Saturday, April 8, 2017

❖ሆሳዕና ፦

   ሆሳዕና ማለት አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው! 
 ከዛሬ 1977 ዓመታት በፊት የሚቀድሙ እና የሚከተሉ ሕፃናት እና አዋቂዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ልብሳቸውን አንጥፈው የሰማዩ ልዑል በተናቀች አህያ ጀርባ ተጭኖ ሲገባ  "ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።" (ማቴ 21:9)
   መረጋጋት ላቃታት ለኢየሩሳሌም ቅኝ አገዛዝ ለጸናባቸው ለአይሁድ አሁን አድነን ትልቅ ልመና ነበረ፡፡እያመሰገኑ መለመን መታደል ነው፡፡በልቡ እንቆቅልሽ ታቅፎ ከከንፈሩ የእግዚአብሔር ምስጋና የማይጎድልበት ምስጉን ነው፡፡ ዛሬም ሆሳዕና እንበል፥ የምስጋና ነዶ በፊቱ እያከማቸን አቤቱ አሁን አድን እንበል፡፡ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ እያልን እንጩህ!
ወንጌል ስለ ሆሳዕና ምን አለ?
ለጌታ ያስፈልጉታል!
"በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።" (ማቴዎስ 21:2)
  ደቀመዛሙርቱ የታሰሩትን እንዲያስፈቱ ተልዕኮ ሲሰጣቸው "ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ" ከሚል ትእዛዝ ጋር ነበረ፡፡ ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣው በኃጢአት የታሰረውን የሰውን ልጅ ለመፍታት ነው፡፡ አዎ!  ታስሮ አስፈትቶናል፥ ወድቆ አንስቶናል፥ ደሙን ክሶ ከማዕሰረ ኃጢአት ቶናል፡፡ ዛሬም በሱስ በኃጢአት በተንኮል በክፋት በአመፃ ወደታሰሩት ሰው ይልካል! ከሞት ጋር ወደተስማሙት የምዋቹን ሞት የማይፈቅድ ጌታ አገልጋዮችን ይልካል፡፡ እኛ ተስፋ የቆረጥንባቸው ሁሉ ለጌታ ያስፈልጉታል፡፡ ዛሬም የታመሙ እንዲፈወሱ፥ የወደቁ እንዲነሱ፥ የታሰሩ እንዲፈቱ፥ ያዘኑ እንዲጽናኑ፥ የተሰበሩ እንዲጠገኑ፥ የጠፉ እንዲገኙ ክርስቶስ ይፈልጋል፡፡ የኃጢአት እሳት ላይ የሚጫወተው፥ በሞት መንደር ያንቀላፋው ትውልድ ባለቤት አለው፡፡ ፈላጊ አለን፥ አክባሪ አለን፥ የማይጸየፈን አባት አለን፡፡ በራሳችን ተስፋ የቆረጥን፥ ለማንም አላስፈልግም የምንል ለጌታ እናስፈልጋለን፡፡
ንጉሣችን ይመጣል! 
" ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።" (ማቴዎስ 21:4-5)
   በመገፋት የእርሱን ቀን ለምትጠብቁ፥ ቀን ያስጎነበሳችሁ፥ ከተማችሁ በቅኝ ገዥዎች የተያዘባችሁ፥ ስጦታው ነክቷችሁ በጸጋ ተሹማችሁ ዙፋን ተከልክላችሁ ወደ ምድረ በዳ የተሰደዳችሁ፥ ወንድማችሁ የቃየልን ድንጋይ እያሳየ የሚያስፈራራችሁ ንጉሣችን ይመጣል የሚያነግሰው ይመጣል ቀን አውጭው ይመጣል የሆሳዕና የዋህ ሆኖ እንደ ትንቢቱ የመጣው በስልጣን ይመጣል!
የሚቀድሙት እና የሚከተሉት የእርሱ የምስጋና ሠራዊት ናቸዉ!
" የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።" (ማቴዎስ 21:9)
  በአህያ ጀርባ ያየነው በእሳታውያን ኪሩቤል እና በሱራፌል ጀርባ የነበረ ነው፤ ይህ ምስጋና ይገባል። የሚቀድሙት ነቢያት፡ የሚከተሉት ሐዋርያት አመስግነውታል። ወደፊትም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በጉን ይከቡታል፤ ወድቀው ይሰግዱለታል፡፡ ትውልድ ለምስጋና ይነሳ ለእርሱ ያንጥፍ ለእርሱ መንገዶች ሁሉ ክፍት ይሁኑ ለእርሱ አንደበት ሁሉ ይቀኝ ለእርሱ ትልቅ ትንሹ አዋቂ ሕፃኑ ምስጋና ያቅርብ!
ይህ ማን ነው ?
"ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ።" (ማቴዎስ 21:10)
  ይህ ማነው ከተማ የሚናወጥለት ? ይህ ማን ነው ዓለሙ ሁሉ የሚከተለው ? ይህ ማነው ? ይህ የኛ ልዑል ነው፡ ይህ የኛ ቤዛ ነው፡፡ ይህ የኛ የዘመናት ወዳጅ ነው፡፡ ይህ የኛ አምላክ ነው። ሞገድ ባሕር የሚታዘዝለት ይህ ማን ነው ? ልዑል ሳለ በትሕትና የተገለጸ ይህ ማነው ? ንጉሥ ሆኖ ሳለ የዋህ የሆነ ይህ ማነው? ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
አንኩራበት፦ 
" ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው።" (ሉቃስ 19:39-40)
  እርሱ የምስጋና ጌታ ነው፤ ባናመሰግነው ምስጉን ነው፡፡ በምስጋና የምንጨምርለት፤ ባለማመስገን የምንቀንስበት ነገር የለም፡፡ ስለዚህ አመስጋኞችን አንገስጽ፡፡ እጃችንን አጣጥፈን ዳር ይዘን ተመልካች አንሁን፡፡  ሜልኮል ኮርታ ምን አተረፈ? አንኩራ አንታበይ እኛ ዝምታን ብንመርጥ ድንጋዮች እንኳ ለቅኔ ሊነሱ ዝግጁ ናቸውና፡፡
የልባችን ደጅ ይከፈት! 
" ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ።እናንት መኳንን በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ።ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል።" (መዝ 24:6-9)
  ዛሬ የቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ በዚህ ቃል የተመሠረተ ነበረ፡፡ ይህ ልዑል የዘላለም ደጆችን የከፈተ ነው፥ የሕይወት ቁልፍ በእጁ ነው፥ የገነት ቁልፍ በእጁ ነው፥ የስኬት ቁልፍ በእጁ ነው፡፡
ለሁሉ የከፈተ እርሱ እንዴት ደጅ ይዘጋበታል? መኳንንት ሆይ ክፈቱ! ሁሉም በተሾመበት ነገር ባለስልጣን ነው በሀብት በእውቀት በውበት በስልጣን ተሹመን ይሆናል እንዳንከፍት እነዚህ ነገሮች አጥምመውን ይሆን ? አታለውን ይሆን? በሚያልፈው ነን ከማያልፈው እንዳንጎድል የልባችንን ደጅ እንክፈት፡፡
እርሱ ይኑርብን፦
አህያዋ እርሱን በመሸከሟ ተከበረች፡፡ በልዩ አጀባው ውስጥ ተራመደች፡፡ እርሱ ያለው ሞገስ አለው፡፡ በተለይ በሰማይ የበለጠ ክብር ይጠብቀዋል፡፡ ልባችን የእርሱ ዙፋን ከሆነ መክበር አለ፡፡እርሱን እያሳየን እንዙር፡፡ " የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።" (2 ቆሮንቶስ 4:10)
ለሰላማችን የሚሆነውን አንግፋ፦ 
"ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮል::ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።" (ሉቃስ 19:42-44)
  ክርስቶስ የሰላም አለቃ ነው፡፡ እርሱ የሌለው ሰላም የለውም፡፡ እርሱ የልብ ሰላም፣ ዕረፍት እና መድኃኒት ነው፡፡ ለሰላማችን የሚሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ለእርሱ ደጅ አንዘንጋ፡፡ለእርሱ ጀርባ አንስጥ፡፡ ሰላሙን ለመጠቀም ልባችንን ክፍት አድርገን እንጠብቀው፡፡


Thursday, March 16, 2017

❖ደብረ ዘይት

የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት ተብሎ ይጠራል።  የጌታችን ዳግም መምጣትና  የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተብሎ ተጠርቷል።  ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተባለ።  (ማቴ.24÷ 3) ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬሕይወት”
ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።”
ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24ን ነው፡ ጌታችን ሲመጣ ፍጥረት እንደማይፀና ኃጢአተኞች ደስታእንደማይሰማቸው ይገልጣል፡ በኃይሉ ፊት ፍጥረት፣ በፍርዱ ፊት ኃጥአን መቆም አይችሉምና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በብሉይ ኪዳን እመጣለሁ ብሎ መጥቷል፡ በአዲስ ኪዳንም እመጣለሁ ብሎ ቤተክርስቲያንን በተስፋ አስገዝቷታል።  ፍጥረት ሁሉ የሚጠብቀው አንድ ታላቅ እንግዳ ከፊታችን ባለው ባልራቀው ዘመን ይመጣል፡፡የሚመጣው በትሕትና ሳይሆን በልዕልና ነው።  በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል።  ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው ሆኖ አይመጣም፣  ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ይመጣል  ከእናቱ ጡትን እየለመነ አይመጣም፣ ለፍጥረት ሁሉ የሩጫውን ዋጋ ለመስጠት ይመጣል።  ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ አይመጣም።  ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ ይሰደዳሉ።  ለእኛ ለክርስቲያኖች መጣልን የምንለው እንግዳችን፣ ፈራጃችን እንጂ መጣብኝ የምንለው አይደለም፡፡

የጌታችን ዳግም ምጽአት፡-

1. የጸሎታችን መልስ ነው።
2. የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።
3. የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
4. የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
5. የእምነታችን ክብር ነው።
6. የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
7. የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡ 

              የጸሎታችን መልስ ነው
  ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ።  ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። ልበ ሙሉ ሆነው  ኃጢአት እንዳይሠሩ የመምጣቱ  ዜና ስለሚረብሻቸው ነው።  የጌታችን ዳግም ምጽአት በሚታሰብበት ቀን እንኳ ብዙ የኃጢአ ትመታሰቢያ ሲደረግ ይውላል።  ለብዙ ሰዎች እኩለ ጾም ከሥጋና ከስካር ከተላቀቁ አንድ ወር መሆኑን ለመገናኘትም ወር እንደሚቀራቸው የሚያስቡበት ቀን ነው።  በጊዜያዊ ጨዋነት የሰነበቱትም ሲሰክሩ የሚውሉበት የተውኔት ቀናቸው ነው።  ሃይማኖት የማይሞት ኃይል ነው።  ከሰው ልብ ግን ሊሞት የሚችለው ሰዎች እንደ ባሕል ቆጥረውት ሲኖሩ ነው።
 የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው።   የምንፈራውና ያርቅልኝ የምንለው ሳይሆን በየዕለቱ “መንግሥትህ ትምጣ”  እያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው።  የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው።  በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ.14÷17) ።  የክርስቶስ መንግሥቱ  የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ  ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው።  ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው።

የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው

ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” ይላል።  (ሮሜ.8÷19)ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” ይላል ቁ.22) ። በሰው ኃጢአት የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው። እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት እየተካፈሉ ነው። እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው። ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግ የሰውን ማረፍ ይናፍቃል።  የራሱም ዕረፍት ነውና።  ዛሬ በብዙ ነገር እናለቅሳለን።  ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን።  የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።

የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው
ማራናታ ማለት ጌታ ይመጣል ወይም ጌታ መጣ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 609) ።  ይህ ቃልዮሐንስ ራእዩን ሲዘጋ ተጠቅሞታል፡- “ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ.22÷20)።  ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው  የዘመናት ጣር ካየበኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌታ መምጣት እንደሆነ ተረዳ  ስለዚህም  ማራናታ አለ።  የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው።  በመጀመሪያ ምጽአቱ ሞት ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ መከራ ገደብ ያገኛል።

የተስፋችን ፍጻሜ ነው

የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡። የምንጠብቃቸው ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም።  ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እስከማያምረን ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “የተባረከውተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ.2÷12 13) ይላል።  ሰዎች ተስፋ ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ።   እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው። የክርስቶስ ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው።  ለቤተ ክርስቲያን የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው።
  
የእምነታችን ክብር ነው

ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡ የዘበቱብንና ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም።  የእግዚአብሔር ልጆች የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን በጉን እረኛችን አድርገን ወደ ፍስሐ ዓለም እንገባለን።

የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው
በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም” ይላል (ራእ.21÷1) ።  አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው።  ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው።  አሁን ፍጥረት አርጅቷል።  በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨመ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው።  ይህን አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣትነው።  ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል።

የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው

ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች።  ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያንበጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ።  ገነት ጊዜያዊ የነፍሶች ማረፊያ ናት። ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ። መንግሥተሰማያትና ገሀነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41) ።

የዘላለም ዘመንም ይከፈታል።  ዘወትር አዲስ የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን።

የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው።  ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው። ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል።

                 የእግዚአብሄር ጸጋና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን//