Sunday, January 17, 2016

❖መልካም እድል

መልካም ዕድል

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሲመላለስ ራሱን የሚያስጠጋበት ጎጆ፣ የሚጸልይበት ልዩ ስፍራ አልነበረውም፡፡ በየጫካው ማደርና መጸለይ ልማዱ ነበር፡፡ ስለ እኛ ሲል የመረጠው ድህነት ልክ አልነበረውም፡፡ እኛ ከሰው ማነስ ያስጨንቀናለ፤ እርሱ ግን ከሰማይ አእዋፋት ከምድር ቀበሮች ያነሰ ኑሮ ኖሯል /ማቴ. 8፡20/፡፡  እርሱ ሞቱ ብቻ ሳይሆን ኑሮውም ቤዛችን ነበር፡፡ ስለ እኛ ድሃ ካልሆነ እኛ በመለኮት ብልጥግና መሞላት አንችልም፡፡ አብዛኛዎቹ የአደባባይ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ ነበሩ፡፡ በራቸውን ከፍተው የሚያስተናግዱት ግን ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ ጥቂቶች መካከል ማርታና ማርያም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

      “ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው” /ሉቃ. 10፡38/፡፡

 እርሱ በመንደራችን ያልፋል፣ ወደ ቤታችን የሚገባው ግን ስንከፍትለት ብቻ ነው፡፡ በመንደራችን ለማለፍ አያስፈቅድም፡፡ ወደ ቤታችን ለመግባት ግን ፈቃዳችንን ይጠይቃል፡፡ ወዳጅን የምንቀበለው በሌላ ቤት ሳይሆን በራሳችን ቤት ነው፡፡ መቀበል በርን መክፈት፣ ጓዳን ማሳየት፣ ማስተናገድ ነው፡፡ ፈሪሳዊው ስምዖን ጌታን እቤቱ ተቀብሎታል፡፡ ግን ቤቱ የተቀበለው ታዋቂ የሆነውን ጌታ በመጋበዝ ለዝነኛነት ነው፡፡ ስለዚህ በቤቱ ጋብዞ ምንም አላደረገለትም፡፡ ለአንድ ተራ እንግዳ የሚቀርበውን ነገር እንኳ አላደረገለትም፡፡ ያቺ ኃጢአተኛ ሴት ግን ያለ ቤቷ ጌታን አስተናገደችው፡፡ ቤቱ የስምዖን ነው፡፡ በዕንባዋና በሽቱዋ ግን እግሩን ያጠበችው ኃጢአተኛዋ ሴት ናት፡፡ ስምዖን ቤቱን ያቺ ሴት ራሷን አቀረበች፡፡ ስምዖን ጋብዞ ታዘበው ያቺ ሴት ግን ኃጢአቷን ተናዘዘችለት /ሉቃ. 7፡36-50/፡፡ እርሱ የሚከብረው በሳሎናችን ሳይሆን በልባችን ነው፡፡ ማርታ ለጌታ በሯም ልቧም ክፍት ነበረ፡፡ ከፍትፍቱ ፊቱ እንዲሉ ፍትፍቱም ፊቱም ሁሉም አልቀረባትም፡፡

ይህች ማርታ፡- “ማርያም የምትባል እህት ነበረቻት፣ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች” /ሉቃ. 10፡39/፡፡ ማርያም ምንም እንኳ ጌታ ትልቅ እንግዳዋ ቢሆንም ለጌታ ከመስጠቷ በፊት ከእርሱ መቀበልን ፈልጋለች፡፡ ከምትሰጠው የሚሰጣት በልጦባት እግሩ ሥር ተቀምጣ ነበር፡፡ ለጌታ አደባባዩም ሆነ ቤቱ ሁሉም ለእርሱ ቃሉን ማወጂያ ነው፡፡ አገልግሎቱ ባለበት ቦታና ጊዜ ሁሉ ይቀጥል ነበር እንጂ በጊዜና በቦታ የተገደበ አልነበረም፡፡ ማርያም የቃሉን መጽናናት ትፈልግ ነበር፡፡ ያለ ቃሉ ሕይወት እንደሌላት ታውቅ ነበር፡፡ ትላንትን ለመርሳት ዛሬን ለመጋፈጥ፣ ነገን ለመናፈቅ ቃሉን ትሻ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የትላንት ካሣ፣ የዛሬ አቅም፣ የነገ ተስፋ ነው፡፡

“ማርታ ግን አገልግሎት ስለበዛባት ባከነች፤ ቀርባም፡- ጌታ ሆይ፣ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አያገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት” አለችው፡፡ማርታ ለጌታና ለደቀ መዛሙርቱ ማዕድ ለማቅረብ ከፍ ዝቅ ትል ነበር፡፡ ቃሉ ግን አልተቻትም፡፡ አገልግሎት እንደ ነበር ይናገራል፡፡ አገልግሎት አገልጋዮችን መደገፍም ነው፡፡ ለሚያስተምሩት ማዕድ ማሰናዳትም አገልግሎት ነው፡፡ አገልግሎት መስበክ፣ መዘመር ብቻ አይደለም፡፡ የማይታይ ደጀን መሆንም አገልግሎት ነው፡፡ ማርታ ግን ብቻዋን ባከነች፡፡ በየዓይነቱ ምግቡን ለማቅረብ ስትጣደፍ ጊዜውና አቅሟ አልበቃ አላት፡፡ ማርያም ግን በቤቷ እንግዳ ሆና ታየቻት፤ ስለዚህ ማርያምን ጌታ ጋ ከሰሰቻት፡፡ በብዙ አገልግሎት መድከም መልካም ቢሆንም ካልተጠነቀቁ ግን ከሳሽ ያደርጋል፡፡ የሌሎችን አለማገልገል ያሳያል፡፡ ይህንን ሐሜትም ለጌታ እንድንናገር ያደርጋል፡፡ ማገልገል የሌሎችን አለማገልገል ካሳየ ፍቅር አልባ ያደርጋል፡፡ ጌታንም፡- “አይገድህምን?” አለችው፡፡ ኤልያስ ብቻዬን ቀረሁ እንዳለ ጉዳዩ ወደ ጌታ መጣ፡፡ አገልግሎት ውጤታማ የሚሆነው ሲጠባበቁ አይደለም፡፡ የቻሉትን በጸጋ ድጋፍ ተወጥቶ ማለፍ ነው፡፡ ፉክክርና መጠባበቅ ካለ አገልግሎት አይጓዝም፡፡ እግዚአብሔር በአንድ ሙሴ አንድ ሚሊየን ሕዝብን ነጻ አውጥቷል፡፡ አንድ የቆረጠ እልፍ ሥራ ይሠራል፡፡



ጌታ ለማርታ አዘነላት፡፡ ማርታ ይህን ቃል ስትናገር ጉባዔው ተፈቷል፡፡ የሚማሩት ትምህርቱ ተቋርጦባቸዋል፡፡ ስንካሰስ ጉባዔ ይፈታል፡፡ ምእመናን ይጎዳሉ፡፡ ምግብ ለማቅረብ ጠርተናቸው ነገር ተመጋቢ ሆነው ይታመማሉ፡፡ አዎ የማዕድ አገልግሎት የቃሉን አገልግሎት እንዳያደናቅፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያት ሰባት ዲያቆናትን የሾሙበት ምሥጢር ይህ ነው /የሐዋ. 6፡2/፡፡ ዛሬም በአሠራር ተይዘን ለማገልገል ጊዜ እንዳናጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ጌታ ማርታን፡- “ማርታ፣ ማርታ በብዙ ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፣ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” /ሉቃ.10፤41-42/

 ማርታ ጭንቀቷ ለምሳ ብቻ አይደለም፡፡ ጭንቀቷ ለዓመት ቀለብ ይመስላል፡፡ ጉዳዩ ትንሽ ጭንቀቷ ግን ትልቅ ነበር፡፡ በርግጥም የሚያስፈልገው ምን ያህል ነው? አሁን የሚያስፈልገውስ ምንድነው? የሚያስፈልገን ብዙ ወዳጅ ብዙ ንብረት አይደለም፡፡ ጥቂት ነገር ነው፡፡ ሕይወትን በዕለት ብንኖር የሚያስፈልገው ጥቂት ነው፡፡ መጨነቅ፣ መታወክ፣ መበጥበጥ፣ መተራመስ፣ እንቅልፍ ማጣት ለምንድነው? ብዙ ብንሰበስብ ብዙ አንበላም፡፡ ብዙ ሰው ብናውቅም ብዙ ወዳጅ አይደለም፡፡ ብዙ ብንወልድም ጠቃሚው አንድ ነው፡፡ ብዙ ብናውቅም አንዱን ለመፈጸም ነው የምንታገለው፡፡ የሚያስፈልገው አንድ ወይም ጥቂት ነው፡፡

 ቤታችን ላስገባናቸው ወዳጆቻችንና የትዳር አጋሮቻችን ብዙ ለማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ ወደ ቤታችን የመጡት ግን በመጀመሪያ እኛን ለማግኘት ነው፡፡ እኛን የሚተካ፣ ፍቅራችንን የሚበልጥ ግብዣ የለም፡፡ ጥቂቱ ነገር በፍቅር ብዙ ነው፡፡ እኛ ግን የምንታወከው በብዙ ነው፡፡ ላስደስት ስንል እንደክማለን፡፡ ስንደሰት ግን እናስደስታለን፡፡

 ልብ አድርጉ! ጌታ ማርታን አልነቀፈም፡፡ የማርታ አገልግሎትም ያስፈልጋል፡፡ ማዕድ ግን ሁሉን አይተካም፡፡ ለአገልጋዮች ጠብ እርግፍ የሚሉ ቃሉን ግን መስማት አይችሉም፡፡ ቤታቸውን ለእግዚአብሔር ሰዎች ለቀዋል በዚህ ብቻም ረክተው ተቀምጠዋል፡፡“ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም” ያ መልካም ዕድል ከጌታ እግር ሥር ተቀምጦ ቃሉን መማር ነው፡፡ ዕድል ሁሉ ፈልጎን የሚመጣ ነው፣ ይህኛው ዕድል ግን የምንመርጠው ነው፡፡ በዓለም ላይ ካሉት ድንቅ ገጠመኞች አንዱ ቃሉን ማግኘት ነው፡፡ አንዳንድ ጸጋዎች ይወሰዳሉ፡፡ ሰውዬው ስለ በደለ ሳይሆን ጊዜ አላቸው፡፡ “ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ” ይላልና /1ቆሮ. 13፡8/፡፡ ቃሉን የመስማት ዕድል ግን ለሚያከበሩት የማይወሰድ ዕድል ነው፡፡ እኛስ ይህንን ዕድል መርጠናል ወይስ በአጋጣሚ ነው ቃሉን የምንሰማው? በቤታችንስ ቃሉን እንሰማለን? ቃሉንስ እንደ ትልቅ ዕድል ቆጥረነዋል? በክብሩ እንድንይዘው እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

Monday, January 11, 2016

❖ ብዙ ሃይል፦

❖ ብዙ ኃይል
‹‹በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፤ የኃጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው።››
(ምሳ. 15÷6)፡፡

         በሰው ልጆች አኗኗር ውስጥ ኃይል እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በኃይል እጦትና እጥረት ሰዎች ያለ መብራት በጨለማ ይሄዳሉ፤ ያልበሰለ በጥሬው ይበላሉ፡፡ ሰዎች በአቅም ማነስ ምክንያት ለተግባር ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ኃይል የማይገባበት የኑሮ ክፍል የለም፡፡ ብዙ ነገሮች በብዙ ኃይል ጭምር የሚተገበሩ ናቸው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በመንፈሳዊው ዓለም ስላለው ከፍተኛ ኃይል ይነግረናል፡፡ ጠቢቡ በዘመኑ ያስተዋለውን ባካፈለበት በዚህ ክፍል ላይ ጻድቅ ቤት ውስጥ ብዙ ኃይል እንዳለ ሲነግረን፤ በኃጢአተኛ መዝገብ ውስጥ ግን ሁከት አለ ይለናል፡፡

        ጠቢቡ ጻድቅና ኃጥእን፤ ቤትና መዝገብን፤ ኃይልና ሁከትን እነዚህን ሁለት ነገሮች ከሰው አንፃር በንጽጽር አቅርቦልናል፡፡ 
ጽድቅ የሚለው አገላለጽ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ያገኘ እውነተኛ ማንነትን ሲያሳይ፤ 
ኃጥእ የሚለው አገላለጽ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ጸብ ውስጥ ያለና መንገድ የሳተ  ማንነትን ያመላክተናል፡፡ ቤት ልንኖርበትና ልንጠለልበት ያለንበትን ክልል ሲያሳይ፤ መዝገብ አንድ ሰው የሚሰበስበውን የሚያኖርበትን ስፍራ ያመለክተናል፡፡ ብዙ ኃይል የሚለው አገላለጽ ጽድቅ የሚለውን አዎንታዊ ቃል ተከትሎ የመጣ እንደ መሆኑ በዚያው መንገድ የምንመለከተው ብርቱ ነገር ሲሆን፤ ሁከት ደግሞ የደፈረሰ ያልጠራ፤ ሰላም የሌለበትን ነገር ያስረዳናል፡፡

    በቀደመው ኪዳን ‹‹ጽድቅና ኃጢአት›› መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ የምናስተውልበት፤ ውጤቱንም በግልጥ የምናይበት ሆኖ ከቀረበልን ነገር ዋናው ‹‹ኃይል›› ነው፡፡ ምድሪቱ ላይ ሰዎች በብዙ ነገራቸው ላይ ኃይልን አብዝተው ይሻሉ፡፡ አቅም ያጣንባቸው ነገሮች ሁሉ አንዳች ኃይልን ለመናፈቅ በቂ ምክንያት ነው፡፡ በዙሪያችን ብዙ የአቅም ማነሶችን እናስተውላለን፡፡ በጤና በኩል፤ በመብል በኩል፤ በሰላም በኩል፤ በደስታ በኩል ወገኖች በጥያቄ ተሞልተው ልብ እንላለን፡፡ ሰዎች መፍትሔን ይሻሉ፡፡ በሰለለና በዛለባቸው ነገር ላይም ምላሽን ይናፍቃሉ፡፡

        በምንኖርበት ዓለምና በሥጋ ለባሽ ላይ ሰዎች መደገፋቸው፤ የሚያልፈውንም ክንድ ማድረጋቸው ከሥጋት ወደ በለጠ ፍርሃት ውስጥ እየጨመራቸው ተጨንቀዋል፡፡ ዳሩ ግን በመዝሙር እንዲህ ተጽፎአል፤ ‹‹እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት። ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ።›› /መዝ. 65÷3/፡፡ ቀና ብልን የምናየው ሰማይ፤ ዝቅ ብለን የረገጥነው ምድር እንደ መጎናጸፊያ እስኪጠቀለል ድረስ ጠላት ዲያቢሎስና መልእክተኞቹ የሚዋሹበት ብዙ ኃይል አለ፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ኃይል ነው፡፡ በሌላ ስፍራ መዝሙረኛው ‹‹ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ›› /መዝ 117፣14/ ይላል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፡፡

        እግዚአብሔር ያለን ብዙ ኃይል ነው፡፡ ምድሪቱ ላይ ብዙ ገንዘብ፤ ብዙ ሥልጣን፤ ብዙ እውቀት፤ ብዙ ጦር፤ ብዙ ብልሃት እንዳላቸው የምናስባቸው ሁሉ ከኃይለኛው አምላካችን፤ ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ናቸው፡፡ ስለ አምላካችን ክንድ፡ ‹‹በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ›› / ዘፀ 15፣16/ ተብሎ ተጽፍአል፡፡ ማን እንደ እግዚአብሔር?

       በጌታ የተወደዳችሁ፤ በውስጣችን ላለው ዝለት፤ በዙሪያችን ለምናስተውለው ተስፋ መቁረጥ ‹‹በጻድቅ ቤት›› የተባለውን ልብ በሉ፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኛችሁ፤ አብርሃም በጸደቀበት በዚያው መንገድ ጽድቅን ያገኛችሁ፤ ያላችሁን አስተውሉ፡፡ በእናንተ ዘንድ ብዙ ኃይል አለ፡፡ ችግርን አልፎ፤ መከራን አልፎ፤ ሀዘንን አልፎ፤ መለያየትን አልፎ፤ በሽታን አልፎ የሚሠራ ኃይል፤ ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ የሆነ አሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ የማይቻል የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ ሰዎች በእጃቸው ሥራ፤ በአስተሳሰባቸው ብልሃት፤ በወገናቸው ትጋት በሚደገፉበት በዚህ የዘመን ማብቂያ እናንተ በእግዚአብሔር መተማመንን ልማድ አድርጉ፡፡

        ሰይጣን ዛሬም ይዋሻል፡፡ የዘመን ርዝማኔ ትምህርት እንደማይሆን ከሰይጣን በላይ አብነት የለም፡፡ እርሱ ውሸትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል /ዮሐ 8፣44/፡፡ በእግዚአብሔር ብዙ ኃይል ላይ ጠላት የማይቋረጥ ዘመቻን ከፍቷል፡፡ መጽናናትን ከእግዚአብሔር ስትሹ፤ ዕረፍትን ከሕያው አምላክ ስትናፍቁ፤ የጉዳዮቻችሁን መከናወን፤ የጉድለቶቻችሁን ሙላት ስትጠባበቁ ጠላት ዲያብሎስ ‹‹አይችልም››ን ወደ ጆሮአችሁ ይዞ ይመጣል፡፡ እርሱ ጌታ ባለ ብዙ ኃይል ነው፡፡ የጻድቅ ቤት በዚህ የተሞላ ነው፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች የገዛ መንገዳቸው ያመጣውን ነገር ሳይሆን የእግዚአብሔርን ኃይልና ማዳን በኑሮአቸው የሚለማመዱ ናቸው፡፡

       እናንተ የምታምኑ ሆይ፤ በኃጥእ መዝገብ አትቅኑ፡፡ በዚህ የሠሩባት የማታ ማታ ሕይወትን ከስረዋልና፡፡ እግዚአብሔር የሁከት አምላክ አይደለም፡፡ የአመፀኞች መዝገብ ለዚህ ዓለም ስርዓትና መሻት እንደ ማጣፈጫ ቢሆንም፤ የክርስቶስ የሆኑቱ ከዚህ እድል ፈንታ የላቸውም፡፡ በእግዚአብሔር ጽድቅ ጥላ ስር የሆኑ ሁሉ ባለ ብዙ ኃይል ናቸው፡፡ እርሱም የዘላለም አምላክ እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህንን ኃይል ከብዙ የኑሮአችን ክፍል ጋር አያይዘን ልናየው እንችላለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ክንድ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ በሉዓላዊነት ሲገለጥ እናስተውላለን፡፡ እኔ ግን ለዚህ ዝግጅት ማየት የፈለኩት ከማዳኑ ጋር የተያያዘውን ነው፡፡

       ‹‹በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና›› /ሮሜ 1፣16/፡፡ እግዚአብሔር ኃይሉን ለማዳን መጠቀሙ ድንቅ ነው፡፡ በዙሪያችን ሰዎች በአቅማቸው ያላቸውን ነገር ለጥፋትና ለሌሎች ውድቀት ሲያውሉት ማየት ልብን ያሳዝናል፡፡ ለነገሩ ትንሽ ያላት እንቅልፍ የላትም አይደል ነገሩ፡፡ ከእግዚአብሔር አንፃር የዚህ ዓለም ቀዳሚ ባለጠጋም የተረቱ ሰለባ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይችላል፡፡ ተስፋችሁን ሊቀጥል፤ ከገባችሁበት መከራ ሊያወጣ ይችላል፡፡ የመረረባችሁን ሊያጣፍጠው፤ የጠመመባችሁን ሊያቀናው እርሱ ይችላል፡፡ ከሞትና ከሲዖል ኃይል የሚያድን ኃይል እርሱ ጌታ ነው፡፡ ሰዎች ባላቸው ብዙ ነገር ሊወጡ የማችሉት ብርቱ ጠላት ዲያቢሎስ የዚህ ዓለም ገዥ በሆነበት ሁኔታ፤ እግዚአብሔር ብቻ ያድናል፡፡

        ስለማናፍርበት ነገር ማውራት እንዴት ደስ ያሰኛል፡፡ ዓለሙ በብዙ የሚያሳፍር ወሬና የቅሌት ኑሮ የተጨናነቀ ነው፡፡ ወንጌላችን በዚህ የጨለማ ድቅድቅ መሐል ብርሃን፤ አልጫ በሆነው ነገር ላይ ጨው ነው፡፡ እናንተ እውነተኞች ሆይ፤ ከፀሐይ በታች የዚህ ዓለም ስርዓት ትኩረትና ከፍታ የሚሰጠው ነገር እናንተ ቤት የለ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ልብ በሉ፤ ሰዎች ሁሉ የሚድኑበት፤ መቃብርን አልፈው ሕያው የሚሆኑበት፤ ከከንቱ ኑሮ የሚገላገሉበት፤ ከሞተ ሥራ ሕሊናቸው የሚነፃበት ኃይል በእናንተ ውስጥ አለ፡፡ ይህንን ብልሃት አያገኘውም፡፡ ሀብትና ንብረት አይገዛውም፡፡ ሥልጣንና ጉልበት አስሮ አያመጣውም፡፡ የልብ እምነት ግን ከዚህ ብዙ ኃይል ጋር ያስተሳስራል፡፡

       ወዳጆቼ፤ ይህንን ዓለም በምን ታሸንፉታላችሁ፡፡ ትብታብና ሰንሰለቱ፤ ጭፍራና ሠራዊቱ ርኩስ መንፈስ የሆነ፤ ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም የሚተጋውን ክፉ እንዴት ትሻገሩታላችሁ? እንዲህ ካለው ባላጋራ መዳን በሌላ በማንም የለም /ሐዋ 4፣12/፡፡ ‹‹እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።›› (1 ቆሮ. 1÷23-24)፡፡

                 ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!

   

Saturday, July 11, 2015

❖የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አገልግሎት፦


 ክርስቶስ ደም አገልግሎት

                     ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ”(1ዮሐ.1÷9)

                     በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን የሚታይ(ዕብ.9÷24)

                    በቅዱስ ደሙ ኃጢአታችንን የሻረ(ትምህርተ ኅቡዐት)

                   መዓዛው የጣፈጠ ንጹህ መስዋዕት”(ቅዱስ ቄርሎስ)

      ፊተኛው የደም አገልግሎት ኃጢአትን ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ ፣ከማንጻት ይልቅ እያዳፈነ የኃጢአት ፍህም በየማለዳው አዲስ እየሆነ ምድርን በእድፈትና በርኩሰት ስላካለለ ኢየሱስ ከዕድፈትና ከርኩሰት ፣ከፊት መጨማደድም ንጹህ የሆነች (ኤፌ.5÷27) ቤተ  ክርስቲያንን ያዘጋጅና ይሞሽር ዘንድ ወደደ፡፡ስለዚህም በገዛ ደሙ የዋጃትንና ያነጻትን ቤተ ክርስቲያን እርሱ በገዛ ፈቃዱ መሠረተልን፡፡ (ሐዋ.20÷28)
     ቤተ ክርስቲያን የደሙን አገልግሎት ፍጹም ታምናለች፡፡የደመቀችበት ፣ያጌጠችበት ለሙሽራው ኢየሱስ የተሞሸረችበትና ሙሽሪት ሆና የቀረበችበት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡የደሙን አገልግሎት የማታምን ቤተ ክርስቲያንና የማያምን አማኝ ፈጽሞ ክርስቶሳዊ ክርስቲያን መሆን አይችልም፡፡ የኢየሱስ የደሙ አገልግሎት ዛሬም ያላቋረጠ፤ የደሙን መስዋዕት አቅራቢው ሊቀ ካህን ክርስቶስ ኢየሱስም የማይለወጥና የዘላለም ክህነት ያለው ነው፡፡(ዕብ.7÷24)
        አስተውሉ!!! የታረደው በግ ዛሬም በዙፋኑ ህያው ሆኖ አለ፤ በእግዚአብሔር አሁን ውስጥ ሆኖም በዙፋኑ የሚታየው እንደታረደ ሆኖ ነው፡፡ በዳግም ምጽአቱ የሚመጣው እንኳ የታረደበትን ችንካር እያሳየ ነው፡፡(ራዕ.5÷9፤ማቴ.24÷30፤ራዕ.1÷7)፡፡ በጉ ሊታረድ ግድ የሆነው ምንም ኃጢአት የሌለበት ሆኖ ለኃጢአተኛው አዳም ሊሞት በሥላሴ ዘንድ ምክሩ ስለፀና ነው፡፡ የሞተውንና የወደቀውን ሊያነሳ የማይሞተው ሞቶ ፤ እንደታረደም ሆኖ ታየ፡፡
            
             ❖ የታረደው በግ ደም ዋና አገልግሎት፦

1- ደሙ አዲሱን ኪዳንና ህያውን መንገድ መርቆ የከፈተ ነው፡፡

      ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለደም አልተመረቀም፡፡ጌታ ደካማዋንና ሙት የነበረችዋን የኩነኔ አገልግሎት መንገዷን መርቆ የከፈተውና ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስቱ ሊገባ ድፍረት የሆነው በእግዚብሔር ፊት የሚያቀርበውና በእጁ የያዘው ደም ነው፡፡ ያለደም ወደቅድስት ፈጽሞ መግባት አይቻልም፡፡
    በአንድ ሐገር የሚሰሩ ታላላቅ የመንገድ ሥራዎች የምረቃ ሥርዐታቸው የሚከናወነው በሐገሪቱ ዋና ባዕለሥልጣን(መሪ) ነው፡፡ ዋናው ባዕለሥልጣን የምረቃዋን ሪባን ገመድ ቆርጦ በመንገዱ ከተራመደበት በኋላ ሌሎች እርሱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ከዚያ ቀንም ጀምሮ መንገዱ ለሁሉም አካላት ክፍት ይሆናል፡፡
    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በር ሆኖ በደሙ መርቆ የከፈተልን አዲስና ህያው መንገድ እርሱ የምህረቱ ዓመት አዲስ ኪዳን ነው፡፡ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት … ”አለን፡፡(ዕብ.10÷19)፡፡ምንም እንኳ ኃጢአተኞችና በደለኞች ብንሆን በልጁ በኩል የምንገባው ወደዘላለም ክብሩ፤የምንወርሰውም የዘላለም ህይወትን ነው፡፡(ቆላ.2÷13 ዮሐ.3÷15) ሕይወታችን የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት በዚያን ጊዜ እኛም ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር እንገለጣለን፡፡(ቆላ.3÷41ተሰ.4÷17)
       “ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእኛ አይደለም … ”(ኤፌ.2÷8)፡፡ያለእርሱ ጸጋና ያለእርሱ መንገድነት ወደአብ መድረስ አይቻልም፡፡(ዮሐ.14÷6)፡፡ቅዱሳን ሁሉ የሄዱበት መንገድ እርሱ መርቆ በከፈተው ቅዱስና ህያው መንገድ ነው፡፡ወደአብ የሚያደርሰው ይህ መንገድ የማያሳስት መንገድ ነው፡፡
    በደሙ ተመርቆ ከተከፈተውም መንገድ በቀር ሌላ ወደህይወትና ወደእረፍት የሚያደርስ መንገድ ፈጽሞ የለም፡፡ደሙ የከፈተልን መንገድ የህይወትና የልምላሜ መንገድ ነው፡፡ክርስትና የሚለው አዲስ መንገድ ላይ መጓዝ የጀመርነው ክርስቶስ መርቆ ከከፈተው በኋላ ነው፡፡አዲሱም ኪዳን ላያረጅ ፍጹም የታተመበት ህትመት ህያውና ለዘላለም ትኩስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፡፡

2- ደሙ ቤዛችን ነው፡፡

     “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን
      እርሱም የበደላችን ስርየት።”(ኤፌ.1÷7)

     “ በኋለኛው ዘመን የምክርህን አበጋዝ መድኀኒት ቤዛ የሚሆን ልጅህን ሰደድህልን፡፡
     (የሐዋርያት ቅዳሴ)                    
   
    "ስለፍጥረትህ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በእግዚአብሔር ቸርነት በሥጋ ሞተ"
               (ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ ምዕ.70 .1 ቁጥር 10)
      “ከአዳም ጀምሮ እስከዛሬ ከተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ማንም ማን ሊያድነን አልቻለም፤ ከእግዚአብሔር ቃል በቀር በሰው ቢሆን አለኝታችን ከንቱ እንዳይሆን የባህርይ አምላክ እርሱ ሰው ኾነ እንጂ፡፡ከሰው ወገን የሚሾም ሊቀ ካህናት ሁሉ በመጽሐፍ እንደተነገረ ስለሰው ይሾማል፤ስለዚህም ጌታ ከወዲያ ዓለም ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከሰው ወገን ተወለደ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ፤ አምላክ በመሆኑ ያድነን ዘንድ ሰው በመሆኑም ለእኛ ቤዛ ሆኖ ይሞትልን ዘንድ፡፡(ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ምዕ.58 .49-50)

        “ቤዛየሚለውን ቃልአዳኝ፣መድኃኒት፡፡ዋቢ፣ሃላፊ፣መድህን፡፡በካሳ መልክ ወይም እንደምትክ ፣እንደመለወጫ፣እንደመያዣ የሚቀርብ…” ብሎ ይፈታዋል፡፡(ኣማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡(2001)፤አዲስ አበባ፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ ቤት፡፡ገጽ.243) በሌላ ትርጉም ደግሞየተያዘን ወይም የተወሰደን ነገር ለማስመለስ የሚከፈል ዋጋ ፣ካሳ ፣ለውጥ … ” ነው ይለናል፡፡(የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፡፡የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9 እትም፣አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡)
        በሞቱ ለሚያምንበት ሁሉ ቤዛ ሆኖ በእግረ አጋንንት ፤በሞት ይገዛ የነበረውን አዳምንና ዘሩን በሞቱ ካሳ ክሶ ፤ደሙን አፍስሶ በመከራና በሐዘኑ ሁሉ ምትክ ሆኖ ወደቀደመና ህያው ክብሩ የመለሰው ሥጋ የለበሰው ክርስቶስ ነው፡፡ጌታ ነፍሱን በቤዛነቱ ላመኑበት ለብዙዎች ራሱን የሰጠ ነው፡፡(ማር.10÷451ጢሞ.2÷5)
     
         ኢትዮጲያውያን ገበሬዎች በልዩ የሥነ መለኰት የእምነት እውቀታቸውቤዛነት አምላክነት   ያሻዋልይላሉ፡፡ክርስቶስን ቤዛችን ነው የምንለው የእኛ ምትክ ሆኖ ከታላቅ የፍቅሩ ባዕለጠግነቱ የተነሳ እኛን ተገብቶ፤ዕዳችንን ሁሉ ከፍሎ በመቤዥ በደሙ ነጻ ስላወጣን ነው፡፡ቤዛነት የክርስቶስ ብቻ ነው፤ከፍጡር ወገን ቤዛ መሆን የሚቻለው ማንም የለም፡፡ዋጋ የሚከፍል አካል እርሱ ቀድሞ ከዕዳ ነጻ መሆን መቻል አለበት፤ከክርስቶስም በቀር ከአዳም በደልና ዕድፈት ነጻ ሆኖ ዕዳችንን ከፍሎ መድኃኒትና ቤዛ የሆነን የለም፡፡እርሱ በንጹህ ደሙ ለበደለኛው የሰው ዘር ሁሉ ዋጋ የሆነና በዋጋውም ገዝቶን የዋጀን ነው፡፡ቤዛነት አምላክነት ያሻዋልየሚባለው ከአምላክ በቀር ፍጹምና ንጹህ ቤዛ ፈጽሞ ስለሌለ ነው፡፡ምክንያቱም ሰው የማይበድል አይደለምና፤በተጨማሪምጻድቅ አንድስ እንኳ የለም” (2ዜና.6÷36   ሮሜ.3÷11)በማለት ቃሉ ስለደመደመ ንጹህና ፍጹም ቤዛ መሆን የሚቻለው ከብርሐን የተገኘው ብርሐን፣ከእውነተኛው አምላክ የተገኘው እውነተኛው አምላክ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋን የነሳውና ዘመዳችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡እርሱ አምላክ የሆነ ሰው፤ሰው የሆነ አምላክ ነውና፡፡
         
    ክርስቶስ የመጣበት ዋና ዓላማውነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥእንደሆነ ተገልጧል፡፡(ማቴ.20÷28፤ማር.10÷45) አዎ! ከአምላክ በቀር ሰው ስለራሱ ነፍስ  ቤዛ መሆን(መስጠት) አይችልም፡፡(ማቴ.16÷26)፡፡ ቤዛነት ምትክ ሆኖ ከእስራት ነጻ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋ ከሆነ፤ኢየሱስ ብዙዎች ስለሆንነው ስለሁላችን ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት ነጻ ሊያወጣን ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ፡፡አምላክ ለፍጡር እንጂ ፍጡር ለፍጡር ቤዛ መሆን ከቶ አይቻለውም፡፡ኃጢአት ላረከሰው የሰው ልጅ ኃጢአትና ዕድፍ ፈጽሞ የሌለበት የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ያስፈለገው ለዚህ ነው፡፡
         ስለዚህ የኃጢአት ክስ ያለበት የትኛውም አዳማዊ ፍጡር መዳን የሚችለው በአንዱ ቤዛ በተሰቀለው መድኃኒት ማመን ሲቻለው ብቻ ነው፡፡እስከዛሬ ለበደለ ባርያ የሞተ ጌታ ወይም አንድ የስስት ልጁን የሰጠ ጌታ አልሰማንም፡፡ጌታ አብ ግን ልጁን እስኪሰጠን በእንዲሁ ፍቅር ወደደን(ዮሐ.3÷16) ወልድም ገና ደካሞች ሳለን ቤዛ ሆኖ በሞቱ ሊታረቀንና ሊያስታርቀን ወደእኛ መጣ፡፡(ሮሜ፣5÷6)እኛ ወደእርሱ የሚያቀርብ ምንም ነገር ስለሌለንና የህይወት በራችንን በራሳችን ላይ ስለዘጋን እርሱ ወደእኛ የተዘጋውን በር ከፍቶ መጥቶ ተቤዠን፡፡ፍቅሩ ከህሊና መረዳት ከማስተዋል ይረቃል!!! ተመርቆ የተከፈተውን ህያውና አዲስ መንገድ የሚያስተዋውቀውና የሞቱን ነገር በልባችን የሚስለውም መንፈስ ቅዱስ ድንቅና ፍቅር ነው፡፡ አዎ! ኢየሱስ መስዋዕት ሆኖ ባፈሰሰልን ደሙ ቤዛችን ሆነልን፡፡ከእርሱ በቀርም ማንም፤ምንም ቤዛ የለንም፡፡
                                         በቤዛችን እንዲህ ተወደናልና ደስ ይበለን፡፡