቱንም በስሙ ጠርቶት ነበር›› (2 ሳሙ. 18፡18) የሚል ተጽፎ እናነባለን፤ እንዲሁም ሞቱን ‹‹አቤሴሎም ከዳዊት ባሪያዎች ጋር በድንገት ተገናኘ፤ አቤሴሎምም በበቅሎ ተቀምጦ ነበር በበቅሎውም ብዙ ቅርንጫፍ ባለው በታላቅ ዛፍ በታች ገባ ራሱም በዛፉ ተያዘ በሰማይና በምድር መካከል ተንጠለጠለ፤ ተቀምጦበትም የነበረው በቅሎ አለፈ›› (2 ሳሙ. 18፡18) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን፡፡

       የአቤሴሎም ፍጻሜ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡ አቤሴሎም ከስሙ ጋር የተያያዘ ፍላጎት እንደ ነበረው አስተውለናል፡፡ በርግጥ አቤሴሎም በዚህ ስፍራ እንዳነበብነው ልጅ ያልነበረው አልነበረም (2 ሳሙ. 14፡27)፡፡ ነገር ግን ዙፋኑ የዳዊት ስለ ነበር አቤሴሎምን የራሱ ልጆች እንኳ ከንግሥና ጋር በተያያዘ ሊያስቡት አይችሉም፡፡ ስለዚህ በንጉሥ ሸለቆ ለራሱ ሐውልት አቆመ፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ በሆነው እኛ እንዳንቆም ይርዳን፡፡ አቤሴሎም እንዳሰበው ሊሆን አልቻለም፡፡ እንደዚያ ያለ ሴረኛ በኤፍሬም ዱር ውስጥ ያለ አንድ የዛፍ ቅርንጫፍ አንጠለጠለው፤ አቤሴሎም ውበቱ ጥፋቱ ሆነበት፡፡

        ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ክብሩ ሳይሆን ስለ ክብራችን ራሱን አዋረደ፤ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መስቀል ላይ ሞተ፡፡ አቤሴሎም ስለ ስሙ በምድርና በሰማይ መካከል በአንዲት ቅርንጫፍ ተንጠልጥሎ በጋሻ ጃግሬዎች ተመትቶ ሞተ፡፡ እርሱም በዱር ባለ በታላቅ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ እጅግ ታላቅ የሆነ የድንጋይ ክምር ሸፈነው (2 ሳሙ. 18፡17)፤ የአቤሴሎም መታሰቢያው እንዲህ ሆነ፡፡ የተወደዳችሁ ሆይ፤ ክርስቶስ ስለ ሁላችንም መከራን ተቀብሎ፤ ሞቶ ከሞት ተነሥቶአል፡፡ ሁሉን በእርሱ ስም እናደርገው ዘንድ እርሱ ዛሬም ሕያው ነው፡፡

       በራሳችን ስም ለራሳችን የሚቆም ሐውልት የለም፡፡ ‹‹. . እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት›› (ቆላ. 3፡17) እንደ ተባለ፤ ለዚህ ሕያውና የሚሠራ ቃል መታዘዝ ያስፈልገናል፡፡ በብሉይ ኪዳን የተተረከልን አቤሴሎም ዛሬ የለ ይሆናል፤ ዳሩ ግን መንፈሱ ባመኑና በሚያገለግሉ ላይ ይሠራል፡፡ እንዲህ ባለው ርኩሰት ራስን አለማሳደፍ እግዚአብሔር ‹‹እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ፤ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ፡፡›› (መዝ. 2፡6) ያለለትን ልጁን ክርስቶስን በተግባር ማክበር ነው፡፡ ከሰማይ ወደ እኛ የወረደ ውበት፤ በአብ ዘንድ መታያ ውበት፤ በዘመናችን ሁሉ ዝርግፍ ጌጥ፤ በመለኮት ዙፋን ፊት የምንታይበት የውበት ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 8፡29)!  

Friday, February 20, 2026

❖የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት:-

የአዲስ ኪዳን ጥናት በቅኝት መልክ
አዲስ ኪዳን ማለት አዲስ ውል አዲስ ስምምነት ማለት ነው፡፡ ለምን አዲስ ኪዳን ተባለ ስንል ፊተኛውን ኪዳን አስረጅቶ ስለገባና የዘላለም ኪዳን ስለሆነ ነው (ዕብ. 8፥13፤ 1፥1-2)፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳን እንደሚገባ አስቀድሞ በነቢያት ተናግሯል (ኤር. 31፥31-34፤ ዕብ. 8፥8-13)፡፡ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ሲነጻጸሩ አዲሱ ኪዳን ብልጫ አስገኝቷል፡፡ ብሉይ ኪዳን ባሰጣጡ ጊዜያዊ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን ዘላለማዊ ነው (ማቴ. 11፥13፤ ሉቃ. 16፥16)፡፡ ብሉይ ኪዳን የተሰጠው በሙሴ መካከለኛነት ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛነት ተሰጥቷል (ገላ. 3፥19፤ 1ጢሞ. 2፥5)፡፡ ብሉይ ኪዳን ሕዝቡን ሊያድን ስላልቻለ የኲነኔ አገልግሎት ነበረ፤ አዲስ ኪዳን ግን የሕይወት አገልግሎት ነው (2ቆሮ. 3፥7-11)፡፡ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ላይ የተጻፈ የሕግ ግዴታ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በልባችን ጽላት ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ ነው (2ቆሮ. 3፥3)፡፡
የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሰባት በሚያህሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተጻፈ የሃያ ሰባት መጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ እስኪያድርባቸው ጌታን ይከተሉ የነበረው ለምድራዊ ትልቅነት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከተነሣና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ከምድራዊ የክብር አሳብ ተላቀው ሁሉን ጥለው ተከተሉት፡፡ ወንጌሉንም በማይመቹ ሁኔታዎች ለዓለም አደረሱ፡፡ መልእክቶቹን የጻፉት በርቀት የነበሩትን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ለማጽናት ነው፡፡ የመልእክቱ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ግን እኛን ጭምር በዚያ መልእክት ውስጥ ይመለከት ነበር፡፡
አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ የራሱ የሆነ አከፋፈል አለው፡፡ ስለዚህ በአራት ተከፍሎ ይጠናል፡፡ ወንጌል፣ ታሪክ፣ መልእክትና ትንቢት፡፡
                                ወንጌል
ወንጌል የሚባለው ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ ያሉት አራት ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መጸነስ፣ መወለድ፣ መኖርና መሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት በሙሉነት ስለሚተርኩ ወንጌል የሚለውን ስያሜ አግኝተዋል፡፡ ወንጌል ማለት ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ መልእክት ነው (ሮሜ. 1፥3-4)፡፡ ወንጌል ቃሉ ዩአንገሊዎን ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡ ትርጉሙም የምሥራች ቃል ወይም የድኅነት ዜና ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተወልዶ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ዓለምን ማዳኑን ስለሚናገርና ፍርድን የሚጠባበቁ ኃጢአተኞች ተስፋ ስለመጣላቸው ወንጌል ወይም የምሥራች ቃል ተብሏል፡፡
አራቱ ወንጌላት ቀጥተኛ ግባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነት የሚጠይቀውን ሙሉ መንገድ ተጉዞ የሰውን ዘር ከዘላለም ጥፋት ማዳኑ ነው፡፡ ፀሐፊዎቹም ሁለቱ ማለትም ማቴዎስና ዮሐንስ ከጌታ አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት መካከል ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ማርቆስና ሉቃስ ከሐዋርያት ጋር በቅርበት የነበሩ ከእነርሱ የሰሙትን በጥንቃቄ የጻፉ ናቸው፡፡ የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌላት ተመሳሳይ ትረካ ያላቸው ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን በመግለጥ እግዚአብሔር በሰውና በሰው ታሪክ መካከል ያደረገውን ይተርካሉ፡፡ ዮሐንስ ግን በተለየ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ክብር በመግለጥ አምላክነቱን ሰዎች እንዲቀበሉት ይጥራል፡፡ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተገልጦ ያደረገው ተአምርና የተናገረው ቃል ሰማይ ብራና፣ ዕፅዋት ሁሉ ብዕር፣ ውቅያኖስ ሁሉ ቀለም ቢሆኑ ተጽፎ አያልቅም (ዮሐ. 21፥25፤20፥30)፡፡ ለመዳናችን የሚበቃን ግን ተጽፎልናል፡፡


አራቱ ወንጌላት
የማቴዎስ ወንጌል፡- በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ምዕራፍ ካላቸው ሁለት መጻሕፍት አንዱ የማቴዎስ ወንጌል ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁድ ስለሆነ የዘር ሐረግን፣ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ አይሁድ መሢሑን እንዲቀበሉ መሢሑ የአብርሃምና የዳዊት ዘር መሆኑን የሚገልጥ የዘር ፍሰትን ያወሳል፡፡ ለማስረጃም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ በዘር ሐረጉ ግን አይሁድ የማይጠቀሙበትን ስልት በመጠቀም አራት ሴቶችን ጠቅሷል (ማቴ. 1፥4 ቁ. 5.6.16)፡፡ አይሁድ በዘር ሐረግ ውስጥ ሴቶችን አስገብተው አይቆጥሩም ነበርና፡፡ ክርስቶስ ግን የመምጣቱ አንዱ ዓላማ ይህን ልዩነት ለማስወገድ ነበር፡፡
የማርቆስ ወንጌል– ከወንጌላት ትንሽ ምዕራፎች ያሉት የማርቆስ ወንጌል ነው፡፡ የትምህርቱም ስልት የክርስቶስን የእጁን ተአምራት በመግለጥ በዘመኑ የነበሩ ሮማውያንን ለማሳመን ነው፡፡ ጌታችን በተያዘ ሌሊት እርቃኑን በነጠላ ሸፍኖ ይከተለው ነበርና በያዙት ጊዜ ነጠላውን ትቶ ራቁቱን የሸሸው ወጣት ማርቆስ መሆኑን ብዙ ሊቃውንቶች ይናገራሉ (ማር. 14፥51-52)፡፡ እናቱ ቤቷን ለአገልግሎት በመልቀቋ የማርቆስ እናት ቤት የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስያሜ አግኝታለች (ሐዋ. 12፥12-17)፡፡ ማርቆስ ከበርናባስ፣ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ብዙ ጊዜ አገልግሏል፡፡ የጴጥሮስም የመንፈስ ልጁ ነው (1ጴጥ. 5፥13)፡ ወንጌሉን የጻፈውም ከእነዚህ ሐዋርያት በጥልቀት በመጠየቅና በማዳመጥ ነው፡፡
የሉቃስ ወንጌል፡- ሉቃስ ከአሕዛብ ወገን የሆነና በክርስቶስ ያመነ የጳውሎስም ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ነው፡፡ በሙያውም ሐኪም እንደ ነበረ ተጠቅሷል (ቈላ. 4፥14)፡፡ ስለ ክርስቶስም ሙሉ ትረካ ያቀረበ ፀሐፊ ነው፡፡ ወንጌሉን የጻፈው ከአሕዛብ ወገን ለነበረና ላመነ ቴዎፍሎስ ለሚባል ወዳጁ ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን ከዘር ሐረግ ይጀምራል፣ ማርቆስ ከጥምቀቱ ይጀምራል፣ ሉቃስ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኛ ከሆነው ከዮሐንስ መጥምቅ የጽንሰት ዜና ይጀምራል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሉቃስ ወንጌሉንና የሐዋርያት ሥራን ጽፎአል፡፡
የዮሐንስ ወንጌል፡- ዮሐንስ ወንጌላዊ ከሦስቱ ወንጌላት በተለየ ሁኔታ ወንጌሉን ጽፎአል፡፡ ሦስቱ ወንጌላውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆንና ሰብአዊ ቅርበቱን ተርከዋል፡፡ ዮሐንስ ደግሞ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር በማጉላት ጽፎአል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት መቻቻል አለባቸው፡፡ ሰውነቱ አምላክነቱን ጋርዶብን አምልኮ እንዳንነፍገው፣ አምላክነቱ ሰውነቱን ሸፍኖብን እንዳናርቀው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የወንጌላውያኑም ጭንቀት ይህ ነው፡፡ ዮሐንስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ወንጌል፣ ሦስት መልእክታት፣ አንድ የራእይ መጽሐፍ ጽፎአል፡፡
ታሪክ
በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል ተብሎ የሚጠራው አንድ ጥራዝ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የሐዋርያት ሥራ ነው፡፡
የሐዋርያት ሥራ፡- የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሉቃስ ነው፡፡ የጻፈውም ወንጌልን ለጻፈለት ቴዎፍሎስ ለተባለው ወዳጁ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ሲናገር የሐዋርያት ሥራ ደግሞ ከዕርገቱ በኋላ ስላሉት ዐሥር ቀኖችና ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ ይናገራል፡፡ የመጽሐፉ ሙሉ ይዘት ወንጌል ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ከዚያም እስከ መላው ዓለም በእንዴት ያለ ጸጋና ዋጋ መድረሱን የሚተርክ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት አድሮ የሠራው ሥራ በመሆኑ የሐዋርያት ሥራ ቢባልም ታሪኩን ስንዘልቀው ግን “የመንፈስ ቅዱስ ሥራ” ቢባል መልካም ነበር ያሰኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በስፋት የተገለጠው የጴጥሮስና የጳውሎስ አገልግሎት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደ ሌሎቹ መልእክታት በሰላምታ ወይም በምርቃት አይዘጋም፡፡ ይህ የሚያስረዳን የሐዋርያት ሥራ በትውልድ ሁሉ መቀጠሉን ነው፡፡
መልእክት
የአዲስ ኪዳን ሦስተኛው አከፋፈል መልእክት ነው፡፡ መልእክት የሚባሉት ከሮሜ እስከ ይሁዳ ድረስ ያሉት 21 የመጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ ፀሐፊዎቹም ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ናቸው፡፡ የተጻፉትም ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡
የጳውሎስ መልእክታት
ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ድረስ ያሉት ዐሥራ አራት መልእክቶች ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ናቸው፡፡ ጳውሎስ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል አይደለም፡፡ ጌታ ካረገ ከስምንት ዓመት በኋላ ነው የተጠራው፡፡ ክርስትናን በብርቱ ይቃወም በነበረ ሰዓት በደማስቆ መንገድ በመብረቅ ብርሃን ጥሎት፣ ሦስት ቀን ዓይኑን አውሮት በወንጌል አመነ (የሐዋ. 9፥18)፡፡ ከሁሉ ኋላ የተጠራ ቢሆንም ከሐዋርያት ይልቅ ሮጧል፣ ዋጋ ከፍሏል፣ አብያተ ክርስቲያናትን መሥርቷል፣ መልእክታትን ጽፏል፡፡ በመጨረሻም በ67 ዓ.ም በሮም አደባባይ በሰይፍ ሞቷል፡፡ መልእክቶቹ ግን ከከዋክብት ደምቀው በዓለም ሁሉ በየዕለቱ ያበራሉ፡፡ መልእክታቱ የተጻፉት ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ሲሆን ምእመናንን ለማጽናት፣ ለመገሰጽ፣ ለማጽናናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ፍሬያማ ለማድረግ ባጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና በማወቅ ለማደግ ተጽፈዋል፡፡ ጳውሎስ መልእክታቱን የጻፈው ከእስር በፊትና በእስር ዘመን ነው፡፡ መልእክታቱም አብያተ ክርስቲያናቱ በሚገኙበት አገርና ግለሰቦች ተሰይመዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የሮሜ መልእክት ሮም ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ሲሆን የጢሞቴዎስ መልእክት ደግሞ የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ ለሆነው ለኤፌሶኑ ጳጳስ ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ነው፡፡
የጴጥሮስ መልእክታት
ጴጥሮስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱና የመጀመሪያው ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስን የእጁን ተአምራት፣ የቃሉን ትምህርት በቀጥታ የተቀበለ ነው፡፡ ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ሲሆን ጴጥሮስ የአይሁድ ሐዋርያ ነበር፡፡ በ67 ዓ.ም በሮም አደባባይ የቊልቊሊት ተሰቅሎ እስኪሞት በብዙ ስደትና መከራ ወንጌልን ሰብኮአል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት መልእክታትን ጽፎአል፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ በተለያዩ የእስያ አውራጃዎች ስለ ወንጌል ለተሰደዱ ክርስቲያን አይሁዶች የጻፈው ሲሆን በመታገሥ ያለውን ሰማያዊ ዋጋ በመግለጥ ሊያጸናቸው ጽፏል፡፡ ሁለተኛይቱ የጴጥሮስ መልእክት ደግሞ በክርስቲያኖች መካከል ሰርገው ስለገቡ የሐሰት መምህራን (መናፍቃን) ምእመናን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጽፎአል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የአረማውያን ነገሥታትን ያህል የሐሰት መምህራንም ጎጂዎቿ ናቸውና፡፡
የዮሐንስ መልእክታት
ዮሐንስ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር ለማጉላት ወንጌሉን እንደ ጻፈ  ዓይተናል፡፡ ደግሞም ሦስት መልእክታትንም አዘጋጅቷል፡፡ መልእክታቱንም ሆነ ወንጌሉን እንዲሁም ራእዩን የጻፈው በዕድሜው መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያይቱን መልእክቱን የጻፈው በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረውን የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመጋፈጥና ምእመናን በፍቅር እየተባበሩ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛይቱን መልእክት ደግሞ የጻፈው ለአንዲት አማኝ ሴት ሲሆን ከስህተት ትምህርት እንድትጠበቅ ነው፡፡ ሦስተኛይቱ የዮሐንስ መልእክት በቤቱ እንግዶችን ለሚቀበል ጋይዮስ ለተባለ በጎ አማኝ ለምስጋና የጻፈለት መልእክት ነው፡፡
የያዕቆብ መልእክት
ያዕቆብ ከጌታ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፡፡ ይህ ያዕቆብ ይህችን ቀደምት መልእክቱን የጻፈው በስደት ለተበተኑት ክርስቲያን አይሁድ ሲሆን የመልእክቱ ዋና ዓላማ በመከራቸው እንዲፀኑና እምነታቸውን በምግባር እንዲገልጡ ለማነቃቃት ነው፡፡
የይሁዳ መልእክት
ባለ አንድ ምዕራፍ ከሆኑት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ የይሁዳ መልእክት ሲሆን ይሁዳም መልእክቱን የጻፈው በስም ላልተጠቀሱ አማንያን ነው፡፡ የመልእክቱም ዓላማ ክርስቲያኖች ሁሉ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማስጠንቀቅ ነው፡፡
ትንቢት
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የትንቢት መጽሐፍ ተብሎ የሚጠራው የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡
የዮሐንስ ራእይ፡- ዮሐንስ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ተግዞ /ታስሮ/ ሳለ በራእይ ያለፈውን፣ ያለውንና የሚመጣውን ተገልጾለት ጽፏል፡፡ የዮሐንስ ራእይ ክርስቲያኖችን ለማይቀረው የክርስቶስ ምጽአት ያዘጋጃል፡፡ አገላለጹም ሥዕላዊ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሥዕል ከብዙ ቃላት ይልቅ የመናገር አቅም ስላለውና ዳግመኛም መጽሐፉን ከአደጋ ለመከላከል ነው፡፡ ትንቢቶቹ በግልጽ ቢጻፉ ኖሮ አረማውያን ነገሥታት በቶሎ ይጠፉታልና ጠላት ለመቀነስ ነው፡፡
ይህንን ጥናት ስናጠና የመጽሐፍ ቅዱሳችንን ማውጫ እየተመለከትን ብናጠና ይበልጥ ይብራራልናል፡፡ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በምዕራፍ ይከፈላል፡፡ ምዕራፉ ደግሞ በቊጥር ይከፈላል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲጠቀስ በአጭሩ ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ፡- ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አሥራ አምስት ቊጥር ስድስት ቀጥሎ ባለው መልኩ ይጠቀሳል፡- (ዘፍ. 15፥ 6)፡፡

Thursday, February 19, 2026

❖የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት:-

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በቅኝት መልክ

መጽሐፍ ቅዱስ ማለት “ልዩ መጽሐፍ” ማለት ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚገኙት መጻሕፍት ልዩ የሚያደርገው በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈና ሕይወት ሰጪ መጽሐፍ በመሆኑ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳን መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚመራው በኪዳኑ መሠረት ነው፡ ከእያንዳንዱ ሰው ጋርም ኅብረት የሚያደርገው በኪዳን ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳኑ ቅዱስ ሰነድ ነው፡፡ እነዚህም ታላላቅ ኪዳናት ሁለት ሲሆኑ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ይባላሉ፡፡ ኪዳን የሚያሟላቸውን ነገሮች ቀጥሎ ባለው ሠንጠረዥ ተገልጿል፡፡
ኪዳኑ
ኪዳን ሰጪ
ኪዳን ተቀባይ
የኪዳን ግዴታ
የኪዳን በረከት
የኪዳን ምልክት
ብሉይ ኪዳን
እግዚአብሔር
እስራኤል
ሕግን መጠበቅ
ከነዓንን መውረስ
ሰንበት
አዲስ ኪዳን
እግዚአብሔር
በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ
እምነት
የዘላለም ሕይወት
ቅዱስ ቊርባን
       
የሰንጠረዡ ማብራሪያ ፡- በሁለቱም ኪዳናት የኪዳኑ ባለቤትና ኪዳን ሰጪ እግዚአብሔር ነው (ኤር. 31፥31-34፤ ዕብ. 8፥8-12)፡፡ የመጀመሪያው ኪዳን (ብሉይ ኪዳን)  የተሰጠው ለአንድ ሕዝብ (ለአይሁድ) ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን የተሰጠው ለመላው ዓለም (ላመኑት ሁሉ) ነው (ዘፀ. 24፥1-8፤ዮሐ. 3፥16)፡፡ ብሉይ ኪዳን የሕግ ግዴታ ሲኖረው አዲስ ኪዳን ደግሞ በክርስቶስ ማመንን ይጠይቃል (2ቆሮ. 3፥4-18፤ ገላ. 2፥16)፡፡ የብሉይ ኪዳን በረከቱ ምድራዊ ሲሆን  የአዲስ ኪዳን ግን ሰማያዊ በረከት ነው (ኢያ. 1፥1-9፤ ኤፌ. 1፥3)፡፡ ኪዳን ማስታወሻ /ምልክት/ ያስፈልገዋል፡፡ የብሉይ ኪዳን ምልክቱ ሰንበት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን ቅ/ቊርባን ነው (ዘፀ. 31፥17፤ ሉቃ. 22፥20)፡፡

የሁለቱ ኪዳናት ሰንሰለት
        ሁለቱ ኪዳናት ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን እንደማያቋርጥ የወንዝ ፈሳሽ፣ አንዱ አንዱን እንደሚስበው ሐረግ፣ አንደኛው በአንዱ እንደ ታሠረ ሰንሰለት የታሪክና የእምነት ትስስር አላቸው፡፡ አንዱ ያለ አንዱ እንደማይቆም የሕንጻ   ካብ ሁለቱ ኪዳናት ተደጋግፈዋል፡፡ ብሉይ ኪዳን ጅምር ሲሆን አዲስ ኪዳን ፍጻሜ ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ያለ አዲስ ኪዳን መጨረሻ የሌለው መጀመሪያ ነው፡፡ አዲስ ኪዳንም ያለ ብሉይ ኪዳን መጀመሪያ የሌለው መጨረሻ ነው። ስለዚህ ስብከታችን ከብሉይ ኪዳን ተነሥቶ ወደ አዲስ ኪዳን ሲመጣ ዘላለማዊነትን ያገኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኪዳናቱን ትስስር ጥላና አካል፣ ምሳሌና እውነት፣ ትንቢትና ፍጻሜ እያለ ይገልጠዋል (ቈላ. 2፥16፤ ዕብ. 10፥1፤ ሉቃ. 24፥44)፡፡
የብሉይ ኪዳን ጥናት በቅኝት መልክ
        ብሉይ ኪዳን ማለት ምን ማለት ነው? ስንል ብሉይ ማለት በግእዝ ቋንቋ አሮጌ /ያረጀ/ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ማለት ደግሞ መሐላ፣ ውል ስምምነት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ብሉይ ኪዳን ማለት የቆየ መሐላ ማለት ነው (ዕብ. 8፥13)፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም፡-
   ኦሪት
   ታሪክ
   ጥበብና
   ትንቢት ይባላሉ፡፡
ኦሪት
        ኦሪት ማለት ሕግ ማለት ነው፡፡ የኦሪት መጻሕፍት የሚባሉትም ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት አምስት መጻሕፍት ናቸው፡፡ ፀሐፊያቸውም ሙሴ ነው፡፡
ኦሪት ዘፍጥረት፡- “ዘ” የሚለው የግእዝ ፊደል “የ” የሚለውን የአማርኛ ቃል የሚተካ አገናኝ ቃል ነው፡፡ ኦሪት ዘፍጥረት ማለትም “የመፈጠር ሕግ” ማለት ነው፡፡ የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች ስለ ዓለምና ስለ ሰው ተፈጥሮ ስለሚናገሩ ከሦስቱ የመግቢያ ምዕራፎች አሳብ በመነሣት ኦሪት ዘፍጥረት ወይም የመፈጠር ሕግ የሚለውን ስያሜ አግኝቷል፡፡
ኦሪት ዘፀአት፡- “የመውጣት ሕግ” ማለት ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ባርነት ነጻ መውጣታቸውን ስለሚተርክ የመውጣት ሕግ ተብሏል።
ኦሪት ዘሌዋውያን፡- “የሌዋውያን ሕግ” ማለት ነው። ሌዋውያን የመቅደስ አገልጋዮች ናቸው። መጽሐፉ ስለ ሌዋውያን አገልግሎት ስለሚናገር የሌዋውያን ሕግ ተብሏል። መልእክቱ ቅድስናን የሚመለከት በመሆኑም “የቅድስና ሕግ” ይባላል። ትልቁ የአገልግሎት መገለጫም ቅድስና ስለሆነ ኦሪት ዘሌዋውያን መባሉ መልካም ነው።
ኦሪት ዘኁልቍ፡- “የመቆጠር ሕግ” ማለት ነው። የእስራኤል ልጆችን እንዲቆጥር እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘበት ክፍል ስለሆነ የመቆጠር ሕግ ተብሏል፡፡
ኦሪት ዘዳግም፡- “የመደገም ሕግ” ማለት ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ ለተወለዱት የእስራኤል ልጆች የሕጉን መጽሐፍ እንደገና ስላስተማራቸው የመደገም ሕግ ተባለ፡፡ በክፍሉ ላይ ሙሴ ከግብጽ ምድር ለወጡት የእግዚአብሔርን ውለታ ሲያዘክር፣ በምድረ በዳ ለተወለዱት ደግሞ ትእዛዙን ይከልስላቸዋል፡፡
ታሪክ
የታሪክ ክፍል የሚባለው ከመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ እስከ መጽሐፈ አስቴር ያሉት 12 መጻሕፍት ናቸው፡፡
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ፡- የነዌ ልጅ የኢያሱ መጽሐፍ ማለት ነው፡፡ የነዌ ልጅ ኢያሱ ከሙሴ ቀጥሎ እስራኤልን የመራና የተስፋቸው ፍጻሜ የሆነችውን ከነዓንን ያከፋፈለ መሪ ነው፡፡ ፀሐፊው እርሱ ስለሆነም መጽሐፉ በስሙ ተሰይሟል፡፡
መጽሐፈ መሳፍንት፡- ከኢያሱ ሞት በኋላ 13 መሳፍንት እስራኤልን አስተዳድረዋል። እግዚአብሔር ሕዝቡን በመሳፍንት አድሮ ከጠላት እንዴት እንደታደጋቸው የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። ሳሙኤል እንደጻፈውም ይገመታል።
መጽሐፈ ሩት፡- በሴት ስም ከተሰየሙት ሁለት መጻሕፍት አንዱ መጽሐፈ ሩት ነው፡፡ ሩት ከዚህም ሌላ አሕዛባዊት ሴት ስትሆን በእግዚአብሔር ጥበብ የዳዊት የሴት ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች፡፡ ፀሐፊው ሳሙኤል እንደሆነ ይነገራል፡፡
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ፡- እነዚህ በታላቁ ነቢይ በሳሙኤል የተሰየሙት ሁለት መጻሕፍት ከመሳፍንት ዘመን ማብቂያ ጀምሮ ያለውን ዘመነ ነገሥትን ይተርካሉ፡፡ ሰፊ ሽፋንም የተሰጣቸው የመጀመሪያው ንጉሥ ሳኦልና ሁለተኛው ንጉሥ ዳዊት ናቸው፡፡ ቀዳማዊ ማለት አንደኛ ማለት ሲሆን ካልዕ ማለትም ሁለተኛ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ መጻሕፍት ፀሐፊ ሳሙኤል ስለሆነ በእርሱ ስም ተሰይመዋል፡፡
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ፡- ከሦስተኛው ንጉሥ ከሰሎሞን እስከ ባቢሎን ምርኮ የነገሡትን የ360 ዓመታት የነገሥታት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፈ ነገሥት ተብሏል፡፡ ፀሐፊው ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ 
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕ– ዜና መዋዕል ማለት የዘመናት ታሪክ ማለት ነው፡፡ ከመጽሐፈ ነገሥት ጋር ሙሉ በሙሉ የዘመን ትስስር አለው፡፡ ወይም አራቱም መጻሕፍት የተወሰኑ ዘመናትን በጣምራነት ይተርካሉ፡፡ ልዩነቱ ግን የነገሥት ሁለት መጻሕፍት የቤተ መንግሥቱን ታሪክና ውድቀት ሲተርኩ የዜና መዋዕል መጻሕፍት ግን የቤተ ክህነቱን ሂደትና ውድቀት ይተርካሉ፡፡ አራቱም መጻሕፍት እስከ ባቢሎን ምርኮ ድረስ ዘግበዋል፡፡ የዜና መዋዕል መጻሕፍትም ዕዝራ እንደ ጻፋቸው ይነገራል፡፡
መጽሐፈ ዕዝራ፡- ዕዝራ ፀሐፊና ካህን ነበር፡፡ በባቢሎን ምርኮ ያደገ ሰው ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ እንዲሠራና ሕዝቡም መንፈሳዊ መነቃቃት እንዲያደርግ የታገለ ሰው ነበር፡፡ ፀሐፊውም ራሱ ስለሆነ መጽሐፈ ዕዝራ ተብሏል፡፡
መጽሐፈ ነህምያ፡- ነህምያ በባቢሎን ምርኮ አገር የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበር፡፡ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ስለ ቅጥርዋ መናድ አብዝቶ ያዝን ነበርና በንጉሡ ፈቃድ ቅጥርን አደሰ፣ አስተዳደርዋንም መለሰ፡፡ መጽሐፉን ራሱ ነህምያ ስለ ጻፈው በስሙ ተሰይሟል፡፡
መጽሐፈ አስቴር፡- አስቴር በምርኮ አገር ንጉሡን ያገባች ሴት ስትሆን ወገኖቿ አይሁድ የታወጀባቸውን የሞት አዋጅ እንዲቀይር በቆራጥነት የደከመች ሴት ናት፡፡ አይሁድም የሞት አዋጁ በሕይወት ተለውጦላቸዋል፡፡ በሴት ስም ከተሰየሙት ሁለት መጻሕፍት አንዱ መጽሐፈ አስቴር ነው፡፡ ፀሐፊው ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ አይሁድ ከሞት የዳኑበትን ቀን “ፉሪም” ዕጣ ማለት ነው ሲያከብሩ መጽሐፈ አስቴርን ያነቡ ነበር፡፡
ጥበብ
የጥበብ መጻሕፍት የሚባሉት ከመጽሐፈ ኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ድረስ ያሉት አምስት መጻሕፍት ናቸው፡፡
መጽሐፈ ኢዮብ፡- በጥንት ዘመን ስለኖረና በሕይወት ብዙ ተፈትኖ ነጥሮ ስለወጣው ስለ ኢዮብ የሚናገር መጽሐፍ ሲሆን መጽሐፉም በራሱ በኢዮብ ተሰይሟል፡፡ ፀሐፊው ማን እንደሆነ አልተገለጸም፡፡
መዝሙረ ዳዊት፡- ነቢዩና ንጉሡ ዳዊት ስለ ሕይወቱ ስለ ኑሮው ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ንግግር ነው። ደራሲውም የመዘምራን አለቃ ዳዊትና ሌሎችም ዘማርያን ናቸው።
መጽሐፈ ምሳሌ፡- የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌ ነው፡፡ ሰሎሞን ሦስት መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ መክብብ፣ መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን ይባላሉ፡፡ መክብብ ማለት ሰባኪ ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ውጭ ስላለው ነገር ከንቱነት ይናገራል፡፡ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ማለት ደግሞ ከመዝሙሮች የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር ማለት ነው፡፡ በሁለት ሰዎች ማለት በሴትና በወንድ ቅላፄ የተዋቀረ መዝሙር ሲሆን የቤተ ክርስቲያንና የክርስቶስን ፍቅር ይገልፃል፡፡
ትንቢት
የትንቢት ክፍሎች ዐሥራ ሰባት መጻሕፍትን ይዘዋል፡፡ ነቢያቱ አንዳንዴ በሁለት፣ ሌላ ጊዜም በሦስት ይከፈላሉ፡፡ በሁለት ሲከፈሉ ዐበይት ነቢያትና ደቂቅ ነቢያት ይባላሉ፡፡ ስለዚህ ዐበይት ነቢያት የሚባሉት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው፡፡ ደቂቅ ነቢያት የሚባሉትም ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት ነቢያት ናቸው በሦስት ሲከፈሉም ከምርኮ በፊት የነበሩ፣ በምርኮ ዘመን የነበሩ፣ ከምርኮ ዘመን በኋላ የነበሩ ነቢያት ተብለው ይከፈላሉ፡፡
   ከምርኮ ዘመን በፊት የነበሩ፡- ኢሳይያስ፣ ሆሴዕ፣ አሞጽ፣ ሚክያስ፣ ኢዩኤል፣ አብድዩ፣ ዮናስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ናቸው፡፡
   በምርኮ ዘመን የነበሩ፡- ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል ናቸው፡፡
   ከምርኮ ዘመን በኋላ የነበሩ፡- ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው፡፡
ከምርኮ ዘመን በፊት የነበሩት ነቢያት ሕዝቡን ይገስጹ፣ ያስጠነቅቁ ነበር፡፡ በምርኮ ዘመን የነበሩ ነቢያት ደግሞ ሕዝቡን ያጽናኑ ነበር፡፡ ከምርኮ ዘመን በኋላ የነበሩ ነቢያት ደግሞ የፈረሰው እንዲጠገን፣ የእግዚአብሔር ቤት እንዲለማ ያበረታቱ ነበር፡፡ ከትንቢት ክፍሎች ትርጉም የሚያሻው አርእስት “ሰቆቃወ ኤርምያስ” ሲሆን ትርጉሙም የኤርምያስ ሐዘን ወይም ልቅሶ ማለት ነው፡፡
የብሉይ ኪዳን ሠላሳ ዘጠኙ መጻሕፍት ከ1400-400 ዓመተ ዓለም ከክርስቶስ በፊት ተጽፈዋል፡፡ የመጨረሻውም ነቢይ ሚልክያስ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ የተጻፉ መጻሕፍትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ እና የካቶሊክ ቤ/ክ ተቀብለዋቸዋል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ዲዩትሮካኖኒካል ወይም ተጨማሪ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አሊያም “የብሉይ ኪዳን 2ኛ የቀኖና መጻሕፍት” በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ከ39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በአንድነት የተቆጠሩት ከሰባ ሊቃናት ትርጉም በኋላ ነው፡፡ ሰባ ሊቃናት የሚባሉት ለመጀመሪያ ጊዜ ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ የተረጎሙ የአይሁድ መምህራን ናቸው፡፡ እነዚህ ሊቃውንት ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ ሲመልሱ እነዚህንም መጻሕፍት አብረው መልሰዋል፡፡ መጻሕፍቱ በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ከባቢሎን ምርኮ በኋላ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ስላለው የታሪክ ሂደት እነዚህ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ የምክርና የጥበብ ትምህርቶችንም ይዘዋል፡፡ ለምሳሌ፡- መጽሐፈ ሲራክንና መጽሐፈ ጥበብን መጥቀስ እንችላለን፡፡
በርግጥ የአይሁድ መምህራን (ረቢዎች) በ90 ዓ.ም. በምዕራብ ኢየሩሳሌም ያምኒያ በሚባለው ቦታ የያምኒያ ጉባዔ ተብሎ በሚጠራው የሊቃውንት ስብሰባ እነዚህን መጻሕፍት እንደማይቀበሉ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ መጻሕፍቱ ግን በኦርቶዶክስና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ እንግዲህ የብሉይ ኪዳን ቀጥተኛ ተቀባዮችና ባለ አደራዎች አይሁዳውያን ሲሆኑ የአዲስ ኪዳን ቀጥተኛ ተቀባይና ባለ አደራ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡