Saturday, June 18, 2016

❖መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

መንፈስ ቅዱስ ማነው?


፩. መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?
  ☞ ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል ነው፡፡
  ☞ የማይጨበጥ፤የማይታይ አካል ያለው መንፈስ ነው፡፡
  ☞ የሰረፀው (የወጣው) ከአብ ነው።
  ☞ ከአብ ከወልድ ጋር እኩል ምስጋና አምልኮ ይገባዋል
  ☞ እግዚአብሔር (አምላክ) ነው፡፡
  ☞ የአብ የወልድ እስትንፋስ (ሕይወት)ነው፡፡
  ☞ በነቢያትና በሐዋርያት አድሮ የተናገረ፥ሕይወትንም ያቀና : ምድርን ለክብሩ ያስጌጠ ነው፡፡

፪. የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ምን ምን ናቸው? ርግብ፣ እሳት፣ ውኃ፣ ዘይትና ነፋስ ናቸው። 
☞  ርግብ የዋህ ናት፡ መንፈስ ቅዱስም የዋህና ቂም የማያውቅ ነው፡፡ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ መድረቁን  ያወጀች  የሰላም ምልክት ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ክርስቶስ ሲጠመቅ የኃጢአት ባሕር መድረቁን በርግብ ምሳሌ ወርዶ የሰበከ የሰላም ጌታ ነው።

☞  እሳት ያበስላል፡ መንፈስ ቅዱስ ሕፃን የሆነውን አእምሮ በጥበብ ያጎለምሳል፡፡ እሳት የከበረ ማዕድንን ከአፈር ይለያል፥ መንፈስ ቅዱስም አምኖ የከበረውን ፡ ካላመነው ይለያል፡፡

☞  ውኃ ያነፃል፥ መንፈስ ቅዱስ ይቀድሳል፡፡

☞  ነፋስ፣ ነፍስና መንፈስ የሚወጡበት የግሪክ ቃል ኒዩማ የሚል ሲሆን ከነፋስ- ነፍስ፤ ከነፍስ- መንፈስ ይረቃል። ነፋስ በእንቅስቃሴው እንደሚታወቅ መንፈስ ቅዱስም በሥራው ይታወቃል፡፡

❖  በብሉይ ኪዳን የመብራት ዘይት ነበረ፥ በየዕለቱ በመቅረዙ ይጨመራል፡፡ ይህ የመብራቱ አለመጥፋት የመንፈስ ቅዱስን መኖር ያመለክታል፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ ለቅርፅ አልባዋ መሬት ውበት ያፈሰሰ፥ ውኆችን ለፍጥረት ጥቅም የቀደሰ ጌታ ነው፡፡ "ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።" ኦሪት ዘፍጥረት 1:2።

❖  መንፈስ ቅዱስ መሳፍንትን በምስፍና፥ ነገሥታትን በንግሥና፥ ካህናትን በክህነት ጸጋ፥ ነቢያትን በሀብተ ትንቢት፥ ዘማርያንን በዝማሬ ጸጋ፥ ፈዋሾችን በሀብተ ፈውስ ......የሾመ...ጸጋ የሰጠና ጸጋን ያደላደለ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም የሆነላትን እንድትረዳ አደረባት፡፡ ድንግል ማርያም በድንግልና እንድትወልድ ሁሉን አስቻላት፡፡ በክርስቶስ አገልግሎት ነበረ፡፡ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት ተናግሯል፡፡

☞   "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።" የዮሐንስ ወንጌል 14:26

☞  "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።" ዮሐንስ 16:7-15::

☞   " ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤" የዮሐንስ 15:26።

☞  " ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" ዮሐንስ 14:15-16::

❖  በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአደራረጉ ምክንያት የእውቀት መንፈስ፣ የጥበብ መንፈስ፣ የኃይል መንፈስ፣ የእውነት መንፈስ፣ የመገለጥ መንፈስ፣ ...ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በክርስቶስ አገለግሎት የነበረው ሱታፌ እንዳለ ሆኖ በክርስቶስ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ ከላይ ባሉት ጥቅሶች አይተናል፡፡ በክርስቶስ ትምህርት አጽናኝ(ጰራቅሊጦስ)፣ የእውነት መንፈስ እና ሁሉን የሚነግር መምህር ተብሏል፡፡ የሚመጣው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ የሚመጣበት አላማ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የማያምኑትን ይወቅሳል፤ የዲያብሎስን መጣል ይናገራል፤ ጽድቅ ወደ አብ በሄደው በክርስቶስ እንደሆነ ይመሰክራል፤ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ይመራል፤ ምእመናንን ያጽናናል፤ ለበጉ ሠርግ ያዘጋጃል፤ አገልጋዮችን ያሰማራል፡፡ 

❖  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም መጣ፤ በጽርሐ ጽዮን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተወለደችውን የክብርት ቤተክርስቲያን ልደት በእሳት ላንቃ በዓለም ቋንቋ አከበረ፡፡ ሐዋርያትን ለእውነት አስጨከነ፤ ምስጢር እና ብዙ ቋንቋዎች ገለጠላቸው፡፡ በጉዞቸው ሁሉ አብሮ ነበረ፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን አገለግሎት ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ነውና ክብር ለመንፈስ ቅዱስ!!

❖  ላመነ ሰው ጥምቀት የሚፈጸመው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ይህም የክርስቶስ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ 28:19:: በጥቅሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አይፈጽሙም፡፡ የምስጢራቱ አፈጻጸም ሥርዓት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ 

በመግቢያዬ እንደጻፍኩት ቤተክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ ጠንካራ አቋም አላት፦ "ማህየዊ በሚሆን በአንድ ጌታ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እርሱም ከአብ የሰረፀ ነው፡፡ በነቢያት እና በሐዋርያት ተናግሯል፡፡ ከአብ ከወልድ ጋር ምስጋና ይገባዋል።" ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ ፰.

መንፈስ ቅዱስ፦
☞  ሕይወት ሰጭ፤ ጥበብ ገላጭ መንፈስ ነው፡፡
☞  የጸጋ ምንጭ እና አደላዳይ ነው፡፡
☞  ለበጎ ሥራ ቀስቃሽ፤ከኃጢአት እንድንወጣ ወቃሽ ነው
☞  ልብን አይቶ የሚሾም፤ ትሁታንን የሚያከብር ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ኃይል ነው፡፡ ብርታት የሆነን እርሱ ነው፡፡ ስንደክም ያግዘናል፡፡ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል(ሮሜ 8:26-27)፥ እንዴት ማምለክ እንዳለብን ይመራናል፥ ከዚያ ጸሎታችንን ይሰማል፤ አምልኮችንን ይቀበላል፡፡

❖  የመንፈስ ቅዱስ ነገር ለፍጥረታዊው ሰው ሞኝነት ነው፡፡ "ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።" 1ቆሮንቶስ 2:14። የመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ በእምነት መንፈስ እንጂ በሥጋ አይመረመርም፡፡ የጰራቅሊጦስ የተቀበልነው ይህን የእውነት መንፈስ ነው፡፡ "እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።" 1ቆሮንቶስ 2:12።

❖  መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታዊ ሰው አይኖርም፡፡ እንዲያውም የክርስቶስ መንፈስ የሌለው የክርስቶስ ወገን አይደለም፡፡ "የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።" ሮሜ 8:9።

❖  ምክር፣ ጥበብ፣ ምስጢር፣ ትንቢት፣ ፈውስ፣ ዝማሬ፣ ሹመት፣ ኃይል .... ከመንፈስ ቅዱስ ይሰጣሉ፡፡ ደስታ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት፣ ትዕግስት፤ በጎነት፣ ቸርነትና ሰላም የመንፈስ ፍሬ ናቸው፡፡ ገላ 5:23:: 

❖  መንፈስ ቅዱስ ከምንተነፍሰው አየር በላይ ያስፈልገናል፡፡ በሥራችን ዐመፃ የመንፈስ ቅዱስን አሠራር ልንቃወም እንችላለን፡፡ "መንፈስን አታጥፉ፤" 1ተሰሎንቄ 5:19። ንጉሥ ዳዊት በበደለ ጊዜ ይህ አጋዥ፣ አስተማሪ፣ መሪ እና አጽናኝ መንፈስ እንዳይወስድበት ለመነ፡፡ "ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።" መዝሙረ ዳዊት 51:11።

❖  መንፈስ ቅዱስ ከተለየን ሕይወት፣ ሰላም፣ ዕረፍት፣ መንፈሳዊነት ... የንስሐ ጸጸት...ይለዩናል፡፡ ስለዚህ "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።" ኤፌ 4:30-32:: የሥጋ ሥራ ከመንፈስ አላማ ያወጣል፡፡ የሥጋ አሠራር መንፈስ ቅዱስን ይቃወማል፡፡ ደስታ የሰጠን ሀዘን ሊቀበል አይችልም፡፡ ባናከብረው ደስታ የምናጣው እኛ ነን፡፡ " ለአሠራሩ እንመች፡፡ በኖህ ዘመን ርግቧ በመጀመሪያው ጉዞዋ ማረፊያ አጥታ እንደተንከራተተች መንፈስ ቅዱስም ለአሠራሩ የሚመች ሰው አጥቶ በዙሪያችን አለ።" ለአሠራሩ እንመች፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሰን፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ አንብቡ ፥ ዘምሩ፡፡ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይገባል!!! 

❖በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተፈጸሙ 6 ተግባራት

፨፨፨ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የተፈጸሙ 6 ተግባራት
1. በሞቱ ከኃጢታችንና ከጥፋተኝነታችን ስርየት አገኘን

~ዮሐ.129 "በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ"። 

~ኢሣ.535 "እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። 6 እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ"።

~ዕብ.926 "እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል"።

2. በሞቱ የእግዚያብሔር ቁጣ ተወገደልን

~ሮሜ.325 "እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ 26 ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው"። 

~ዕብ. 217 "ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። 18 እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና"።

~1ኛዩሐ.410 "ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም"።

3. በሞቱ ከእግዚያብሔር ጋር አስታረቀን 

~ሮሜ.510 "ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤11 ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን"።

~1ኛቆሮ.517 "ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 18 ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤19 እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ"።

4. በሞቱ ከኃጢአታችን ዳንን
                   - ከእስራት ዋጀን
                   - በዋጋ ገዛን
                   - ነፍሱን ስለእኛ ቤዛ አደረገ

~1ኛቆሮ.620 "በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ"።

~ማቲ.2028 "እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም"።

*በሞቱ ከሦስት እስራቶች ዋጀን/ተፈታን

4.1. ከህግ እርግማን ዋጀን፦
~ገላ.313 "በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ 14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ"። 

4.2. ከኃጢአተኝነት/ ከጥፋተኝነት ዋጀን
~ሮሜ.324 "በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ"።

4.3. ከኃጢአት ጉልበት ዋጀን፦ 
~1ኛጴጥ.118-19 "ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ"።

5. በሞቱ የጨለማው ገዢ ሰይጣንን አሸነፈ፦

~ቆላ213 "እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ። 14 በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል"። 

~ቆላ215 "አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው"።

6. እኛ ሞት እየተገባን እሱ በእኛ ፈንታ ሞተልን

~ሮሜ.58 "ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል"።

~ገላ.220 "ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ"።

~ኢሣ.535 "እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።6 እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ"።

~ማቴ.2028 "እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም"።

~ገላ.313 "በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤"

~1ኛ ጴጥ.318 "ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ" ።

~2ኛ ቆሮ.521 "እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው"። 

~1ኛ ጴጥ.224 "ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤25 በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል"።

~ዩሐ.1513 "ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም"።
        ~~~~~||~~~~~