Thursday, April 4, 2019

❖ገብርሄር፦

ጸጋን ለሰጠን መታመን፦

ገብርኄር ማለት መልካም ፥ ቸር ፥ ለጋስ ፥ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ መታመንን፥ ታማኝ አገልጋይነትን፥ የመታመንን ዋጋ፥ የአለመታመንን ቅጣት ያመለከተበት ምሳሌያዊ ታሪክ እንደሚከተለው ቀርቧል በማስተዋል እናጥናው፦

  "ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው።አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ።ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ።ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ።ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥.....እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር።ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።"ማቴ 25:14-30

ይህ ታሪክ ምን አስተማረን? ራሳችንን አሳየን? ምንድነው የተቀበልነው ? ምን ያህል አተረፍንበት ? የጸጋ ስጦታችንን እናውቃለን? ድርሻችንን ተወጥተናል ? የኛ መክሊት ለሌሎች ምን ጠቀመ? በሌሎችስ መክሊት ምን ተጠቀምን ? በመክሊታችን ሰጭውን አከበርንበት ? እግዚአብሔር እንደ አቅማችን ማትረፊያ መክሊት ሰጥቶናል፡፡ የሰጠንን መቅበር አንችልም፡፡ በተሾምንበት ነገር ታማኝ መሆን አለብን፡፡ የተቀበልን ነን የተቀበለ ደግሞ ይሰጣል የተቀበለ ሰጪውን ያከብራል የተቀበለ እንዳልተቀበለ አይኩራራም፡፡የተሰጠንን ሳንሰጥ ከሄድን እንጠየቃለን፡፡ በተሰጠን መክሊት ራሳችንን እና ሌሎችን ለእግዚአብሔር ክብር ማትረፍ አለብን፡፡ ድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ በአቅማችን ከሠራን በተሰጠን ከታመንን እግዚአብሔር በዚህ ደስ ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር አለመታመንን ይጠላል፡፡በተሰጠን ታምነን ማትረፍ አለብን፡፡

ከምድር የጠፋ ትልቁ ሀብት ታማኝነት ነው፡፡ሰው እንኳን ሰውን ራሱን የሚያታልልበት፥ ለራሱ እንኳ መታመን ያልቻለበት ሁኔታ አለ፡፡እግዚአብሔር ሳይሰጥ አልጠየቀም። ለጋስነቱን እያመሰገንን በተሰጠን ልክ ታምነን መሥራት አለብን፡፡በተሰጠን በተሾምንበት በጥቂቱ ከታመንን እግዚአብሔር በብዙ ይሾመናል፡፡ ገብርኄር የአገልግሎቱ ባለቤት እግዚአብሔር ከአገልጋዮች የሰጠውን አደራ ሊቀበል እንደሚመጣም ያሳያል፡፡ አገልጋይ ጌታ ወይም አሠሪ አለው፡፡ አሠሪው ሁሉንም በአቅሙ ልክ ጸጋ ሰጥቶ ነው ያሠማራው፡፡እንደሰጠን መጠን በኋላ ዋጋ ይከፍላል፡፡ ስለዚህ አገልጋይ አትራፊ መሆን አለበት፡፡ በተለይ መንጋውን ማትረፍ አለበት፡፡ታማኝ አገልጋይ ወይም እረኛ ለበጎቹ ሕይወት ዋጋ ይከፍላል፡፡ የተበተነውን ይሰበስባል፤የወደቀውን ያነሳል ያዘነውን ያጽናናል፥ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የራሱን ጥቅም አይፈልግም፤ በጎችን ለጥቅሙ አይሰዋም፤ ግን እረኝነት እንዲህ እየሆነ አይደለም።

እረኞች ሆይ ሕዝቡ ባለቤት አለው፥ በአግባቡ ምሩ። የሾማችሁ አንድ ቀን ወደ እናንተ ይመጣል፥ ያኔ ምን ልትመልሱ እንዳላችሁ አስቡ። ቃሉ እንደሚል "ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።" የሚለው እየተፈፀመ ነው፡፡ ሕዝ 34:3።

እግዚአብሔር የጠፉበትን ከእርሱ ርቀው እንዲሞቱ የተፈረደባቸውን ነፍሳት ደም ከእረኞች እጅ ይፈልጋል፡፡ ታምኖ የሚሠራ አገልጋይ ከክብር ጋር ከሽልማት ጋር ነው ወደ ጌታ ደስታ የሚገባው፡፡  ታምኖ የማይሰራ ከመንጋው ጮማውን እየበላ፣ ጠጉሩን እየለበሰ፣ አጥንቱን እየቀለጣጠመ ራሱን የሚያሰማራ እረኝነቱ( ፀጋው) ይወሰድበታል። ሌላ ታምኖ የሚሰራ ይዘጋጃል ዘካ 11:15 ። ታምኖ የጠፋውን በመፈለገ ማዳን ፣ የዳነውንም መቀለብ የበጎ ታማኝ አገልጋይ መገለጫ ነው።
     ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!

No comments:

Post a Comment