Friday, June 5, 2020

❖አቤቱ ሞትህን እንናገራለን ድንቅ ትንሳኤህን እናወራለን፦ (1ቆሮ 11:26)

አቤቱ ሞትህን እንናገራለን ድንቅ ትንሳኤህን እናወራለን፦

አብዛኛው  የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ እርሱ እንደሚናገር ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮአል። « ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ….. እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።»  (ሉቃ 24:27:44)

መላው መጽሐፍ ቅዱስ በአቀራረቡ ከፍጥረተ-ዓለም እስከ ኅልፈተ-ዓለም ያሉ ነገሮችን በአብዛኛው ጠቅለል አድርጎ ሲናገር የክርስቶስን ሕይወት ግን ከልደቱ እስከ ሞቱና ትንሣኤው በዝርዝር ዘግቧል። ከሚናገርለት የብዙ ሺህ ዓመታት ጉዳይ እና ብዙ ሰዎች አንጻር ስናየው ስለ ክርስቶስ ከሁሉም የበለጠ ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። በተለይም መከራና ሞቱን(ከትንሣኤው ጋር) በተለየ ሁኔታ በየሰዓቱ ማለት ይቻላል የነበረውን ዝርዝር ሁኔታ በመናገር ከሌላው የሕይወት ክፍሉ የላቀ ትኩረት እንደሰጠው እናስተውላለን። 

ይህም የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አጀንዳ በልጁ ከልጁ ለልጁ ራሱ እንደሆነ፤ በልጁ ያደረገው እያደረገው ያለውና በልጁ ዳግመኛ መምጣትም የሚያደርገው የዘላለሙ አጀንዳው እንደሆነ ልብ ይሏል።

የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሞት እንዲሁም ትንሳኤ በአጠቃላይ የመስቀሉን ሥራ ሊተካ፣ ሊተካከል ወይም ሊወዳደር የሚችል አንዳች ነገር የለም አይኖርምም። ስለሆነም የአንድ ሰሞን አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የዘወትር ርእሳችን ነው። በየዕለቱ ዘወትር የክርስቶስን መከራና ሞት ልናስብ ልንናገር ይገባል። 

ሞቱና ትንሳኤውን ማውራት ማለት ጲላጦስ ፊት ቆመ፣ ተገረፈ፣ ተቸነከረ፣ ...ወዘተ ማለት ብቻ አይደለም ይልቁንም በመስቀሉ ሥራ የተገኘውን ውጤትም ጭምር እንጅ። ጳውሎስ ስለጌታ ራት በጻፈበት መልዕክቱ የጌታ እራትን ዓላማ ሲገልጥ ሞቱን መናገር እንዲሁም ማሰብ እንደሆነ ነግሮናል። « ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና። » (1ቆሮ 11:26)

ቢጻፍ ዓለም የማይበቃው ቢወራ የማይ'ሰለቸውን የክርስቶስ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት፤ የእግዚአብሔር መልእክት እንደሆነ ሁሉ የኛም የስብከታችን ትኩረት፣ የመዝሙራችንና የጸሎታችን ማዕከል ነው።  የቤተክርስቲያን የዘወትር ርእሷ፤ የሁልጊዜ መልእክቷ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ብቻ ነው ሊሆንም ይገባል።  ጳውሎስ ወሬው ሁሉ እውቀቱ ሁሉ ኑሮውም ጭምር ለዚህ ነበር። (1ቆሮ 1:23 1ቆሮ 2:2 ፊልጽ 3:8-9) 

ሰው የእግዚአብሔርን መልክ እየገለጠ እንዲኖር ቢፈጠርም ፈቃድ ያለው ፍጥረት ስለሆነ ፈቃዱን ተጠቅሞ ለእግዚአብሔር እንዲገዛ፣ እርሱን እንዲያከብር አትብላ የሚል ትዕዛዝ አግዚአብሔር ሰጥቶታል።  (ዘፍ 2:16-17።)

 ነገር ግን በሰይጣን ተንኮል በሔዋን መተላለፍ አዳም በመተላለፍ አትብሉ ከተባሉት ከዛፉ በላ። ከዛፉ በበሉ ጊዜ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ አመጹ። አዳም ትሞታለህ በተባለው መሠረት ወዲያው በስጋ አልሞተም ነገር ግን ከእግዚአብሔር በመንፈስ ተለየ (በመንፈስ ሞተ)። 

የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ተለየ(ሞተ)። ከኤደን ገነት አባረራቸው። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ሕብረታቸው ተቋረጠ። በኋላም ዘጠኝ መት ሃምሳ ዓመት ኑሮ በስጋም ሞተ። ኃጢአት ሞትን አመጣበት። በዚህ ምንክያት ኃጢያት በአንድ ሰው ምክንያት ወደ ዓለም ገባ። ሞት የኃጢያት ውጤት ነውና በኃጢያትም ምክንያት ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።  (ሮሜ 5:12)

መጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ በሆነ መልኩ እንደሚነግረን፥ ከተካፈልነው የኃጢአት ተፈጥሮ የተነሳ፦ " ሁሉ ኃጢያትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል"  ይላል። (ሮሜ 3:23)

 በአንዱ አዳም አለመታዘዝ ሁሉ ኃጢያተኛ ሆነ ከእግዚአብሔር ክብር ጎደለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ታላቅ ቁጣ ሥር ነው ያለው። የሰው ልጅ ሙት እና የእግዚአብሔር ጠላት ሆነ። (አፌ 2:1-3 ቆላ 1:20-21)

 የኃጢያት ደመወዝ ሞት ነውና ለዘላለም የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ተለይቶ ቆዬ። (ሮሜ 6:23)

እግዚአብሔር ግን የምህረት አምላክ ሰለሆነ ለወደቀውና የዘላለም ፍርድ ለሚጠብቀው የሰው ዘር ሁሉ የምሕረት ዕድል ሰጠን። ስለዚህ በዘላለም ክብር የነበረው አምላክ እኛን ለማዳን በስጋ ተገለጠ። 

ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ መስቀል ላይ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ የሁላችንን ኃጢያት ተሽክሞ ምትክ ሆኖ ሊሞት ተሰቀለ። በኛ ላይ ሊያርፍ የነበረ የእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ላይ አረፈ። እኛ መሞት የነበረብንን ሞት እሱ ሞተልን። በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን። አሁን የኃጢያት ስርየት አገኘን። (ሮሜ 3:25)

 "እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥" ስለዚህ ክርስቶስ በሞቱ የኃጢያታችን ዕዳ ከፈለልን፤ እኛን ለማጽደቅ ደግሞም በአዲስ ማለትሜ በራሱ ሕይወት እንድንመላለስ ከሙታን ተነሳ። (ሮሜ 4:24-25 ኤፌ 2፣5)

 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለኃጢአታችን መስዋዕትን ሲከፍል የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተከናውነውልናል፡፡

የመጀመሪያው የኃጢአት ሥራ እና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ነው። 

መስቀሉን ስንመለከት የኃጢአት ሥራ አስፈሪነትና አስቀያሚነት ይታየናል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአት ነው ክርስቶስን ከክብር ዙፋኑ ላይ ወደ እኛ እንዲመጣ ያደረገው፡፡ የሰው ኃጢአት ነው እርሱን የሀዘን ሰው ያደረገው፡፡ እኛን አሁን ባለንበት አሰቃቂ ክፋት እልቂት ጭከናና ጦርነት ሁኔታ ውስጥ የጣለን ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፣ ስለዚህ ኃጢአትን ይቀጣ ዘንድ ልጁ በመስቀል ተንጠለጠለ። ኃጢአት ለእግዚአብሔር ባህሪ የማይስማማው መሆኑን ኃጢአትን በክርስቶስ ስጋ ላይ ሲቀጣ እንገነዛባለን እናም እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። ሮሜ 3:25-26

ሁለተኛው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። 

1ዮሐ 4:10 የታረደውን በግ በመስቀሉ ላይ ሆኖ ስናይ ሌላ የምናስተውለው ነገር የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው። እኛ የሰው ልጆች በኃጢአት የቆሸሸ ሕይወት ያለን ነን፡፡ እኛ እራሳችንን ለኃጢአት ሸጠናል፣ በኃጢአት ውስጥ ዘቅጠናል፣ ጥላቻ፣ ነፍስ ግድያ፣ ስርቆት፣ ውሸት፣ አመንዝራ፣ ወዘተ ታሪካችንን ሞልቶታል፡፡ ከእነዚህ ከወደቅንባቸው ኃጢአቶች የተነሳ ንፁህና ፍፁም የሆነው እግዚአብሔር የዘላለም ፍርድ ሊሰጠን ይገባዋል፡፡ 

ነገር ግን በመስቀል ላይ የታረደውን በግ ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍቅርና የምህረቱን ብዛት እንገነዘባለን፡፡ ጻድቅ እግዚአብሔር ፍርዳችንን በንፁህ ጌታ ኢየሱስ ላይ አድርጎ እኛን ለማዳን እርሱ በእኛ ምትክ እንዲታረድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ይህ ከኛ የተነሳ ሳይሆን ከእርሱ ፍቅር ብቻ የተነሳ እንደተደረገ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ምን ዓይነት ፍቅር ነው፡፡ እኛን ጠላቶቹን እግዚአብሔር ወደደን። ይህንን ፍቅር በቃላት ለመግለፅ አይቻልም፡፡ ምን ማድረግ ይገባናል? መጽሐፍ ቅዱሳችን በውድ ልጁ እንዲያው የሠጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይኼን አደረገ ስለሚል በምስጋና እናወድሰው። (ኤፌ 1:6)


ሦስተኛ የእግዚአብሔር የዘላለም ዕቅድ ነው። 

አንዳንዶች የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሞት እንደ ድንገተኛ አደጋ አድርገው ሊቆጥሩት ያስባሉ፡፡ በድንገት አዳምና ሔዋን ስለተሳሳቱ እግዚአብሔር እቅዱ እንዳይበላሽበት "በል እስኪ ሂድ ልጄ አድናቸው" ተብሎ የመጣ ድንገተኛ ሃሳብ አይደለም። ሲጀመርም ከዘላለም እግዚአብሔር ልጆቹ እንድንሆን ያሰበው በልጁ ስራ ነው። (ኤፌ 1:5)

 ይኼን ሃሳብ ጴጥሮስ በመልክቱ ያጠናክረዋል። "ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። (1ጴጥ 1:18-21)

 ይህ የሚያሳየው የእርሱ የመስቀል ሞት በእግዚአብሔር ጥንት የታቀደ፤ የታሰበበት፣ ነገር ግን በድንገት ያልተፈፀመ መሆኑን ነው፡፡

በልጁ ሞት የኃጢአት ዕዳችን ተከፍሏል። ከእግዚአብሔር ቀጣ ተርፈናል። በልጁ ከሙታን መነሳት እኛም አብረን ከሞት መንደር ተነስተናል። የራሱን የእግዚአብሔርን ሕይወት ተካፍለናል፣ ጸድቀናል፣ ተቀድሰናል፣ ልጆች ሁነናል.....ወዘተ ይኼ ሁሉ በልጁ ሞት እና ትንሳኤ አግኝተን እንዴት ስለእርሱ አናወራ!

❖ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል ፦(ዮሐ 16:13-15)

የእግዚአብሔር መንፈስ ምንድነው የሚገልጠው?

በእኛ ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ከአብ ና ከወልድ ጋር ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያንን ከአካሏ ከክርስቶስ እንዲሁም በተለያዩ የምድር ስፍራ ካሉት ከምናውቃቸውም ከማናውቃቸውም አማኞች ጋር በሕይወት እንድንተሳሰር አድርጎናል። 

መጽሐፍ ቅዱስ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል እንዲል፤ (1ቆሮ 12:13።)

ከዚህ መንፈስ ቅዱስ የተነሳ እኛ በአብና በወልድ ውስጥ  እንዲሁ አብና ወልድም በእኛ ውስጥ ለመሆን ችለዋል። "ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን"።  (1ዮሐ 4:13።)

የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ከመሆኑ የተነሳ የክርስቶስ ወገን ሁነናል። (ሮሜ 8:9።) ይሁን እንጅ ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ሁኖ ዝም ብሎ መቀመጥ ሳይህን የሚሠራው ሥራ የሚገልጠው ነገር አለ። 

መንፈስ ቅዱስ  በእኛ ሕይወት የሚገልጠው በልጁ የተገለጠውን የአብን ፍቅር ወይም ልጁን ኢየሱስን ነው። "በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። (ሮሜ 5:5 )

እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፡— ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።"   (ዮሐ 16:13-15)

መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሕይወት የሚገልጠው የዘላለም ሕይወትን ነው። የሰማዩን መንግሥት ነው። የማያልፈውን ነው። በአጠቃላይ መንፈስ ቅዱስ የሚገልጠው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው እርሱ ሲገለጥ ደግሞ በርግጥም አብም ይገለጣል። መንፈስ ቅዱስ አብን ይገልጣል ስንል የአብን የዘላለም ሐሳብ ማለት ነው። ይኼም ሐሳቡ በልጁ የመስቀል ስራ የጀመረው፤ መንፈሱን በመላክ እየሠራ ያለው እንዲሁም በልጁ ዳግመኛ መገለጥ የሚጠቀልለውን የዘላለሙን ሐሰብ ማለት ነው።

❖ዘመኑን ማወቅ፦

   ዘመኑን ማወቅ፦
          (ሮሜ 13:11-14)

"ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤" (ሮሜ 13:11-13)

ሰላም ለእናንተ ይሁን። ጳውሎስ በወንጌል ስለተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ በሚያወራበት በሮሜ መልዕክት ውስጥ ሰው እንዴት እንደሚጸድቅ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ጽድቅ በተለያየ አቅጣጫ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ዘግቧል። በዚህ በመረጥነው ክፍልም ዘመንን ስለማወቅ ይነግረናል። እኛም በሚከተሉት ሁለት ንዑስ ርዕስ ከፍለን እንመለከታለን።

1. ዘመኑ ምንድነው?፣

ዘመንን ማወቅ ታላቅ ጥበብ ነው። ዘመንን ማወቅ ጥቅም እንደነበረው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ይነግረናል። ለምሳሌ ዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ከሆነ በኋላ እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ሁለት መቶ ከይሳኮር ልጆች አለቆች ነበሩ። (1ዜና 12:32።) 

ዛሬም በአዲስ ኪዳን ዘመንን ማወቅ የሚገባውን እናደርግ ዘንድ አስፈላጊ ነገር ነው። ዘመንን ያለማወቅ ችግር የክርስትናችንን ሩጫ እንደሚገባ እንዳንሮጥ መሰናክል ከሚሆኑብን ነገሮች አንዱ እና ዋናው  ነው።

 መቼም ዘመኑ የተገለባበጠበት፥ ዘመኑንም  ማስተዋል የተሳነው ክርስቲያን እንደዚህ ዘመን የበዛ አይመስልም። 

ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ ዘመኑን እወቁ የሚለን ከእኛ አንጻር ነው። ዘመኑ ለእኛ ለአማኞች ምንድነው? ዘመኑስ ምን ዓይነት ነው? ይኼን ያላስተዋለ አማኝ ብዙ ነገሩን ይስታል። እግዚአብሔር አብ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሳ በልጁ ወንጌል ለጠራን በክርስቶስ የመስቀል ሥራ አምነን ለዳንን ለእኛ ለአማኞች ዘመኑ ምንድነው? ዘመኑን ማወቅ ካለብን በእርግጥም ለእኛ ለአማኞች ዘመኑ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ሰዓት ነው ይለናል።

ከእንቅልፍ መነሳት ማለት ምንድነው?

ይኼን ለማብራራት ጳውሎስ እንዲህ ይለናል። "ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል"። 

 የሌሊትን ማለፍ እና የቀንን መቅረብ ሁኔታ በአትኩሮት ስናጤን በርግጥም ጳውሎስ ምን ሊለን እንደፈለገ ይገባናል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሦስት የተለያዩ ጊዜዎችን ይነግረናል። ጊዜዎቹም ሌሊት፥ ቀን እና በሌሊትና በቀን መካከል ያለ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ጊዜ ነው። ሌሊቱ የሚለው በክርስቶስ ከማመናችን በፊት የነበረውን በጨለማ ወይም በኃጢአት የነበርንበት ጊዜ ነው። ቀን የሚለው ደግሞ የክርስቶስ መምጣትና ከዚያ በኋላ ያለውን የዘላለም ዘመንን ነው። ሦስተኛው ደግም ከእንቅልፍ የምንሳበትን ወቅት ነው።

በእርግጥ ከእንቅልፍ የመነሻ ጊዜ በአሁኑ የሰለጠነው ዓለም የተለወጠ ቢሆንም ያኔ እዚያ መልክቱ የተጻፈበትን ዘመን ስንመረምር ሰዎች ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ከሌሉቱ 10:30 ጀምሮ እስከ 11:30 ባለው ውስጥ እንደሆነ ታሪካዊ ዳራዎች ያመለክታሉ። በእርግጥ አሁንም ራቅ ወዳሉ የገጠር የሃገራችን ክፍሎች ስንሄድ ሰዎች ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ከላይ በጠቀስኩት የሰዓት ክልል ውስጥ ነው።

ይኼ ከእንቅልፍ የመነሻ ጊዜ የእኛን ከጨለማ ማለትም ከኃጢአት ባርነት ወጥተን አሁን በእምነት በክርስቶስ ድነን ያለንበትን ጊዜ ይወክላል።  አዎ!  አሁን በክርስቶስ አምነን ከዚያ ከጨለማ ከሌሊቱ ጊዜ ወጥተናል። 

መጽሐፍም "ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን.." ይለናል። (1ጴጥ 2:9።)  በጌታም ብርሃን ሁነናል ነገር ግን እንደዚህ የሮሜ ክፍል አውድ ወደሙሉ ቀን ወይም ሙሉ ብርሃን ገና አልደረስንም። ወገግታው ላይ ነን።  ለዚያም ነው "ቀኑ" ተብሎ የጠራውን የክርስቶስን ዳግመኛ መገለጥ "ቀኑ ቀርቧል" የሚለን ጳውሎስ።

2. ለምንድነው ዘመኑን እንድናውቅ የተፈለገው?

ጳውሎስ ለምንድነው ዘመኑን እንዲያውቁ ወይም እንድናውቅ የፈለገው ለሚለው ጥያቄ  መልሱ ለዘመኑ እንደሚገባ እንድንኖር ነው። ዘመኑን አውቀናል እርሱም ከእንቅልፍ መነሻ ነው። 

ከእንቅልፉ የሚነሳ ሰው ደግሞ የሌሊት ልብሱን አውልቆ የቀኑን ልብስ ይለብሳል። ለዚያም ነው ጳውሎስ "ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፤ " የሚለን። 

ሌሊቱ ስላለፈ ቀኑ ስለቀረበ የሌሊቱን ልብስ ማለትም የጨለማን ሥራ በማውለቅ የቀን ልብስ መልበስ አለብን። 

እኛም ሌሊቱ(በክርስቶስ ከማመናችን በፊት የነበረው ጊዜ) አልፎ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ጊዜ ላይ ነን። "ቀኑ" ማለትም የክርስቶስን ምጻት ከፊት ለፊታችን ቀርቧል። ታዲያ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር ልንለብስ ይገባል። 

ጳውሎስም "በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤" ይለናል። ይልቁንም ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን እየቀረበ ስለሆነ (የስጋ ትሥሳኤ) ኢየሱስን ልንለብስ ይገባል። 
ኢየሱስን መልበስ ሲባል  የኢየሱስን ባህሪ ፍቅርን፣ ጽድቅን፣ ቅድስናን..በሕይወታችን መግለጥ ነው።

Monday, June 1, 2020

❖የመዳን ወንጌል እና የተስፋው መንፈስ፦


«እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፣ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤»ብሏል /ኤፌ.1፡13/፡፡

1. ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነው፦

ለሞት በሚያደርስ በሽታ እንደተያዙ የማያውቁ ሕሙማን ወደ ሐኪም ዘንድ ሄደው ለመታከምም ሆነ መድኃኒት ለማግኘት እንደማይንቀሳቀሱ ሁሉ ኃጢአተኛ መሆናቸውንና ኃጢአትም ዘላለማዊ ሞትን የሚያስከትል መሆኑን የማያውቁ ብዙ ሰዎች ስለመዳን መንገድ ለመረዳት ፍላጐት ላይኖራቸው ወይም ጊዜ ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ እንደሚከተለው ይናገራል፡፡

«ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም እንኳ የለም»/መዝ.13፡3/፡፡

«ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም»/ሮሜ.3፡11-12/፡፡

«... ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል»/ሮሜ.3፡22-23/፡፡

ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምንረዳው ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ሊሆን የቻለውም በኃጢአት ከወደቀው ከአንድ ሰው ማለትም ከአዳም የተወለደ በመሆኑ ነው፡፡ ኃጢአት ወደ ዓለም የገባውም በዚሁ በመጀመሪያው ሰው በኩል ነው፤ አዳም የተሰጠውን ትእዛዝ ቢተላለፍ ሞትን እንደሚሞት አስቀድሞ ተነግሮት ነበር /ዘፍ.2፡16-17/፡፡ ስለሆነም ትእዛዙን በተላለፈ ጊዜ ኃጢአት ወደ ዓለም ከመግባቱም ሌላ በኃጢአት ምክንያት የተፈረደው የሞት ፍርድ ለሰው ሁሉ ሊደርስ ችሏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲናገር «ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ሞት፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ» ይላል /ሮሜ.5፡12/፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው በኃጢአት ከወደቀው ከመጀመሪያው ሰው ስለተወለደ ኃጢአተኛ ከመሆኑም ሌላ የሞት ፍርድ የተፈረደበትም ነው፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር ለሰዎች ካለው ፍቅር የተነሣ ሰዎች ከዚህ ዘላለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ አንድ ልጁን አዳኝ አድርጎ ወደ ዓለም ልኳል፡፡

2. የእግዚአብሔር ፍቅር፦

እግዚአብሔር ጻድቅ ከመሆኑ አንጻር በኃጢአት ላይ የሚፈርድ እውነተኛ ፈራጅ የመሆኑን ያህል ኃጢአተኞችን ለማዳን የሚወድ የፍቅር አምላክም ነው፤ ይህ ፍቅሩ የተገለጠውም አንድ ልጁን ለእኛ በመስጠቱ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲገልጽ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፤ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና» ይላል /ዮሐ.3፡16-17/፡፡ ስለዚህ ኃጢአተኝነቱን ያወቀና በፍርድ ሥር እንዳለ የተረዳ አንድ ሰው ተስፋ ቈርጦ ከእግዚአብሔር ከመራቅ ይልቅ እግዚአብሔር ልጁን እስከመስጠት ድረስ እንደወደደው ሊገነዘብ ይገባል፡፡

ስለዚህይ አሁን ያለነው በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን እግዚአብሔር ልጁን ስለ እኛ ለሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ የወደደን  መሆኑን ልናውቅ ይገባናል፡፡ 

ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው ሞት ይህን የእግዚአብሔርን ፍቅር ያስረዳል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲናገር፦  «ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና፡፡ ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል» ይላል /ሮሜ.5፡6-8/፡፡ 

እግዚአብሔር ይህን ያህል እኛን  ኃጢአተኞቹን የሚወደን  ከሆነ እኛ ደግሞ እርሱ የሚያቀርብልንን የፍቅር ጥሪ ልንቀበል ይገባናል፡፡ 

እርሱ የሚጠራን እኛን ከዘላለም ጥፋት ለማዳን ነው፡፡ ስለዚህ የቀረበልንን የፍቅር ጥሪ ብንቀበል ለዘላለም የምንድነው እኛው ራሳችን ነን፡፡

3. የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት፦

ሰው ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት እንዲድን እግዚአብሔር ያዘጋጀው የመዳን መንገድ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።  /ዮሐ.14፡6/፡፡ 

ኢየሱስ የሚለው የጌታችን ስም ትርጉምም አዳኝ ማለት ነው፡፡ በማቴ.1፡21 ላይ፦  «እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ» የሚለው ቃል ይህንን ያስረዳል። 

 እርሱ ወደ ዓለም የመጣበት ዋነኛ ዓላማም ሰውን ለማዳን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ፦  «የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቷልና /ማቴ.18፡11፤ ሉቃ.19፡10/፤ እንዲሁም፦  «ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው» /1ጢሞ.1፡15/ ይላል፡፡

 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ይህንን ሰውን የማዳን ዓላማ ለመፈጸም እስከሞት ድረስ ታዝዟል፤ እርሱ በመስቀል ላይ የሞተው የሁላችንን ኃጢአት ተሸክሞና የሁላችን ምትክ ሆኖ ነው፤ «... እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ» /1ጴጥ.2፡24/ «አንዱ ስለሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ» /2ቆሮ.5፡14/ የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ይህን ያረጋግጣሉ። 

 እርሱ ኃጢአት የሌለበት በመሆኑ ስለኃጢአተኞች መሞትና ኃጢአተኞችን ማዳን ተችሎታል፤ ኃጢአት ያለበት ማንም ቢሆን ይህን ማድረግ አልተቻለውም፡፡ ስለዚህ በሰማይም ሆነ በምድር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አዳኝ የለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከእርሱ በቀር ሌላ አዳኝ እንደሌለ አስረግጦ ሲናገር «መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና» ይላል /የሐ.ሥ.4፡12/፡፡ 

ከኃጢአተኝነታቸው የተነሣ በሞት ፍርሃት ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉ ይህን የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነት መስማት ታላቅ የምስራች ነው፡፡ ይህም «የመዳን ወንጌል» ይባላል፡፡ 

ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ «እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፣ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤» ብሏል /ኤፌ.1፡13/፡፡ ይህም ቃል የመዳን ወንጌልን ተቀብለው በክርስቶስ ያመኑት ሁሉ የዘላለም መዳንን ከማግኘታቸውም በላይ በመንፈስ ቅዱስ መታተማቸውንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡

መዳንንም  የምናገኘው በተሰተን ጸጋ ነው እንጂ መልካም ሥራን በመሥራታችን አይደለም። 
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ሲናገር፦

 «ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፣ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን፤ በጸጋ ድናችኋልና፣.. .. ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም» /ኤፌ.2፡4-9/ ይላል፡፡ 

እንዲሁም በሌላ ስፍራ «ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፣ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፣ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም፤ ያን መንፈስም በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፣ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው፡፡ ቃሉ የታመነ ነው» የሚል ቃል እናነባለን /ቲቶ3፡4-7/፡፡ 

ስለሆነም መዳን በጸጋ እንጂ በሥራ እንዳልሆነ ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ መልካም ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን ከመዳናችን የተነሣ የምንሠራው ነው እንጂ መዳንን ለማግኘት የምንሠራው አይደለም፡፡ ሆኖም ከዳንን በኋላ መልካም ሥራን በመሥራት መዳናችን ይገልጣል፡፡ 

በኤፌ.2፡10 ላይ «እኛ ፍጥረቱ ነንና እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን» ተብሎ በተጻፈው ቃል መልካም ሥራ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት የመሆናችን ውጤት መሆኑን መረዳት ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ሰው ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን ልናውቅ ይገባናል፡፡ ከእኛ  የሚፈለገው ኃጢአተኝነታችንን በማመን ንስሐ መግባትና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ጊዜ ሳናጠፋ አሁኑኑ ልንወስ ይገባናል፡፡ 

መጽሐፍ ቅዱስ «እነሆ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው» ይላልና /2ቆሮ.6፡2/፡፡

በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሰብሰብ፦

ስለጌታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ሰምተው በእርሱ ያመኑና የዳኑ ሰዎች ከማያምኑት ተለይተው  በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሰብሰብ አለባቸው፡፡ 

ጌታችን በስሙ ስለመሰብሰብ ሲናገር፦  «ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ እኔ በመካከላቸው እሆናለሁና» ብሏል /ማቴ.18፡20/፡፡ 

ከማያምኑት ተለይተው በኢየሱስ ስም የሚሰበሰቡትን እግዚአብሔር በዚያ ስፍራ ይቀበላቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከማያምኑት ስለመለየት በሚናገርበት ክፍል ውስጥ «ስለዚህም ጌታ፡- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵሱንም አትንኩ» ይላል፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ እኔም እቀበላችኋለሁ ለእናንተም አባት እሆናለሁ፤ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል፡፡» በማለት ይናገራል /2ቆሮ.6፡17-18/፡፡ እንዲሁም በዕብ.13፡13 ላይ «እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ» በማለት የአማኞች ስፍራ የት እንደሆነ በግልጽ ይነግረናል፡፡ 

ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ» በማለት ሰዎችን ወደ ራሱ ይጠራል /ማቴ.11፡28/፡፡

  ውዳሴና አምልኮት የዘላለምን ሕይወት ለሰጠን ለነፍሳችን እረኛና ጠባቂው ክርስቶስ ይሁን!!!

Sunday, May 31, 2020

❖በልዑል መጠጊያ የሚኖር፦

ይህ የመዝሙር ክፍል አማኞች እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ምን ያህል ዋስትና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። እግዚአብሔር በአደጋዎች ሁል መጠጊያችን እንደሚሆን፣ ከዚህም የተነሣ መንፈሳዊና ሥጋዊ አደጋ ሲመጣ ቀድመን የእግዚአብሔርን ጥበቃ ልንፈልግ እንድምንችል የሚረጋግጥ ስንኝ ነው።

በእግዚአብሔር ለተወደድን ይኸውም ራሳችንን ለልዑል እግዚአብሔር ፈቃድና ጥበቃ አሳልፈን ለምንሰጥ፣ በእግዚአብሔር ሀልዎት ዕለት ዕለት ለመኖር ለምንፈልግ እጅግ ዋስትና ይሰጣል። 

 "በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤ የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤ በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ"።እንዳለው ነብዪ (ኢሳ 49፥2) እግዚአብሔር የእውነት መደበቂያችን ነው። ተሸጉጠን ክፉውን የምናሳልፍበት ምሽጋችን።

የዚህን መዝሙር ስንኞችን ሲያነብ ከነችግሩና መከራው አንብቦ የሚጨርስ ማነው? ስትጀምር የነበረው አደጋ ወይም መከራ ሁሉ ቁጥር አንድ ጋር አብቅቶ ሌላ ርዕስ ውስጥ ትገባላችሁ። እስኪ ከፋፍለን የእግዚአብሔርን ጥበቃ እንቃኘው

1) መዝሙሩ 91፥1-2 ፦
'' በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ። ''

ከሁሉ በላይ የሆነውንና የኃይሉን አምላክ መጠጊያው አድርጎ የሚኖር ሰው የሕይወቱ ዋስትና የሚያስተማምን በመሆኑ እግዚአብሔር መጠጊያዬና ምሽጌ የምተማመንበት ፈጣሪዬም ነው ብሎ ይመሰክራል።
   =} ምሳሌ:- አንድ ህፃን አባቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ እየወረወረ ሲያጫውተው ከሚተማመነው በላይ አደጋ ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር መተማመን። ይህንንም በእምነት መመስክር ያጋጠመን አደጋ ከእኛ ያሸሸዋል።

2) መዝሙር 91፥3-4፦
'' እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ''

እግዚአብሔር ሕዝቡን ከጠላት ይጠብቃል፣ በላባዎቹ ይጋርዳቸዋል፣ ጋሻ እና መከታ ይሆናቸዋል። ለእርሱ የአደጋውም ሆነ የችግሩ ግዝፈት እኛን ከመጠበቅ አያስቀረውም።
   =} አባባል:- ለእግዚአብሔር የችግርህን መጠን ከምትነግረው ይልቅ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለችግርህ ንገረው። የተባለውም ለዚህ ነው።

3) መዝሙር 91፥5-6፦
'' ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። ''

የእግዚአብሔር እንክብካቤ ጽኑና በቂ ነው ምክንያቱም ጥበቃው የተመሰረተው በማንነቱ ላይ ስለሆነ። እርሱ ሲጠብቅ ቀን አይል ሌሊት አይል ሁልጊዜ ነው። በጊዜ አይወሰን በስፍራም እንዲሁ በመዞር የተደረገ ጥላ የለበትምና። የእግዚአብሔር ጥበቃ በቀንና በሌሊት እንደ ሆነ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ምክንያቶች ከሚመጣ ፍርሀትና ድንጋጤ ይጠብቀናል።
=} ሰባኪው:- እንኳን ሌሊት ተኝተን አይደለም ቆመንም አይተን ከምናልፈው አደጋ ሳናየው ጠብቆን ያሳለፈን እጅግ ብዙ ነው። ተውት ያስተዋልነውን!!!

4) መዝሙር 91፥7፦

'' በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። ''

እርሱ በምድር ላይ በሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን ስላለው ለጥበቃው ወሰን የለውም። እንክብካቤውና ጥበቃው የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለማሳየት ሺህ እና አሥር ሺህ በማለት ይገልፀዋል። እግዚአብሔርን የሚያልፍ ችግር የለም።
   =} መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ:- ሕዝያስ እንዳጽናናቸው
(መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 32፥7-8 ) ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።

5) መዝሙር 91፥8፦
'' በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። ''

ጻድቃን የእግዚአብሔርን ማዳን በእምነት ዐይን ማየታቸው ይበለጥ እንዲበረቱ ያደርጋቸዋል እግዚአብሔር ጻድቃንን ለመጠበቅና ለመባረክ ቃል ገብቷል ጻድቃን የእግዚአብሔርን ፍትሕና ታማኝነት እንዲሁም የክፉዎችን መቀጣት በዐይናቸው ይመለከታሉ።
=} አመለካከት:- ሰው በሚያየው ሳይሆን በሚያምነው ይኖራልና።

6) መዝሙር 91፥9-10፦
'' አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። ''

ልዑሉን መጠጊያችን በማድረግ የጥበብን መንገድ እንድንከተል ያበረታታል እርሱ መጠጊያችን ነው በምድር ላይ የሚሆነው ማንኛውም ነገር በእርሱ ቁጥጥር ሥር ነው ክፉ ነገር ወይም መቅሠፍት ቢሆን ያል እርሱ ፈቃድ አይሆንምና።
=} ሂሳባዊ ቀመር:- ይጠጌ አይነኬ (asymptote)፤ ቅርብ ቢመስልህም፣ ሊነካ የቀረበ ቢመስልም ሁሉን ማድረግ በሚቻለው ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ በማይቸለው ተአምር አድራጊነት ሳይነካህ ያልፋል። ይታከክሃል አይነካህም ይቀርብሃል አይደርስብህም ይመጣብሃል አያገኝህም።

7) መዝሙር 91፥11-13፦
'' በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። ''

እግዚአብሔር እኛን አማኞችን በምንሄድበት ሁሉ ይጠብቁን ዘንድ መላእክቱን ያዛቸዋል። መላእክቱ እኛን ከአደጋ ለማስመለጥ እንዲጠብቁን ዘወትር እንዲታደጉን በተጠንቀቅ በዙሪያችን አሉ። እግዚአብሔር በልጆቹ ላይ ብዙ ነገር እንዲደርስ ሊፈቅድ ይችላል ይሁንና አንድም ኅይል ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ አንዳልሆነ ያውቃሉ።

8) መዝሙር 91፥14፦
'' በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ''

እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት እና ስሙም ለሚያውቁ ሁሉ የማዳኑን ንግር ያበሰረበት ክፍል ነው። መውደድ የሚለው ቃል እግዚአብሔርን ከልብ መናፈቅንና መሻትን ይሆንላቸዋል።
=} የጌታ ቃል:- ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ በታች እንደምትሰበሰብ እንዴት ይልቅ እርሱ እንደሚጋርደን።

9) መዝሙር 91፥15፦
'' ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። ''

ይህ ቃል የአማኝ የድምፅ ብክነትን የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል። ሲጣር ደመና አይከለክለውም፣ የፀሐይ ግርዶሽ አይዘውም፣ ንፋስ አይወስደውም፣ ዝናብ አይመልሰውም። አቤት የሚል ብቻ ሳይሆን በመከራ የማይተወን አብሮን የሚሆን ደግሞም የሚያድነን ጌታ አለ።

10) መዝሙር 91፥16፦
'' ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። ''

ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ ሲገረም ''እንግዲህ ምን እንላለን'' ይላል ደግሞስ ምንስ ይባላል እኔም ከምናገር እጅህን አፍህ ላይ ጫን ይለኛል። ይህ ሁሉ ጥበቃ ለእኔና ለአናንተ ነው። እውን ከዚህ የቀረበ ደግሞም ህያው የሆነ ነገር ምን አለ?
      እግዚአብሄር ይክበር ይመስገን!!!

Wednesday, May 27, 2020

❖እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፦

  እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፦
        (ዮሐ 21፡17)
የክርስቶስ በጥብርያዶስ መገለጽ ሦስተኛው መገለጥ ነው። ጥብርያዶስ በባህር አጠገብ ያለ ቦታ ነው። ባህሩም የጥብርያዶስ ባህር ተብሎ ይጠራል። ክርስቶስ ዓሳ እያጠመዱ ሳሉ ተገልጾላቸዋል። 

በዚህች ሌሊት እነ ጴጥሮስ ምንም ዓሣ አልያዙም አለመያዛቸው የጌታ ፍቃድ አለመሆኑን ያስረዳል። ሰውን እንጅ ዓሣን እንደማያጠምድ አስቀድሞ የተናገራቸውን መዘንጋታቸው በዝህች ሌሊት ድካማቸው ከንቱ እንዲሆን ሆኗል። 

ያለ ጌታ ፍቃድ የሚሰራ ሥራና የሚደከም ድካም ውጤት እንደሌለው እንዲረዱ አድርጎአቸዋል። ሌሊት ያልተያዘው ዓሣ በንጋት በጌታ ቃል መረባቸውን ወደ ባህር በጣሉ ጊዜ ብዙ ዓሣ ተይዞአል። 

ይህም የጌታ ቃል ሁሉን እንደሚያደርግና ማድረግም እንደሚችል። እንዲያምኑ ረድቶአቸዋል። መታዘዛቸው ብዙ ዓሣ ለማግኘታቸው ዋነኛ ነው። ተስፋም አልቆረጡም። ሌሊቱን ሁሉ አልያዝንም ብለው መረባችንን አንጥልም አላሉምና። 

ጌታ መሆኑን ያወቁት ከታዘዙት በኋላ ነው በመታዘዛቸው ብዙ ዓሳ ሲያዝላቸው ነው። መታዘዝ የተሰወረውን ይገልጻል ያጡትንም ያስገኛል። 

ወደ ወደቡ ወይም ከባህሩ ከወጡ በኋላ የተጠበሰ ዓሳና የተዘጋጀ እንጀራ፤ የነደደ እሳት አግኝተዋል። ይህ ሁሉ ያልደከሙበት ነው፤ ታዘዙ በመታዘዝ የሰሩት ውጤታማ ሁነላቸው። የተዘጋጀ እንጀራና ዓሳ አገኙ።

ምስጢሩ ለሐዋርያነት ታዘው ዓለምን ሲያስተምሩ ሰውን እንደ ዓሳ ይስበስባሉ። በጌታ የተዘጋጀ ስማያዊ ጸጋንም ያገኛሉ። 

ተዘጋጅቶ የተገኘው እንጀራና ዓሳው እግዚአሔር የሚሰጠውን ጸጋ ያመለክታል።

ጴጥሮስን ትወደኛለህን? ብሎ ሦስት ጊዜ ጠይቆታል። እንደሚወደውም ባረጋገጠ ጊዜ በጎቼን፤ግልገሎቼን፤ጠበቶቼን ጠብቅ ብሎታል።  ጴጥሮስ የጌታን ፍቅር መግለጽ ያለበት እነዚህን በመጠበቅ ነው። ከዚህ የበለጠ ፍቅርም እንደማይኖር ደጋግሞ በመጠየቅና ከወደድከኝ ጠብቅ በማለት አስረድቶታል። በወደደው ልክ ምዕመናኑን መጠበቅ እንዳለበት ተረድቷል። 

ክርስቶስ ለጴጥሮስ ሲናገር ሽማግሌና ጎልማሳ ብሎታል። በጎልማሳነቱም ጊዜ የወደደውን የሚሰራበት ነበር ይህ ማለት ስሜቱን ተከትሎ ይኖር ነበር ማለት ነው። ሽምግልናው ግን የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ተከትሎ እንደሚሄድ ያስረዳል። 

ሽምግልና በአእምሮና በእውቀት በመንፈስ ቅዱስም ማደጉ ነው። ትጥቁም የመንፈስ ቅዱስ ነው። ሌላ ያስታጥቅሃል ወደ ማትወደውም ትሄዳለህ ተብሎአል። የማይወደውን ሞትና መከራ ለመቀበል እግጁ መሆኑን ያስረዳል። 
           ክብር ለስሙ ይሁን!!!

❖አርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወነበረ በየማነ አቡሁ፦

አርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወነበረ በየማነ አቡሁ፦
       (ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ 7)

    ዓለምን በሞቱ ና በትንሳኤው በፍቅሩና በኀይሉ ማርኮ ዐረገ። 

ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።
ሰይጣንን የማረከው በሃያልነቱ ነው።
ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ መጥቶ ሲያሸንፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን ጋሻና ጦር ይወስድበታል ምርኮውንም ያካፍላል።    (ሉቃ 11፥22) 

ሰይጣን የሚታመንበት የክፋትና የጥላቻ ጋሻና ጦር ነበረው። በሁሉም ላይ በፍቅሩ መልቶ ለመኖር ከሰማይ ወረደ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው ። (ኤፌ 4፥8-10)
በዓለም ላይ ሃይሎ የነበረውን ሰይጣንን አስሮታል። ተቆጣጥሮት የነበረውን ሁሉ ወስዶበታል። 

"ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።" (ማቴ 12 .29 )

ጌታችን እንደተናገረው ኀይለኛው ባይታሰር ኖሮ ተቆጣጥሮት የነበረውን ሁሉ መማረክ አይችልም ነበር በኀጢአታችን ላይ በርትቶ የነበረው ታስሯል ።ጌታችን ድል አድርጎ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ዳግማኛም ይመጣል።
          ለርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን!!!