መንፈስ ቅዱስ ማነው?
፩. መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?
☞ ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል ነው፡፡
☞ የማይጨበጥ፤የማይታይ አካል ያለው መንፈስ ነው፡፡
☞ የሰረፀው (የወጣው) ከአብ ነው።
☞ ከአብ ከወልድ ጋር እኩል ምስጋና አምልኮ ይገባዋል
☞ እግዚአብሔር (አምላክ) ነው፡፡
☞ የአብ የወልድ እስትንፋስ (ሕይወት)ነው፡፡
☞ በነቢያትና በሐዋርያት አድሮ የተናገረ፥ሕይወትንም ያቀና : ምድርን ለክብሩ ያስጌጠ ነው፡፡
፪. የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ምን ምን ናቸው? ርግብ፣ እሳት፣ ውኃ፣ ዘይትና ነፋስ ናቸው።
☞ ርግብ የዋህ ናት፡ መንፈስ ቅዱስም የዋህና ቂም የማያውቅ ነው፡፡ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ መድረቁን ያወጀች የሰላም ምልክት ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ክርስቶስ ሲጠመቅ የኃጢአት ባሕር መድረቁን በርግብ ምሳሌ ወርዶ የሰበከ የሰላም ጌታ ነው።
☞ እሳት ያበስላል፡ መንፈስ ቅዱስ ሕፃን የሆነውን አእምሮ በጥበብ ያጎለምሳል፡፡ እሳት የከበረ ማዕድንን ከአፈር ይለያል፥ መንፈስ ቅዱስም አምኖ የከበረውን ፡ ካላመነው ይለያል፡፡
☞ ውኃ ያነፃል፥ መንፈስ ቅዱስ ይቀድሳል፡፡
☞ ነፋስ፣ ነፍስና መንፈስ የሚወጡበት የግሪክ ቃል ኒዩማ የሚል ሲሆን ከነፋስ- ነፍስ፤ ከነፍስ- መንፈስ ይረቃል። ነፋስ በእንቅስቃሴው እንደሚታወቅ መንፈስ ቅዱስም በሥራው ይታወቃል፡፡
❖ በብሉይ ኪዳን የመብራት ዘይት ነበረ፥ በየዕለቱ በመቅረዙ ይጨመራል፡፡ ይህ የመብራቱ አለመጥፋት የመንፈስ ቅዱስን መኖር ያመለክታል፡፡
❖ መንፈስ ቅዱስ ለቅርፅ አልባዋ መሬት ውበት ያፈሰሰ፥ ውኆችን ለፍጥረት ጥቅም የቀደሰ ጌታ ነው፡፡ "ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።" ኦሪት ዘፍጥረት 1:2።
❖ መንፈስ ቅዱስ መሳፍንትን በምስፍና፥ ነገሥታትን በንግሥና፥ ካህናትን በክህነት ጸጋ፥ ነቢያትን በሀብተ ትንቢት፥ ዘማርያንን በዝማሬ ጸጋ፥ ፈዋሾችን በሀብተ ፈውስ ......የሾመ...ጸጋ የሰጠና ጸጋን ያደላደለ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡
❖ መንፈስ ቅዱስ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም የሆነላትን እንድትረዳ አደረባት፡፡ ድንግል ማርያም በድንግልና እንድትወልድ ሁሉን አስቻላት፡፡ በክርስቶስ አገልግሎት ነበረ፡፡ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት ተናግሯል፡፡
☞ "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።" የዮሐንስ ወንጌል 14:26
☞ "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።" ዮሐንስ 16:7-15::
☞ " ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤" የዮሐንስ 15:26።
☞ " ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" ዮሐንስ 14:15-16::
❖ በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአደራረጉ ምክንያት የእውቀት መንፈስ፣ የጥበብ መንፈስ፣ የኃይል መንፈስ፣ የእውነት መንፈስ፣ የመገለጥ መንፈስ፣ ...ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በክርስቶስ አገለግሎት የነበረው ሱታፌ እንዳለ ሆኖ በክርስቶስ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ ከላይ ባሉት ጥቅሶች አይተናል፡፡ በክርስቶስ ትምህርት አጽናኝ(ጰራቅሊጦስ)፣ የእውነት መንፈስ እና ሁሉን የሚነግር መምህር ተብሏል፡፡ የሚመጣው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ የሚመጣበት አላማ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የማያምኑትን ይወቅሳል፤ የዲያብሎስን መጣል ይናገራል፤ ጽድቅ ወደ አብ በሄደው በክርስቶስ እንደሆነ ይመሰክራል፤ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ይመራል፤ ምእመናንን ያጽናናል፤ ለበጉ ሠርግ ያዘጋጃል፤ አገልጋዮችን ያሰማራል፡፡
❖ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም መጣ፤ በጽርሐ ጽዮን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተወለደችውን የክብርት ቤተክርስቲያን ልደት በእሳት ላንቃ በዓለም ቋንቋ አከበረ፡፡ ሐዋርያትን ለእውነት አስጨከነ፤ ምስጢር እና ብዙ ቋንቋዎች ገለጠላቸው፡፡ በጉዞቸው ሁሉ አብሮ ነበረ፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን አገለግሎት ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ነውና ክብር ለመንፈስ ቅዱስ!!
❖ ላመነ ሰው ጥምቀት የሚፈጸመው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ይህም የክርስቶስ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ 28:19:: በጥቅሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አይፈጽሙም፡፡ የምስጢራቱ አፈጻጸም ሥርዓት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
በመግቢያዬ እንደጻፍኩት ቤተክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ ጠንካራ አቋም አላት፦ "ማህየዊ በሚሆን በአንድ ጌታ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እርሱም ከአብ የሰረፀ ነው፡፡ በነቢያት እና በሐዋርያት ተናግሯል፡፡ ከአብ ከወልድ ጋር ምስጋና ይገባዋል።" ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ ፰.
መንፈስ ቅዱስ፦
☞ ሕይወት ሰጭ፤ ጥበብ ገላጭ መንፈስ ነው፡፡
☞ የጸጋ ምንጭ እና አደላዳይ ነው፡፡
☞ ለበጎ ሥራ ቀስቃሽ፤ከኃጢአት እንድንወጣ ወቃሽ ነው
☞ ልብን አይቶ የሚሾም፤ ትሁታንን የሚያከብር ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡
❖ መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ኃይል ነው፡፡ ብርታት የሆነን እርሱ ነው፡፡ ስንደክም ያግዘናል፡፡ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል(ሮሜ 8:26-27)፥ እንዴት ማምለክ እንዳለብን ይመራናል፥ ከዚያ ጸሎታችንን ይሰማል፤ አምልኮችንን ይቀበላል፡፡
❖ የመንፈስ ቅዱስ ነገር ለፍጥረታዊው ሰው ሞኝነት ነው፡፡ "ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።" 1ቆሮንቶስ 2:14። የመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ በእምነት መንፈስ እንጂ በሥጋ አይመረመርም፡፡ የጰራቅሊጦስ የተቀበልነው ይህን የእውነት መንፈስ ነው፡፡ "እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።" 1ቆሮንቶስ 2:12።
❖ መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታዊ ሰው አይኖርም፡፡ እንዲያውም የክርስቶስ መንፈስ የሌለው የክርስቶስ ወገን አይደለም፡፡ "የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።" ሮሜ 8:9።
❖ ምክር፣ ጥበብ፣ ምስጢር፣ ትንቢት፣ ፈውስ፣ ዝማሬ፣ ሹመት፣ ኃይል .... ከመንፈስ ቅዱስ ይሰጣሉ፡፡ ደስታ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት፣ ትዕግስት፤ በጎነት፣ ቸርነትና ሰላም የመንፈስ ፍሬ ናቸው፡፡ ገላ 5:23::
❖ መንፈስ ቅዱስ ከምንተነፍሰው አየር በላይ ያስፈልገናል፡፡ በሥራችን ዐመፃ የመንፈስ ቅዱስን አሠራር ልንቃወም እንችላለን፡፡ "መንፈስን አታጥፉ፤" 1ተሰሎንቄ 5:19። ንጉሥ ዳዊት በበደለ ጊዜ ይህ አጋዥ፣ አስተማሪ፣ መሪ እና አጽናኝ መንፈስ እንዳይወስድበት ለመነ፡፡ "ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።" መዝሙረ ዳዊት 51:11።
❖ መንፈስ ቅዱስ ከተለየን ሕይወት፣ ሰላም፣ ዕረፍት፣ መንፈሳዊነት ... የንስሐ ጸጸት...ይለዩናል፡፡ ስለዚህ "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።" ኤፌ 4:30-32:: የሥጋ ሥራ ከመንፈስ አላማ ያወጣል፡፡ የሥጋ አሠራር መንፈስ ቅዱስን ይቃወማል፡፡ ደስታ የሰጠን ሀዘን ሊቀበል አይችልም፡፡ ባናከብረው ደስታ የምናጣው እኛ ነን፡፡ " ለአሠራሩ እንመች፡፡ በኖህ ዘመን ርግቧ በመጀመሪያው ጉዞዋ ማረፊያ አጥታ እንደተንከራተተች መንፈስ ቅዱስም ለአሠራሩ የሚመች ሰው አጥቶ በዙሪያችን አለ።" ለአሠራሩ እንመች፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሰን፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ አንብቡ ፥ ዘምሩ፡፡ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይገባል!!!
No comments:
Post a Comment