Wednesday, February 8, 2017

❖መንፈሳዊ እድገት


           መንፈሳዊ እድገት፦

መንፈሳዊ ዕድገት በማይታየው ቅዱስ መንፈስ የተደገፈ የሚታይ ኑሮ ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት ያመነ ሰው እምነቱን በሥራ የሚገልጥበት ሂደታዊ(ዘላቂነት ያለው) አኗኗር ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት የመንፈሳዊ ሰው የከፍታ ምስጢር ነው፡፡
መንፈሳዊ እድገት መንፈሳዊ ሰው በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ በመንፈስ ፍሬዎች የሚያጌጥበት የሕይወት ውበት ነው፡፡ይህ ኑሮ ሰው እንዲጠቀምበት፥ እግዚአብሔር እንዲከብርበት በመለኮት ዕቅድ ቀድሞ የታሰበ ኑሮ ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት የቅድስና መንገድ ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት በግንዱ በክርስቶስ በመሆን ፍሬ የምናፈራበት አኗኗር ነው፡፡ከግንዱ ተለይቶ ማፍራት አይቻልም፡፡"እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።"ዮሐንስ 15:5
በመንፈሳዊ ሕይወት የገጠመን ዝለት እና ስልቹነት ከግንዱ ጋር አለመተባበር ነው፡፡በግንዱ ካልሆነ ድርቀት እንጂ እድገት አይኖረንም፡፡የመንፈሳዊ እድገት መሠረቱ በግንዱ ሆኖ ማፍራት ነው፡፡መንፈሳዊ እድገት ሰሞነኛነት አይደለም፡፡መንፈሳዊ ሕይወት የማይቋረጥ ኑሮ ነው፡፡በየጥቂቱ የሚያድግ አኗኗር ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ኑሮ በሚገባ ተርኮታል፦
"ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።" 2ጴጥ 1:5-10፡፡
 እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ መንፈሳዊ ሕይወታችን እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ ነው? በቦታ እና በሁኔታዎች አይወስንም ??? በጊዜ ሂደት አልቀነሰም ??? መንፈሳዊ ሰው በመጨመር በማብዛት እና በመብዛት ፍሬው ይገለጣል፡፡መንፈሳዊ ዕድገት ክርስቶስን ወደመምሰል የምናደርገው ጉዞ ነው፡፡

1. የመንፈሳዊ ዕድገት መሠረት፦
    ሕንፃ ያለ መሠረት እንደማይመሠረት መንፈሳዊ ዕድገትም ያለ መሠረት አይወጠንም፡፡የመንፈሳዊ ሕይወት ጽኑ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ጥሩ መሠረት ያለው ቤት ሞገድ እና ነፋስ እንደማይነቅለው በክርስቶስ ላይ ሥር ሰዶ በመታነጽ የመንፈሳዊ ዕድገት ጉዞ የወጠነ አማኝም በምንም ሁኔታ በፍጹም አይናወጽም፡፡መሠረቱ ላይ ያልተተከለ፥ ራስ በሆነው ያልተጋጠመ ይህን ክፉ ዘመን አያልፍም፥ ነፋስ አቅጣጫ ያስቀይረዋል፡፡ተወዳጆች ሆይ፦ እምነት እና አላማችንን መሠረቱ ላይ እናድርግ፡፡የሁሉም መነሻ እና መድረሻ እርሱ ነውና፡፡ "የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።" ዕብ 12:1-2
መሠረቱ አንድ ነው፥ ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም፡፡ "ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።"
1ኛ ቆሮንቶስ 3:11 ይህ መሠረት ላይ የቆመ ዕድገቱ አስተማማኝ ነው፥ አይንሸራተትም፥ አይሰነጠቅም፥ መከራ ወደ ኋላ አይመልሰውም፡፡ከተመሠረትን በኋላ ጸንተን በብዙ ፍሬ ለማደግ የሚከተሉትን መንፈሳዊ ተግባራት ሳናቋርጥ እናድርግ፦
1. ቃሉን መመገብ
2. ጸሎት
3. ጾም
4. መንፈሳዊ እውቀት መጨመር
5. ትጋት
6. ቅዱስ ቁርባን

1.ቃሉን መመገብ፦
  በተፈጥሮ ህግ የማይመገብ ሰው ይራባል ፣ይደክማል፣ ይታመማል ፣ባለመመገቡ ከጸና ይሞታል።ቃሉን የማይመገብ ክርስትያን መንፈሳዊ ረሃብ (የፍቅር፣የትህትና ፣የበጎነት ፣የቅንነት ወዘተ…  ረሃብተኛ)፣ ድካም( ለፀሎት ፣ለአገልግሎት ፣ለፆም ወዘተ…  ደካማ)፣ ህመም ( ቃሉ ምንድነው ? መንፈሳዊነት ምንድነው ? ቤተክርስትያን ምንድናት ወዘተ…  የሚል ህመምተኛ )፣ሞት( ያለእግዚአብሔርና ያለቃሉ የሚኖር ስም ያለው ነገር የሞተ ማንነት ያለው ይሆናል) ።
"ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።"
1ኛ ጴጥሮስ 2:2-3። እንደተባለ ቃሉ ለእድገታችን ጠቃሚ የሆነ ዋና ምግብ ነው፡፡በቃሉ በኩል እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የፈቃዱን ምስጢራት እናውቃለን፡፡ስለዚህ እንደ ፈቃዱ የሆነ እድገት ይኖረናል፡፡የቃሉ ወተት የሚያስፈልገን አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ነው፡፡ወተት አሁን ለተወለዱ ሕፃናት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ካደጉ በኋላ ግን ብዙ አማራጭ ይኖራቸዋል፡፡መንፈሳዊ ሰው በዋናነት ሁልጊዜ የቃል ወተት ያስፈልገዋል፡፡ቃሉ የልጅነት ትዝታችን፥ የጉልምስና ትጥቃችን፥ የሽምግልና ወራት ኃይላችን ነው፡፡ቃሉ የማያስፈልግበት ጊዜ የለም፡፡ስለዚህ ሁልጊዜ የቃሉ ወይን ጠጅ የማይጎድልባቸው ማድጋዎች እንሁን፡፡ያለ ቃሉ ድጋፍ መንፈሳዊ እድገት አይከናወንም፡፡ሕፃናት ከእናታቸው የሚያገኙት ወተት ጤናማ እንደሚያደርጋቸው ሁሉ የጌታ ምክርም ጤናማ ዕድገት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

2. ጸሎት፦
     ለምን እንጸልያለን?
-ፈቃዱን ለማወቅ ዘፍ 24:11-14
-ለማመስገን መዝ 12:6
-ወደፈተና እንዳንገባ ማቴ 26:41
-ከክፉ ለመጠበቅ ማቴ 6:13
-ዲያብሎስን ለመርታት ማቴ 17:21
እኛ መሥራት ያልቻልነውን እግዚአብሔር እንዲሠራልን የምንጠይቅበት መሳሪያ ጸሎት ይባላል፡፡ነገር ግን መጸለይ ባለመቻላችን የጸሎትን ኃይል መጠቀም አልቻልንም፡፡ባለመጸለያችን ከነችግራችን እንኖራለን።ጸሎት የሕይወታችን እንቅስቃሴ በጌታ ፈቃድ እንዲመራ ፈቃደኝነታችንን የምናሳውቅበት መንገድ ነው፡፡"ከልብ የሆነ ጸሎት ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው መብአ ነው" እንዳለ ቅዱስ አግናጥዮስ ጸሎት የአምልኮ መገለጫ ነው፡፡ለመንፈሳዊ ዕድገት እጅግ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ጸሎት የማይቋረጥ ድርጊት ነው፡፡ጸሎት በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ የግንኙነት መስመር ነው፡፡መጸለይ ካቆምን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ እንሆናለን፡፡በብዙ ጉዳዮች ስለተያዝን የጸሎት ጊዜና አቅም አጥተናል፡፡ስለዚህ ለመጸለይ እንኳ ጸሎት ያስፈልጋል፡፡ጸሎት የመንፈስ ብልጽግና ያመጣል፤ ኃይል ያጎናጽፋል፤ በጸጋ ያሳድጋል፡፡<ጸሎት ለነፍስ ሰላምና እርጋታን ያመጣል፡፡> ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡ጸሎታችን፦ በእምነት፥ በመንፈስ፥ በስሙ፤ እንደ ፈቃዱ መሆን አለበት፡፡ያለ ጸሎት የመንፈሳዊ ዓለም ተጋድሎ አይቻልም፡፡ድል የኛ እንዲሆን፥ እንድናድግ ጸሎት ያስፈልገናል፡፡ጸሎታችን ምስጋናን፥ የኃጢአት ይቅርታን፣ምልጃን እና ልምናን ማካተት አለበት፡፡ 1ጢሞ 2:13፡፡

3 ·ጾም፦
   ጾም በራስ ፈቃድ ለጊዜው ከምግብ፤ ለዘላለም ከኃጢአት መከልከል ነው፡፡ጾም የክርስቲያን ሕይወት አካል ነው፡፡ ጾም የአዲሱ ሰው ኑሮ ማሳያ ነው፡፡<ጾም የሥራ መጀመሪያ ነው፡፡>ጾም ለመንፈሳዊ ዕድገት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ጾም ስለ እግዚአብሔር ክብር የሥጋ ፍላጎትን መተው ነው፡፡በሁለቱም ኪዳናት መልካም ታሪክ ያላቸው አባቶች የጾም ሕይወት ነበራቸው፡፡ሙሴ፥ ኤልያስ፥ አስቴር፥ ዳንኤል፥ ዕዝራከብሉይ ኪዳን ይጠቀሳሉ፡፡በአዲስ ኪዳን ሐዋርያት እና ሌሎች ለእግዚአብሔር ያደላ ኑሮ ያላቸው በጾም ይታወቀሉ፡፡የክርስትና አርአያ ጌታችን ኢየሱስ ጾሟል፡፡የእርሱን ፍለጋ የምንከተል በጾም ላይ ጠንካራ አቋም ሊኖረን ይገባል፡፡በመብል የሠሩባት አልተጠቀሙምና፡፡ዕብ 13:9:: በመንፈሳዊ እድገት ከፍ ለማለት፥ለመንፈስ ቅዱስ አሠራር ለመመቸት ሥጋችንን መጎሰም አለብን፡፡
ለምን እንጾማለን?
-ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳችንን ለማስገዛት መዝ 35:13 ዕዝ 8:21
-ለንስሐ ዮናስ 3:10
-ለአገልግሎት ጥንካሬ እና ለበረከት ማቴ 6:17-18
እንዴት እንጹም፦
-በደልን በመናዘዝ ኢሳ 58:8 ሉቃስ 18:11
-ፍትሐዊ በመሆን ኢሳ 58:3
-ራስን በመግዛት 1ቆሮ 7:5
-ሥጋን ከነመሻቱ በመስቀል ገላ 5:24
-የዲያብሎስን ማታለያ በመናቅ ማቴ 4:1-11
-ታይታ ባለመፈለግ ማቴ 6:16-18
-ሌላውን ባለመንቀፍ ሮሜ 14:41.

4 ·እውቀት፦
     መንፈሳዊ እውቀት ለዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ ለማደግ የጥበብን ደጅ ማንኳኳት አለብን፡፡እውቀት በትምህርት፣ በልምድ፣ በምንባብ፣ በጥናት እና ምርምር ይገኛል፡፡ቅዱስ አትናቴዎስ <ለእግዚአብሔር ራሱን የሰጠ ሰው ፀሐይ ንጋት ላይ ስትወጣ በእጆቹ ላይ ቅዱስ መጽሐፍ መገኘት አለበት>እንዳለ ከመጻሕፍት ጋር መዛመድ አለብን፤ መንፈሳዊ እውቀት ግን የልብ ቅንነት እና እምነት ይፈልጋል፡፡መንፈስ ቅዱስ ለሚያስተምረን ልባችን ክፍት መሆን አለበት፡፡ዕድገትን የሚያቀጭጩ ከንቱ ፍልስፍናዎችን መራቅ አለብን፡፡ብዙ ማብራሪያ የሚያገላብጥ፥ ጥንታዊ ቋንቋዎች አመሣክሮ ቃሉን የሚያጠና አማኝ በኑሮም ምስክር መሆን አለበት

5. ትጋት፦
     ትጋት የፍሬ መሠረት ነው፡፡ ትጋት የመንፈሳዊ ዕድገት ትጥቅ ነው፤ ያለ ትጋት ዕድገት የለም፡፡የተሰጠንን ጸጋ እና ኃላፊነት በማክበር ለተፈጠርንበት አላማ እንድንታመን መትጋት አለብን፡፡ትጋት በስም ሳይሆን በሥራ የሚገለጽ ጥንካሬ ነው፡፡ስንፍና፥ ዳተኝነት፥ ግዴለሽነት፥ ዝለት፥ ቅምጥልነት የዕድገት ፀር ናቸውቅ.ጳውሎስ "በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።"ዕብ 6:11—12፡፡መንፈሳዊ ሰው የዕድገቱ ቀጣይነት የሚረጋገጠው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ባለው ድጋፍ ሲሆን ትጋት የከበረ ሀብቱነው፡፡ይህ ትጋት የዘመን ሙሉ ኃይል ነው፡፡ያለ ትጋት ምንም ለውጥ አናመጣም፡፡በእምነት የተስፋ ቃል ተቀብለናል፤ በትዕግስት ለመቀበል ትጋት ትልቁ መሳሪያ ነው፡፡ሥራ ጀምረን ለመጨረስ ኃይል፥ መንፈሳዊ ኑሮ ለመቀጠል አቅም፥ ለመበልጸግ ሀብት፥ ለማሸነፍ አቅም ትጋት ነው፡፡ "ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው"ምሳ 12:27።

6· ቅዱስ ቁርባን፦
    የክርስቶስ ሥጋና ደም/ ቅዱስ ቁርባን/ ሞቱን የምንመሰክርበት አንደበት ነው፡፡"ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።" 1ቆሮ 11:26፡፡ቅዱስ ቁርባን የኪዳን ምልክት፥ የምስክርነት ራስ፥ የኅብረት ማህተም፥ የግንኙነት መሠረት ነው፡፡ለመንፈሳዊ ዕድገት እጅግ በጣም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሰበብ ማብዛቱን ትተን ቁርባንን የመንፈሳዊ ሕይወታችን አካል እናድርግ፡፡መንፈሳዊ ሕይወት ቀጣይነት ያለው የክርስትና ፍሬ ነው፡፡ ክርስትና ለእግዚአብሔር የተለየ አኗኗር በመሆኑ ቃሉን በማጥናት፥ እውቀት በመጨመር፥ በጸሎት እና በጾም በመጽናት፥ መልካሙን ሁሉ በትጋት በማድረግ፥ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል  አለብን፡፡
                 የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁይሁን !!!

No comments:

Post a Comment