Friday, August 21, 2020

❖የክርስቶስ ራስነት:-

የክርስቶስ ራስነት:-

ራስ የሚለው ቃል በመፅሐፍ ቅዱስ ውሰጥ ያለው ትርጉም የነገሮች ዋና:የበላይ የሆነ:ከሁሉም ከፍ ያለ:ሁሉን ገዢ የሁሉ መሪ ማለት ነው።ታድያ ክርስቶስ ኢየሱስ የብዙ ነገር ዋናና የበላይ ነው።ይህን ስፍራ እንዲይዝ አሰቀድሞ መከራን መቀበል ቀጥሎም ወደ ክብሩ መግባት ነበረበት።

የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህን እውነት በአፅንዖት ተናግረዋል።ሉቃ 24:26 1ኛ ጴጥ 1:11 ይህን እውነት ሐዋርያት መሰክረዋል።ዕብ 2:18 12:2 13:12-13። እግዚአብሔር አንድያ ልጁ ኢየሱስን ያለ ልክ ከፍ ከፍ አድርጎታል።ፊሊ 2:9 በግርማዊ ዙፋን ቀኝም ጌታም ክርስቶስም አድርጎ የነገሮች ሁሉ ራስ አድርጎታል።የሐዋ 2:36 ይህ እንደ መደርደሪያ ካልን ኢየሱስ ራስ የሆነባቸው ጉዳዬች በጥቂቱ እንመልከት፦

1ኛ,ክርስቶስ ኢየሱስ የቤተክርትያን ራስ ነው።

ኤፌ 1:21-22"ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተክርስትያን ሰጠው።ክርስቶስ ሲሰቀል ሰይጣንና ዓለም ያላቸውን ኃይልና ብርታት አሳይተዋል።ያለ የሌለ ኃይል በመጠቀም ክርስቶስ ወደ መስቀለ ሞት ገፍተውታል።ይህን እንዲሆን የአይሁድ ሃይማኖትና የሮም የመንግስት ሰርዓት ተጠቅማል።ክርስቶስ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ስለ ፅድቅና የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ስለ ኃጢአት ሞተ።እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት በማስነሳት የኃይሉ ብርታት አሳዬ።ከጌትነት ከአለቅነት ከኃይላትና በዓለም ከሚጠራ ስም ሁሉ በላይ እግዚአብሔር አደረገው።ለአካሉ ማለትም ለቤተክርትያንም ራስ እንደሆን ሰጠው።ቤተክርስትያን አንድ ራስ ነው ያላት እርሱም ክርስቶስ ብቻ ነው።የቤተክርስትያን head office ክርስቶስ ነው።

2ኛ,ከዚህ የቤተክርስትያን ጉዳይ ጋር ክርስቶስ የማዕዘን ድንጋይ ራስ ነው።

ኤፌ 2:20"በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኅል።የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።አማኞች ሕያዋን ድንጋይ ናቸው።1ኛ ጴጥ 2:5 እነዚህ አማኞች በክርስቶስ የማዕዘን ድንጋይ ራስነት ይገጣጠማሉ።ክርስቶስ በአማኞች ላይ የበላይ ዋና የሆነ ብቻ ሳይሆን አማኞች ሚገጣጠሙበት ነው።በእርሱ ተገጣጥመው ቅዱስ መቅደስ ይሆናሉ።

3ኛ,ክርስቶስ የህይወት ራስ።

የሐዋ 3:14-15"እናንተ ግን,,,የሕይወት ራስ ገደላችሁት እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው።ሰው በበደል በኃጢአት ሙት ነው።ኤፌ 2:1ነገር ግን ሰው ህይወትን ለማግኘት ወደ ክርስቶስ መምጣት አለበት።ዮሐ 17:2 ስለዚህ በስሙ ለሚያምኑ ኢየሱስ ህይወትን ይሰጣቸዋል።ምክንያቱም የህይወት ራስ ነው።ዮሐ 3:36 1ኛ ዮሐ 5:12

4ኛ,ክርስቶስ የመዳን ራስ ነው።

ዕብ 2:10"ብዙ ልጆች ወደ ክብር ያመጣ ዘንድ የመዳናቸውንም ራስ በመከራው ይፈፅም ዘንድ ለእርሱ ተገብቶታልና።ሰው መዳን የሚችል ከፍጡር ዘንድ አንድም የለም።መዳን በማንም በሌላ የለም።የሐዋ 4:12 በእርሱ(በክርስቶስ) የሚመጡትን ፈፅሞ ያድናቸዋል።ዕብ 7:23 ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ሊያድን መጣ።1ኛ ጢም 1:15 ስለዚህ መዳንን በተመለከተ ክርስቶስ ብቻ ይመለከተዋል።ክርስቶስ የመዳናችን ዋና ነው።

5ኛ,ክርስቶስ የእምነታችን ራስ ነው።

ዕብ 12:3"የእምነታችን ራስና ፈፃሚውን ኢየሱስን ተመልከቱ።አንድ እምነት አለ።እርሱም ለቅዱሳን የተሰጠ ነው።ይሁዳ 1:3 የዚህ እምነት የበላይ ኢየሱስ ነው።ብዙ ሃይማኖቶች ራስ አላቸው። መፅሐፍ ግን ኢየሱስ የእምነታችን ራስ ነው ይለናል።አዎን ኢየሱስ ብቻ የሃይማኖት ራስ ነው።

❖በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር መስደድ:-

በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር መስደድ!
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች ምዕ. 2)
----------
6፤ እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።
7፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ።
በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ውስጥ ብቻ በፍልስፍና እና የሰው ስርዓት በሆነ ሃይማኖት እየተናወጡ ለነበሩት ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ድንቅ ምክር ተለግሷቸዋል። በክርስቶስ መመላለስ፣ በክርስቶስ ሥር መስደድ እና በክርስቶስ መታነፅ ወይም መገንባት ሶስቱ ቁልፍ ነገሮች ናቸው።
ለሁለቱ ነገሮች መሰረት ወደሆነው ቃል እንምጣ። ተክል፣ ሁሉ ነገሩ ያለው ሥሩ ላይ ነው። ሥሩ ለተክሉ ዋና ነገር ከሆነ ደግሞ በተመቻቸ ቦታ ሊተከል ይገባዋል። ጥሩ አፈር እና ውሃ ያለበት ቦታ ላይ ትንሽ የነበረው ሥር በሚገርም ሁኔታ አድጐ ይሰፋል። ተክሉም ያድጋል። ገና ሲተከል አካባቢ ህፃናት እንኳ በቀላሉ ሊጎዱት ይችላሉ። ከጊዜያት በኃላ ግን ጐልማሳም እንኳ አይደፍረውም።
እንዲህ ነው። እኛን በተመለከተ የተተከልንበት ቦታ ፍፁም፣ አስፈላጊው ሁሉ የሚገኝበት ውብ ስፍራ ነው። በዚያ የሕይወት ውሃ ምንጭ ሳያቋርጥ ይፈልቃል። ከእኛ የሚጠበቀው ዝም ብሎ የሚልቀውን ምንጭ እየጠጡ ሥርን ማስፋት ብቻ ነው።
ክርስቶስ የሕይወት ውሃ ምንጭ ነው። በእርሱ ዘንድ ሁሉም አለ። እርሱ ሁሉም ነው።
" ክርስቶስ ሁሉ ነው"
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3:11)
ነፍስ ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ ከክርስቶስ እየተመገበች፣ ከክርስቶስ ጋር በቃሉ በኩል ጊዜ እየሰጠች ስታሳልፍ፣ በክርስቶስ ውስጥ ስር ትሰድዳለች። ዕለት ዕለት ከቃሉ ጋር በፅሎት ስትጣበቅ ሥሯ ይሰፋል።
> የዚህም ውጤት ያች ነፍስ በሕይወቷ የምትመራው በክርስቶስ ሆኖ በእርሱ ትመላለሳለች፣ ደግሞ በዛው በክርስቶስ እየተገነባች በፍሬ ትታጀባለች።
" በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።"
(የዮሐንስ ወንጌል 15:5)
ያኔ ሙቀት ቢመጣ ድርቅ ማለትም የሰው ፍልስፍና ሆነ የሰው ሐይማኖት ሊያናውጧት እና ሊያሰጓት አይችሉም።
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕ. 17)
----------
7፤ በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8፤ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።

Sunday, June 28, 2020

❖ቤተክርስቲያን፦

ቤተክርስቲያን ማለት ምን ማለት ነው?
በግሪክኛ ቋንቋ ቤተክርስቲያን"አቅሌስያ"ተብላ ተጠርታለች።ትርጉሙም"የተጠሩ "ማለት ነው።ይህንን ትርጉም በተለያዩ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተለይም በቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እናገኘዋለን፦
 " በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤"
    (1ኛ ወደ ቆሮ1:2)።
ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ አስራ ሁለት ቅዱሳን ሐዋርያትን ጠራ።ከእነዚህ ጋር የተጠሩ 36 ቅዱሳት አንስትን ጨምሮ 72 አርድእት ነበሩ።ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚህ ቤተክርስቲያንን መሠረተ።

ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች የእግዚአብሔር ተቋም ናት። የተመሠረተችውም ለአንድ ዓላማ ነው።የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ለመሆን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የምድር አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀመዛሙርቱን እንዲህ ብሎአል፦
 "ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ።" (የሐዋ ሥራ 1:8)። 

ይህ ዓላማ ቤተክርስቲያን ለምን እዚህ ምድር ላይ እንደምትኖር በሚገባ ያሳያል። የቤተክርስቲያን ሠሪዋም መሠረቷም እንዲሁም ማእዘንዋም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።"አንተ ዓለት ነህ ዓለት የተባለ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው ብሎ የመሰከረው መስክርነት ነው።  በአንተ ዓለትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።" (የማቴ 16:18)" 
ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።"
  (1ኛ  ቆሮ 3:11)
"በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ፤፤(ኤፌ2:20)።

ቤተክርስቲያን እስከ አሁን ድረስ በነቢያትና ሐዋርያት ትሠራለች፤ ሠራተኞችም ነቢያትና ሐዋርያት ናቸው። ነገር ግን እያንዳንዱ እንዴት እንደሚሠራ መጠንቀቅ ይኖርበታል።

" የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ።"(1ኛ  ቆሮ 3:10)።

ቤተክርስቲያንን ለማነጽ የሁሉም የቤተክርስቲያን አካል ደርሻ ነው። ነገር ግን በፊተ አውራሪነት የሚመግቡ መሪዎች አሉ።" እግዚአብሔርም በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛም ነቢያትን፥ ሦስተኛም አስተማሪዎችን፥ ቀጥሎም ተአምራት ማድረግን፥ ቀጥሎም የመፈወስን ስጦታ፥ እርዳታንም፥ አገዛዝንም፥ የልዩ ልዩ ዓይነት ልሳኖችንም አድርጎአል።"(1ኛ ቆሮ 12:28)።
እነዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ሥራ ሥራቸውን መሥራት አለበቸው።" አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ።" (1ኛቆሮ3:5) 

ቤተክርስቲያንና ዓላማዋ፦

1.ሁሉንም እየስተማሩ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ማዳረግ፦


እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። (ማቴ 28፥19-20 ) ይህ ካልሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተክርስቲያንና ከአገለጋዮቹ ጋር አይኖርም

2. ለእግዚአብሔር ቃልና ለክርስቲያናዊ ስነምግባር ግዴለሽ አለመሆን፦

በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። (ራዕ 3፥16 ) ይህ ደንታ ቢስነት ቤተክርስቲያንን አለማዊ ያደርጋታል .ከእግዚአብሔር መንግሥትም ያወጣታል ቤተክርስቲያን በምድር ያለሽ የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና

3. በምድር የምታበራ መቅረዝ ናት፦

በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። (ራዕ 1፥13) መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። የቤተክርስቲያን መኖር በጨለማው ዓለም እንድታበራ ነው የተቃጠለ አንቦል ለምንም አይጠቅም ። ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ብርሃን ያለማቋረጥ ማብራት ይኖርባታል

4. የዲብሎስን ሥራ ማፍርስ፦

 ይህም ዘርኘነት፤ ጥላቻ፤ ርኩሰት በአጠቃላይ ከእግዚአብሔር ቅዱስ ባህርይ የማይሠማሙትን ሁሉ ማስወገድ ዓላማዋና ተልኮዋ ነው።
ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። (1ኛ ዮሐ 3፥9)

5. ፍቅርን መግለጽ፦

ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። (1ኛ ዮሐ 4 ፡7-12)
 ፍቅር የሌላት ቤትክርስቲያንና ፍቅር የሌለው ክርስቲያን እግዚአብሔር በውስጡ የለም ያለፍቅር ክርስትና የለም።

Tuesday, June 23, 2020

❖ የማይገባ ደግነት:-

ይቅርታ በደልን ለመርሳት የሚደረግ ሙከራ፣ ወይም
ሰውዬውን መርሳት አይደለም፡፡ ይቅርታ ለበደለኛው
የማይገባውን መስጠት ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት ምሥጢሩ ይህ የማይገባን ደግነት ነው፡፡
ለሰማያዊው አባት ያለንን ፍቅር ልንገልጥ የምንችለው እርሱ የፈጠራቸውን ሰዎች በመውደድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያሳየንን
ፍቅር እኛም ለጎረቤታችን ማሳየት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር
የጠፋውን ዓለም በእኛ ውስጥ ሆኖ ሊወደው ይፈልጋል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስደናቂ ይቅርታ ስላሳዩ ሰዎች
እናነባለን፡፡ ከእነርሱም ሦስቱን በዚህ ክፍል ለማየት
መርጠናቸዋል፡፡ እነርሱም አዳም፣ ዮሴፍና የእስጢፋኖስ
ቤተሰቦች ናቸው፡፡
አዳም በሚወዳትና በሚያዳምጣት ሚስቱ አማካይነት
በኃጢአት ወደቀ፡፡ ጸጋው ተገፈፈ፣ ነጻነት የሌለው ሰው ሆነ፣
ፍርሃትና ሽሽት ከማያመልጠው ማንነት ጋር ገጠመው፡፡
ምክንያትም ሳያስጥለው የዘላለም ሞት ተፈረደበት፡፡ በሥጋ ሞት
ላይ የነፍስ ሞት፣ ወደ መቃብር በመውረድ ላይ ወደ ሲኦል
መውረድ ተፈረደበት፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ እግዚአብሔር ተለየው፡፡
አዳም የሚስቱን ዓይን ላለማየት ቢወስን፣ ቢሸሻትና እርሷን
ይቅር ለማለት ቢፈተን ማንም አይፈርድበትም፡፡ እርሱ ግን ፍጹም
ይቅር ባይ ነበርና ያን የማይገባ ደግነት አሳያት፡፡ ሞትን
ላመጣችበት ሴት «አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፣
የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና» (ዘፍ3፡20)፡፡
ሔዋን አሁን ሕያው አይደለችም፡፡ ሙታንም ከእርሷ
ይወጣሉ፡፡ ነገር ግን አዳም የአሁኑን ሳይሆን የተስፋዋን ፍጻሜ
አየ፡፡ የሆነችውን ሳይሆን ልትሆን ያላትን አሰበ፡፡ ስለዚህ የሕያዋን
እናት አላት፡፡ ለወደቁት ሰዎች የመነሣት ጉልበታቸው ዛሬም
በእነርሱ ላይ ያለን እምነት ነው፡፡ ምን እንደሚሆኑ ያለን ተስፋ
አንድ ቀን ራእያቸው ይሆናል፡፡ «የወደቁ ሰዎች የተዘረጉ እጆችን
ይፈልጋሉ፡፡»
ጋብቻ እንደ አዳምና እንደ ሔዋን ነው፡፡ ውድቀት ያልፈታው
ትዳር የእነዚህ ወገኖች ትዳር ነው፡፡ ዛሬ ብዙዎች ትዳራቸውን
ይቅር ማለት አልቻሉም፡፡ ስለ ንብረታቸውና ስለ ልጆቻቸው እያዘኑ
ይኖራሉ፡፡ ዘይቱ እንዳለቀበት መቅረዝ ፍቅር አልቆባቸው
ጨልመዋል፡፡ ተዋደው የገቡ ሳይሆን በፍርድ ቤት ትእዛዝ
የተጣመሩ እስኪመስል መሸካከም አልቻሉም፡፡ ብዙ ጊዜም
አንዳቸው በመንፈስ ጭንቀት ሲያዙ የጠባይ ለውጥ እየመሰለ
ይበልጥ ይከፋፋሉ፡፡ የትዳር ጓደኛ መነጫነጭ፣አለመርካት፣
የትዳር ውሳኔውን መርገም፣ ልጆቹንና የትዳር ጓደኛውን ማየት
ሲጠላ . . . የጠባይ ለውጥ ብቻ ላይሆን ይችላልና መመርመሩ
መልካም ነው፡፡ በትዳር ውስጥ ትልቁ ጉዳትም ስህተትን
የሚፈልግ ዓይን በመሆኑ ከዚህ መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ በየዕለቱ
ከምንሞላው ኃይል አንዱ ፍቅር ነውና ስንጎድልና ማፍቀር
ሲያቅተን በጸጋው ዙፋን ፊት ወድቀን ሙላኝ ልንል ይገባል፡፡

ሌላው የተደነቀ የይቅርታ ሕይወት የሚታየው በዮሴፍ
ላይ ነው፡፡ ዮሴፍ ከወንድሞቹ ይልቅ አባቱ ይወደው ነበር፡፡ ምንም
ባይበድላቸው መወደድም የመጠላት ምክንያት ይሆናልና
ወንድሞቹ ጠሉት (ዘፍ. 37፡4)፡፡ ዮሴፍ ሕልሙን በነገራቸው ጊዜ
ደግሞ ወደፊት ይሆናል የሚሉትን ነገር ሲያስቡ በቅንዓት አበዱ፡፡
በበረሃ እየተቅበዘበዘ ሲፈልጋቸው እነርሱ ግን ሊገድሉት
ተማክረው በጉድጓድ ጣሉት፡፡ የግብጽ ነጋዴዎች ሲያልፉ
አይተውም በሃያ ብር ሸጡት፡፡ በጉስቁልና ከሕልሙ ያራቁት
መስሏቸው ይበልጥ ወደ ሕልሙ ትርጓሜ ገፉት፡፡ «መገፋት ጥሩ
ነው እምብዛም ሳይወድቁ፣ የተገፉት ቆመው የገፉት ወደቁ፤»
ዮሴፍም ገና በልጅነቱ ብርቱ መከራ ደረሰበት፣ በባዕድ
አገር በአገልጋይነትና በእስር ተንገላታ፡፡ በኃጢአት አልተባበርም
ማለት በዓለም ያስቀጣልና አሥራ ሦስት ዓመት ተቀጣ፡፡ ነገር
ግን ይህ ጠባብ መንገድ ወደ ሰፊው ጎዳና የሚያወጣ ነበር፡፡
ዮሴፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ራእይ የጠላትነት ብዛት
ሊያሸንፈው አልቻለም፡፡ እንደውም ጠላቶቹ ወደ ራእዩ እንዲደርስ
ያቻኩሉት ነበር ፡፡ አንድ ሰው «እግዚአብሔር ታላቅ በረከት
እንዳዘጋጀልኝ ቀድሞ የሚነግረኝ ሰይጣን ነው፡፡ ይተነኳኮለኛል»
ብሏል፡፡
ዮሴፍ የግብፅ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ፡፡
እግዚአብሔር ያለው አይቀርምና ወንድሞቹ ሰገዱለት፡፡ በከነዓን
ምድር ረሃብ እያሯሯጠ ወደ ግብጽ አመጣቸው፡፡ ዮሴፍ
አወቃቸው እነርሱ ግን አላወቁትም፡፡ ራሱን በገለጠላቸው ጊዜ
በጭንቀት ተናጡ፡፡ በልባቸው ሌላውን ከመበደል ራስ መበደል
ይሻላል ሳይሉ አልቀሩም፡፡ የዮሴፍን ፊቱን ማየት አልቻሉም፡፡
እርሱ ግን አልበደላቸውምና ፊታቸውን አየ፡፡ መልካምነት
ሥልጣን ካልሆነን በቀር የማንንም ፊቱን ማየት አይቻለንም፡፡
ዮሴፍ አሁን ሊበቀላቸው ይችላል፡፡ እነርሱም ፈርተው
ነበር፡፡ ዮሴፍ ግን እግዚአብሔር ክፉውን ለውጦ ለመልካም
እንዳደረገው ስለተረዳ ይቅር አላቸው፡፡ ምንም ክፉ
ቢያደርጉበትም ወደ ተስፋው እንዳቀረቡት ተረዳ፡፡ እግዚአብሔር
አንዳንዴ እምነታችን እንዲያድግ በክፉ ሰዎች መካከል
ያስቀምጠናል፡፡ እንድንጠነክር ታዝዘው መከራ ያደርሱብናል፡፡
ታዲያ ከንጉሡ ታዝዞ ሎሌው አርባ ቢገርፈን እንቀየመዋለን?
ከሰዎች ጋር መታገል ከንቱ ነው፡፡
ዮሴፍ መበቀል እየቻለ አልተበቀላቸውም፡፡ በቀል
የእግዚአብሔር፣ ይቅርታ የእርሱ መሆኑን ተረዳ
(ዘፍ.50፣19-20)፡፡ ሕጋዊ መንግሥት ባለበት አገር የበደለንን
ሰው ራሳችን ብንቀጣ መንግሥትን እንደካድን ይቆጠራል፡፡
እንዲሁም በጽድቅ የሚፈርድ አምላክ እያለ እኛ ተበቃይ ብንሆን
እግዚአብሐርን ክደነዋል ማለት ነው (ሮሜ.12፣19-21)፡፡ አዎ
የእግዚአብሔር ሰዎች በእግዚአብሔር ቦታ ሆነው የነገሮችን
አካሄድ መለወጥ እንደማይችሉ ሲረዱ እግዚአብሔርም ለእነርሱ
ነገሮችን ወደ በጎ የሚለውጥ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ዮሴፍ ቢበቀል
ኖሮ ከእግዚአብሔር ጋር በተጣላና ያን ክብር ባላገኘ ነበር፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ እግዚአብሔር የአገር መሪዎችና ባለሥልጣናት
የይቅርታ ሰዎች እንዲሆኑለት ይፈልጋል፡፡ የበለጠ ኃላፊነትን
ለመሸከም እግዚአብሔር ይቅር ባዮችን ያጫል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናየው ሦስተኛው የይቅርታ
ሕይወት የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ያደረጉት ነው፡፡ ወጣቱ ሰማዕት
እስጢፋኖስ የሞተው በአሁኑ ጳውሎስና በግብረ አበሮቹ
በድንጋይ ተወግሮ ነው፡፡ እስጢፋኖስ ግን «ጌታ ሆይ፡ ይህን
ኃጢአት አትቊጠርባቸው» እያለ ጸለየላቸው፡፡ ይህንን ጸሎት
የጸለየው «የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም» ካየ በኋላ ነው
(የሐዋ.ሥራ.7፣55-60)፡፡ ክርስቶስን ስናይ ብቻ ልባችን
ለይቅርታ ይለዝባል፡፡ ከወጋሪዎቹ አንዱ ጳውሎስ የድሮው ሳውል
ክርስቲያን ሆነ፡፡ ጳውሎስ የእስጢፋኖስ የይቅርታ ጸሎት ልቡን
ነክቶታል፣ ወይም ልብን የሚነካ ጸጋ አምጥቶለታል፡፡
ይህ ጳውሎስ ያውም ለትምክሕት «የእስጢፋኖስንም
ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ ጨምሬ ሌላ አጥምቄ
እንደሆነ አላውቅም» (1ቆሮ.1፣16) ማለቱ ያስገርመናል፡፡ እኛ
ይቅር ብንል እንኳ ቤተሰብ በቶሎ ይቅር አይልም፡፡ ቤተሰብ
ስለልጅ መቀየም ጽድቅ ነው የሚመስለው፡፡ የእስጢፋኖስ
ቤተሰቦች ግን በልጃቸው ገዳይ በጳውሎስ እጅ መጠመቃቸው
የይቅርታን ጽኑነት ያሳየናል፡፡
እኛ ገንዘብ የካዱንን ይቅር ማለት ሲያቅተን አዳም
ገነትንና እግዚአብሔርን ያሳጣችውን ሔዋንን ይቅር አላት፡፡ ዮሴፍ
ልጅነቱን ለመከራ እቶን የዳረጉት ወንድሞቹን በበቀል ሳይሆን
በይቅርታ አሸነፋቸው፡፡ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ደም መላሽ
ቢሆኑ ኖሮ ጳውሎስን በመልእክቱ ዛሬ አናገኘውም ነበር፡፡ ይቅርታ
ለትውልድ የምናቆየው ውለታ ነው፡፡ በእርግጥም ይቅርታ
የማይገባንን በሰጠን በእግዚአብሔር ፊት ሰውዬው
የማይገባውን መስጠት ነው፡፡
                  *ይቅርታ*
       የይቅርታ ልብ ይስጠን!!!

Friday, June 19, 2020

❖የጌታ መልአክና ወንጌል፦

የጌታ መልአክና ወንጌል፦
የእግዚአብሔር መልአክ ሕይወት የሆነው ጌታ ለዓለም እንዲበሰር ተናገረ። 

የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና፦
ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው። (የሐዋ 5፡19፡20)
ምክንያቱም ሰው ሕይወት እንዲኖረው ይፈልጋል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። (ዮሐ 5፡24)

በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።

ቆርኔሌዎስን ከቅዱስ ጴጥሮስ ወንጌልን እንዲሰማ አዘዘው፦

ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት።ርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና፦ ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤እርሱ ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ዘንድ እንግድነት ተቀምጦአል፤ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል።

ይህ መልአክ ጴጥሮስ ስለዘዓለአለም ሕይወት እንደሚነገር ያውቃል።

በዘመን መጨረሻ የእግዚአብሔር መልአክ ወንጌልን ለዓለም ያውጃል፦

በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ።  (ራእይ14፥6 )

በጨረሻም ቢሆን እንኳ ሰው ሁሉ ሕይወትን እንዲያገኝ የእግዚአብሔር መልአክ ያውጃል የሰው ልጅ ለሚያገኝው የዘለአለም ሕይወት ያለቸውን ከፍታኛ ፍለጎት ያረጋግጣል እኛ ግን ለኛ የሆነውን ሕይወት ቦታ አልሰጠነውም ።

   

                የእግዚአብሄር ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!!

Sunday, June 7, 2020

❖መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ውኃ ወንዝ ነው፦

☞መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ውኃ ወንዝ ነው፦

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲስተምር፦
"በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ ይላል "ቅዱስ ወንጌል 

  (ዮሐ 7፥38)

❖  ይህን የተናገረው ለማን እንደሆነ ሲገልጽ፦

"ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ [ስላልተሰቀለ ማለት ነው] መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና" ብሏል። 

ወንዝ ሳያቋርጥ የሚፈስ ነው የመንፈስ ቅዱስ ፀጋና በረከትም ለሚቀበሉት ሁሉ ያለማቋረጥ ሲሰጥ ይኖራል። 


❖  ቅዱስ ጴጥሮስ በሃምስኛው ቀን ለደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ መውረዱን ሲያስረዳ፦


እግዚአብሔር ይላል፦ 

"በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ"።

     (የሐዋ 2፥17-18)

   ወንዝ የፈሰሰበት ሁሉ ይለመልማል ያፈራል። መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሁሉ በእግዚአብሔር ፀጋ ይለመልማል የእግዚአብሔር የሆነውን ያፈራል ። 

  ሕዝቅኤል የመንፈስ ቅዱስን ፀጋና በረከት ከመቅደሱ የሚፈስ የሕይወት ውኀ መሆኑን ገልጿል።

ከመቅደሱ የሚወጣ ዉሃ ወደ ምስራቅ ሲፈስ ይመለከታል፡፡ 

ሰውየው (የሚያሳየው መልአክ ማለት ነው) ገመዱን በእጁ ይዞ 1000 ክንድ ለካ፡፡ 

  በዉሃው ውስጥ አሻገረኘ ዉሃው እስከ ቁርጭምጭሚት ደረሰ።

   ሁለተኛ ሲሻገረው እስከ ጉልበት።

   ሶስተኛ እስከ ወገብ ።

  አራተኛ እጀግ ጥልቅና ሰፊ ወንዝ በመሆኑ ማንም ሊሻገረው የማይችል ወንዝ ሆነ፡፡ 


❖  ወንዙ የእግዚአብሔርን በረከትና ፀጋ ዘልዓለማዊ ሕይወትን ይገልጻል፡፡ 


  እስከ ቁርጭምጭሚት በዘመነ አበው የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ፣ 

  እስከ ጉልበት በዘመነ መሳፍንት የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ፣ 

  እስከ ወገብ በዘመነ ነቢያት የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ ደህንነት፣ 

  ማንም ሊሻገረው የማይችለው ዉሃ በጌታችን በኢየሱስ ክረስቶስ የተሰጠውን በረከትና ፀጋ ዘልዓለማዊ ሕይወት የሚገልጽ ነው፡፡


ማንም ሊሻገረው የማይችል ታላቅ ወንዝ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና የሚለውን ያረጋግጣል። 

  መሲህ የሕይወት ዉሃ መሆኑን ተናግሯል፡፡ 

  መንፈስ ቅዱስም የሕይወት ውሃ መሆኑን ተናግሯል። 

  በርሱ የሚያምን የሕይወት ዉሃ ከርሱ እንደሚመነጭ አስተምሯል፡፡ 

   በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።


❖  ዉሃው ወደ ምስራቅ ባሕር በገባ ጊዜ የምስራቁ ባሕር ሙት ባሕር ነው፡፡ ዉሃው ይፈወሳል። 

  ዉሃው የሚወክለው የረከሰውን ሕዝብ ሰለሆነ በመሲህ ያመነ ሁሉ ፈውስንና የዘልዓለም ሕይወትን ማግኘቱን ያረጋግጣል፡፡ 

   ዉሃው ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ በሕይወት የሚኖርበት መሆኑን ይናገራል፡፡ 

  ወንዙ በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል፡፡ 

ዉሃው የሚፈሰው እጅግ በበረሃማነት ወደሚታወቀው ወደ ይሁዳ ምድረበዳና ወደ ጨው ባሕር ነው፡፡ መራራው የጨው ባሕር የብዙ ዓሳዎችና ተንቃሳቃሽ ሕያዋን ፍጥረታት መኖርያ ይሆናል፡፡ ይህም የሆነው ጨዋማው ዉሃ በመቅደሱ ውሃ ስለተፈወሰ ነው፡፡ 

ረግረግና እቋሪው ግን ጨው እንደሆነ ይኖራል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑትን ይመለከታል፡፡ በወንዙ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ቅጠሉ የማይረግፍ ፍሬው ለሁልጊዜ የሚያፈራ አለ፡፡ ፍሬው ለመብል ቅጠሉ ለመድኀኒት የሕይወት ዛፍ ነው የሚወክለውም ዘልዓለማዊ ሕይወትን ነው፡፡

                                               (ሕዝቅኤል 47፥1-12)


                እግዚአብሄር ይክበር ይመስገን!!!

❖መንፈስ ቅዱስ፦

መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

፩. መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

  ☞ ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል ነው፡፡

  ☞ የማይጨበጥ፤የማይታይ አካል ያለው መንፈስ ነው፡፡

  ☞ የሰረፀው (የወጣው) ከአብ ነው።

  ☞ ከአብ እና ከወልድ ጋር እኩል ምስጋናና አምልኮ የሚገባው ነው። 

  ☞ እግዚአብሔር (አምላክ) ነው፡፡

  ☞ የአብ እና የወልድ እስትንፋስ (ሕይወት)ነው፡፡

  ☞ በነቢያትና በሐዋርያት አድሮ የተናገረ፥ሕይወትንም ያቀና : ምድርን ለክብሩ ያስጌጠ ነው፡፡

፪. የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ምን ምን ናቸው? 

   ርግብ፣ እሳት፣ ውኃ፣ ዘይትና ነፋስ ናቸው። 

☞  ርግብ የዋህ ናት፦ መንፈስ ቅዱስም የዋህና ቂም የማያውቅ ነው፡፡ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ መድረቁን  ያወጀች  የሰላም ምልክት ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ክርስቶስ ሲጠመቅ የኃጢአት ባሕር መድረቁን በርግብ ምሳሌ ወርዶ የሰበከ የሰላም ጌታ ነው።

☞  እሳት ያበስላል፦  መንፈስ ቅዱስም ሕፃን የሆነውን አእምሮ በጥበብ ያጎለምሳል፡፡ እሳት የከበረ ማዕድንን ከአፈር ይለያል፥ መንፈስ ቅዱስም አምኖ የከበረውን ፡ ካላመነው ይለያል፡፡

☞  ውኃ ያነፃል፥ መንፈስ ቅዱስ ይቀድሳል፡፡

☞  ነፋስ፣ ነፍስና መንፈስ የሚወጡበት የግሪክ ቃል ኒዩማ የሚል ሲሆን ከነፋስ- ነፍስ፤ ከነፍስ- መንፈስ ይረቃል። ነፋስ በእንቅስቃሴው እንደሚታወቅ መንፈስ ቅዱስም በሥራው ይታወቃል፡፡

❖  በብሉይ ኪዳን የመብራት ዘይት ነበረ፥ በየዕለቱ በመቅረዙ ይጨመራል፡፡ ይህ የመብራቱ አለመጥፋት የመንፈስ ቅዱስን መኖር ያመለክታል፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ ለቅርፅ አልባዋ መሬት ውበት ያፈሰሰ፥ ውኆችን ለፍጥረት ጥቅም የቀደሰ ጌታ ነው፡፡ "ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።" ኦሪት ዘፍጥረት 1:2።

❖  መንፈስ ቅዱስ መሳፍንትን በምስፍና፥ ነገሥታትን በንግሥና፥ ካህናትን በክህነት ጸጋ፥ ነቢያትን በሀብተ ትንቢት፥ ዘማርያንን በዝማሬ ጸጋ፥ ፈዋሾችን በሀብተ ፈውስ ......የሾመ...ጸጋ የሰጠና ጸጋን ያደላደለ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም የሆነላትን እንድትረዳ አደረባት፡፡ ድንግል ማርያም በድንግልና እንድትወልድ ሁሉን አስቻላት፡፡ በክርስቶስ አገልግሎት ነበረ፡፡ 

  ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት ተናግሯል፡፡

☞   "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።" የዮሐንስ ወንጌል 14:26

☞  "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።" ዮሐንስ 16:7-15::

☞   " ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤" የዮሐንስ 15:26።

☞  " ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" ዮሐንስ 14:15-16::

❖  በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአደራረጉ ምክንያት:- 

    ☞  የእውቀት መንፈስ፣ 

    ☞  የጥበብ መንፈስ፣ 

    ☞  የኃይል መንፈስ፣ 

    ☞  የእውነት መንፈስ፣ 

    ☞  የመገለጥ መንፈስ፣ ...ተብሎ ተጠርቷል፡፡ 

በክርስቶስ አገለግሎት የነበረው ሱታፌ እንዳለ ሆኖ በክርስቶስ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ ከላይ ባሉት ጥቅሶች አይተናል፡፡ በክርስቶስ ትምህርት አጽናኝ(ጰራቅሊጦስ)፣ የእውነት መንፈስ እና ሁሉን የሚነግር መምህር ተብሏል፡፡ የሚመጣው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ የሚመጣበት አላማ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የማያምኑትን ይወቅሳል፤ የዲያብሎስን መጣል ይናገራል፤ ጽድቅ ወደ አብ በሄደው በክርስቶስ እንደሆነ ይመሰክራል፤ የቤተክርስቲያንን እንቅስቃሴ ይመራል፤ ምእመናንን ያጽናናል፤ ለበጉ ሠርግ ያዘጋጃል፤ አገልጋዮችን ያሰማራል፡፡ 

❖  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም መጣ፤ በጽርሐ ጽዮን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተወለደችውን የክብርት ቤተክርስቲያን ልደት በእሳት ላንቃ በዓለም ቋንቋ አከበረ፡፡ ሐዋርያትን ለእውነት አስጨከነ፤ ምስጢር እና ብዙ ቋንቋዎች ገለጠላቸው፡፡ በጉዞቸው ሁሉ አብሮ ነበረ፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን አገለግሎት ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ነውና ክብር ለመንፈስ ቅዱስ!!

❖  ላመነ ሰው ጥምቀት የሚፈጸመው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ይህም የክርስቶስ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ 28:19:: በጥቅሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አይፈጽሙም፡፡ የምስጢራቱ አፈጻጸም ሥርዓት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ 

በመግቢያዬ እንደጻፍኩት ቤተክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ ጠንካራ አቋም አላት፦ "ማህየዊ በሚሆን በአንድ ጌታ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እርሱም ከአብ የሰረፀ ነው፡፡ በነቢያት እና በሐዋርያት ተናግሯል፡፡ ከአብ ከወልድ ጋር ምስጋና ይገባዋል።" ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ ፰.

መንፈስ ቅዱስ፦

☞  ሕይወት ሰጭ፤ ጥበብ ገላጭ መንፈስ ነው፡፡

☞  የጸጋ ምንጭ እና አደላዳይ ነው፡፡

☞  ለበጎ ሥራ ቀስቃሽ፤ከኃጢአት እንድንወጣ ወቃሽ ነው

☞  ልብን አይቶ የሚሾም፤ ትሁታንን የሚያከብር ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ኃይል ነው፡፡ ብርታት የሆነን እርሱ ነው፡፡ ስንደክም ያግዘናል፡፡ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል(ሮሜ 8:26-27)፥ እንዴት ማምለክ እንዳለብን ይመራናል፥ ከዚያ ጸሎታችንን ይሰማል፤ አምልኮችንን ይቀበላል፡፡

❖  የመንፈስ ቅዱስ ነገር ለፍጥረታዊው ሰው ሞኝነት ነው፡፡ "ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።" 1ቆሮንቶስ 2:14። የመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ በእምነት መንፈስ እንጂ በሥጋ አይመረመርም፡፡ የጰራቅሊጦስ የተቀበልነው ይህን የእውነት መንፈስ ነው፡፡ "እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።" 1ቆሮንቶስ 2:12።

❖  መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታዊ ሰው አይኖርም፡፡ እንዲያውም የክርስቶስ መንፈስ የሌለው የክርስቶስ ወገን አይደለም፡፡ "የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።" ሮሜ 8:9።

❖  ምክር፣ ጥበብ፣ ምስጢር፣ ትንቢት፣ ፈውስ፣ ዝማሬ፣ ሹመት፣ ኃይል .... ከመንፈስ ቅዱስ ይሰጣሉ፡፡ ደስታ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት፣ ትዕግስት፤ በጎነት፣ ቸርነትና ሰላም የመንፈስ ፍሬ ናቸው፡፡ ገላ 5:23:: 

❖  መንፈስ ቅዱስ ከምንተነፍሰው አየር በላይ ያስፈልገናል፡፡ በሥራችን ዐመፃ የመንፈስ ቅዱስን አሠራር ልንቃወም እንችላለን፡፡ "መንፈስን አታጥፉ፤" 1ተሰሎንቄ 5:19። ንጉሥ ዳዊት በበደለ ጊዜ ይህ አጋዥ፣ አስተማሪ፣ መሪ እና አጽናኝ መንፈስ እንዳይወስድበት ለመነ፡፡ "ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።" መዝሙረ ዳዊት 51:11።

❖  መንፈስ ቅዱስ ከተለየን ሕይወት፣ ሰላም፣ ዕረፍት፣ መንፈሳዊነት ... የንስሐ ጸጸት...ይለዩናል፡፡ ስለዚህ "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።" ኤፌ 4:30-32:: የሥጋ ሥራ ከመንፈስ አላማ ያወጣል፡፡ የሥጋ አሠራር መንፈስ ቅዱስን ይቃወማል፡፡ ደስታ የሰጠን ሀዘን ሊቀበል አይችልም፡፡ ባናከብረው ደስታ የምናጣው እኛ ነን፡፡ " ለአሠራሩ እንመች፡፡ በኖህ ዘመን ርግቧ በመጀመሪያው ጉዞዋ ማረፊያ አጥታ እንደተንከራተተች መንፈስ ቅዱስም ለአሠራሩ የሚመች ሰው አጥቶ በዙሪያችን አለ።" ለአሠራሩ እንመች፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሰን፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ አንብቡ ፥ ዘምሩ፡፡ 

 ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይገባል!!!