“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ”
“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ፤ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ ➟በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ [ላረገ] ለእግዚአብሔር ዘምሩ!” መዝ 67 (68)፥33
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው 9 የጌታ ዐበይት (ታላላቅ) በዓላት አንዱ የዕርገት በዓል ነው።
የተቀሩት ስምንቱ፦
➠ በዓለ ትስብእት (ብስራት - Annunciation)
➟ ልደት
➟ ጥምቀት
➟ ደብረ ታቦር
➟ ሆሣዕና
➟ ስቅለት
➟ ትንሣኤ እና
➟ ጰራቅሊጦስ ናቸው።
የደብረ ታቦር በዓል በምሥራቅ አኀት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን (The Feast of Transfiguration) በመባል ይታወቃል። የመገለጥ/የመለወጥ በዓል ብለው ይጠሩታል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት 9 በዓላት በተጨማሪ ምሴተ ሐሙስን አካትቶ ፥ በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረና በብዕር ስሙ “ርቱዓ ሃይማኖት - ሃይማኖቱ የቀና” በመባል የሚታወቀው ሊቅ “ድርሳናት ዘበዓላት ዐበይት” በሚል ርእስ ፥ የጌታችንን 9 ዐበይት በዓላት የተመለከቱ ድንቅ ድርሳናትን ደርሷል።
ቤተ ክርስቲያናችን የዕርገትን በዓል በማሕሌትና በቅዳሴ እንደምታከብረው እናውቃለን። ሊቃውንቱም፦ “ዮም ፍስሓ ኮነ በእንተ ዕርገቱ ለክርስቶስ እምድኅረ ተንሥአ እሙታን በ፵ ዕለት በይባቤ ወበቃለ ቀርን ፤ አማን መንክር ስብሐተ ዕርገቱ። ማለት ፦ ከሙታን ከተነሣ ከ፵ ቀን በኋላ በዝማሬና በመለከት ድምጽ ዛሬ ክርስቶስ ስላረገ ፥ [በዕርገቱ] ደስታ ሆነ” እያሉ በደስታና በሐሴት ያዜማሉ።
ነገር ግን አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ለምን ይህን የመዳናችን ክፍል የሆነውን ታላቅ በዓል እንደሚረሱትና ልብ እንደማይሉት ግልጽ አይደለም። ምናልባት ዕርገት የሚከበርበት ቀን ሐሙስን ስለማይለቅ የሥራ ቀን ሆኖባቸው ነው እንዳንል ፥ በሥራ ቀን የሚውሉ ሌሎች በዓላትን በድምቀት ሲያከብሩ እናያለን። ስለጌታ ዕርገት ያላስተዋልነውና ብዙ ልንማረው የሚገባ ነገር አለ።
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በይባቤ መላእክት በክብር ወደ ሰማያት ላረገው ጌታና አምላክ እንድንዘምር ያዘናል። አበው መተርጉማን “ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ፤ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ” የሚለውን የዳዊትን መዝሙር ሲተረጉሙ፦ ለገነት ምዕራብ ከምትሆነው ከሲኦል ነፍሳትን አውጥቶ ወደገነት ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ፤ አንድም ➟ ለኢየሩሳሌም ምሥራቅ በምትሆነው በደብረ ዘይት በኩል ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ማለት ነው ብለዋል። ይህ የድል ዝማሬ ነው ፤ በዚሁ በ67ኛው የዳዊት መዝሙር ቁጥር 18 ላይ “ዐረገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ - ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም (ሰማይ) አረግህ” ተብሎ እንደተዘመረ ፥ ነፍሳትን ከሲኦል ግዞት ነጻ አውጥቶ በክብር ላረገው ጌታና መድኃኒት የአምልኮ ዝማሬ ይገባል።
መቼም ነቢይ ወንጉሥ የሆነው ዳዊት “እግዚአብሔር ዐረገ” “ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ” ሲለን እግዚአብሔር መውጣት መውረድ እንደሌለበት እናውቃለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ፥ ይህ ትንቢታዊ ቃል የተነገረው ቃልን ለተዋሐደው ሥጋ እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ። በድጋሚ ዳዊት በ46ኛው መዝሙሩ (ቁ.5 ላይ) ፦ “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ፥ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ፥ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ - ጌታችን እግዚአብሔር በይባቤ መላእክት ፥ በቅዳሴ ፥ በሥልጣን ዐረገ ፤ ለአምላካችንና [ለንጉሣችን ለክርስቶስ] ዘምሩ (ምስጋና አቅርቡ)” ይለናል። ወረድ ብሎ ደግሞ (ቁ.8 ላይ)
➟ “እግዚአብሔርሰ ይነብር ዲበ መንበሩ ቅዱስ - እግዚአብሔር ግን በቅዱስ መንበሩ ይቀመጣል” ሲል ይዘምራል። ይህም ከላይ እንደተገለጸው ፥ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም ደግሞ የእግሩ መረገጫ ለሆነችለት ለእግዚአብሔር መውረድና መውጣት እንደሌለበት (ዐረገ ፥ ወጣ ፥ ወረደ እንደማይባል) ፤ ነገር ግን ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል (ወልድ) በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም የእኛን ባህርይ ወስዶ ሥጋን ስለተዋሐደ ፥ ያረገውም ከድንግል በነሣው በዚሁ ሥጋ ስለሆነ “እግዚአብሔር ዐረገ” ወይም ቃል በሥጋ ዐረገ ማለት እንደሚቻል ያመለክታል። በሌላ መልኩ ይህ ዝማሬ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ከሚያስረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች አንዱ ነው።
እንደ አባቶቻችን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትርጓሜ ፤ ቃለ እግዚአብሔርን የተዋሐደው ሥጋ በተዋሕዶ እንዳረገ የሚያስረዳው ተጨማሪ የዳዊት ዝማሬ፦ “ተፅዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሠረረ - በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ” የሚለው ነው (መዝ 17/18፥10)፡፡ ዳዊት ይህን ዝማሬ የሚዘምረው ➟ “አጽነነ ሰማያተ ወወረደ” (ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ወረደ) ካለ በኋላ ነው። “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ፥ መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም ፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንደጻፈልን (2፥6-7) እኛን ያድነን ዘንድ በትህትና የተገለጠው ወልደ እግዚአብሔር ፥ የማዳኑን ሥራ ፈጽሞ ዐረገ። መድኃኒታችን ክርስቶስ ፥ ሰው የሆነ አምላክ ነውና “በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ (ዐረገ)” የሚለው የዳዊት ዝማሬ ሥጋ በተዋሕዶ ማረጉን ያመለክታል።
ከላይ የጠቀስነው “ርቱዓ ሃይማኖት” በሚል ስም እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ በጌታችን ዕረገት ላይ ድርሳን (treatise) የጻፈው ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ዘሰግላ) ግሩም በሆነ ትርጓሜ “መጽሐፈ ምሥጢር” በተሰኘው መጽሐፉ ፦ “ያዕቆብ ሆይ ከኛ ጋር በዓልን ታደርግ ዘንድ ና! ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የወርቅ መሰላል ደብረ ዘይት ላይ ተተክሎ ጫፉ ሰማይ ደርሷል ፤ ይህ የወርቅ መሰላል ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ሰማይ ከወጣው የወልድ ሥጋ ዕርገት ሌላ ምንድን ነው?” ይለናል። በፊልጶስ ምክንያት ወደ መድኃኒታችን ክርስቶስ የመጣው ናትናኤል ከጌታ “ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” የሚል ቃል እንደሰማ እናውቃለን (ዮሐ 1፥52)፡፡ ለዚህ ነው አባ ጊዮርጊስ ፥ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ከምድር እስከ ሰማይ በሚደርስ መሰላል ላይ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያየውን ያዕቆብን ፥ የህልምህ ፍቺ በጌታ ዕርገት ቀን ተፈጽሟልና ይህን ምሥጢር ታይ ዘንድ ፥ ከእኛም ጋር “በዓልን ታደርግ ዘንድ ና!” የሚለው።
በተመሳሳይ መልኩ ፥ በደብረ ታቦር ሙሴ የጌታችንን ግርማ-መለኮት እንዳየ ፥ ግሩምና ድንቅ የሆነውን ዕርገቱን ያይ ዘንድ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር እንዲህ ሲል ይዘክረዋል፦ “ሙሴ ሆይ! ሕዝብህን ቀን በደመና ፥ ሌሊት በእሳት ዐምድ የመራቸው ጌታ ፥ ወደ ላከው ወደ አብ በእሳት ዐምድ ዐረገ።” የምስጋና ንጉሥ ፥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ሆኖ በመላእክት ይባቤ ሲያርግ ፥ ለንጉሡ የሰማይ ደጅን ይከፍቱ ዘንድ የሰማይ መላእክት “አርኅዉ ኆኃተ መኳንንት” በሚል ቃል ታዝዘዋል። ንጉሡ ሲያርግ መላእክት ያጅቡት እንደነበር ፥ በሰው መልክ ተገልጠውና ነጫጭ ልብሶች ለብሰው ሐዋርያትን ካናገሯቸው መላእክት መረዳት እንችላለን። ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምና ከሌሎች ቅዱሳት አንስት ጋር በአንድ ልብ ለጸሎት ይተጉ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ፥ በቢታንያ ተራራ ላይ እጆቹን አንሥቶ የባረካቸውን ጌታ እያዩት ከፍ ከፍ ሲል ደመናም ከአይናቸው ሰውራ ስትቀበለው ፈዝዘው ይመለከቱ ነበር። በዚህ ጊዜ ምስጋና ለሚገባው ንጉሥ ይባቤ እና ውዳሴ ያቀርቡ ከነበሩት መላእክት መካከል ሁለቱ፦ “የገሊላ ሰዎች ሆይ ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት ፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (የሐዋ ሥራ 1፥11)፡፡
ከሰማይ የወረደው እርሱ ወደ ሰማይ ሲወጣ ➟ “እናንተ መኳንንቶች ፥ በሮችን ክፈቱ ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” የሚል ዝማሬ በሰማይ ተሰማ። (መዝ 23/24፥9) የሰማይ መኳንንት የሆኑት እነ ሚካኤል ፣ ገብርኤል ፣ ሩፋኤልና ሌሎችም ቅዱሳን መላእክት የሰማይን ደጆች አንዲከፍቱ ታዘዙ። ስለሆነም “ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” የሚለው የጌታችን ትንቢታዊ ቃል ተፈጸመ። በሰማይ መከፈትና መዘጋት ባይኖርበትም ፥ ይህ አባባል በዕርገተ ኢየሱስ የተገለጠውን ታላቅ የሥጋዌ ምሥጢር ያመለክታል፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “ኦ አዳም ናሁኬ ተፈጸመ ዘይቤ እግዚአብሔር አመ ፀአትከ እምገነት አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ ➟አዳም ሆይ ከገነት በወጣህ (በተባረርክ) ጊዜ እግዚአብሔር “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ያለውን [ትንቢታዊ ቃል] እነሆ ተፈጸመ” ሲል አመስጥሮ እንደጻፈልን። አዳምን ካነሳ አይቀር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ሔዋንንም፦ “ኦ ሔዋን ተፈሥሒ በሞገሰ ወለትኪ …ዝኩ ዘወለደቶ በአንቀጸ ሥጋሃ ኅቱም ተለዓለ ኀበ አቡሁ ሰማያዊ እንዘ ትኔጽሮ ቀዊማ ምስለ አርዳኢሁ ቡሩካን ➠ ሔዋን ሆይ በሴት ልጅሽ (በድንግል ማርያም) ሞገስ ደስ ይበልሽ ፤ . . . በታተመ ድንግልና የወለደችው እርሱ ፥ ከተባረኩ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆማ እያየችው ወደ ሰማያዊ አባቱ ዐረገ” ይላታል።
የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ክርስቶሳውያን! መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዳነን ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ባደረገው አጠቃላይ (holistic) የማዳን ሥራ (እንደ አበው አባባል ፦ በሁሉ እየካሰልን) ስለሆነ ፥ የዕርገት በዓል የድኅነታችን (የመዳናችን) በዓል ነው። አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ በተሰበሰቡት 318 አባቶች ስም የተሰየመው የቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴ፦ “ተዘከር ሥጋ እንተ ነሣእከ እምቅድስት ድንግል ከመ ውእቱ ሥጋ ዘዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ➠ ወደ ሰማይ ያረገውና በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ከድንግል የነሳኸው ሥጋ እንደሆነ አስብ” ይላል። ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተነሳው ሥጋ ፥ የእኛ ሥጋ ነው። ስለዚህ ዕርገትን ስናከብር ፥ ሥጋችን ዐርጎ በኪሩቤል ጀርባ ፥ በአብ ቀኝ መቀመጡን ልብ እንበል። በእውነት ለተወደድንበት ዘላለማዊ ፍቅር ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ያለጥርጥር ታላቅ” እያለ ለሚያደንቀው በሥጋ ለተገለጠው ምሥጢር አንክሮ ይገባል! (1 ጢሞ 3፥16)፡፡ አባቶቻችን በቅዳሴ እንደነገሩንም፡- “ኦ እንተ አፍቀርካ ለዛቲ ዘመድነ ➠ አቤቱ ባህርያችንን የወደድሃት” እያልን የተወደድንበትን በሞት የተገለጸ ፍቅር እናድንቅ እናወድስም!
ከመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ ስለሆንን (2ኛ ጴጥ 1፥4) “ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአል” ተብሎ እንደተጻፈ (ሮሜ 8፥29) የልጁ መልክ በውስጣችን እስኪሳል ድረስ ኃጢአትንና ርኵሰትን ተጸይፈን የተጠራንበትን የቅድስና ሕይወት ልንለማመድ ይገባል! ሥጋችንን ያከበረው ፥ ከአእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢረ ተዋሕዶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደው አምላካችን ፥ ሰውነታችንን (ሁለመናችንን) እርሱን ደስ የሚያሰኝና ፥ ሕያው ፥ ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን እንድናቀርብ ያዝዘናል። (ሮሜ 12፥1) አገልግሎታችንንና “የምስጋና መሥዋዕት” የተባለው (መዝ 49/50፥14) የከንፈራችንን ፍሬ (ዝማሬያችንን) እግዚአብሔር ፊት ስናቀርብ ሥጋንና ነፍስን ከሚያስነውር ማንኛውም ዓይነት ርኵሰት ርቀን ፥ ኃጢአትንም ተጸይፈን መሆን አለበት።
የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን በዝሙት እያረከሰን ፥ መቅደሱን አፍርሰን እንዘምር ብንል በእግዚአብሔር ላይ መዘበት ይመስልብናል። የምናመልከው አምላክ ደግሞ ሽንገላን የማይወድ “እውነት ፥ መንገድና ሕይወት” ተብሎ የተጠራ ጻድቅ ነውና “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ተብሎ ተጽፏል (ገላትያ 6፥7)፡፡ ቅዱስ ያሬድን በመከተል ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ስለጌታ ዕርገት ሲያስተምሩ፦ “ዐርገ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ➠ የጻድቃንን (የእውነተኛ ልጆቹን) ዕርገት ያጠይቅ ዘንድ ዐረገ” ይላሉ። እውነት ነው “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ . . . ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ 14፥2-3) ሲል በማይታበል ቃሉ የነገረን አምላካችንና መድኃኒታችን ለእኛ ለልጆቹ ሰማያዊ ሥፍራ ያዘጋጅልን ዘንድ ዐረገ። በእርሱ ያመኑ ፣ እርሱን በፍቅር የተከተሉ ልጆቹ ቢሞቱ እንኳ ወደ ሕይወት ይሻገራሉ እንጂ ሞት የለባቸውምና: ነፍሶቻቸውን ቅዱሳን መላእክት በክብር ያሳርጋሉ። ጌታዋንና አምላኳን የምትወድድ ነፍስ ከሥጋዋ በሞት ተለይታ ወደ ሰማይ በምታርግበት ጊዜ ፥ “በውዷ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?” የሚለው ፥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚበልጠው የሰሎሞን መዝሙር ይዘመርላታል (መሐልየ መሐልይ ዘሰሎሞን 8፥5)፡፡
በመጨረሻም ወገኖቼ፦ በመላእክት ቅዳሴ እና ይባቤ ላረገው ለንጉሡ ኢየሱስ (ለኢየሱስ ክርስቶስ) የተዘመሩ ዝማሬያትን ልብ እንበል። ስለ ዕርገቱ የተቃኙ የዳዊት ዝማሬያት በሙሉ “ዘምሩ” የሚል ትእዛዝ አለባቸው፦ “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ . . . ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ ፤ ዘምሩ ለንጉሥነ ዘምሩ ➠ አምላክ በእልልታ ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ ፤ ዘምሩ ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ፤ ዘምሩ ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ” (መዝ 46/47፥5-6)፤ “ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ➠ ወደ ሰማይ ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (መዝ 67/68፥33)፡፡ ስለሆነም የዕርገት ቀን የዝማሬና የይባቤ ቀን ነው ፤ ዛሬ ያልዘመርን መቼ ልንዘምር ነው? ጥምቀትን ደመቅ አድርገን ስናከብር ፥ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ . . .” የሚል አገርኛ አባባል አለን። ስለጌታ ዕርገት ከላይ የተዘረዘሩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ኦርቶዶክሳዊ ምልከታዎችን ልብ ብለን “ለዕርገት ያልሆነ መዝሙር . . .” የሚል አዲስ አባባል ልንፈጥር ይገባል።
አዎን! በይባቤ ፥ በመለከት ድምጽ ላረገው ጌታና ንጉሥ ከመላእክቱ ጋር አብረን እንዘምር።
ይህ የምስጋና ንጉሥ ስለኃጢአታችን የተሠዋ የእግዚአብሔር በግ ነውና። በሰማያት ለታረደው በግ የሚቀርበውን ዝማሬና ውዳሴ እኛም በምድር እንድገመው።
➦ ራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ 5፥8 . . . አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
➦ 9-10 መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ፥ ታርደሃልና ፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው ፥ በምድርም ላይ ይነግሳሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።
➦ 11 አየሁም ፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር።
➦ 12 በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።
➦ 13 በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።
➦ 14 አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።
✟➫ ሥጋችንን ከመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ አድርጎ ላከበረን ፥ ከድንግል ማርያም በነሳው በእኛ ሥጋ ወደ ሰማያት ላረገው ፥ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ለተቀመጠው ፥ በክብር እንዳረገ ከደመና ጋር ዳግም ለሚመጣው ፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ ለእርሱ ፥ ከባሕርይ አባቱና ማሕየዊ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ፣ ኃይል ፣ እልልታ ፣ ይባቤና ሽብሸባ ፣ ምስጋናና ውዳሴም ይሁን።
~~~~~~||~~~~~~
No comments:
Post a Comment