Tuesday, June 23, 2020
❖ የማይገባ ደግነት:-
Friday, June 19, 2020
❖የጌታ መልአክና ወንጌል፦
የጌታ መልአክና ወንጌል፦
የእግዚአብሔር መልአክ ሕይወት የሆነው ጌታ ለዓለም እንዲበሰር ተናገረ።
የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና፦
ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው። (የሐዋ 5፡19፡20)
ምክንያቱም ሰው ሕይወት እንዲኖረው ይፈልጋል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። (ዮሐ 5፡24)
በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።
ቆርኔሌዎስን ከቅዱስ ጴጥሮስ ወንጌልን እንዲሰማ አዘዘው፦
ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት።ርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና፦ ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።
ይህ መልአክ ጴጥሮስ ስለዘዓለአለም ሕይወት እንደሚነገር ያውቃል።
በዘመን መጨረሻ የእግዚአብሔር መልአክ ወንጌልን ለዓለም ያውጃል፦
በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ። (ራእይ14፥6 )
በጨረሻም ቢሆን እንኳ ሰው ሁሉ ሕይወትን እንዲያገኝ የእግዚአብሔር መልአክ ያውጃል የሰው ልጅ ለሚያገኝው የዘለአለም ሕይወት ያለቸውን ከፍታኛ ፍለጎት ያረጋግጣል እኛ ግን ለኛ የሆነውን ሕይወት ቦታ አልሰጠነውም ።
የእግዚአብሄር ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!!
Sunday, June 7, 2020
❖መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ውኃ ወንዝ ነው፦
☞መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ውኃ ወንዝ ነው፦
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲስተምር፦
"በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ ይላል "ቅዱስ ወንጌል
(ዮሐ 7፥38)
❖ ይህን የተናገረው ለማን እንደሆነ ሲገልጽ፦
"ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ [ስላልተሰቀለ ማለት ነው] መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና" ብሏል።
ወንዝ ሳያቋርጥ የሚፈስ ነው የመንፈስ ቅዱስ ፀጋና በረከትም ለሚቀበሉት ሁሉ ያለማቋረጥ ሲሰጥ ይኖራል።
❖ ቅዱስ ጴጥሮስ በሃምስኛው ቀን ለደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ መውረዱን ሲያስረዳ፦
እግዚአብሔር ይላል፦
"በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ"።
(የሐዋ 2፥17-18)
☞ ወንዝ የፈሰሰበት ሁሉ ይለመልማል ያፈራል። መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሁሉ በእግዚአብሔር ፀጋ ይለመልማል የእግዚአብሔር የሆነውን ያፈራል ።
☞ ሕዝቅኤል የመንፈስ ቅዱስን ፀጋና በረከት ከመቅደሱ የሚፈስ የሕይወት ውኀ መሆኑን ገልጿል።
ከመቅደሱ የሚወጣ ዉሃ ወደ ምስራቅ ሲፈስ ይመለከታል፡፡
ሰውየው (የሚያሳየው መልአክ ማለት ነው) ገመዱን በእጁ ይዞ 1000 ክንድ ለካ፡፡
☞ በዉሃው ውስጥ አሻገረኘ ዉሃው እስከ ቁርጭምጭሚት ደረሰ።
☞ ሁለተኛ ሲሻገረው እስከ ጉልበት።
☞ ሶስተኛ እስከ ወገብ ።
☞ አራተኛ እጀግ ጥልቅና ሰፊ ወንዝ በመሆኑ ማንም ሊሻገረው የማይችል ወንዝ ሆነ፡፡
❖ ወንዙ የእግዚአብሔርን በረከትና ፀጋ ዘልዓለማዊ ሕይወትን ይገልጻል፡፡
☞ እስከ ቁርጭምጭሚት በዘመነ አበው የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ፣
☞ እስከ ጉልበት በዘመነ መሳፍንት የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ፣
☞ እስከ ወገብ በዘመነ ነቢያት የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ ደህንነት፣
☞ ማንም ሊሻገረው የማይችለው ዉሃ በጌታችን በኢየሱስ ክረስቶስ የተሰጠውን በረከትና ፀጋ ዘልዓለማዊ ሕይወት የሚገልጽ ነው፡፡
ማንም ሊሻገረው የማይችል ታላቅ ወንዝ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና የሚለውን ያረጋግጣል።
☞ መሲህ የሕይወት ዉሃ መሆኑን ተናግሯል፡፡
☞ መንፈስ ቅዱስም የሕይወት ውሃ መሆኑን ተናግሯል።
☞ በርሱ የሚያምን የሕይወት ዉሃ ከርሱ እንደሚመነጭ አስተምሯል፡፡
❖ በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።
❖ ዉሃው ወደ ምስራቅ ባሕር በገባ ጊዜ የምስራቁ ባሕር ሙት ባሕር ነው፡፡ ዉሃው ይፈወሳል።
☞ ዉሃው የሚወክለው የረከሰውን ሕዝብ ሰለሆነ በመሲህ ያመነ ሁሉ ፈውስንና የዘልዓለም ሕይወትን ማግኘቱን ያረጋግጣል፡፡
❖ ዉሃው ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ በሕይወት የሚኖርበት መሆኑን ይናገራል፡፡
☞ ወንዙ በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል፡፡
ዉሃው የሚፈሰው እጅግ በበረሃማነት ወደሚታወቀው ወደ ይሁዳ ምድረበዳና ወደ ጨው ባሕር ነው፡፡ መራራው የጨው ባሕር የብዙ ዓሳዎችና ተንቃሳቃሽ ሕያዋን ፍጥረታት መኖርያ ይሆናል፡፡ ይህም የሆነው ጨዋማው ዉሃ በመቅደሱ ውሃ ስለተፈወሰ ነው፡፡
ረግረግና እቋሪው ግን ጨው እንደሆነ ይኖራል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑትን ይመለከታል፡፡ በወንዙ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ቅጠሉ የማይረግፍ ፍሬው ለሁልጊዜ የሚያፈራ አለ፡፡ ፍሬው ለመብል ቅጠሉ ለመድኀኒት የሕይወት ዛፍ ነው የሚወክለውም ዘልዓለማዊ ሕይወትን ነው፡፡
(ሕዝቅኤል 47፥1-12)
እግዚአብሄር ይክበር ይመስገን!!!
❖መንፈስ ቅዱስ፦
መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?
፩. መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?
☞ ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል ነው፡፡
☞ የማይጨበጥ፤የማይታይ አካል ያለው መንፈስ ነው፡፡
☞ የሰረፀው (የወጣው) ከአብ ነው።
☞ ከአብ እና ከወልድ ጋር እኩል ምስጋናና አምልኮ የሚገባው ነው።
☞ እግዚአብሔር (አምላክ) ነው፡፡
☞ የአብ እና የወልድ እስትንፋስ (ሕይወት)ነው፡፡
☞ በነቢያትና በሐዋርያት አድሮ የተናገረ፥ሕይወትንም ያቀና : ምድርን ለክብሩ ያስጌጠ ነው፡፡
፪. የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ምን ምን ናቸው?
ርግብ፣ እሳት፣ ውኃ፣ ዘይትና ነፋስ ናቸው።
☞ ርግብ የዋህ ናት፦ መንፈስ ቅዱስም የዋህና ቂም የማያውቅ ነው፡፡ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ መድረቁን ያወጀች የሰላም ምልክት ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ክርስቶስ ሲጠመቅ የኃጢአት ባሕር መድረቁን በርግብ ምሳሌ ወርዶ የሰበከ የሰላም ጌታ ነው።
☞ እሳት ያበስላል፦ መንፈስ ቅዱስም ሕፃን የሆነውን አእምሮ በጥበብ ያጎለምሳል፡፡ እሳት የከበረ ማዕድንን ከአፈር ይለያል፥ መንፈስ ቅዱስም አምኖ የከበረውን ፡ ካላመነው ይለያል፡፡
☞ ውኃ ያነፃል፥ መንፈስ ቅዱስ ይቀድሳል፡፡
☞ ነፋስ፣ ነፍስና መንፈስ የሚወጡበት የግሪክ ቃል ኒዩማ የሚል ሲሆን ከነፋስ- ነፍስ፤ ከነፍስ- መንፈስ ይረቃል። ነፋስ በእንቅስቃሴው እንደሚታወቅ መንፈስ ቅዱስም በሥራው ይታወቃል፡፡
❖ በብሉይ ኪዳን የመብራት ዘይት ነበረ፥ በየዕለቱ በመቅረዙ ይጨመራል፡፡ ይህ የመብራቱ አለመጥፋት የመንፈስ ቅዱስን መኖር ያመለክታል፡፡
❖ መንፈስ ቅዱስ ለቅርፅ አልባዋ መሬት ውበት ያፈሰሰ፥ ውኆችን ለፍጥረት ጥቅም የቀደሰ ጌታ ነው፡፡ "ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።" ኦሪት ዘፍጥረት 1:2።
❖ መንፈስ ቅዱስ መሳፍንትን በምስፍና፥ ነገሥታትን በንግሥና፥ ካህናትን በክህነት ጸጋ፥ ነቢያትን በሀብተ ትንቢት፥ ዘማርያንን በዝማሬ ጸጋ፥ ፈዋሾችን በሀብተ ፈውስ ......የሾመ...ጸጋ የሰጠና ጸጋን ያደላደለ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡
❖ መንፈስ ቅዱስ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም የሆነላትን እንድትረዳ አደረባት፡፡ ድንግል ማርያም በድንግልና እንድትወልድ ሁሉን አስቻላት፡፡ በክርስቶስ አገልግሎት ነበረ፡፡
❖ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት ተናግሯል፡፡
☞ "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።" የዮሐንስ ወንጌል 14:26
☞ "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።" ዮሐንስ 16:7-15::
☞ " ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤" የዮሐንስ 15:26።
☞ " ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" ዮሐንስ 14:15-16::
❖ በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአደራረጉ ምክንያት:-
☞ የእውቀት መንፈስ፣
☞ የጥበብ መንፈስ፣
☞ የኃይል መንፈስ፣
☞ የእውነት መንፈስ፣
☞ የመገለጥ መንፈስ፣ ...ተብሎ ተጠርቷል፡፡
በክርስቶስ አገለግሎት የነበረው ሱታፌ እንዳለ ሆኖ በክርስቶስ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ ከላይ ባሉት ጥቅሶች አይተናል፡፡ በክርስቶስ ትምህርት አጽናኝ(ጰራቅሊጦስ)፣ የእውነት መንፈስ እና ሁሉን የሚነግር መምህር ተብሏል፡፡ የሚመጣው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ የሚመጣበት አላማ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የማያምኑትን ይወቅሳል፤ የዲያብሎስን መጣል ይናገራል፤ ጽድቅ ወደ አብ በሄደው በክርስቶስ እንደሆነ ይመሰክራል፤ የቤተክርስቲያንን እንቅስቃሴ ይመራል፤ ምእመናንን ያጽናናል፤ ለበጉ ሠርግ ያዘጋጃል፤ አገልጋዮችን ያሰማራል፡፡
❖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም መጣ፤ በጽርሐ ጽዮን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተወለደችውን የክብርት ቤተክርስቲያን ልደት በእሳት ላንቃ በዓለም ቋንቋ አከበረ፡፡ ሐዋርያትን ለእውነት አስጨከነ፤ ምስጢር እና ብዙ ቋንቋዎች ገለጠላቸው፡፡ በጉዞቸው ሁሉ አብሮ ነበረ፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን አገለግሎት ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ነውና ክብር ለመንፈስ ቅዱስ!!
❖ ላመነ ሰው ጥምቀት የሚፈጸመው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ይህም የክርስቶስ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ 28:19:: በጥቅሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አይፈጽሙም፡፡ የምስጢራቱ አፈጻጸም ሥርዓት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
በመግቢያዬ እንደጻፍኩት ቤተክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ ጠንካራ አቋም አላት፦ "ማህየዊ በሚሆን በአንድ ጌታ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እርሱም ከአብ የሰረፀ ነው፡፡ በነቢያት እና በሐዋርያት ተናግሯል፡፡ ከአብ ከወልድ ጋር ምስጋና ይገባዋል።" ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ ፰.
መንፈስ ቅዱስ፦
☞ ሕይወት ሰጭ፤ ጥበብ ገላጭ መንፈስ ነው፡፡
☞ የጸጋ ምንጭ እና አደላዳይ ነው፡፡
☞ ለበጎ ሥራ ቀስቃሽ፤ከኃጢአት እንድንወጣ ወቃሽ ነው
☞ ልብን አይቶ የሚሾም፤ ትሁታንን የሚያከብር ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡
❖ መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ኃይል ነው፡፡ ብርታት የሆነን እርሱ ነው፡፡ ስንደክም ያግዘናል፡፡ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል(ሮሜ 8:26-27)፥ እንዴት ማምለክ እንዳለብን ይመራናል፥ ከዚያ ጸሎታችንን ይሰማል፤ አምልኮችንን ይቀበላል፡፡
❖ የመንፈስ ቅዱስ ነገር ለፍጥረታዊው ሰው ሞኝነት ነው፡፡ "ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።" 1ቆሮንቶስ 2:14። የመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ በእምነት መንፈስ እንጂ በሥጋ አይመረመርም፡፡ የጰራቅሊጦስ የተቀበልነው ይህን የእውነት መንፈስ ነው፡፡ "እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።" 1ቆሮንቶስ 2:12።
❖ መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታዊ ሰው አይኖርም፡፡ እንዲያውም የክርስቶስ መንፈስ የሌለው የክርስቶስ ወገን አይደለም፡፡ "የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።" ሮሜ 8:9።
❖ ምክር፣ ጥበብ፣ ምስጢር፣ ትንቢት፣ ፈውስ፣ ዝማሬ፣ ሹመት፣ ኃይል .... ከመንፈስ ቅዱስ ይሰጣሉ፡፡ ደስታ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት፣ ትዕግስት፤ በጎነት፣ ቸርነትና ሰላም የመንፈስ ፍሬ ናቸው፡፡ ገላ 5:23::
❖ መንፈስ ቅዱስ ከምንተነፍሰው አየር በላይ ያስፈልገናል፡፡ በሥራችን ዐመፃ የመንፈስ ቅዱስን አሠራር ልንቃወም እንችላለን፡፡ "መንፈስን አታጥፉ፤" 1ተሰሎንቄ 5:19። ንጉሥ ዳዊት በበደለ ጊዜ ይህ አጋዥ፣ አስተማሪ፣ መሪ እና አጽናኝ መንፈስ እንዳይወስድበት ለመነ፡፡ "ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።" መዝሙረ ዳዊት 51:11።
❖ መንፈስ ቅዱስ ከተለየን ሕይወት፣ ሰላም፣ ዕረፍት፣ መንፈሳዊነት ... የንስሐ ጸጸት...ይለዩናል፡፡ ስለዚህ "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።" ኤፌ 4:30-32:: የሥጋ ሥራ ከመንፈስ አላማ ያወጣል፡፡ የሥጋ አሠራር መንፈስ ቅዱስን ይቃወማል፡፡ ደስታ የሰጠን ሀዘን ሊቀበል አይችልም፡፡ ባናከብረው ደስታ የምናጣው እኛ ነን፡፡ " ለአሠራሩ እንመች፡፡ በኖህ ዘመን ርግቧ በመጀመሪያው ጉዞዋ ማረፊያ አጥታ እንደተንከራተተች መንፈስ ቅዱስም ለአሠራሩ የሚመች ሰው አጥቶ በዙሪያችን አለ።" ለአሠራሩ እንመች፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሰን፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ አንብቡ ፥ ዘምሩ፡፡
ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይገባል!!!
Friday, June 5, 2020
❖አቤቱ ሞትህን እንናገራለን ድንቅ ትንሳኤህን እናወራለን፦ (1ቆሮ 11:26)
አቤቱ ሞትህን እንናገራለን ድንቅ ትንሳኤህን እናወራለን፦
አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ እርሱ እንደሚናገር ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮአል። « ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ….. እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።» (ሉቃ 24:27:44)
መላው መጽሐፍ ቅዱስ በአቀራረቡ ከፍጥረተ-ዓለም እስከ ኅልፈተ-ዓለም ያሉ ነገሮችን በአብዛኛው ጠቅለል አድርጎ ሲናገር የክርስቶስን ሕይወት ግን ከልደቱ እስከ ሞቱና ትንሣኤው በዝርዝር ዘግቧል። ከሚናገርለት የብዙ ሺህ ዓመታት ጉዳይ እና ብዙ ሰዎች አንጻር ስናየው ስለ ክርስቶስ ከሁሉም የበለጠ ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። በተለይም መከራና ሞቱን(ከትንሣኤው ጋር) በተለየ ሁኔታ በየሰዓቱ ማለት ይቻላል የነበረውን ዝርዝር ሁኔታ በመናገር ከሌላው የሕይወት ክፍሉ የላቀ ትኩረት እንደሰጠው እናስተውላለን።
ይህም የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አጀንዳ በልጁ ከልጁ ለልጁ ራሱ እንደሆነ፤ በልጁ ያደረገው እያደረገው ያለውና በልጁ ዳግመኛ መምጣትም የሚያደርገው የዘላለሙ አጀንዳው እንደሆነ ልብ ይሏል።
የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሞት እንዲሁም ትንሳኤ በአጠቃላይ የመስቀሉን ሥራ ሊተካ፣ ሊተካከል ወይም ሊወዳደር የሚችል አንዳች ነገር የለም አይኖርምም። ስለሆነም የአንድ ሰሞን አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የዘወትር ርእሳችን ነው። በየዕለቱ ዘወትር የክርስቶስን መከራና ሞት ልናስብ ልንናገር ይገባል።
ሞቱና ትንሳኤውን ማውራት ማለት ጲላጦስ ፊት ቆመ፣ ተገረፈ፣ ተቸነከረ፣ ...ወዘተ ማለት ብቻ አይደለም ይልቁንም በመስቀሉ ሥራ የተገኘውን ውጤትም ጭምር እንጅ። ጳውሎስ ስለጌታ ራት በጻፈበት መልዕክቱ የጌታ እራትን ዓላማ ሲገልጥ ሞቱን መናገር እንዲሁም ማሰብ እንደሆነ ነግሮናል። « ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና። » (1ቆሮ 11:26)
ቢጻፍ ዓለም የማይበቃው ቢወራ የማይ'ሰለቸውን የክርስቶስ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት፤ የእግዚአብሔር መልእክት እንደሆነ ሁሉ የኛም የስብከታችን ትኩረት፣ የመዝሙራችንና የጸሎታችን ማዕከል ነው። የቤተክርስቲያን የዘወትር ርእሷ፤ የሁልጊዜ መልእክቷ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ብቻ ነው ሊሆንም ይገባል። ጳውሎስ ወሬው ሁሉ እውቀቱ ሁሉ ኑሮውም ጭምር ለዚህ ነበር። (1ቆሮ 1:23 1ቆሮ 2:2 ፊልጽ 3:8-9)
ሰው የእግዚአብሔርን መልክ እየገለጠ እንዲኖር ቢፈጠርም ፈቃድ ያለው ፍጥረት ስለሆነ ፈቃዱን ተጠቅሞ ለእግዚአብሔር እንዲገዛ፣ እርሱን እንዲያከብር አትብላ የሚል ትዕዛዝ አግዚአብሔር ሰጥቶታል። (ዘፍ 2:16-17።)
ነገር ግን በሰይጣን ተንኮል በሔዋን መተላለፍ አዳም በመተላለፍ አትብሉ ከተባሉት ከዛፉ በላ። ከዛፉ በበሉ ጊዜ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ አመጹ። አዳም ትሞታለህ በተባለው መሠረት ወዲያው በስጋ አልሞተም ነገር ግን ከእግዚአብሔር በመንፈስ ተለየ (በመንፈስ ሞተ)።
የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ተለየ(ሞተ)። ከኤደን ገነት አባረራቸው። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ሕብረታቸው ተቋረጠ። በኋላም ዘጠኝ መት ሃምሳ ዓመት ኑሮ በስጋም ሞተ። ኃጢአት ሞትን አመጣበት። በዚህ ምንክያት ኃጢያት በአንድ ሰው ምክንያት ወደ ዓለም ገባ። ሞት የኃጢያት ውጤት ነውና በኃጢያትም ምክንያት ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ። (ሮሜ 5:12)
መጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ በሆነ መልኩ እንደሚነግረን፥ ከተካፈልነው የኃጢአት ተፈጥሮ የተነሳ፦ " ሁሉ ኃጢያትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል" ይላል። (ሮሜ 3:23)
በአንዱ አዳም አለመታዘዝ ሁሉ ኃጢያተኛ ሆነ ከእግዚአብሔር ክብር ጎደለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ታላቅ ቁጣ ሥር ነው ያለው። የሰው ልጅ ሙት እና የእግዚአብሔር ጠላት ሆነ። (አፌ 2:1-3 ቆላ 1:20-21)
የኃጢያት ደመወዝ ሞት ነውና ለዘላለም የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ተለይቶ ቆዬ። (ሮሜ 6:23)
እግዚአብሔር ግን የምህረት አምላክ ሰለሆነ ለወደቀውና የዘላለም ፍርድ ለሚጠብቀው የሰው ዘር ሁሉ የምሕረት ዕድል ሰጠን። ስለዚህ በዘላለም ክብር የነበረው አምላክ እኛን ለማዳን በስጋ ተገለጠ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ መስቀል ላይ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ የሁላችንን ኃጢያት ተሽክሞ ምትክ ሆኖ ሊሞት ተሰቀለ። በኛ ላይ ሊያርፍ የነበረ የእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ላይ አረፈ። እኛ መሞት የነበረብንን ሞት እሱ ሞተልን። በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን። አሁን የኃጢያት ስርየት አገኘን። (ሮሜ 3:25)
"እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥" ስለዚህ ክርስቶስ በሞቱ የኃጢያታችን ዕዳ ከፈለልን፤ እኛን ለማጽደቅ ደግሞም በአዲስ ማለትሜ በራሱ ሕይወት እንድንመላለስ ከሙታን ተነሳ። (ሮሜ 4:24-25 ኤፌ 2፣5)
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለኃጢአታችን መስዋዕትን ሲከፍል የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተከናውነውልናል፡፡
የመጀመሪያው የኃጢአት ሥራ እና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ነው።
መስቀሉን ስንመለከት የኃጢአት ሥራ አስፈሪነትና አስቀያሚነት ይታየናል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአት ነው ክርስቶስን ከክብር ዙፋኑ ላይ ወደ እኛ እንዲመጣ ያደረገው፡፡ የሰው ኃጢአት ነው እርሱን የሀዘን ሰው ያደረገው፡፡ እኛን አሁን ባለንበት አሰቃቂ ክፋት እልቂት ጭከናና ጦርነት ሁኔታ ውስጥ የጣለን ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፣ ስለዚህ ኃጢአትን ይቀጣ ዘንድ ልጁ በመስቀል ተንጠለጠለ። ኃጢአት ለእግዚአብሔር ባህሪ የማይስማማው መሆኑን ኃጢአትን በክርስቶስ ስጋ ላይ ሲቀጣ እንገነዛባለን እናም እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። ሮሜ 3:25-26
ሁለተኛው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው።
1ዮሐ 4:10 የታረደውን በግ በመስቀሉ ላይ ሆኖ ስናይ ሌላ የምናስተውለው ነገር የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው። እኛ የሰው ልጆች በኃጢአት የቆሸሸ ሕይወት ያለን ነን፡፡ እኛ እራሳችንን ለኃጢአት ሸጠናል፣ በኃጢአት ውስጥ ዘቅጠናል፣ ጥላቻ፣ ነፍስ ግድያ፣ ስርቆት፣ ውሸት፣ አመንዝራ፣ ወዘተ ታሪካችንን ሞልቶታል፡፡ ከእነዚህ ከወደቅንባቸው ኃጢአቶች የተነሳ ንፁህና ፍፁም የሆነው እግዚአብሔር የዘላለም ፍርድ ሊሰጠን ይገባዋል፡፡
ነገር ግን በመስቀል ላይ የታረደውን በግ ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍቅርና የምህረቱን ብዛት እንገነዘባለን፡፡ ጻድቅ እግዚአብሔር ፍርዳችንን በንፁህ ጌታ ኢየሱስ ላይ አድርጎ እኛን ለማዳን እርሱ በእኛ ምትክ እንዲታረድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ይህ ከኛ የተነሳ ሳይሆን ከእርሱ ፍቅር ብቻ የተነሳ እንደተደረገ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ምን ዓይነት ፍቅር ነው፡፡ እኛን ጠላቶቹን እግዚአብሔር ወደደን። ይህንን ፍቅር በቃላት ለመግለፅ አይቻልም፡፡ ምን ማድረግ ይገባናል? መጽሐፍ ቅዱሳችን በውድ ልጁ እንዲያው የሠጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይኼን አደረገ ስለሚል በምስጋና እናወድሰው። (ኤፌ 1:6)
ሦስተኛ የእግዚአብሔር የዘላለም ዕቅድ ነው።
አንዳንዶች የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሞት እንደ ድንገተኛ አደጋ አድርገው ሊቆጥሩት ያስባሉ፡፡ በድንገት አዳምና ሔዋን ስለተሳሳቱ እግዚአብሔር እቅዱ እንዳይበላሽበት "በል እስኪ ሂድ ልጄ አድናቸው" ተብሎ የመጣ ድንገተኛ ሃሳብ አይደለም። ሲጀመርም ከዘላለም እግዚአብሔር ልጆቹ እንድንሆን ያሰበው በልጁ ስራ ነው። (ኤፌ 1:5)
ይኼን ሃሳብ ጴጥሮስ በመልክቱ ያጠናክረዋል። "ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። (1ጴጥ 1:18-21)
ይህ የሚያሳየው የእርሱ የመስቀል ሞት በእግዚአብሔር ጥንት የታቀደ፤ የታሰበበት፣ ነገር ግን በድንገት ያልተፈፀመ መሆኑን ነው፡፡
በልጁ ሞት የኃጢአት ዕዳችን ተከፍሏል። ከእግዚአብሔር ቀጣ ተርፈናል። በልጁ ከሙታን መነሳት እኛም አብረን ከሞት መንደር ተነስተናል። የራሱን የእግዚአብሔርን ሕይወት ተካፍለናል፣ ጸድቀናል፣ ተቀድሰናል፣ ልጆች ሁነናል.....ወዘተ ይኼ ሁሉ በልጁ ሞት እና ትንሳኤ አግኝተን እንዴት ስለእርሱ አናወራ!
❖ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል ፦(ዮሐ 16:13-15)
በእኛ ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ከአብ ና ከወልድ ጋር ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያንን ከአካሏ ከክርስቶስ እንዲሁም በተለያዩ የምድር ስፍራ ካሉት ከምናውቃቸውም ከማናውቃቸውም አማኞች ጋር በሕይወት እንድንተሳሰር አድርጎናል።
የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ከመሆኑ የተነሳ የክርስቶስ ወገን ሁነናል። (ሮሜ 8:9።) ይሁን እንጅ ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ሁኖ ዝም ብሎ መቀመጥ ሳይህን የሚሠራው ሥራ የሚገልጠው ነገር አለ።
መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሕይወት የሚገልጠው የዘላለም ሕይወትን ነው። የሰማዩን መንግሥት ነው። የማያልፈውን ነው። በአጠቃላይ መንፈስ ቅዱስ የሚገልጠው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው እርሱ ሲገለጥ ደግሞ በርግጥም አብም ይገለጣል። መንፈስ ቅዱስ አብን ይገልጣል ስንል የአብን የዘላለም ሐሳብ ማለት ነው። ይኼም ሐሳቡ በልጁ የመስቀል ስራ የጀመረው፤ መንፈሱን በመላክ እየሠራ ያለው እንዲሁም በልጁ ዳግመኛ መገለጥ የሚጠቀልለውን የዘላለሙን ሐሰብ ማለት ነው።
❖ዘመኑን ማወቅ፦
(ሮሜ 13:11-14)
"ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤" (ሮሜ 13:11-13)
ሰላም ለእናንተ ይሁን። ጳውሎስ በወንጌል ስለተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ በሚያወራበት በሮሜ መልዕክት ውስጥ ሰው እንዴት እንደሚጸድቅ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ጽድቅ በተለያየ አቅጣጫ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ዘግቧል። በዚህ በመረጥነው ክፍልም ዘመንን ስለማወቅ ይነግረናል። እኛም በሚከተሉት ሁለት ንዑስ ርዕስ ከፍለን እንመለከታለን።
ዘመንን ማወቅ ታላቅ ጥበብ ነው። ዘመንን ማወቅ ጥቅም እንደነበረው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ይነግረናል። ለምሳሌ ዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ከሆነ በኋላ እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ሁለት መቶ ከይሳኮር ልጆች አለቆች ነበሩ። (1ዜና 12:32።)
መቼም ዘመኑ የተገለባበጠበት፥ ዘመኑንም ማስተዋል የተሳነው ክርስቲያን እንደዚህ ዘመን የበዛ አይመስልም።
ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ ዘመኑን እወቁ የሚለን ከእኛ አንጻር ነው። ዘመኑ ለእኛ ለአማኞች ምንድነው? ዘመኑስ ምን ዓይነት ነው? ይኼን ያላስተዋለ አማኝ ብዙ ነገሩን ይስታል። እግዚአብሔር አብ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሳ በልጁ ወንጌል ለጠራን በክርስቶስ የመስቀል ሥራ አምነን ለዳንን ለእኛ ለአማኞች ዘመኑ ምንድነው? ዘመኑን ማወቅ ካለብን በእርግጥም ለእኛ ለአማኞች ዘመኑ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ሰዓት ነው ይለናል።
ከእንቅልፍ መነሳት ማለት ምንድነው?
ይኼን ለማብራራት ጳውሎስ እንዲህ ይለናል። "ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል"።
በእርግጥ ከእንቅልፍ የመነሻ ጊዜ በአሁኑ የሰለጠነው ዓለም የተለወጠ ቢሆንም ያኔ እዚያ መልክቱ የተጻፈበትን ዘመን ስንመረምር ሰዎች ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ከሌሉቱ 10:30 ጀምሮ እስከ 11:30 ባለው ውስጥ እንደሆነ ታሪካዊ ዳራዎች ያመለክታሉ። በእርግጥ አሁንም ራቅ ወዳሉ የገጠር የሃገራችን ክፍሎች ስንሄድ ሰዎች ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ከላይ በጠቀስኩት የሰዓት ክልል ውስጥ ነው።
ይኼ ከእንቅልፍ የመነሻ ጊዜ የእኛን ከጨለማ ማለትም ከኃጢአት ባርነት ወጥተን አሁን በእምነት በክርስቶስ ድነን ያለንበትን ጊዜ ይወክላል። አዎ! አሁን በክርስቶስ አምነን ከዚያ ከጨለማ ከሌሊቱ ጊዜ ወጥተናል።
2. ለምንድነው ዘመኑን እንድናውቅ የተፈለገው?
ጳውሎስ ለምንድነው ዘመኑን እንዲያውቁ ወይም እንድናውቅ የፈለገው ለሚለው ጥያቄ መልሱ ለዘመኑ እንደሚገባ እንድንኖር ነው። ዘመኑን አውቀናል እርሱም ከእንቅልፍ መነሻ ነው።
እኛም ሌሊቱ(በክርስቶስ ከማመናችን በፊት የነበረው ጊዜ) አልፎ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ጊዜ ላይ ነን። "ቀኑ" ማለትም የክርስቶስን ምጻት ከፊት ለፊታችን ቀርቧል። ታዲያ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር ልንለብስ ይገባል።