Wednesday, June 5, 2019

❖እርገት፦

“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ”

“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ፤ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ ➟በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ [ላረገ] ለእግዚአብሔር ዘምሩ!” መዝ 67 (68)፥33
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው 9 የጌታ ዐበይት (ታላላቅ) በዓላት አንዱ  የዕርገት በዓል ነው።
የተቀሩት ስምንቱ፦
➠ በዓለ ትስብእት (ብስራት - Annunciation)
➟ ልደት
➟ ጥምቀት
➟ ደብረ ታቦር
➟ ሆሣዕና
➟ ስቅለት
➟ ትንሣኤ እና
➟ ጰራቅሊጦስ ናቸው።
የደብረ ታቦር በዓል በምሥራቅ አኀት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን (The Feast of Transfiguration) በመባል ይታወቃል። የመገለጥ/የመለወጥ በዓል ብለው ይጠሩታል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት 9 በዓላት በተጨማሪ ምሴተ ሐሙስን አካትቶ ፥ በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረና በብዕር ስሙ “ርቱዓ ሃይማኖት - ሃይማኖቱ የቀና” በመባል የሚታወቀው ሊቅ “ድርሳናት ዘበዓላት ዐበይት” በሚል ርእስ ፥ የጌታችንን 9 ዐበይት በዓላት የተመለከቱ ድንቅ ድርሳናትን ደርሷል።

ቤተ ክርስቲያናችን የዕርገትን በዓል በማሕሌትና በቅዳሴ እንደምታከብረው እናውቃለን። ሊቃውንቱም፦ “ዮም ፍስሓ ኮነ በእንተ ዕርገቱ ለክርስቶስ እምድኅረ ተንሥአ እሙታን በ፵ ዕለት በይባቤ ወበቃለ ቀርን ፤ አማን መንክር ስብሐተ ዕርገቱ። ማለት ፦ ከሙታን ከተነሣ ከ፵ ቀን በኋላ በዝማሬና በመለከት ድምጽ ዛሬ ክርስቶስ ስላረገ ፥ [በዕርገቱ] ደስታ ሆነ” እያሉ በደስታና በሐሴት ያዜማሉ።
ነገር ግን አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ለምን ይህን የመዳናችን ክፍል የሆነውን ታላቅ በዓል እንደሚረሱትና ልብ እንደማይሉት ግልጽ አይደለም። ምናልባት ዕርገት የሚከበርበት ቀን ሐሙስን ስለማይለቅ የሥራ ቀን ሆኖባቸው ነው እንዳንል ፥ በሥራ ቀን የሚውሉ ሌሎች በዓላትን በድምቀት ሲያከብሩ እናያለን። ስለጌታ ዕርገት ያላስተዋልነውና ብዙ ልንማረው የሚገባ ነገር አለ።

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በይባቤ መላእክት በክብር ወደ ሰማያት ላረገው ጌታና አምላክ እንድንዘምር ያዘናል። አበው መተርጉማን “ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ፤ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ” የሚለውን የዳዊትን መዝሙር ሲተረጉሙ፦ ለገነት ምዕራብ ከምትሆነው ከሲኦል ነፍሳትን አውጥቶ ወደገነት ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ፤ አንድም ➟ ለኢየሩሳሌም ምሥራቅ በምትሆነው በደብረ ዘይት በኩል ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ማለት ነው ብለዋል። ይህ የድል ዝማሬ ነው ፤ በዚሁ በ67ኛው የዳዊት መዝሙር ቁጥር 18 ላይ “ዐረገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ - ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም (ሰማይ) አረግህ” ተብሎ እንደተዘመረ ፥ ነፍሳትን ከሲኦል ግዞት ነጻ አውጥቶ በክብር ላረገው ጌታና መድኃኒት የአምልኮ ዝማሬ ይገባል።

መቼም ነቢይ ወንጉሥ የሆነው ዳዊት “እግዚአብሔር ዐረገ” “ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ” ሲለን እግዚአብሔር መውጣት መውረድ እንደሌለበት እናውቃለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ፥ ይህ ትንቢታዊ ቃል የተነገረው ቃልን ለተዋሐደው ሥጋ እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ። በድጋሚ ዳዊት በ46ኛው መዝሙሩ (ቁ.5 ላይ) ፦ “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ፥ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ፥ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ - ጌታችን እግዚአብሔር በይባቤ መላእክት ፥ በቅዳሴ ፥ በሥልጣን ዐረገ ፤ ለአምላካችንና [ለንጉሣችን ለክርስቶስ] ዘምሩ (ምስጋና አቅርቡ)” ይለናል። ወረድ ብሎ ደግሞ (ቁ.8 ላይ) 

➟ “እግዚአብሔርሰ ይነብር ዲበ መንበሩ ቅዱስ - እግዚአብሔር ግን በቅዱስ መንበሩ ይቀመጣል” ሲል ይዘምራል። ይህም ከላይ እንደተገለጸው ፥ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም ደግሞ የእግሩ መረገጫ ለሆነችለት ለእግዚአብሔር መውረድና መውጣት እንደሌለበት (ዐረገ ፥ ወጣ ፥ ወረደ እንደማይባል) ፤ ነገር ግን ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል (ወልድ) በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም የእኛን ባህርይ ወስዶ ሥጋን ስለተዋሐደ ፥ ያረገውም ከድንግል በነሣው በዚሁ ሥጋ ስለሆነ “እግዚአብሔር ዐረገ” ወይም ቃል በሥጋ ዐረገ ማለት እንደሚቻል ያመለክታል። በሌላ መልኩ ይህ ዝማሬ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ከሚያስረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች አንዱ ነው።

እንደ አባቶቻችን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትርጓሜ ፤ ቃለ እግዚአብሔርን የተዋሐደው ሥጋ በተዋሕዶ እንዳረገ የሚያስረዳው ተጨማሪ የዳዊት ዝማሬ፦ “ተፅዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሠረረ - በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ” የሚለው ነው (መዝ 17/18፥10)፡፡ ዳዊት ይህን ዝማሬ የሚዘምረው ➟ “አጽነነ ሰማያተ ወወረደ” (ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ወረደ) ካለ በኋላ ነው። “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ፥ መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም ፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንደጻፈልን (2፥6-7) እኛን ያድነን ዘንድ በትህትና የተገለጠው ወልደ እግዚአብሔር ፥ የማዳኑን ሥራ ፈጽሞ ዐረገ። መድኃኒታችን ክርስቶስ ፥ ሰው የሆነ አምላክ ነውና “በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ (ዐረገ)” የሚለው የዳዊት ዝማሬ ሥጋ በተዋሕዶ ማረጉን ያመለክታል።

ከላይ የጠቀስነው “ርቱዓ ሃይማኖት” በሚል ስም እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ በጌታችን ዕረገት ላይ ድርሳን (treatise) የጻፈው ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ዘሰግላ) ግሩም በሆነ ትርጓሜ “መጽሐፈ ምሥጢር” በተሰኘው መጽሐፉ ፦ “ያዕቆብ ሆይ ከኛ ጋር በዓልን ታደርግ ዘንድ ና! ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የወርቅ መሰላል ደብረ ዘይት ላይ ተተክሎ ጫፉ ሰማይ ደርሷል ፤ ይህ የወርቅ መሰላል ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ሰማይ ከወጣው የወልድ ሥጋ ዕርገት ሌላ ምንድን ነው?” ይለናል። በፊልጶስ ምክንያት ወደ መድኃኒታችን ክርስቶስ የመጣው ናትናኤል ከጌታ “ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” የሚል ቃል እንደሰማ እናውቃለን (ዮሐ 1፥52)፡፡ ለዚህ ነው አባ ጊዮርጊስ ፥ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ከምድር እስከ ሰማይ በሚደርስ መሰላል ላይ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያየውን ያዕቆብን ፥ የህልምህ ፍቺ በጌታ ዕርገት ቀን ተፈጽሟልና ይህን ምሥጢር ታይ ዘንድ ፥ ከእኛም ጋር “በዓልን ታደርግ ዘንድ ና!” የሚለው።

በተመሳሳይ መልኩ ፥ በደብረ ታቦር ሙሴ የጌታችንን ግርማ-መለኮት እንዳየ ፥ ግሩምና ድንቅ የሆነውን ዕርገቱን ያይ ዘንድ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር እንዲህ ሲል ይዘክረዋል፦ “ሙሴ ሆይ! ሕዝብህን ቀን በደመና ፥ ሌሊት በእሳት ዐምድ የመራቸው ጌታ ፥ ወደ ላከው ወደ አብ በእሳት ዐምድ ዐረገ።” የምስጋና ንጉሥ ፥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ሆኖ በመላእክት ይባቤ ሲያርግ ፥ ለንጉሡ የሰማይ ደጅን ይከፍቱ ዘንድ የሰማይ መላእክት “አርኅዉ ኆኃተ መኳንንት” በሚል ቃል ታዝዘዋል። ንጉሡ ሲያርግ መላእክት ያጅቡት እንደነበር ፥ በሰው መልክ ተገልጠውና ነጫጭ ልብሶች ለብሰው ሐዋርያትን ካናገሯቸው መላእክት መረዳት እንችላለን።  ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምና ከሌሎች ቅዱሳት አንስት ጋር በአንድ ልብ ለጸሎት ይተጉ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ፥ በቢታንያ ተራራ ላይ እጆቹን አንሥቶ የባረካቸውን ጌታ እያዩት ከፍ ከፍ ሲል ደመናም ከአይናቸው ሰውራ ስትቀበለው ፈዝዘው ይመለከቱ ነበር። በዚህ ጊዜ ምስጋና ለሚገባው ንጉሥ ይባቤ እና ውዳሴ ያቀርቡ ከነበሩት መላእክት መካከል ሁለቱ፦ “የገሊላ ሰዎች ሆይ ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት ፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (የሐዋ ሥራ 1፥11)፡፡

ከሰማይ የወረደው እርሱ ወደ ሰማይ ሲወጣ ➟ “እናንተ መኳንንቶች ፥ በሮችን ክፈቱ ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” የሚል ዝማሬ በሰማይ ተሰማ። (መዝ 23/24፥9) የሰማይ መኳንንት የሆኑት እነ ሚካኤል ፣ ገብርኤል ፣ ሩፋኤልና ሌሎችም ቅዱሳን መላእክት የሰማይን ደጆች አንዲከፍቱ ታዘዙ። ስለሆነም “ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” የሚለው የጌታችን ትንቢታዊ ቃል ተፈጸመ። በሰማይ መከፈትና መዘጋት ባይኖርበትም ፥ ይህ አባባል በዕርገተ ኢየሱስ የተገለጠውን ታላቅ የሥጋዌ ምሥጢር ያመለክታል፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “ኦ አዳም ናሁኬ ተፈጸመ ዘይቤ እግዚአብሔር አመ ፀአትከ እምገነት አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ ➟አዳም ሆይ ከገነት በወጣህ (በተባረርክ) ጊዜ እግዚአብሔር “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ያለውን [ትንቢታዊ ቃል] እነሆ ተፈጸመ” ሲል አመስጥሮ እንደጻፈልን። አዳምን ካነሳ አይቀር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ሔዋንንም፦ “ኦ ሔዋን ተፈሥሒ በሞገሰ ወለትኪ …ዝኩ ዘወለደቶ በአንቀጸ ሥጋሃ ኅቱም ተለዓለ ኀበ አቡሁ ሰማያዊ እንዘ ትኔጽሮ ቀዊማ ምስለ አርዳኢሁ ቡሩካን ➠ ሔዋን ሆይ በሴት ልጅሽ (በድንግል ማርያም) ሞገስ ደስ ይበልሽ ፤ . . . በታተመ ድንግልና የወለደችው እርሱ ፥ ከተባረኩ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆማ እያየችው ወደ ሰማያዊ አባቱ ዐረገ” ይላታል።

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ክርስቶሳውያን! መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዳነን ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ባደረገው አጠቃላይ (holistic) የማዳን ሥራ (እንደ አበው አባባል ፦ በሁሉ እየካሰልን) ስለሆነ ፥ የዕርገት በዓል የድኅነታችን (የመዳናችን) በዓል ነው። አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ በተሰበሰቡት 318 አባቶች ስም የተሰየመው የቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴ፦ “ተዘከር ሥጋ እንተ ነሣእከ እምቅድስት ድንግል ከመ ውእቱ ሥጋ ዘዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ➠ ወደ ሰማይ ያረገውና በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ከድንግል የነሳኸው ሥጋ እንደሆነ አስብ” ይላል። ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተነሳው ሥጋ ፥ የእኛ ሥጋ ነው። ስለዚህ ዕርገትን ስናከብር ፥ ሥጋችን ዐርጎ በኪሩቤል ጀርባ ፥ በአብ ቀኝ መቀመጡን ልብ እንበል። በእውነት ለተወደድንበት ዘላለማዊ ፍቅር ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ያለጥርጥር ታላቅ” እያለ ለሚያደንቀው በሥጋ ለተገለጠው ምሥጢር አንክሮ ይገባል! (1 ጢሞ 3፥16)፡፡ አባቶቻችን በቅዳሴ እንደነገሩንም፡- “ኦ እንተ አፍቀርካ ለዛቲ ዘመድነ ➠ አቤቱ ባህርያችንን የወደድሃት” እያልን የተወደድንበትን በሞት የተገለጸ ፍቅር እናድንቅ እናወድስም!

ከመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ ስለሆንን (2ኛ ጴጥ 1፥4) “ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአል” ተብሎ እንደተጻፈ (ሮሜ 8፥29) የልጁ መልክ በውስጣችን እስኪሳል ድረስ ኃጢአትንና ርኵሰትን ተጸይፈን የተጠራንበትን የቅድስና ሕይወት ልንለማመድ ይገባል! ሥጋችንን ያከበረው ፥ ከአእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢረ ተዋሕዶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደው አምላካችን ፥ ሰውነታችንን (ሁለመናችንን) እርሱን ደስ የሚያሰኝና ፥ ሕያው ፥ ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን እንድናቀርብ ያዝዘናል። (ሮሜ 12፥1) አገልግሎታችንንና “የምስጋና መሥዋዕት” የተባለው (መዝ 49/50፥14) የከንፈራችንን ፍሬ (ዝማሬያችንን) እግዚአብሔር ፊት ስናቀርብ ሥጋንና ነፍስን ከሚያስነውር ማንኛውም ዓይነት ርኵሰት ርቀን ፥ ኃጢአትንም ተጸይፈን መሆን አለበት።

የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን በዝሙት እያረከሰን ፥ መቅደሱን አፍርሰን እንዘምር ብንል በእግዚአብሔር ላይ መዘበት ይመስልብናል። የምናመልከው አምላክ ደግሞ ሽንገላን የማይወድ “እውነት ፥ መንገድና ሕይወት” ተብሎ የተጠራ ጻድቅ ነውና “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ተብሎ ተጽፏል (ገላትያ 6፥7)፡፡ ቅዱስ ያሬድን በመከተል ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ስለጌታ ዕርገት ሲያስተምሩ፦ “ዐርገ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ➠ የጻድቃንን (የእውነተኛ ልጆቹን) ዕርገት ያጠይቅ ዘንድ ዐረገ” ይላሉ። እውነት ነው “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ . . . ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ 14፥2-3) ሲል በማይታበል ቃሉ የነገረን አምላካችንና መድኃኒታችን ለእኛ ለልጆቹ ሰማያዊ ሥፍራ ያዘጋጅልን ዘንድ ዐረገ። በእርሱ ያመኑ ፣ እርሱን በፍቅር የተከተሉ ልጆቹ ቢሞቱ እንኳ ወደ ሕይወት ይሻገራሉ እንጂ ሞት የለባቸውምና: ነፍሶቻቸውን ቅዱሳን መላእክት በክብር ያሳርጋሉ። ጌታዋንና አምላኳን የምትወድድ ነፍስ ከሥጋዋ በሞት ተለይታ ወደ ሰማይ በምታርግበት ጊዜ ፥ “በውዷ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?” የሚለው ፥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚበልጠው የሰሎሞን መዝሙር ይዘመርላታል (መሐልየ መሐልይ ዘሰሎሞን 8፥5)፡፡

በመጨረሻም ወገኖቼ፦ በመላእክት ቅዳሴ እና ይባቤ ላረገው ለንጉሡ ኢየሱስ (ለኢየሱስ ክርስቶስ) የተዘመሩ ዝማሬያትን ልብ እንበል። ስለ ዕርገቱ የተቃኙ የዳዊት ዝማሬያት በሙሉ “ዘምሩ” የሚል ትእዛዝ አለባቸው፦ “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ . . . ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ ፤ ዘምሩ ለንጉሥነ ዘምሩ ➠ አምላክ በእልልታ ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ ፤ ዘምሩ ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ፤ ዘምሩ ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ” (መዝ 46/47፥5-6)፤ “ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ➠ ወደ ሰማይ ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (መዝ 67/68፥33)፡፡ ስለሆነም የዕርገት ቀን የዝማሬና የይባቤ ቀን ነው ፤ ዛሬ ያልዘመርን መቼ ልንዘምር ነው? ጥምቀትን ደመቅ አድርገን ስናከብር ፥ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ . . .” የሚል አገርኛ አባባል አለን። ስለጌታ ዕርገት ከላይ የተዘረዘሩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ኦርቶዶክሳዊ ምልከታዎችን ልብ ብለን “ለዕርገት ያልሆነ መዝሙር . . .” የሚል አዲስ አባባል ልንፈጥር ይገባል።
አዎን! በይባቤ ፥ በመለከት ድምጽ ላረገው ጌታና ንጉሥ ከመላእክቱ ጋር አብረን እንዘምር።
ይህ የምስጋና ንጉሥ ስለኃጢአታችን የተሠዋ የእግዚአብሔር በግ ነውና። በሰማያት ለታረደው በግ የሚቀርበውን ዝማሬና ውዳሴ እኛም በምድር እንድገመው።
➦ ራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ 5፥8 . . . አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
➦ 9-10 መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ፥ ታርደሃልና ፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው ፥ በምድርም ላይ ይነግሳሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።
➦ 11 አየሁም ፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር።
➦ 12 በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።
➦ 13 በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።
➦ 14 አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።
✟➫ ሥጋችንን ከመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ አድርጎ ላከበረን ፥ ከድንግል ማርያም በነሳው በእኛ ሥጋ ወደ ሰማያት ላረገው ፥ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ለተቀመጠው ፥ በክብር እንዳረገ ከደመና ጋር ዳግም ለሚመጣው ፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ ለእርሱ ፥ ከባሕርይ አባቱና ማሕየዊ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ፣ ኃይል ፣ እልልታ ፣ ይባቤና ሽብሸባ ፣ ምስጋናና ውዳሴም ይሁን።
   ~~~~~~||~~~~~~

Tuesday, May 14, 2019

❖ፋሲካ፦

“ፋሲካ”
              የእስራኤል ልጆች የብሉይ ኪዳኑን ፋሲካ በተለያየ ዘመን እንዴት እንዳከበሩት ስናስተውል እንዲህ የሚመስሉ ቁም ነገሮችን እናገኝበታለን፦

 በሙሴ ዘመን፦
  የመጀመርያው ፋሲካ እንዲፈጸም የተሰጠው ለሙሴ ሲሆን ይህም በፈርዖን ቤት የበኵር ልጅ ሲገደል፥ በቤተ እስራኤል ይህ መቅሰፍት እንዳይደርስና እንዲያልፋቸው  ተሰጠ። (ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነውና) 

ይህም የዘለዓለም ሥርዓት እንዲሆናቸው ተሰጣቸው፡፡ (ዘጸ.12፥14)

ለፋሲካው የሚቀርበው ጠቦት በግ “ነውር የሌለበት”(ዘጸ.12፥5) ነው፡፡ ይህ በግ የሚበላው በመራራ ቅጠልና እርሾ በሌለበት ቂጣ እንዲሆን ታዘዋል፡፡

በእነዚህ የበዓል ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የሚበላ፦
“ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ” (ቁ.15) የሚል ግልጥ ማስጠንቀቂያ አለ፡፡
ስለዚህም ከዚህና ከሌሎችም ማስጠንቀቂያዎች የእስራኤል ልጆች ራሳቸውን ይጠብቁ ነበር፡፡ (ዘኍል.9፥6)

ነውርና ዕድፍ የሌለበትን ጠቦት በጉን ለመመገብ እርሾ የሌለበት ቂጣ አብሮ መቅረብ እንዳለበት ተነገረ፡፡

ይህ ነገር ለአዲስ ኪዳኑ በግ በምሳሌነት (ዮሐ.1፥29) መነገሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እርሱ ነውርና  እድፍ የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ አምላክና ሰው ነውና (1ጴጥ.1፥18-19)፡፡ 

ከእርሱ መዋጀትና መቤዠት የተነሳም ሞትና ሲዖል ደጅ ደጃችንን እያየ ሳይነካን አልፎናል፡፡
እርሱ ፋሲካችን ፤ ሞትን መሻገሪያ መርከብ ፤ ማለፊያ ታንኳችን ሆኖልናልና (1ቆሮ.5፥7)፡፡
ዋና ፋሲካችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ለማክበርና ለማምለክ ግን የኃጢአትና የመበስበስ ምሳሌ ከሆነው ከእርሾ ሕይወት መራቅና ንስሐ በመግባት መመለስ አለብን፡፡

የኃጢአተኞች ምክር ፣ የክፉዎች ትምህርት እርሾ ፤ ኃጢአት ተብሎ ተጠርቷል (ማቴ.16፥6-12 ፤ ማር.8፥15 ፤ ሉቃ.12፥1 ፤ 1ቆሮ.5፥6-8)፡፡ 
ቅዱሱን ፋሲካ በቅዱስ ሕይወትና ኑሮ ልናከብረውና ልናመልከው ተጠርተናል፡፡

 በኢያሱ ዘመን፦
የእስራኤል ልጆች የግብጽን ሸለፈት በጌልጌላ እንዲያስወግዱ ከተደረገ በኋላ፥ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ከነሸለፈታቸው ወይም ከነግብጽ ነውራቸው በዓሉን እንዲያከብሩ የፈቀደ አይመስልም፡፡ ስለዚህም ንጹሐን እንዲሆኑ ከዚያም በዓሉን እንዲያከብሩ ወደደ (ኢያ.5፥7-10)፡፡
     ሸለፈት የኃጢአትና የነውር ምሳሌ ሆኖ ተገልጧልና የእስራኤል ልጆች ወደተስፋይቱ ምድር ሳይገቡና የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው በፊት እንዲያስወግዱ ተነገራቸው፡፡

ከጾሙ በፊት በነበርበት ማንነት ከጾሙም በኋላ ብንገኝ፥ እጅግ በሚብስ ኃጢአት ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ የቀድሞውን ሳናውቅ ሊሆን ይችላል ፤ ከነሸለፈታችንና ከነነውር ኃጢአታችን እንመላለስ ይሆናል ፤ ከጾሙና ከጸሎቱ በኋላ በዚያው ኑሮ ብንመላላስ ግን አውቀን በድፍረት ኃጢአት ውስጥ እየተመላለስን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አመጸኞች መሆናችንን ያሳያል፡፡ ታዲያ ጽኑ ፍርድ ቢያገኘን ምን ይደንቃል? ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡

 በኢዮስያስ ዘመን፦
የስምንት ዓመቱ ትንሹ ንጉሥ የልቡ ማስተዋል ትልቅ ነበር፡፡ የስሙ ትርጉም እንኳ “እግዚአብሔር ይደግፋል” ማለት ነው፡፡ 

አሥራ ስድስተኛው የይሁዳ ንጉሥ ሲሆን፥ ከዳዊት ቤት ከተነሡት መልካም ነገሥታት የመጨረሻውም ነበር፡፡ ለእግዚአብሔር አምልኮ በመቅናቱም ምክንያት፦
“መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፥ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ።”(1ነገ.13፥2) ተብሎ የተነገረውን ትንቢት በመፈጸም ከይሁዳ እስከገሊላ ምድር ድረስ ባዕድ አምልኮን ከምድሪቱ ሁሉ አጠፋ፡፡
  
በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመን የሆነው እጅግ ውብ ነገር፥ 

1/ በሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ አማካይነት የጠፋው የሕጉ መጽሐፍ ተገኝቶ ነበር፡፡ 

2/ መጽሐፉንም ካነበበው በኋላ ሕዝቡና እርሱ ያለበትን አስከፊ የኃጢአትና የውድቀት ሕይወት በመመልከት፥ ራሱን እጅግ በማዋረድ እግዚአብሔርን እጅግ ደስ አሰኘ፡፡ ከአምላኩ ጋር ያለውንም መንገድ ለማስተካከል፦
“ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ፥ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ” (1ነገ.22፥19 ፤ 2ነገ.23፥3) ይላል፡፡

እንዴት የሚደንቅ ውብ ነገር ነው! ከዚህ በኋላ እጅግ በሚታዘዝ መንፈስ እንደሕጉም መጽሐፍ ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ፥ ታላቅ የፋሲካን በዓል አደረገ፡፡ 
       “ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተፈሰከ” (2ነገ.23፥23)
ንጉሥ ኢዮስያስ እጅግ የሚደንቅ ንጉሥ ነው፡፡ እንደስሙ ትርጉምም እግዚአብሔር በእርግጥ ደግፎታል፡፡ ገና ከማለዳ እግዚአብሔር መንገዱን ስላቀናለት በመንፈሳዊ ቅንአት ፍጹም ተመላ፡፡ ጣዖታትን ሁሉ ፤ ኃጢአትን ሁሉ ፍጹም ተጠየፈና አምላኩ የሚከብርበት መንገድ ፈለገ፡፡

እግዚአብሔርን ለማክበርና ለማምለክ ጣዖታትን ማጥፋትና ኃጢአትን መጠየፍ በራሱ አይበቃም፡፡ ስለዚህም ኢዮስያስ ኃጢአትን ተጠይፎ በምትኩ እርሱና ሕዝቡ ፊታቸውን ወደአምላካቸው ፍጹም የሚመለሱትበን ለሕጉ መጽሐፍ ቃል ታማኞች ሆኑ፡፡ በሕይወታችን ሁሉ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና በአምልኮም ሁሉ እርሱን ደስ ልናሰኘው ኃጢአትን መጠየፍ ብቻ ሳይሆን እንደቃሉ ከሆነ በጐ ነገር ሁሉ ጋር ልንተባበር ይገባናል (ሮሜ.12፥9)፡፡
  
የቀደመው ለጣዖታት የተገባውን ኪዳን ንጉሡ ሻረው፡፡ እንደሕጉ መጽሐፍ አዲስ ኪዳንን ፣ ሕይወትና ተሃድሶን ለሕዝቡ አደረገላቸው፡፡ በጨለማ ለሚኖረው ሕዝብ መሪ ብርሃን ቃሉን አመጣ ፤ እንዲነበብም አደረገው፡፡ ፋሲካውን ለእግዚአብሔር እንዲያደርጉ አዘዛቸው፡፡

  ቀድሞ ይገዛን የነበረውን ጠላትና አስጨናቂ ፤ ተቃዋሚያችንንም “በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ ያስወገደልን አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድልም የነሳልን” (ቈላ.2፥14-15) ፤ መካከለኛም ሆኖ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን “የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰና በመስቀሉ የገደለ” (ኤፌ.2፥14-16) እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡

የረሳነውንና የጣልነውን የአምላካችንን የሕግ መጽሐፍ መጥቶ ያስታወሰንና ዳግም በማስተማርና በመፈጸምም የሕግ ፍጻሜያችን የሆነልን እርሱ ጌታ ኢየሱስ ነው (ማቴ.5፥7 ፤ ሮሜ.10፥4 ፤ 13፥10)፡፡
  
  እርሱ የአዲሱ ኪዳን የመጨረሻው ፋሲካችን ነው፡፡ ከእርሱ በኋላ ሌላ ምንም ፋሲካ ፤ ምንም በዓል ፤ ምንም ደስታ ፤ ምንም እርካታ ፤ ምንም ደስታና ተድላ የለንም፡፡

እርሱ በፋሲካነቱ አባቱን ብቻ ያያደለ እኛንም አርክቶናልና ለአንድ ቀን ብቻ ያይደለ ለዘወትር የምናከብረው ውዱ ፋሲካችን ነው!!!

ለመሆኑ እኛ ፋሲካን ለእግዚአብሔር ነው የምንፈስከውን? በበዓሉ ቀን የወንጌሉ ቃል ይነበባል? ኃጢአተኞችን ሰብስበን የእንመለስ ጥሪና አዋጅ እናውጅ ይሆን? በሕይወታችን እግዚአብሔር አምላካችንን የማያከብረውን ነውርና እድፈት የምናስወግድበት ቀናችን ነውን? ራሳችንን እንመርምር!

 በዕዝራ ዘመን፦
     ፈጣኑ ጸሐፊ ዕዝራ፥ ፋሲካን ከሌዋውያን ካህናት ጋርና ከሕዝቡ ጋር ያከበረበትን ሁኔታ ታላቁ መጽሐፍ ሲገልጠው፦

“ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር ሁሉም ንጹሐን ነበሩ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ” (ዕዝ.6፥19-20)፡፡

    ንጹሐን ነበሩ የሚለው ቃል ፍጹም በእግዚአብሔር ፊት ንስሐ ገብተው ለእግዚአብሔር ሥራ ዝግጁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡
      እኛ ለእግዚአብሔር ሥራ ዝግጁ ሆነን ነው አሁን የቆምነው?
     ዕዝራ በምርኮ ምድር ብዙ ዘመኑን ቢኖርም ለእግዚአብሔር ሥራ ምቹ ፤ ጻድቅና ንጹሕ ነው፡፡ ሌሎችም እንደእርሱ የበረቱ እንዲሆኑ የሕጉን መጽሐፍ በፍጥነት በመጻፍ ያባዛዋል፡፡
  የንጽሕና መሠረቱና ሚዛኑ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የፋሲካው በግ መሥዋዕቱና የሕጉ ቃል ነው፡፡
  የእኛ ሚዛናችን ማን ነው? ቅዱስ ቃሉ ነው ወይስ የብዙሃን ድምጽ? ዕዝራ ንጹሐንን ለእግዚአብሔር ያጨው በቅዱሱ ሕግ ላይ ቆሞ ነው፡፡ ከእኛ ጋር እንዲሆኑ የምንወዳቸው ሰዎች ምን አይነት ሰዎች ናቸው? እንደቃሉ የሚኖሩ ወይስ የሚሸቃቅጡ?
    በክርስቶስ ኢየሱስ የጽድቅ ሚዛን ላይ ሳንቆም የቤተ ክርስቲያንን ቅድስናና ንጽሕናና የምንጠብቅ ከሆንን እጅግ ተታልለናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን “እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ሆና በክብር የምታጌጠው” ራሷን በሰጣትና በሞተላት ጌታ ፊት እንደቃሉ የተገባ ሆና ስትገኝ ብቻ ነው(ኤፌ.5፥27)፡፡
  
የሕጉን ቃል ለሕይወታችን ፣ ለኑሮአችን ፣ ለመንፈሳዊነታችን ፣ ለትዳራችን ፣ ለፖለቲካችን ፣ ለትምህርታችን ፣ ለወጣትነታችን ፣ ለሽምግልናችን ፣ ለአገራችን ሰላምና ለሰው ልጅ ሁሉ እረፍትና መዳን መመርያ አድርገን እናስቀምጣለን?

ከጾሙ በኋላ ስምምነታችን ከማን ጋር ነው? በእውኑ ከቃሉ ጋር ነው ወይስ ከዝሙትና ጭፈራው ጋር? በበዓሉ መታሰቢያ ማግስት ቀጠሮአችን የትና ከነማን ጋር ነው? ከጭፈራው ኮንሰርትና ዳንኪራው ፤ መጠጥ ቤቱና በየመሸታው ቤት አይደለምን? እኛ እኰ ወንጌል በየአባወራው ቤት ሲሰበክ የምንበሳጭ፥ በየጭፈራ ቤቱ ሄደን ስንረክስ ግን እንደጀብዱ የምናወራ ከፈሪሳውያን የባስን ግብዞች ነን፡፡ በጾሙ “ንጽሕናችንን” ጠበቅነው “ያቆየነው” በየጭፈራ ቤቱ ለመርከስ አልመሰለብን ይሆን?
      ከእነዚህ የብሉይ ኪዳን የፋሲካ መታሰቢያ በዓል ጥቂት ምንባባት የምናስተውለው እጅግ ብዙ የሆኑ ሃሳቦችን አሉ፡፡ ፋሲካችንን በእውኑ አውቀነዋልን? በፍሰካችን ፈስከን የምናከብረውና የምናመልከው ማንን ነው? እንዳለመታደል ዘፋኝነትና የዘፈን ኮንሰርት ፤ ዝሙትና ጭፈራ … ከክርስቲያናዊ በዓላት ጀርባ ያለማንምና ምንም ከልካይ ክርስቲያን ነን እያሉ አቧራ በሚያስነሱ ዘፋኞችና ዳንኪረኛ አማኞች የበዓሉ ምሽት መቅኖውን ያጣል፡፡ በእኛ እንደሚሆነው ብዙ ሕዝባዊና የሌላ ሃይማኖት በዓላት ሲከበሩ የሚጨፈረውን፥ በዝሙትና በኃጢአት ትውልድ የሚረግፈውንና በኃጢአት የሚረክሰውን ያህል በሌሎች በዓላት አይደረግም፡፡ ለምን? ሰይጣን ክርስትናን ለማሰደብ  “ክርስቲያኖችን” እንደተጠቀመባቸው ሳይ እጅግ አለቅሳለሁ፡፡ እጅግ የሚገርመው በዋናነት የዚህ ነውር አዘጋጆችና ተሳታፊዎች “ክርስቲያን ነን” ባዮችና ምናልባትም ለደንቡ ጿሚ የነበሩም ናቸው፡፡ አቤቱ ፍረድልን፡፡ አሜን፡፡
     መንፈሳዊነታችን ይታይ ቢባል በፋሲካው መታሰቢያ ቀን በዓል የት ነው መዋያችንና ማደሪያችን? በብሉይ ኪዳን የነበሩትና የጥላውንና የምሳሌውን ፋሲካ እንዲያ በብዙ ክብር ካከበሩት እኛ እንዴት በሚበዛ መንፈሳዊ ክብር ዘመናችንን በሙሉ ልናከብር ይገባን ይሆን? በመታሰቢያ ቀኑማ እንዴት ባለ ታላቅ አምልኮ ልናከብር ይገባ ይሆን? በእውኑ ከአሥራ ሁለት ሚሊየን ሕዝብ በላይ የተራበ ሕዝብ ባለባት አገር ላይ (በሠላሙ ተፈቅዷል የሚሉ እንዳይኖሩ ፈራሁ)  መአትና መቅሰፍት ለመጥራት ካልሆነ በቀር ጭፈራና ዳንኪራው ምንድር ነው? ያውም በተቀደሰው በዓል መታሰቢያ ቀን፡፡
“የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል ፤የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?” (ዕብ.10፥28-29)
      የተመረጥንበትንና የዳንንበትን ቅዱሱን ፋሲካችንን ክርስቶስን እንድንዘብትበት አልተባለልንም፡፡ ፋሲካውን ክርስቶስን ደስ በሚያሰኝ ሕይወትና ኑሮ እናስደስተው፡፡ የእስከዛሬው ርኩሰትና በበዓላት ሰበብ ልክን አልፎ በመብልና መጠጥ በመቅበዝበዝ የኖርንበት ይብቃንና (1ጴጥ.4፥4) ከአምላካችን ጋር ኪዳናችንን የምናድስበት እንዲሆንልን ፤ የዕርቅ ቀን እንዲሆንልን ለኃጢአታችን ሞቶ ፤ ለጽድቅ እንድንኖር ከሙታን መካከል ወደተነሣልን ፋሲካችን ወደሆነው ጌታ ኢየሱስ ፊታችንን እናቅና፡፡ የኃጢአትን ቀጠሮ አፍርሰን የሕይወትን ኪዳን ቀጠሮ ከአዳኛችን ጋር እንግባባ፡፡
            ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!!!

Friday, April 26, 2019

❖እንደ ተሰቀለ...!

መስቀል ላይ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ይታዬን!

" የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?"
ገላትያ ሰዎች 3:1

እንኳን አደረሰን!! ዛሬ ነፃነታችን በደም የተገዛበት ዕለት ነው።
ዛሬ የፍቅር ጥግ የታየበት ጌታችን ነፍሱን ለወዳጆቹ አሳልፎ የሰጠበት ነው።
ዛሬ ለእኛ የሚገባውን መከራ ሁሉ ተቀብሎ ልጆች የተደረግንበት ነው።የሰማይና የምድር ንጉስ ልጅ ሆነን አንነስ እባካችሁ በልባችን ይታተም እንኑርበት ፣
ዛሬ ተርቦ እኛን ያጠገበበት ፣ተጠምቶ እኛን ያረካበት ፣ቆስሎ እኛን የፈወሰበት፣የማይገባውን ሞት ተቀብሎ የማይገባንን ሕይወት ለእኛ የሰጠበት ቀን ነው፡፡ይህ ሁሉ ለእኛ ነው።

ከዘመናት በፊት ጌታችን ኢየሱስ በዛሬው ዕለት ትውልድ ፊቱን አዞረበት( ዛሬም ከተፈጠርንለት አላማ ውጪ መኖር እርሱ ላይ ፊትን ማዞር እንደሆነ ይሰመርበት)።በአይሁድ ተገርፎ፥ በወዳጅ ተከድቶ ታመመ፡፡በገዥዎች ፊት በሐሰት ተከሶ ቀረበ፥ ያለ በደሉ ተፈረደበት፥ እርጥብ መስቀል ተሸክሞ ደከመ፥ በደላችንን ተሸክሞ ተራራ ወጣ፥ በክፉዎች መሀል ተሰቀለ፥ ውኃ ፈልጎ በቸርነት የሚሰጠው አጣ፥ የጭፍሮች መሳለቂያ ሆነ፡፡ይህን መከራ ኢሳይያስ እንዲህ ይተነትናል
" በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። " ኢሳ 53 ሙሉውን ያንብቡ! ይህን የታመነ ጌታ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊታችን ተስሏልና ይታዬን፦ ብናየው አንለያይም፥ ብናየው አንከፋም፥ ብናየው አንሸነፍም፥ ብናየው ለእውነት እንታዘዛለን፡፡ ኢትዮጵያ የተሰቀለውን ስታይ ታርፋለቺ፣የችግሮች ሁሉ መንስኤ እርሱን አለማየት ነው፡፡አዚምን ቆርጦ እንድናየው ያግዘን።
 
  ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

Wednesday, April 24, 2019

❖ጸሎተ ሐሙስ፦

የመጨረሻው እራት፦

ዛሬ ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የበላበት እና እግራቸውን በትሕትና ያጠበበት ዕለት ነው፡፡ማቴ. 26፡20-29።ይህን እራት ጌታ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሊበላ በናፍቆት ይጠብቀው ነበረ፡፡ " እርሱም። ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤"ሉቃስ  22:15።

በሞት ዋዜማ ራት፡ በመከራ ዋዜማ ራት፡ ወዳጅ እንደሚሸሽ እየተረዳ ከወዳጅ ጋር ራት ይገርማል፡፡የመጨረሻ ነገር ትዝታ የሞላው ነው፡፡ልቡ ውስጥ ዘመናት የማያስረጁት ጥልቅ ፍቅር እና ክብር አለ፡፡ቃሉ እንዲህ ሲል አረጋገጠው፦ "ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።"ዮሐንስ 13:1 ይህ ሁላችንም እርግጠኛ ሆነን የምንናገረው ፍቅር ነው፡፡አምላክ አለን ወገን የሆነን፥ወዳጅ አለን ወገን ያደረገን፡፡ልባችን በዚህ ይታመን አጥብቆ ወዶናል፡፡አንስጋ የወደደን ለዘላለም ነው፡፡

ዛሬ ልዩ ነው፦ ደቀመዛሙርቱም እራት ከበሉ በኋላ የዘመሩበት የምስጋና ምሽት ነበር፡፡ ማቴ. 26፡30።

በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ- የሐዲስ ኪዳን ሥርዓት ሰርቷል፤አዲስ ኪዳን ስላደረገ ስለዚህ  ዕለቱ የአዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ማቴ. 26፡26።

የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቧል፤ስለዚህ ዕለቱ ሕጽበተ እግር ሐሙስ ተብሏል፡፡ዮሐ. 13፡2-14።

በአረንጓዴው የአትክልት ስፍራ ጸልዮአል፤ስለዚህ ዕለቱን ጸሎተ ሐሙስ ተብሏል፡፡ማቴ. 26፡36-41

እስከ መጨረሻ ከወደዳቸው መካከል  በችኮላ የሚታወቀው  ጴጥሮስ፥ ተጠራጣሪው ቶማስ፥ አፍቃሪው ዮሐንስ፥ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ይገኙበታል፡፡ይህን ሁሉ ችሎ እስከ መጨረሻው መውደድ እጅግ ይገርማል  እኛ ሰውን ሳናውቀው ወደነው ስናውቀው እንጠላዋለን፡፡
ይህ ምን አይነት ፍቅር ነው? ስንደክምም ስንበረታም ስናጠፋም ስናለማም የማይለወጥ ፍቅር፡፡ይህ ፍቅር
በትህትና  ሲገለጽ መምህሩ ተማሪዎችን፥ ጌታ ባሪያዎችን እግራቸውን ሲያጥብ አየን፡፡እሱ ያላጠበው አይነፃም፡፡እሱ ያላጠበው ከእርሱ ጋር እድል የለውም፡፡ከዘላለማዊ በደል በደሙ ያጠበን ይህ ትሑት ሊቀካህናት ነው፡፡ይህን የተደረገልንን እናስተውላለን?እርሱም በቃሉ ያደረኩላችሁን ታስተውላላችሁን  ? ብሎናል።ልዑሉ በፍቅር ጎንበስ ማለቱ ይግባን፡፡ውለታ አናጥፋ፡፡ ዝቅ ብሎ ከፍ ማድረጉን አንርሳ፡፡በእውነት ፍቅሩን አስተዋይ ትውልድ መሆን አለብን፡፡መተጣጠቡን  እርስ በእርሳችን እንዲሁ እናድርገው፡፡ለበዓሉ ብቻ ሳይሆን የዘወትርም ተግባራችን ይሁን፡፡ቃሉ ይህን ብታዉቁ ማወቅ ብቻ አይጠቅምምና ብታደርጉ ብፁዓን ናችሁ ይለናል፡፡ክርስትና የፍቅር ድርጊት እንጂ የአፍ ማስመሰል አይደለም፡፡ጌታ በሕይወት በድርጊት ነው ያስተማረን፡፡  
  
   ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

Thursday, April 18, 2019

❖ሆሳዕና፦

          እንኳን ለሆሳዕና በዓል አደረሰን!!!
❖ሆሳዕና ፦
        ሆሳዕና ማለት አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው!
የሚቀድሙ እና የሚከተሉ ሕፃናት እና አዋቂዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ፥ልብሳቸውን አንጥፈው የሰማዩ ልዑል በተናቀች አህያ ጀርባ ተጭኖ ሲገባ፦  "ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስምየሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።" (ማቴ. 21፥9)
   መረጋጋት ላቃታት ለኢየሩሳሌም ቅኝ አገዛዝ ለጸናባቸው ለአይሁድ "አሁን አድነን" ትልቅ ልመና ነበረ፡፡እያመሰገኑ መለመን መታደል ነው፡፡ በልቡ እንቆቅልሽ ታቅፎ ከከንፈሩ የእግዚአብሔር ምስጋና የማይጎድልበት ምስጉን ነው፡፡ ዛሬም ሆሳዕና እንበል፥ የምስጋና ነዶ በፊቱ እያከማቸን አቤቱ አሁን አድን እንበል፡፡ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን ፥ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ እያልን እንጩህ!

❖ወንጌል ስለ ሆሳዕና ምን አለ?
      1/☞ለጌታ ያስፈልጉታል!
"በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ፈትታችሁ አምጡልኝ።ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።" (ማቴ. 21፥2)
  ደቀመዛሙርቱ የታሰሩትን እንዲያስፈቱ ተልዕኮ ሲሰጣቸው "ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ" ከሚል ትእዛዝ ጋርነበረ፡፡ ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣው በኃጢአት የታሰረውን የሰውን ልጅ ለመፍታት ነው፡፡

  አዎ!  ታስሮ አስፈትቶናል፥ ወድቆ አንስቶናል፥ ደሙን ክሶ ከማዕሰረ ኃጢአት ፈትቶናል፡፡.  
    ዛሬም በሱስ በኃጢአት በተንኮል በክፋት በአመፃ ወደታሰሩት ሰው ይልካል! ከሞት ጋር ወደተስማሙት የሟቹን ሞት የማይፈቅድ ጌታአገልጋዮችን ይልካል፡፡ እኛ ተስፋ የቆረጥንባቸው ሁሉ ለጌታ ያስፈልጉታል፡፡ ዛሬም የታመሙ እንዲፈወሱ፥ የወደቁ እንዲነሱ፥ የታሰሩ እንዲፈቱ፥ ያዘኑ እንዲጽናኑ፥ የተሰበሩ እንዲጠገኑ፥ የጠፉ እንዲገኙ ክርስቶስ ይፈልጋል፡፡

የኃጢአት እሳት ላይ የሚጫወተው፥ በሞት መንደር ያንቀላፋው ትውልድ ባለቤት አለው፡፡ ፈላጊ አለን፥ አክባሪ አለን፥ የማይጸየፈን አባት አለን፡፡ በራሳችን ተስፋ የቆረጥን፥ ለማንም አላስፈልግም የምንል ለጌታ እናስፈልጋለን፡፡
   
        2/☞ንጉሣችን ይመጣል!

    " ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደአንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።" (ማቴ. 21፥4-5)
   በመገፋት የእርሱን ቀን ለምትጠብቁ፥ ቀን ያስጎነበሳችሁ፥ ከተማችሁ በቅኝ ገዥዎች የተያዘባችሁ፥ ስጦታው ነክቷችሁ በጸጋ ተሹማችሁ ዙፋን ተከልክላችሁ ወደ ምድረ በዳ የተሰደዳችሁ፥ ወንድማችሁ የቃየልን ድንጋይ እያሳየ የሚያስፈራራችሁ ንጉሣችን ይመጣል የሚያነግሰው ይመጣል ቀን አውጭው ይመጣል የሆሳዕና የዋህ ሆኖ እንደ ትንቢቱ የመጣው በስልጣን ይመጣል!
     
     3/☞የሚቀድሙት እና የሚከተሉት የእርሱ የምስጋና ሠራዊት ናቸዉ!

 " የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም  ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕናበአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።" (ማቴ. 21፥9)
  በአህያ ጀርባ ያየነው በእሳታውያን ኪሩቤል እና በሱራፌል ጀርባ የነበረ ነው፤ ይህ ምስጋና ይገባል። የሚቀድሙት ነቢያት፡ የሚከተሉት ሐዋርያት አመስግነውታል።

ወደፊትም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በጉን ይከቡታል፤ ወድቀው ይሰግዱለታል፡፡ ትውልድ ለምስጋና ይነሳ ፥ ለእርሱ ያንጥፍ ፥ ለእርሱ መንገዶች ሁሉ ክፍት ይሁኑ ፥ ለእርሱ አንደበት ሁሉ ይቀኝ ፥ ለእርሱ ትልቅ ትንሹ አዋቂ ሕፃኑ ምስጋና ያቅርብ!
   
        4/☞ይህ ማን ነው ?

     "ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ።" (ማቴ 21:10)
  ይህ ማነው ከተማ የሚናወጥለት ? ይህ ማን ነው ዓለሙ ሁሉ የሚከተለው ? ይህ ማነው ? ይህ የኛ ልዑል ነው፡ ይህ የኛ ቤዛ ነው፡፡ ይህ የኛ የዘመናት ወዳጅ ነው፡፡ ይህ የኛ አምላክ ነው። ሞገድ ባሕር የሚታዘዝለት ይህማን ነው ? ልዑል ሳለ በትሕትና የተገለጸ ይህ ማነው ? ንጉሥ ሆኖ ሳለ የዋህ የሆነ ይህ ማነው? ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
     
        5/☞አንኩራበት፦

   " ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። መልሶም።እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው።" (ሉቃስ 19:39-40)
  እርሱ የምስጋና ጌታ ነው፤ ባናመሰግነው ምስጉን ነው፡፡ በምስጋና የምንጨምርለት፤ ባለማመስገን የምንቀንስበትነገር የለም፡፡ ስለዚህ አመስጋኞችን አንገስጽ፡፡ እጃችንን አጣጥፈን ዳር ይዘን ተመልካች አንሁን፡፡  ሜልኮል ኮርታምን አተረፈች? አንኩራ አንታበይ እኛ ዝምታን ብንመርጥ ድንጋዮች እንኳ ለቅኔ ሊነሱ ዝግጁ ናቸውና፡፡
     
          6/☞የልባችን ደጅ ይከፈት!

     " ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ። እናንት መኳንንት፥ በሮችን ክፈቱ፥የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱናኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል።" (መዝ 24:6-9)
  ዛሬ የቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ በዚህ ቃል የተመሠረተ ነበረ፡፡ ይህ ልዑል የዘላለም ደጆችን የከፈተ ነው፥ የሕይወት ቁልፍ በእጁ ነው፥ የገነት ቁልፍ በእጁ ነው፥ የስኬት ቁልፍ በእጁ ነው፡፡
ለሁሉ የከፈተ እርሱ እንዴት ደጅ ይዘጋበታል? መኳንንት ሆይ ክፈቱ! ሁሉም በተሾመበት ነገር ባለስልጣን ነው ፥በሀብት በእውቀት በውበት በስልጣን ተሹመን ይሆናል እንዳንከፍት እነዚህ ነገሮች አጥምመውን ይሆን ? አታለውን ይሆን? በሚያልፈው ታምነን ከማያልፈው እንዳንጎድል የልባችንን ደጅ እንክፈት፡፡
     
        7/☞እርሱ ይኑርብን፦

     አህያዋ እርሱን በመሸከሟ ተከበረች፡፡ በልዩ አጀባው ውስጥ ተራመደች፡፡ እርሱ ያለው ሞገስ አለው፡፡ በተለይ በሰማይ የበለጠ ክብር ይጠብቀዋል፡፡ ልባችን የእርሱ ዙፋን ከሆነ መክበር አለ፡፡እርሱን እያሳየን እንዙር፡፡ " የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።" (2ኛ ቆሮንቶስ 4:10)።
   
      8/☞ለሰላማችን የሚሆነውን አንግፋ፦

  "ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮል::ወራት ይመጣብሻልና፥ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።" (ሉቃ 19:42-44)
  ክርስቶስ የሰላም አለቃ ነው፡፡ እርሱ የሌለው ሰላም የለውም፡፡ እርሱ የልብ ሰላም፣ ዕረፍት እና መድኃኒት ነው፡፡ለሰላማችን የሚሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ለእርሱ ደጅ አንዘንጋ፡፡ለእርሱ ጀርባ አንስጥ፡፡ ሰላሙን ለመጠቀም ልባችንን ክፍት አድርገን እንጠብቀው፡፡               

               የእግዚአብሄር ጸጋና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
                            ===●===●===●=== 

Friday, April 12, 2019

❖ኒቆዲሞስ፦

❖ኒቆዲሞስ፦
    "ዳግም መወለድ"
የዐቢይ ጾም ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ባለ ታሪኩ ኒቆዲሞስ የጌታ የማታ ተማሪ፥ የአይሁድ መምህር እና የሸንጓቸው አባል ነው፡፡ዮሐ 3:1-14 ተመልከቱ። ክርስቶስ በስውርም በግልጥም መማር ለሚፈልጉ አስተምሯል፡፡ ኒቆዲሞስ የአይሁድ ሊቅ ስለነበረ ከወገኖቹ ተሰውሮ በማታ ነበረ የተማረው፡፡ የማታ አእምሮ ሥራ የጨረሰ የተረጋጋ ነው፥ ለትምህርት እና ለጸሎት መልካም ጊዜ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን አብዛኛው የቃልና የዜማ ትምህርት በማታ የሚሰጥ ነው፡፡ የኒቆዲሞስ ሌሊት የተመስጦ፥ ቁጭ ብሎ መማሪያ፥ የሕይወትን መምህር ክርስቶስን መስሚያ ነበረ ፤ የእኛስ ሌሊት ምን እየሠራንበት ያልፋል ? በተመስጦ፣ በዝማሬ፣ በጸሎት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ነው የምናሳልፈው ?

ኒቆዲሞስ መምህርም ሆኖ ይማራል፡ መምህር መማር አለበት፡ መማር ያቆመ መምህር ማስተማር ማቆሙ አይቀርም፥ እውቀት መጨመር ያስፈልጋል! እኛ አንድ ዘመን የተማርነውን ነው ስንናገር የምንኖረው ቁጭ ብሎ መማር ውርደት ይመስለናል፡፡ መማር አያሳፍርም፤ የሚያፍር ካለ ተሰውሮም ቢሆን ይማር፡፡ የተማርነውን በጥናት በምንባብ አናሰፋም። ኒቆድሞስ የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር ጊዜ የለንም ለምንል ሰዎች አስተማሪ ነው። ጌታ ለኒቆዲሞስ የዳግም ልደት ትምህርት ነው ያስተማረው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን ዳግም መወለድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ልደት ረቂቅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የምንዛመድበት መንፈሳዊ ልደት ነው፡፡ ዳግም መወለድ ወደ እናት ሆድ ተመልሶ መግባት አይደለም፡፡ ዳግም ልደት ላመነ ሰው በመንፈስ ቅዱስ አሠራር የሚከናወን ሰማያዊ ልደት ነው፡፡

ዳግም ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ስለተወለድን የመለኮት ክብር ተካፋዮች ሆነናል፡፡ ስለተወለድን እግዚአብሔርን አባት ስንለው ልጅነት ይሰማናል። ስለተወለድን የልጅነት ስልጣን አለን።

ኒቆዲሞስ በክርስቶስ ላይ ከንቱ ክስ ሲነሳ ወገኖቹን ተከራክሯል፥ ሁሉ በሸሸበት ሰዓት የጌታን ቅዱስ ሥጋ በክብር የቀበረ ወዳጅ ነው! በስውር ቢማርም በሕይወት ተገልጧል፡፡ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ነው፡፡አንድ ቀን ለእግዚአብሔር እንኳን መኖር መታደል ነው! ከመስቀል ልናወርደው መቼ ነው የምንመጣው ? መቼ ነው ለክብሩ ቀንተን ተገልጠን የምንናገርለት ? መቼ ነው ለእርሱ መቆጠርን የማናፍርበት?
ከመንፈስ እንደ ተወለደ መንፈሳዊ ሰው ኖረን መንፈሳዊውን ዓለም በክብር ለመውረስ ያብቃን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
===●===●===●===

Friday, April 5, 2019

❖ላከበረን መኖር፦

ላከበረን መኖር

ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን እንደ ሞተ እና እኛን ስለማጽደቅ እንደ ተነሳ ካመንን እና በዚህ እምነት የተቀበልነውን ስልጣን መጠቀም ከጀመርን የሚጠበቅብን ላከበረን ክብር መኖር ነው፡፡ እኛ እንድንከብር የተዋረደ አለ፤ እኛ በነፃ እንድንለቀቅ የታሰረ አለ፤ እኛ እንድንለብስ የተራቆተ አለ፤ እኛ እንድናርፍ ያቃሰተ አለ፡፡ እርሱም፡- ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ነው፡፡ እንዲህ ሆኖ ላከበረን ለእርሱ መኖር አለብን፡፡
እኛ የራሳችን አይደለንም፤ በደም ዋጋ የገዛን አለ፡፡ 1ቆሮ 6፡20፡፡ ላከበረን መኖር መጀመር አለብን፡፡ “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” እንደተባለ፡፡ 2ቆሮ 5፡15፡፡ እኛ እና ዓለማችን ለክብሩ መንበርከክ አለብን፡፡ በእኛ ላይ በሚሰራው የእግዚአብሔር ኃይል በዙሪያችን መልካም ተጽዕኖ ማምጣት አለብን፡፡
የራሳችንንም የሌሎችንም ሕይወት ውብ በማድረግ አባታችንን እናስከብር፡፡ መብላታችን እና መጠጣታችን አንኳን ሳይቀር ለክብሩ እዲሆን ይፈለጋል፡፡ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።” 1ቆሮ 10፡31፡፡ እያንዳንዱ የኑሯችን ገጽ አዳኛችንን መተረክ አለበት፡፡ ለራሳችን የሮጥንበት ዘመን ይብቃ እና ደግሞ ላከበረን እንኑር፡፡

  ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!