Friday, April 5, 2019

❖የዘለዓለም መኖርያ፦

የዘላለም መኖሪያ

"ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥
በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም። መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥  የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤" ዘዳ 33:27

የሰው መሠረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፥ መጠለያ፥ ልብስ ናቸው።ልብስ እና ምግብ ኖሮን በኪራይ መኖሪያ ተጠልለን እንኖራለን።አንዳንዶች ይህንም ስላልቻሉ በየጎዳናው ያድራል።ቃሉ ለሁሉ የሚበቃ የዘላለም መኖሪያ እግዚአብሔር እንደሆነ ይነግረናል።ከእርሱ ርቃን በደጅ ያለን፥ ከፍቅሩ ተለይተን ራሳችንን በስቃይ የምንጎዳ፥ ያለ እርሱ ወጥታን ባክነን  የምንመለስ፥ ያለእርሱ ዘምተን የተሸነፍን ፥ ያለ እርሱ ሮጠን ያልቀደምን ፥ ያለ እርሱ በልተን ያላማረብን፥ ያለ እርሱ ለብሰን የበረደን፥ ያለርሱ ሰብስበን የተበተነብን ሁሉ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር እንበል  ብለን እንማልዳችኋለን።ወደ የዘላለም መኖሪያ ከተን ገብተን እንረፍ።ስለሚፈርስ ቤት፥ ዝናብ እና ነፋስ ስለሚያስገባ ቤት አይደለም የማወራችሁ።ከመከራ እና ከጉዳት የሚጠብቅ የዘላለም መጠለያ ስለሆነው አምላክ ነው።
ቃሉ እንዲህ ይለናል፦ "በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና።" መዝ 90:2 ይህ የዘላለም መኖሪያ የዘላለም አምላክ ነው።በመከራ ጊዜ መሸሸጊያ ነው።ከክፉ መዳኛ ነው።ወደ እርሱ የገቡ በውጭ ያለው የዓለም ነገር ያንስባቸዋል። እንደ እርሱ የለም።እግዚአብሔር ካለን ምንም አልጎደለን፥እርሱ ከሌለን ምንም የለንም፤ እኛም እንዳለን አንቁጠረው።ሕይወት በእርሱ መገኘት ውስጥ ስትሆን ነው በደስታ እና በባርኮት የምትጎበኘው።
የእስራኤል መኖሪያ ከነአን አይደለም።መኖሪያቸው የበረሀው ገነት እግዚአብሔር ነው።ዓለም ጭንቅ እየናጣት እኛ በደስታ የተሞሸርንበት የደስታ እልፍኝ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ትውልድ በርኩሰት ሲነድድ የእግዚአብሔር ልጆች መጠለያ መንፈስ ቅዱስ ነው።ተንከራታቾች ሆይ ወደ ዘላለም መኖሪያ ወደ ዘላለም አምላክ እንሰብሰብ።

   ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

❖የእግዚአብሔር ጸጋ፦

የእግዚአብሔር ጸጋ

የእግዚአብሔር ቃል "ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤" ይላል፡፡ወደ ቲቶ 2:11 የተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ፡-
1/ ዘር ሳይለይ ሰዎችን ሁሉ ያድናል!
2/ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ያስክዳል!
3/ የተባረከውን ተስፋችንን የኢየሱስን መገለጥ ያስጠብቃል!
4/ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንድንኖር ያስተምረናል!

የእግዚአብሔር ጸጋ የተገለጠው ኢየሱስ በሥጋ ሲገለጥ ነው፡፡ ቃሉ "ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።" እንደሚል፡፡          ዮሐንስ 1:14 የተገለጠዉ ጸጋ ለዓለም ህዝብ ሁሉ ይበቃል፡፡ ሁሉንም ለማዳን በቂ የሆነ ጸጋ ነዉ፡፡ በጸጋው ለመዳን ፈቃደኝነት እና እውነተኛ እምነት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” ይላልና፡፡ መዳን በነፃ ነው፤ ሰው ምንም ዋጋ አይከፍልበትም፡፡ ስላልከፈልንበት መዳናችን ዋጋ አልተከፈለበትም ማለት አይደለም፡፡ እርሱ ከፍሎልን ለእኛ ግን ስናምን እንዲያው (Freely) በነፃ ሰጠን፡፡ “"በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።" ሮሜ 3:24 እምነቱ እንኳን ከእኛ ነው ብለን እንዳንሞግት “የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” አለን፡፡ እንዲያው የእርሱ ሥራ ይደንቃል፡፡ አሜን ብለን እንስማማ!! እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ሊያድን እጁን በጸጋ ዘርግቷል፤ እኛም የልባችንን እጅ በእምነት እንዘርጋ።
  
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

❖የመከናወን ምንጭ፦

የመከናወን ምንጭ

ብዙዎቻችን ነገር እንዲከናወንልን፤ ኑሮ እንዲቀናልን እንፈልጋለን፡፡ ዛሬ የክንውንን ምንጭ እንመለከታለን፡፡ ዳዊት “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ (ቃል) ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም (ቃሉንም) በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።” አለ፡፡ መዝ 1፡1-3፡፡

እንዲከናወንልን ምርጫችንን (ዝንባሌያችንን) እንቀይር፡፡ በክፉዎች ምክር አንሂድ፤ በኃጢአተኞችም መንገድ አንቁም፤ በዋዘኞችም ወንበር አንቀመጥ፡፡ ሥራ ስንሰራ በጽድቅ እንስራ፡፡ ክፉዎች፣ ኃጢአተኞች እና ዋዘኞች የተባሉት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የማይሰሩ ናቸው፡፡ ምክር ወደ መንገድ ይመራል፤ መንገድ ወደ ወንበር ያደርሳል፤ ወንበር ደግሞ መድረሻን (ስኬትን) ያሳያል፡፡ የጽድቅም የአመጻም መንገድ ስኬት ይደርሳል፡፡ስለዚህ ዋናው ወደ ስኬት መድረስ ሳይሆን ወደ ስኬት ለመሄድ የመረጥነው መንገድ ነው፡፡ ብር ማግኘት ሳይሆን ያገኘንበት መንገድ መታየት አለበት፡፡ እንዲከናወንልን በእግዚአብሔር ሕግ (ቃል) እንጠቅለል፡- ደስታችን በሕጉ (በቃሉ) ይሁን፤ ቀንና ሌሊታችን ሕጉን (ቃሉን) በማሰብ፤ ለቃሉ በመታዘዝ መኖር ይሁን፡፡ ከዚያ ውጤቱ፡- በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ እንሆናለን፤ ወቅት ሳንጠብቅ እናፈራለን፡፡ የምንሰራው ሁሉ ይከናወንልናል፡፡

ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

❖የአለማወቅ ጥፋት፦

አለማወቅ የደገሰው ሞት

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አለማወቅ የጥፋት ሁሉ ምንጭ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ "ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ" ሆሴዕ 4:6 ሰው የሳተው ትልቅ እውቅት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
በአዲስ ኪዳን ደግሞ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመፈለግ ወደ ሞት እንደሚያደርስ ተናግሯል፡፡ “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ዓመፃ ሁሉ፥ ግፍ፥ መመኘት፥ ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን፥ ነፍስ መግደልን፥ ክርክርን፥ ተንኰልን፥ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፤ የሚያሾከሹኩ፥ ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።” ሮሜ 1፡28-32 እነዚህ የተዘረዘሩት 21 ነውሮች እግዚአብሔርን ለማወቅ ባለመውደድ ለማይረባ አእምሮ በተሰጡ ሰዎች የተሠሩ ናቸው፡፡ወገኖቼ እውቀትን መጥላት የለብንም፡፡ እውቀት ካጣን እንጠፋለን፡፡ በተለይ እግዚአብሔርን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ውስጣችን  እግዚአብሔርን ይጠማ፤ ፊቱን እንፈልግ፤ ሳንፈልገው የፈለገንን አምላክ እንፈልገው፡፡

ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

Thursday, April 4, 2019

❖ገብርሄር፦

ጸጋን ለሰጠን መታመን፦

ገብርኄር ማለት መልካም ፥ ቸር ፥ ለጋስ ፥ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ መታመንን፥ ታማኝ አገልጋይነትን፥ የመታመንን ዋጋ፥ የአለመታመንን ቅጣት ያመለከተበት ምሳሌያዊ ታሪክ እንደሚከተለው ቀርቧል በማስተዋል እናጥናው፦

  "ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው።አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ።ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ።ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ።ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥.....እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር።ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።"ማቴ 25:14-30

ይህ ታሪክ ምን አስተማረን? ራሳችንን አሳየን? ምንድነው የተቀበልነው ? ምን ያህል አተረፍንበት ? የጸጋ ስጦታችንን እናውቃለን? ድርሻችንን ተወጥተናል ? የኛ መክሊት ለሌሎች ምን ጠቀመ? በሌሎችስ መክሊት ምን ተጠቀምን ? በመክሊታችን ሰጭውን አከበርንበት ? እግዚአብሔር እንደ አቅማችን ማትረፊያ መክሊት ሰጥቶናል፡፡ የሰጠንን መቅበር አንችልም፡፡ በተሾምንበት ነገር ታማኝ መሆን አለብን፡፡ የተቀበልን ነን የተቀበለ ደግሞ ይሰጣል የተቀበለ ሰጪውን ያከብራል የተቀበለ እንዳልተቀበለ አይኩራራም፡፡የተሰጠንን ሳንሰጥ ከሄድን እንጠየቃለን፡፡ በተሰጠን መክሊት ራሳችንን እና ሌሎችን ለእግዚአብሔር ክብር ማትረፍ አለብን፡፡ ድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ በአቅማችን ከሠራን በተሰጠን ከታመንን እግዚአብሔር በዚህ ደስ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር አለመታመንን ይጠላል፡፡በተሰጠን ታምነን ማትረፍ አለብን፡፡

ከምድር የጠፋ ትልቁ ሀብት ታማኝነት ነው፡፡ሰው እንኳን ሰውን ራሱን የሚያታልልበት፥ ለራሱ እንኳ መታመን ያልቻለበት ሁኔታ አለ፡፡እግዚአብሔር ሳይሰጥ አልጠየቀም። ለጋስነቱን እያመሰገንን በተሰጠን ልክ ታምነን መሥራት አለብን፡፡በተሰጠን በተሾምንበት በጥቂቱ ከታመንን እግዚአብሔር በብዙ ይሾመናል፡፡ ገብርኄር የአገልግሎቱ ባለቤት እግዚአብሔር ከአገልጋዮች የሰጠውን አደራ ሊቀበል እንደሚመጣም ያሳያል፡፡ አገልጋይ ጌታ ወይም አሠሪ አለው፡፡ አሠሪው ሁሉንም በአቅሙ ልክ ጸጋ ሰጥቶ ነው ያሠማራው፡፡እንደሰጠን መጠን በኋላ ዋጋ ይከፍላል፡፡ ስለዚህ አገልጋይ አትራፊ መሆን አለበት፡፡ በተለይ መንጋውን ማትረፍ አለበት፡፡ታማኝ አገልጋይ ወይም እረኛ ለበጎቹ ሕይወት ዋጋ ይከፍላል፡፡ የተበተነውን ይሰበስባል፤የወደቀውን ያነሳል ያዘነውን ያጽናናል፥ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የራሱን ጥቅም አይፈልግም፤ በጎችን ለጥቅሙ አይሰዋም፤ ግን እረኝነት እንዲህ እየሆነ አይደለም።

እረኞች ሆይ ሕዝቡ ባለቤት አለው፥ በአግባቡ ምሩ። የሾማችሁ አንድ ቀን ወደ እናንተ ይመጣል፥ ያኔ ምን ልትመልሱ እንዳላችሁ አስቡ። ቃሉ እንደሚል "ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።" የሚለው እየተፈፀመ ነው፡፡ ሕዝ 34:3።

እግዚአብሔር የጠፉበትን ከእርሱ ርቀው እንዲሞቱ የተፈረደባቸውን ነፍሳት ደም ከእረኞች እጅ ይፈልጋል፡፡ ታምኖ የሚሠራ አገልጋይ ከክብር ጋር ከሽልማት ጋር ነው ወደ ጌታ ደስታ የሚገባው፡፡  ታምኖ የማይሰራ ከመንጋው ጮማውን እየበላ፣ ጠጉሩን እየለበሰ፣ አጥንቱን እየቀለጣጠመ ራሱን የሚያሰማራ እረኝነቱ( ፀጋው) ይወሰድበታል። ሌላ ታምኖ የሚሰራ ይዘጋጃል ዘካ 11:15 ። ታምኖ የጠፋውን በመፈለገ ማዳን ፣ የዳነውንም መቀለብ የበጎ ታማኝ አገልጋይ መገለጫ ነው።
     ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

Thursday, March 21, 2019

❖መጻጉዕ

 መጻጉዕ፦
( ፈዋሻችን ኢየሱስ ክርስቶስ)

መጻጉዕ የዐቢይ ጾም 4ኛ ሳምንት ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠበት ዘመን የፈወሳቸውን ሕሙማን ማስረጃ በማድረግ ከፈወሳቸው ሕሙማን፥ ካነጻቸው ለምጻሞች፥ ቀን ካወጣላቸው ሰዎች፥ ከሰው ከቀላቀላቸው ግፉአን፥ ጋር በመቆም ቤዛችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናመሰግንበት ሳምንት ነው፡፡ ለአምልኮ የተመረጠው የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ነው፡፡በወንጌሉ እንደተጻፈው ባለታሪኩ ሰውነቱ የሰለለ፤ ወደ መጠመቂያይቱ ተጋፍቶ የሚያስገባው ሰው የሌለው፤ ለብዙ ዘመናት ፈውሱን በተስፋ ሲጠብቅ የነበረ ሰው ነው፡፡ፈዋሹ ጌታ ኢየሱስ "ልትድን ትወዳለህን ? " ብሎ ጠየቀው፡፡እርሱም "ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።" ኢየሱስ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው።ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ዮሐ 5:7-12:: ክብር ለፈዋሹ!!

➊ ፈዋሽ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰዎች በተለያዩ ደዌዎች ሊያዙ ይችላሉ፤ ፈዋሹ ግን ሁሉን በሁሉ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው፡፡ ፈዋሹ በነፃ የሚፈውስ፥ ጤናን የሚመልስ አምላክ ነው"እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቁስልህንም እፈውሳለሁ" ኤር 30:17፡፡ በአንድም በሌላም በብዙም በጥቂትም ያድናል፡፡እኔ ፈዋሽህ ነኝ ያለ ቁስላችንን የማይፀየፍ አምላክ ነው፡፡ፈዋሹን የጠበቀ አንድ ቀን አልጋውን ተሸክሞ መሄዱ አይቀርም፡፡በዘመናችን ከእግር ጥፍራ እስከ ራስ ፀጉር ደዌ በሁሉ ሆኗል ፣ራስ ሁሉ ለህመም ልብም ለድካም ሆኗል ስሙን እየቀያየረ ደዌ ይመጣል፤ የስጋት ምንጭም ሆኗል፤ መፍትሔው ፈዋሹ ነው። ኢየሱስ ዛሬም በስሙ፣ በቃሉ እና በመንፈሱ ይፈውሳል። "እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝ" ዘጸ 15:26

➋ድኅነት የሰውን ፈቃድ ይፈልጋል፡፡ ፈውስ፣ ስጦታ እና ድኅነት የእግዚአብሔር የቸርነት ብልጽግና ፍሬዎች ናቸው፡፡እግዚአብሔር ለጥቅማችን የሆነን ነገር እንኳ አስፈቅዶ ያደርጋል፡፡ልትድን ትወዳለህ ብሎ ጠይቆ ነውና ያዳነው፡፡ጌታ ሲፈውስ ያለ ፈቃድ የፈወሳቸው በአጋንንት እስራት የተያዙትን ብቻ ነው፤ ይህን ያደረገው አእምሯቸው በሌላ አዛዥ ስለተያዘ ተናጋሪው ተከራዩ እንጂ ሕመምተኛው ስላልሆነ ነው፡፡እኛም የተያዝንበት ሕመም፥ ፈውስ ፍለጋ የወጣንበት ቁስል ይኖረናል። ፈዋሹ እግዚአብሔር ሊፈውሰን ፈቃዱ ነው፤ ምሕረቱ ግን ለሮጠ ወይም ለቀደመ ሳይሆን በእምነት ፈቃድ ለተከተለ ነው፡፡"እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ።"ሮሜ 9:16። በደዌ ሥጋ ወነፍስ ለተያዝን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፈውስ ይሁን!!!

❖ምኩራብ


 ምኩራብ፦
~የቤትህ ቅናት...!
    (መዝ.68፥9)

የዐብይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኩራብ ይባላል፡፡ይህ ሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደሱን የጎበኘበት ነው፡፡ታሪኩ በማቴዎስ እና በዮሐንስ ወንጌል ተመዝግቧል፡፡ ጌታ፣ አምላክ፣ ሕይወት እና መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቅደስ ሲገባ መቅደሱ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ የንግድ ቤት ሆኖ አገኘ፡፡ እጅግ አዘነ፥ ጅራፍ አበጅቶ እንስሳትን ከመቅደሱ አወጣቸው፡፡ሰዎችን ገሰጸ፡፡ "ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።" (ዮሐ 2፥16)  ደቀመዛሙርቱ "የቤትህ ቅናት በላኝ" የሚለውን አሰቡ፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ የምናያቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦

1- መቅደሱ የጸሎት ቤት ነው፦
በጊዜው የነበረው መቅደስ የጸሎት ቤት ነበረ። ሰዎቹ ግን የገበያ አዳራሽ አድርገውት ነበረ። ወዳጆቼ ዛሬም ቢሆን በስሙ የተሰየሙ የጸሎት ቤቶች ለታሰበላቸው አላማ መዋል አለባቸው። ቤቱ መንፈሳዊ ነው ሥጋዊነት ሊነግስበት አይገባም፡፡ ቤቱ የዕረፍት ቤት ነው ሁከት መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ቤቱ የግለሰቦች ቤት አይደለም፤ ስለዚህ ማንም ማንንም የመንካት መብት የለውም፡፡ ቤቱ የሽፍቶች ዋሻ አይደለም፡፡ ቤቱ በንስሐ ለሚመለሱ እንጂ በዐመፅ ለሚቀጥሉት መደበቂያ አይደለም፡፡

 2- ሕያው እና ቅዱስ መቅደስ እንሁን፦
ሰውነታችን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው፤ (1ቆሮ 6፥19):: ስለዚህ ሰውነታችን የቅድስና መኖሪያ ብቻ ይሁን፡፡አመፅ፣ ግፍ፣ የክፋት አሳብ በውስጣችን መኖር የለበትም፡፡በእግዚአብሔር ላይ ያመጹ አጋንንት በኛ ልብ ሸፍተው ሊደበቁ አይገባም፡፡እኛ የልዑል ማደሪያ ብቻ ለመሆን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እንሰራ፡፡ሰውነታችን በመልካምነት አጊጦ በክርስቶስ ደም ተቀድሶ የአባቱ ቤት ይሁን፡፡ቤቱን ለታሰበለት መንፈሳዊ ዓላማ መጠቀም አለብን፡፡እግዚአብሔር ያያል፥ በቤቱ የሚሆነውን እና የምንሆነውን ያያል፡፡ "ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።" (ኤርምያስ 7፥11)። ስለዚህ ራሳችንን ቅዱስ፣ ሕያው እና እግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መስዋዕት አድርገን እናቅርብ።

3- ለቤቱ እንቅና፦
ቤቱ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ነው፡፡በዚህ ዘመን ዓይናችን እያየ ብዙ የሥላሴ ቤቶች እየፈረሱ ነው፡፡ትውልድ በሱስ ሲፈርስ፥ ተስፋ ቢስ ሆኖ ሲንከራተት፥ የአጋንንት ማደሪያ ሆኖ ሲሰቃይ፥ የትውልድ ዝንባሌ ወደ አመፃ ሲሆን እያየን ተደላድለን መቀመጣችን ለቤቱ እንደማንቀና ያሳያል፡፡ወልድ የተወለደው ቀንቶልን ነው፤ መዳናችን የተፈፀመው በእግዚብሔር ቅናት ነው፡፡ (ኢሳ. 9፥7) ኤልያስ ለእግዚአብሔር ክብር ቀንቶአል፡፡"ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።" (1ነገሥት 19፥10)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጅራፍ ያነሳው ለቤቱ ቀንቶ ነው፡፡በልባችን መሽገው የነበሩትን አጋንንት በደሙ ኃይል ጠራርጎ አስወጣ፥ ለአባቱ ቅዱስና ሕያው ቤት አድርጎ ሠራን፡፡እኛ በደም የተሠራን የሠው እጅ ያልሠራን የልዑል ማደሪያ ነን፡፡የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ነን፡፡ክርስቶስ ለሞተለት የደም ዋጋ ለተከፈለለት እንቅና፡፡

4- ቅጣት ከቤቱ እንደሚጀምር እናስተውል፦ እግዚአብሔር ፈራጅ ነው፤ ከብዙ ትዕግስት በኋላ ጅራፍ ያነሳል። ያኔ ቅጣቱ የሚጀምረው ከመቅደሱ ነው ሕዝብ ጋር ከመሄዱ በፊት ባለ አደራዎቹ ከሆኑት ከአገልጋዮቹ ይጀምራል፡፡መቼ ነው የምንመለሰው ? መቼ ነው በቤቱ ተገቢ ነገር ብቻ የምናደርገው ? ንግዱ ላይ በርትተን ቢመጣስ ? ነፍሳትን እየበተኑ ገንዘብ መሰብሰብ እስከ መቼ ?
ቅጣቱ ከእኛ ይጀምራል፡፡                                       
     ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!!
===●===●===●===