Thursday, March 16, 2017

❖የአዲስ ኪዳን ጥናት በቅኝት መልክ

አዲስ ኪዳን ማለት አዲስ ውል አዲስ ስምምነት ማለት ነው፡፡ ለምን አዲስ ኪዳን ተባለ ስንል ፊተኛውን ኪዳን አስረጅቶ ስለገባና የዘላለም ኪዳን ስለሆነ ነው (ዕብ. 813 11-2)፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳን እንደሚገባ አስቀድሞ በነቢያት ተናግሯል (ኤር. 3131-34 ዕብ. 88-13)፡፡ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ሲነጻጸሩ አዲሱ ኪዳን ብልጫ አስገኝቷል፡፡ ብሉይ ኪዳን ባሰጣጡ ጊዜያዊ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን ዘላለማዊ ነው (ማቴ. 1113 ሉቃ. 1616)፡፡ ብሉይ ኪዳን የተሰጠው በሙሴ መካከለኛነት ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛነት ተሰጥቷል (ገላ. 319 1ጢሞ. 25)፡፡ ብሉይ ኪዳን ሕዝቡን ሊያድን ስላልቻለ የኲነኔ አገልግሎት ነበረ፤ አዲስ ኪዳን ግን የሕይወት አገልግሎት ነው (2ቆሮ. 37-11)፡፡ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ላይ የተጻፈ የሕግ ግዴታ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በልባችን ጽላት ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ ነው (2ቆሮ. 33)፡፡

የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሰባት በሚያህሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተጻፈ የሃያ ሰባት መጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ እስኪያድርባቸው ጌታን ይከተሉ የነበረው ለምድራዊ ትልቅነት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከተነሣና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ከምድራዊ የክብር አሳብ ተላቀው ሁሉን ጥለው ተከተሉት፡፡ ወንጌሉንም በማይመቹ ሁኔታዎች ለዓለም አደረሱ፡፡ መልእክቶቹን የጻፉት በርቀት የነበሩትን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ለማጽናት ነው፡፡ የመልእክቱ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ግን እኛን ጭምር በዚያ መልእክት ውስጥ ይመለከት ነበር፡፡
አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ የራሱ የሆነ አከፋፈል አለው፡፡ ስለዚህ በአራት ተከፍሎ ይጠናል፡፡ ወንጌል፣ ታሪክ፣ መልእክትና ትንቢት፡፡
                                ወንጌል

ወንጌል የሚባለው ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ ያሉት አራት ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መጸነስ፣ መወለድ፣ መኖርና መሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት በሙሉነት ስለሚተርኩ ወንጌል የሚለውን ስያሜ አግኝተዋል፡፡ ወንጌል ማለት ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ መልእክት ነው (ሮሜ. 13-4)፡፡ ወንጌል ቃሉ ዩአንገሊዎን ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡ ትርጉሙም የምሥራች ቃል ወይም የድኅነት ዜና ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተወልዶ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ዓለምን ማዳኑን ስለሚናገርና ፍርድን የሚጠባበቁ ኃጢአተኞች ተስፋ ስለመጣላቸው ወንጌል ወይም የምሥራች ቃል ተብሏል፡፡

አራቱ ወንጌላት ቀጥተኛ ግባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነት የሚጠይቀውን ሙሉ መንገድ ተጉዞ የሰውን ዘር ከዘላለም ጥፋት ማዳኑ ነው፡፡ ፀሐፊዎቹም ሁለቱ ማለትም ማቴዎስና ዮሐንስ ከጌታ አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት መካከል ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ማርቆስና ሉቃስ ከሐዋርያት ጋር በቅርበት የነበሩ ከእነርሱ የሰሙትን በጥንቃቄ የጻፉ ናቸው፡፡ የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌላት ተመሳሳይ ትረካ ያላቸው ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን በመግለጥ እግዚአብሔር በሰውና በሰው ታሪክ መካከል ያደረገውን ይተርካሉ፡፡ ዮሐንስ ግን በተለየ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ክብር በመግለጥ አምላክነቱን ሰዎች እንዲቀበሉት ይጥራል፡፡ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተገልጦ ያደረገው ተአምርና የተናገረው ቃል ሰማይ ብራና፣ ዕፅዋት ሁሉ ብዕር፣ ውቅያኖስ ሁሉ ቀለም ቢሆኑ ተጽፎ አያልቅም (ዮሐ. 21252030)፡፡ ለመዳናችን የሚበቃን ግን ተጽፎልናል፡፡

                                     አራቱ ወንጌላት

የማቴዎስ ወንጌል- በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ምዕራፍ ካላቸው ሁለት መጻሕፍት አንዱ የማቴዎስ ወንጌል ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁድ ስለሆነ የዘር ሐረግን፣ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ አይሁድ መሢሑን እንዲቀበሉ መሢሑ የአብርሃምና የዳዊት ዘር መሆኑን የሚገልጥ የዘር ፍሰትን ያወሳል፡፡ ለማስረጃም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ በዘር ሐረጉ ግን አይሁድ የማይጠቀሙበትን ስልት በመጠቀም አራት ሴቶችን ጠቅሷል (ማቴ. 14 . 5.6.16)፡፡ አይሁድ በዘር ሐረግ ውስጥ ሴቶችን አስገብተው አይቆጥሩም ነበርና፡፡ ክርስቶስ ግን የመምጣቱ አንዱ ዓላማ ይህን ልዩነት ለማስወገድ ነበር፡፡

የማርቆስ ወንጌል- ከወንጌላት ትንሽ ምዕራፎች ያሉት የማርቆስ ወንጌል ነው፡፡ የትምህርቱም ስልት የክርስቶስን የእጁን ተአምራት በመግለጥ በዘመኑ የነበሩ ሮማውያንን ለማሳመን ነው፡፡ ጌታችን በተያዘ ሌሊት እርቃኑን በነጠላ ሸፍኖ ይከተለው ነበርና በያዙት ጊዜ ነጠላውን ትቶ ራቁቱን የሸሸው ወጣት ማርቆስ መሆኑን ብዙ ሊቃውንቶች ይናገራሉ (ማር. 1451-52)፡፡ እናቱ ቤቷን ለአገልግሎት በመልቀቋ የማርቆስ እናት ቤት የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስያሜ አግኝታለች (ሐዋ. 1212-17)፡፡ ማርቆስ ከበርናባስ፣ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ብዙ ጊዜ አገልግሏል፡፡ የጴጥሮስም የመንፈስ ልጁ ነው (1ጴጥ. 513) ወንጌሉን የጻፈውም ከእነዚህ ሐዋርያት በጥልቀት በመጠየቅና በማዳመጥ ነው፡፡
የሉቃስ ወንጌል- ሉቃስ ከአሕዛብ ወገን የሆነና በክርስቶስ ያመነ የጳውሎስም ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ነው፡፡ በሙያውም ሐኪም እንደ ነበረ ተጠቅሷል (ቈላ. 414)፡፡ ስለ ክርስቶስም ሙሉ ትረካ ያቀረበ ፀሐፊ ነው፡፡ ወንጌሉን የጻፈው ከአሕዛብ ወገን ለነበረና ላመነ ቴዎፍሎስ ለሚባል ወዳጁ ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን ከዘር ሐረግ ይጀምራል፣ ማርቆስ ከጥምቀቱ ይጀምራል፣ ሉቃስ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኛ ከሆነው ከዮሐንስ መጥምቅ የጽንሰት ዜና ይጀምራል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሉቃስ ወንጌሉንና የሐዋርያት ሥራን ጽፎአል፡፡

የዮሐንስ ወንጌል- ዮሐንስ ወንጌላዊ ከሦስቱ ወንጌላት በተለየ ሁኔታ ወንጌሉን ጽፎአል፡፡ ሦስቱ ወንጌላውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆንና ሰብአዊ ቅርበቱን ተርከዋል፡፡ ዮሐንስ ደግሞ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር በማጉላት ጽፎአል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት መቻቻል አለባቸው፡፡ ሰውነቱ አምላክነቱን ጋርዶብን አምልኮ እንዳንነፍገው፣ አምላክነቱ ሰውነቱን ሸፍኖብን እንዳናርቀው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የወንጌላውያኑም ጭንቀት ይህ ነው፡፡ ዮሐንስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ወንጌል፣ ሦስት መልእክታት፣ አንድ የራእይ መጽሐፍ ጽፎአል፡፡




                                      ታሪክ

በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል ተብሎ የሚጠራው አንድ ጥራዝ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የሐዋርያት ሥራ ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ- የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሉቃስ ነው፡፡ የጻፈውም ወንጌልን ለጻፈለት ቴዎፍሎስ ለተባለው ወዳጁ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ሲናገር የሐዋርያት ሥራ ደግሞ ከዕርገቱ በኋላ ስላሉት ዐሥር ቀኖችና ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ ይናገራል፡፡ የመጽሐፉ ሙሉ ይዘት ወንጌል ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ከዚያም እስከ መላው ዓለም በእንዴት ያለ ጸጋና ዋጋ መድረሱን የሚተርክ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት አድሮ የሠራው ሥራ በመሆኑ የሐዋርያት ሥራ ቢባልም ታሪኩን ስንዘልቀው ግንየመንፈስ ቅዱስ ሥራቢባል መልካም ነበር ያሰኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በስፋት የተገለጠው የጴጥሮስና የጳውሎስ አገልግሎት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደ ሌሎቹ መልእክታት በሰላምታ ወይም በምርቃት አይዘጋም፡፡ ይህ የሚያስረዳን የሐዋርያት ሥራ በትውልድ ሁሉ መቀጠሉን ነው፡፡

                                     መልእክት

የአዲስ ኪዳን ሦስተኛው አከፋፈል መልእክት ነው፡፡ መልእክት የሚባሉት ከሮሜ እስከ ይሁዳ ድረስ ያሉት 21 የመጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ ፀሐፊዎቹም ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ናቸው፡፡ የተጻፉትም ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡

የጳውሎስ መልእክታት

ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ድረስ ያሉት ዐሥራ አራት መልእክቶች ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ናቸው፡፡ ጳውሎስ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል አይደለም፡፡ ጌታ ካረገ ከስምንት ዓመት በኋላ ነው የተጠራው፡፡ ክርስትናን በብርቱ ይቃወም በነበረ ሰዓት በደማስቆ መንገድ በመብረቅ ብርሃን ጥሎት፣ ሦስት ቀን ዓይኑን አውሮት በወንጌል አመነ (የሐዋ. 918)፡፡ ከሁሉ ኋላ የተጠራ ቢሆንም ከሐዋርያት ይልቅ ሮጧል፣ ዋጋ ከፍሏል፣ አብያተ ክርስቲያናትን መሥርቷል፣ መልእክታትን ጽፏል፡፡ በመጨረሻም 67 . በሮም አደባባይ በሰይፍ ሞቷል፡፡ መልእክቶቹ ግን ከከዋክብት ደምቀው በዓለም ሁሉ በየዕለቱ ያበራሉ፡፡ መልእክታቱ የተጻፉት ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ሲሆን ምእመናንን ለማጽናት፣ ለመገሰጽ፣ ለማጽናናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ፍሬያማ ለማድረግ ባጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና በማወቅ ለማደግ ተጽፈዋል፡፡ ጳውሎስ መልእክታቱን የጻፈው ከእስር በፊትና በእስር ዘመን ነው፡፡ መልእክታቱም አብያተ ክርስቲያናቱ በሚገኙበት አገርና ግለሰቦች ተሰይመዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የሮሜ መልእክት ሮም ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ሲሆን የጢሞቴዎስ መልእክት ደግሞ የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ ለሆነው ለኤፌሶኑ ጳጳስ ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ነው፡፡

የጴጥሮስ መልእክታት

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱና የመጀመሪያው ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስን የእጁን ተአምራት፣ የቃሉን ትምህርት በቀጥታ የተቀበለ ነው፡፡ ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ሲሆን ጴጥሮስ የአይሁድ ሐዋርያ ነበር፡፡ 67 . በሮም አደባባይ የቊልቊሊት ተሰቅሎ እስኪሞት በብዙ ስደትና መከራ ወንጌልን ሰብኮአል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት መልእክታትን ጽፎአል፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ በተለያዩ የእስያ አውራጃዎች ስለ ወንጌል ለተሰደዱ ክርስቲያን አይሁዶች የጻፈው ሲሆን በመታገሥ ያለውን ሰማያዊ ዋጋ በመግለጥ ሊያጸናቸው ጽፏል፡፡ ሁለተኛይቱ የጴጥሮስ መልእክት ደግሞ በክርስቲያኖች መካከል ሰርገው ስለገቡ የሐሰት መምህራን (መናፍቃን) ምእመናን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጽፎአል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የአረማውያን ነገሥታትን ያህል የሐሰት መምህራንም ጎጂዎቿ ናቸውና፡፡

የዮሐንስ መልእክታት

ዮሐንስ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር ለማጉላት ወንጌሉን እንደ ጻፈ  ዓይተናል፡፡ ደግሞም ሦስት መልእክታትንም አዘጋጅቷል፡፡ መልእክታቱንም ሆነ ወንጌሉን እንዲሁም ራእዩን የጻፈው በዕድሜው መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያይቱን መልእክቱን የጻፈው በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረውን የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመጋፈጥና ምእመናን በፍቅር እየተባበሩ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛይቱን መልእክት ደግሞ የጻፈው ለአንዲት አማኝ ሴት ሲሆን ከስህተት ትምህርት እንድትጠበቅ ነው፡፡ ሦስተኛይቱ የዮሐንስ መልእክት በቤቱ እንግዶችን ለሚቀበል ጋይዮስ ለተባለ በጎ አማኝ ለምስጋና የጻፈለት መልእክት ነው፡፡

የያዕቆብ መልእክት

ያዕቆብ ከጌታ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፡፡ ይህ ያዕቆብ ይህችን ቀደምት መልእክቱን የጻፈው በስደት ለተበተኑት ክርስቲያን አይሁድ ሲሆን የመልእክቱ ዋና ዓላማ በመከራቸው እንዲፀኑና እምነታቸውን በምግባር እንዲገልጡ ለማነቃቃት ነው፡፡

የይሁዳ መልእክት

ባለ አንድ ምዕራፍ ከሆኑት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ የይሁዳ መልእክት ሲሆን ይሁዳም መልእክቱን የጻፈው በስም ላልተጠቀሱ አማንያን ነው፡፡ የመልእክቱም ዓላማ ክርስቲያኖች ሁሉ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማስጠንቀቅ ነው፡፡

                                          ትንቢት

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የትንቢት መጽሐፍ ተብሎ የሚጠራው የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡

የዮሐንስ ራእይ- ዮሐንስ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ተግዞ /ታስሮ/ ሳለ በራእይ ያለፈውን፣ ያለውንና የሚመጣውን ተገልጾለት ጽፏል፡፡ የዮሐንስ ራእይ ክርስቲያኖችን ለማይቀረው የክርስቶስ ምጽአት ያዘጋጃል፡፡ አገላለጹም ሥዕላዊ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሥዕል ከብዙ ቃላት ይልቅ የመናገር አቅም ስላለውና ዳግመኛም መጽሐፉን ከአደጋ ለመከላከል ነው፡፡ ትንቢቶቹ በግልጽ ቢጻፉ ኖሮ አረማውያን ነገሥታት በቶሎ ይጠፉታልና ጠላት ለመቀነስ ነው፡፡

ይህንን ጥናት ስናጠና የመጽሐፍ ቅዱሳችንን ማውጫ እየተመለከትን ብናጠና ይበልጥ ይብራራልናል፡፡ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በምዕራፍ ይከፈላል፡፡ ምዕራፉ ደግሞ በቊጥር ይከፈላል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲጠቀስ በአጭሩ ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ፡- ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አሥራ አምስት ቊጥር ስድስት ቀጥሎ ባለው መልኩ ይጠቀሳል፡- (ዘፍ. 15 6)፡፡
                                                             


Thursday, March 9, 2017

❖መፃጉዕ፣

 ሰው የለኝም
         ዓበይተ ኃይላተ፣ ዓበይተ ኃይላተ ገብረ ኢየሱስ በእለተ ሰንበት፣ እም ኩሉ ዘየዓቢ እነግር ዘገብረ ጽቡር ያአውር ህያወ ዓይነ ውእቱኒ ወረቀ ምድረ  ወገብረ ጽቡረ ወአህየዎ ለዘእውሩ ተወልደ፡፡  

“በሰንበት ቀን ኢየሱስ ታላላቅ ተአምራትን ደረገ፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ያደረገውንም እናገራለሁ፡፡ ጭቃ ደህናውን ዓይን ያጠፋል፣ እርሱ ግን በምድር ላይ ተፍቶ ጭቃ አድርጎ ዕውር ሆኖ የተወለደውን አዳነ፡፡”
      የዓቢ ጾም አራተኛው ሳምንት መጻጉዕ ይባላል፡፡ ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው ጌታ ድውያንን መጎብኘቱንና መፈወሱን በማስተዋል ያነሳል፡፡  
የስያሜው ዋና ታሪክ፥በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ በምትባልና አምስት መመላለሻ በነበረባት አንዲት መጠመቂያ ሥፍራ ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ ስለታመመ አንድ ሰው የሚተርክ ነው፡፡
  ጌታ ወደዚህ ሥፍራ የመጣው በሰንበት ቀን ነው፡፡ በዚያም የመጠመቂያውን ቦታ ውኃ የእግዚአብሔር መልአክ ባንቀሳቀሰው ጊዜ ቀድሞ በመግባት ለመፈወስ፦ “በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።”(ዮሐ.5፥2)
      ይህ ሰው የነበረበት በሽታ ከፍ ሲል የሥጋ ደዌ ወይም የሰውነት መስለል ወይም ሽባነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከንባቡ እንደምንረዳውም ሰውየው እጅግ በጣም ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም እንደእርሱ አይነት ሰዎች ውኃው በተንቀሳቀሰ ጊዜ ፈጥነው ገብተው መፈወስ የሚያስችል አቅም ወይም ዘመድ ሲኖራቸው እርሱ ግን አልነበረውም፡፡
ጌታችን ወደዚህ ሰው በመምጣት፦ “እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን? ለው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጋሪ የማያስፈልገው ሁሉን አዋቂ ነው፡፡
    በዚህ ክፍል አንድ ልዩ ነገር እናያለን፡፡ ጌታ ብዙ ጊዜ ሲፈውስ የምናየው ሰዎች እንዲያድናቸ በጠየቁት ጊዜ ነው፡፡ በእርግጥ ሰውየው፥ “አድነኝ” ቢለው እንኳ የጌታ ኢየሱስ ጥያቄ ተገቢና ትክክል ነው፡፡ እርሱ መሻታችንን አስገድዶ የሚገባ አይደለምና፡፡
    ሰውየው፦ “ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።” (ቁ.7) ፡፡
  ይህ ሰውዬ ሰው የለኝም ብሎ ተስፋ በመቁረጥ የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ሰውየው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው 38 ዓመት በመጠበቁ ይሆናል፡፡ በእርግጥ የዘመኑ ርዝመት ነፍስን ያዝል ይሆናል ፤ ነገር ግን ታማኙ ጌታ በዙፋኑ አለ፡፡ ለዚህ ሰው ዙርያው ሁሉ ጨለማ ነው ፤ ጌታ ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ መጥቶ አጠገቡ ቆመ፡፡
       የረዘመ መከራ ፣ እልህ አስጨራሽ ሙከራ ፣ ባለመድኃኒትቶች ሁሉ ያላወቁት የሕመም እንቆቅልሽ ፣ ዳኛ ያጣመመው ፍርድ ፣ ደርሶባችሁ ዙርያው ሁሉ ገደል የሆነባችሁ አይዟችሁ አዳኙ በደጅ ነው፡፡
     የሰውየው ናፍቆት ፈጥኖ ከውኃው በመግባት መፈወስ ነበር፡፡ ለዚያ ደግሞ የሚረዳው ሰው የለውም፡፡ ይህ እጅግ የሚያም ነገር አለው ፤ ቀና ማለት ፣ ከሰው እኩል መቆም ፣ መፈወስ ፣ መዳን ፣ ከመከራ መውጣት መሻቱ ቢኖረውም ... በኢየሱስ ላይ ያለው እምነት ደካማ ነበር፡፡ እንዲያው ከፈወሰውም በኋላ እንኳ ጌታን ላወቀውም፡፡ ጌታ ግን፦ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።” 
    ጌታ ብዙ በሽተኞች በዚያ ቢኖሩም የሄደው ግን ምንም ሰው ወደሌለው ወደዚህ አንድ ሰው እንደሆነ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
በእርግጥም እርሱ፦“ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል።” (ዘዳግ.10፥18)
   “ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።” ፤ “እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።” (መዝ.10፥14 ፤ 68፥5)
  “መበለቲቱንና ድሀ አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦” (ሚል.3፥5) 
   አዎ! እግዚአብሔር ሰው ለሌላቸው ሰው ሆኖ በሥጋ የተገለጠ ነው፡፡ ሰው ለናቃቸውና ለገፋቸው ፣ ሰው ለሚጠየፋቸው ፣ ጐባጣና ድውይም ... እርሱ የድሆች አምላክ ነውና ከመከራ ሁሉ ያድናቸዋል ፤ ይሟገትላቸዋልም፡፡ እኛም ይህን እውነት ከክርስቶስ ተምረናል፡፡ (1ጴጥ.2፥21)
     ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሰውየው ጌታን እንኳ ባያውቀውም ጌታ ኢየሱስ ግን በበሽታው ላይ ያለውን ፍጹም ሥልጣን አሳይቶናል፡፡  ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ በሁሉ በሽታዎች ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ሰውየው ባያውቀው እንኳ ጌታችን ከደዌው ሁሉ ፈውሶታል፡፡ ውለታን ሳይጠብቅ ፈወሰው፡፡ እኛ ለሰዎች መልካምን ነገር ለማ ምንም ዓይነት ቅድመ  ሁኔታ አይኑረን ለተጠቃውና ለድኃው ፤ የሰው ያለህ እያለ ለሚጮኸው እንድለት፡፡ እንሟገትለትም፡፡

                 የእግዚአብሄር ጸጋና  ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን//

Tuesday, March 7, 2017

❖ለሰዎች እንደጦመኛ አትታዩ (ማቴ.6÷16)

ለሰዎች እንደጦመኛ አትታዩ (ማቴ.6÷16)

       ጾም ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ አምልኮአችንን ከምንገልጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በዓላማ ከምናደርጋቸው ዝግጅቶችም አንዱ የጾም ዝግጅት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጾምን በማያሻማ መልኩ መጾም እንደሚገባን አስረግጦ ይነግረናል፡፡ጌታ ይህን ትምህርት በሚያስተምርበት ወራት በአይሁድ ዘንድ ጾም የታወቀና የተረዳ ነገር ነበር፡፡ ምንም እንኳ መንፈሳዊ መልኩና ለዛው ፈጽሞ በግብዝነት የጠወለገ ቢሆንም፡፡
     
     አይሁድና አህዛብ

ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ለማዋረድ የቀናውን መንገድ ለመለመን (ዕዝ.8÷21፤መዝ.69÷10)፣

ስለህዝብና ስለዓለም ሁሉ ስለራስም በደልና ኃጢአት በማዘንና በመጸጸት ለመናዘዝ (ነህ.9÷1-2)፣

ንስሐ ለመግባትና እግዚአብሔር ሊያመጣ ያለውን ቁጣ እንዲተወውና በምህረትና በይቅርታ ህዝቡን     ይቅር እንዲል(ኢዩ.2÷12፤ዮና.3÷5-10)፣

የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃድ ለማወቅ ፣መገለጥንና ጥበብን ለማግኘትም (ዳን.9÷3) … ለተለያዩ ብዙ ምክንያቶች አይሁድ ጾመዋል፡፡

 ቤተ ክርስቲያንም
    በክርስቶስ ኢየሱስ የተከፈለላትን ትልቁን ውለታና ማዳን በማሰብና ለሁልጊዜም ባለመዘንጋት

ለአዲስ ሥራ ፀጋን ለመሻትና ለእግዚአብሔር መለየታችንን እንደገና ለማረጋገጥ (ማቴ.4÷2)፣

ጌታ እግዚአብሔርን በመቅረብ እርሱን ለመፈለግና ተቃዋሚ የመናፍስት ኀይሎችን መታገል ይቻል ዘንድ በጸሎት ለመጽናት(ሉቃ.18÷3፤ሐዋ.9÷10)፣

ሰዎችን ከክፋት እስራት ለማዳንና ለመፍታት እንዲሁም ለእውሮች ማየትን የተጠቁትንም ነጻ በማውጣት ለመስበክ(ማቴ.17÷14፤ሉቃ.4÷18)፣

መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድና ክርስቶስ ለህዝቡ ወደምድር ዳግም እንዲመጣ መንገድ ለመክፈት (ማቴ.9÷18) እና ለሌሎችም ዓቢይና ንዑስ ምክንያቶች ቤተ ክርስቲያን ልትጾም ከሁሉ በፊት ይገባታል፡፡
    
  ቤተ ክርስቲያን በክፉ ከተያዘው ከዚህ አለም ፊት እንድታመልጥ ክርስቶስ በደሙ አስጊጦአታል፡፡ ይህን በደም ያጌጠ የጽድቅ ልብስ እንዳያድፍና እንዳይረክስ የመጠበቅ ኃላፊነት አለባት፡፡ እንዳትረክስ ራስዋን የምትጠብቅበት አንዱ ጋሻ በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ጾም ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን ጾሟ ሊገለጥና ሊታይ የሚገባው  በእግዚአብሔር ፊት ብቻ እንጂ በሰው ፊት ሰው እንዲያያት ሊሆን አይገባውም፡፡
    የጾማችን ደም ግባቱ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ እንጂ በሰው ፊት ሲመሰገን አይደለም፡፡ስለዚህም አይሁድ ሲጾሙ በራሳቸው አመድ ነስንሰው ማቅ ለብሰው ተዋርደው በሐዘን መሄዳቸውን በሰው ፊት ለመመስገን አድርገውታልና ከሰው ስለተቀበሉት ዋጋቸው ተነቅፈውበታል፡፡ይልቁን አይሁድ በደስታ ጊዜ እንደሚያደርጉት ፊትን በመታጠብ፣ ራስን በመቀባት፣ የጌታ ሞቱ ህይወታችንን ፣ ውርደቱ ክብራችንን ፣ጉስቁልናው የጸጋ ልብሳችንን …  ስለመለሰልን ያለግብዝነት በሙሉ ደስታ፤ ፊታችን እየበራ፤ ደስም እያለን ልንጾም ይገባናል፡፡
     የጾም ወራት ሲመጣ አብዛኛው ሰው የልማዱን ሥርዓት ሳያጓድል ይፈጽመዋል፡፡ወጭቶች በአጃክስና በፈላ ውኃ ተቀቅለው ይታጠባሉ፣ጥሉላት ምግብና መጠጦች የደረሱበት ላለመድረስ ብርቱ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ፡፡ ግና ሁሉም ነገር በጊዜ ገደብ ተጠብቆ ነው፡፡ ለመርከስ ቀጠሮዎች ከጾም በኋላ ተይዘዋል፡፡ ጾመን ለሚበልጥ ትልቅ የቅድስና ሥራና አገልግሎት የማንነቃው ጾማችን ጊዜያዊ ቁጥብነትና በሰው ዘንድ ብቻ የሚታይ ስለሆነብን ነው፡፡ እንጂማ ከአርባ የቀንና የሌሊት ጾም በኋላ ዳግመኛ በኃጢአት የተፈታን ባልሆንን ነበር፡፡ በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛውን ጾም ከጾሙ በኋላ ብዙ ቅዱሳን ታላላቅ መንፈሳዊ ሥራዎችን ሰርተዋል እንጂ ከቶውንም ለመብልና መጠጥ ራሳቸውን አላዘጋጁም፡፡
     ጾማችንን እግዚአብሔር እንደሚያየው ያለነቀፋ የምንጾም ከሆነ ከመብልና መጠጥ ብቻ ሳይሆን ከሚያረክሰው ክፉ መሻትና ከዓለማዊነት ህይወት ልንርቅ ይገባናል፡፡ “ … በኃጢአት መኖርንና አለማዊ ምኞትን ክደን በአሁኑ ዘመናችን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ ፣በእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት ለመኖር” (ቲቶ.2÷11-12) ዛሬላይ ጾማችን መጨከን ካልቻለ እውነት ለመናገር ጾማችን ገና ... ሌላ እውነተኛ ጾም፣ ሌላ እውነተኛ ጸሎት፣ ሌላ እውነተኛ ንስሐ ያስፈልገዋል፡፡ ዋጋቸውን በሰው ፊት እንደተቀበሉት ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሳይሆን ሙሉ ዋጋቸውን በሰማያት ባለው አባታችን ፊት እንደተቀበሉ ቅዱሳን  ተግተን ከጸሎት ጋር ጾማችንን በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት እንፁም፡፡
                    እግዚአብሄር ጸጋና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን//


Thursday, March 2, 2017

❖ምኩራብ

ምኩራብ
       (ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ  አይሁድ ወመሀረ  ቃለ ሃይማኖትትርጉም፥ ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖትንም ቃል አስተማረ፡፡)
  ቅዱስ ያሬድ የጌታን ጾም ሳምንታት በሠየመበት ስያሜው ሦስተኛውን ሳምንት ምኩራብ ብሎ ሰይሞታል፡፡ጌታ በምኩራብ ማስተማሩን፤መስበኩንና መፈወሱን ለማስታወስ፡፡ምኩራብ የእስራኤል ልጆች ወደባቢሎን በንጉስ ናቡከደነጾር በተማረኩ ጊዜ ጎበዛዝት ተግዘው፤ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና መቅደሷም ፈርሶ ተፈታ በነበረችበት ወቅት በባዕድ ምድር እግዚአብሔርን ለማምለክ የሰሩት የአምልኮ ሥፍራ ነው፡፡የሄዱባት ባቢሎን ጣኦትና ቤተ ጣኦት እንጂ እግዚአብሔርና ቤተ መቅደስ አልነበሩባትምና አይሁድ የእግዚአብሔርን ፊት ለመፈለግ ፣ቃሉን ለማጥናትና ለጸሎት እንዲያመቻቸው በየሥፍራው ምኩራብን መሥራት ጀመሩ፡፡
   የእስራኤል ልጆች ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው ወደደሀገራቸው በተመለሱ ጊዜም ከመቅደሱ ጎን ለጎን ምኩራብን ሠሩ፡፡ምኩራብ በጌታ ዘመን ለአይሁድ ዋነኛ የአምልኮ ሥፍራ በመሆኑ ቅዱሳት መጻህፍትን በውስጡ በማከማቸት ፣ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማንበብና በመተርጎም እንዲሁም እግዚአብሔርን ማምለክ የሚያዘወትሩበት ሥፍራ ሆነ፡፡
    በአንድ ሥፍራ ላይ ከሰባት እስከአስር ብዛት ያላቸው አባወራዎች ካሉ ምኩራብን እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ዋና አላማው በአንድ ሥፍራ ያሉ ወገኖች በቅርብ በመገናኘት ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲያጠኑና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ማድረግ ነው፡፡ የምኩራቡ አገልጋይም ዋና ሥራው ልጆችን ማስተማር፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ጥቅልሎች ማቅረብ ፣ሌሎችንም ሥራዎችን መስራት ነው፡፡(ሉቃ.4÷20)
    አገልግሎቱ ስለማቋረጥና ብዙ ምኩራቦችም ስለነበሩ(ሐዋ.9÷2፤13÷3)በየቀኑና በየሰንበቱ ህዝቡ ሁሉ በአቅራቢያው ወዳሉት ምኩራቦ ይሰበሰብ ነበር፡፡(ሐዋ.13÷14፤17÷17)፡፡ የሚሰበሰቡት ሁልጊዜም ከላይ  ለሠፈረው ዓላማ ብቻ ነው፡፡ ምኩራብ ከመቅደስ ያነሰ መስዋዕት የማይቀርብበት የአምልኮ ሥፍራ ነው፡፡ጥቂት አባወራዎችና መንገደኞችም ጎራ እያሉ ቃሉን በማጥናት እግዚአብሔርን የመፍራት ጥበብ ይማሩበታል፡፡ 

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ወደእነዚህ ምኩራቦች በተደጋጋሚ በመገኘት አስተምሯል፤ የመንግስትንም ወንጌል ሰብኳል፤ በህዝብም ሁሉ ያለውን ደዌና ህማም ፈውሷል፡፡ (ማቴ.4÷23፤ ማር.1÷39)፡፡ በአንድ ምኩራብ የሚሰባሰቡት ሰዎች ጥቂት ሰዎች ስለሆኑ ለማስተማር ቀላልና የእያንዳንዱን አማኝ ሐሳብና ራዕይ ለማወቅም አያደክምም፡፡ጌታ በአንድ ምኩራብ በተደጋጋሚና ባለመሰልቸት ከመቅደስ ይልቅ እየተገኘ ማስተማሩን ወንጌል ይመሰክርልናል፡፡
    እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባሊያነብም ተነሣ።”(ሉቃ.4÷16)፡፡
ሐዋርያትም እንደጌታ ልማድ እንዲሁ በመቅደስ እየተገኙ በተደጋጋሚ አስተምረዋል፡፡ “በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ”(ሐዋ.13÷5)፡፡“ በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ። ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር …”(ሐዋ.17÷1-2)፡፡
    ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን መምሰል ካለባት አገልግሎቷ እርሱ ያገለገለው እንጂ ሌላ አገልግሎት ሊኖራት አይገባም፡፡ምንም እንኳ ምኩራቡን የሰሩት አይሁድ ቢሆኑም ጌታ ግን በምኩራባቸው ተገኝቶ አስተምሯል፡፡
        በአገልግሎት ዓለም የአማኙን ልብና ፈቃድ ሃሳብና ምኞት አኝቶ እንደማገልገል የሚያረካ ነገር የለም፡፡የምኩራብ ዋና ዓላማ ይህ ነው፡፡ አባወራዎቹን በአድራሻቸው ማግኘት፡፡እነርሱ በተሰበሰቡበት በመንደራቸው ምኩራብ በዚያ አገልጋዩ አብሯቸው ሊገኝ ይሄዳል፡፡የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የመቅደስ እንጂ የምኩራብ አገልግሎት የላትም፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ፍሬና ብዙ አማኝ የነበረው ግን በመቅደሱ ብቻ ሳይሆን በምኩራቡ ነበር፡፡ ጌታም ብዙ ለማስተማር የደከመው ከመቅደሱ ይልቅ በምኩራቡ ነበር፡፡ የምኩራብ አገልግሎት ለህዝቡ የቀረበ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቁ የወንጌል ሥራ ነው፡፡
     ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የምኩራቡ ዓይነት አገልግሎት ያስፈልጋታል፡፡በቤተ መቅደሱ አንድ ሺህና አምስት መቶ ሰው ሰብስቦ በቅዳሴ ማሳተፍና በጉባኤ ማስተማሩ መም ቢሆንም ፍሬው ሲመዘን ግን እንደ ምኩራቡ አገልግሎት የጠራ አለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ብዙ ሰው ከኃጢአት ርቆ ከክርስቶስ ሥጋና ደም ከመሳተፍ ይልቅ የራሱ ምክንያት ይበልጥበታል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ቁጥራቸው ደግሞ ሚሊየንን ያልፋል፡፡ እኒህን ነው አማኝ ብለን  ዕድሜ ልክ ተሸክመን የኖርነው፤አሁንምያለነው፡፡እንዲህ ያሉ ሰዎችን ግን ከመቅደሱ ልግት ባለፈ በምኩራቡ ዓይነትአገልግሎት ማግኘት ይገባናል፡፡በአድራሻቸው ሄደን የተቸገሩበትንና የታሰሩበትን እስራት ልንፈታላቸው ይገባናል፡፡ አስራት በኩራት ለመሰብሰብ የሰው በር እያንኳኩ ከማሰልቸት አማኙ ወዶ እንዲሰጥ ቤቱን ምኩራብ አድርገን ከሚስቱ ከዘመዶቹና ከልጆቹ ጋር ልናስተምረው ይገባናል፡፡በመቅደሱ አውደ ምህረት ላይ ብቻ ከመጮህ ወደምኩራብ ዝቅ ብለን ህዝቡን በያለበት አድራሻው ፈልገን እናገለው ዘንድ ይገባና፡፡
  አዎ! የህይወት አገልጋይና አማኝ ለማፍራት የምትሻ ቤተ ክርስቲያን መቅደስ ብቻ ሳይሆን ምኩራብም ያሻታል፡፡ማደግ በየጥቂቱ ነው፡፡ ስለዚህም ለጤናማ መንፈሳዊ እድገት ከምኩራብ ወደመቅደስ ማደግን እንደግ፡፡ጊዜያችንን በድንጋይ ብቻ “መቅደስን” በመስራት አናባክነው፡፡የዳኑ ነፍሳት ያሉባቸውን ጥቃቅን ምኩራቦችም ይልቅ ይሁኑልን፤ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ነውና የምትታነጸው፡፡
                   የእግዚአብሄር ጸጋና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን//