Saturday, April 8, 2017

❖ሆሳዕና ፦

   ሆሳዕና ማለት አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው! 
 ከዛሬ 1977 ዓመታት በፊት የሚቀድሙ እና የሚከተሉ ሕፃናት እና አዋቂዎች የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ልብሳቸውን አንጥፈው የሰማዩ ልዑል በተናቀች አህያ ጀርባ ተጭኖ ሲገባ  "ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።" (ማቴ 21:9)
   መረጋጋት ላቃታት ለኢየሩሳሌም ቅኝ አገዛዝ ለጸናባቸው ለአይሁድ አሁን አድነን ትልቅ ልመና ነበረ፡፡እያመሰገኑ መለመን መታደል ነው፡፡በልቡ እንቆቅልሽ ታቅፎ ከከንፈሩ የእግዚአብሔር ምስጋና የማይጎድልበት ምስጉን ነው፡፡ ዛሬም ሆሳዕና እንበል፥ የምስጋና ነዶ በፊቱ እያከማቸን አቤቱ አሁን አድን እንበል፡፡ የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ እያልን እንጩህ!
ወንጌል ስለ ሆሳዕና ምን አለ?
ለጌታ ያስፈልጉታል!
"በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።" (ማቴዎስ 21:2)
  ደቀመዛሙርቱ የታሰሩትን እንዲያስፈቱ ተልዕኮ ሲሰጣቸው "ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ" ከሚል ትእዛዝ ጋር ነበረ፡፡ ጌታ ወደዚህ ዓለም የመጣው በኃጢአት የታሰረውን የሰውን ልጅ ለመፍታት ነው፡፡ አዎ!  ታስሮ አስፈትቶናል፥ ወድቆ አንስቶናል፥ ደሙን ክሶ ከማዕሰረ ኃጢአት ቶናል፡፡ ዛሬም በሱስ በኃጢአት በተንኮል በክፋት በአመፃ ወደታሰሩት ሰው ይልካል! ከሞት ጋር ወደተስማሙት የምዋቹን ሞት የማይፈቅድ ጌታ አገልጋዮችን ይልካል፡፡ እኛ ተስፋ የቆረጥንባቸው ሁሉ ለጌታ ያስፈልጉታል፡፡ ዛሬም የታመሙ እንዲፈወሱ፥ የወደቁ እንዲነሱ፥ የታሰሩ እንዲፈቱ፥ ያዘኑ እንዲጽናኑ፥ የተሰበሩ እንዲጠገኑ፥ የጠፉ እንዲገኙ ክርስቶስ ይፈልጋል፡፡ የኃጢአት እሳት ላይ የሚጫወተው፥ በሞት መንደር ያንቀላፋው ትውልድ ባለቤት አለው፡፡ ፈላጊ አለን፥ አክባሪ አለን፥ የማይጸየፈን አባት አለን፡፡ በራሳችን ተስፋ የቆረጥን፥ ለማንም አላስፈልግም የምንል ለጌታ እናስፈልጋለን፡፡
ንጉሣችን ይመጣል! 
" ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።" (ማቴዎስ 21:4-5)
   በመገፋት የእርሱን ቀን ለምትጠብቁ፥ ቀን ያስጎነበሳችሁ፥ ከተማችሁ በቅኝ ገዥዎች የተያዘባችሁ፥ ስጦታው ነክቷችሁ በጸጋ ተሹማችሁ ዙፋን ተከልክላችሁ ወደ ምድረ በዳ የተሰደዳችሁ፥ ወንድማችሁ የቃየልን ድንጋይ እያሳየ የሚያስፈራራችሁ ንጉሣችን ይመጣል የሚያነግሰው ይመጣል ቀን አውጭው ይመጣል የሆሳዕና የዋህ ሆኖ እንደ ትንቢቱ የመጣው በስልጣን ይመጣል!
የሚቀድሙት እና የሚከተሉት የእርሱ የምስጋና ሠራዊት ናቸዉ!
" የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።" (ማቴዎስ 21:9)
  በአህያ ጀርባ ያየነው በእሳታውያን ኪሩቤል እና በሱራፌል ጀርባ የነበረ ነው፤ ይህ ምስጋና ይገባል። የሚቀድሙት ነቢያት፡ የሚከተሉት ሐዋርያት አመስግነውታል። ወደፊትም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በጉን ይከቡታል፤ ወድቀው ይሰግዱለታል፡፡ ትውልድ ለምስጋና ይነሳ ለእርሱ ያንጥፍ ለእርሱ መንገዶች ሁሉ ክፍት ይሁኑ ለእርሱ አንደበት ሁሉ ይቀኝ ለእርሱ ትልቅ ትንሹ አዋቂ ሕፃኑ ምስጋና ያቅርብ!
ይህ ማን ነው ?
"ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ።" (ማቴዎስ 21:10)
  ይህ ማነው ከተማ የሚናወጥለት ? ይህ ማን ነው ዓለሙ ሁሉ የሚከተለው ? ይህ ማነው ? ይህ የኛ ልዑል ነው፡ ይህ የኛ ቤዛ ነው፡፡ ይህ የኛ የዘመናት ወዳጅ ነው፡፡ ይህ የኛ አምላክ ነው። ሞገድ ባሕር የሚታዘዝለት ይህ ማን ነው ? ልዑል ሳለ በትሕትና የተገለጸ ይህ ማነው ? ንጉሥ ሆኖ ሳለ የዋህ የሆነ ይህ ማነው? ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
አንኩራበት፦ 
" ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው።" (ሉቃስ 19:39-40)
  እርሱ የምስጋና ጌታ ነው፤ ባናመሰግነው ምስጉን ነው፡፡ በምስጋና የምንጨምርለት፤ ባለማመስገን የምንቀንስበት ነገር የለም፡፡ ስለዚህ አመስጋኞችን አንገስጽ፡፡ እጃችንን አጣጥፈን ዳር ይዘን ተመልካች አንሁን፡፡  ሜልኮል ኮርታ ምን አተረፈ? አንኩራ አንታበይ እኛ ዝምታን ብንመርጥ ድንጋዮች እንኳ ለቅኔ ሊነሱ ዝግጁ ናቸውና፡፡
የልባችን ደጅ ይከፈት! 
" ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፥ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ።እናንት መኳንን በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ።ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል።" (መዝ 24:6-9)
  ዛሬ የቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮ በዚህ ቃል የተመሠረተ ነበረ፡፡ ይህ ልዑል የዘላለም ደጆችን የከፈተ ነው፥ የሕይወት ቁልፍ በእጁ ነው፥ የገነት ቁልፍ በእጁ ነው፥ የስኬት ቁልፍ በእጁ ነው፡፡
ለሁሉ የከፈተ እርሱ እንዴት ደጅ ይዘጋበታል? መኳንንት ሆይ ክፈቱ! ሁሉም በተሾመበት ነገር ባለስልጣን ነው በሀብት በእውቀት በውበት በስልጣን ተሹመን ይሆናል እንዳንከፍት እነዚህ ነገሮች አጥምመውን ይሆን ? አታለውን ይሆን? በሚያልፈው ነን ከማያልፈው እንዳንጎድል የልባችንን ደጅ እንክፈት፡፡
እርሱ ይኑርብን፦
አህያዋ እርሱን በመሸከሟ ተከበረች፡፡ በልዩ አጀባው ውስጥ ተራመደች፡፡ እርሱ ያለው ሞገስ አለው፡፡ በተለይ በሰማይ የበለጠ ክብር ይጠብቀዋል፡፡ ልባችን የእርሱ ዙፋን ከሆነ መክበር አለ፡፡እርሱን እያሳየን እንዙር፡፡ " የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።" (2 ቆሮንቶስ 4:10)
ለሰላማችን የሚሆነውን አንግፋ፦ 
"ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮል::ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።" (ሉቃስ 19:42-44)
  ክርስቶስ የሰላም አለቃ ነው፡፡ እርሱ የሌለው ሰላም የለውም፡፡ እርሱ የልብ ሰላም፣ ዕረፍት እና መድኃኒት ነው፡፡ ለሰላማችን የሚሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ለእርሱ ደጅ አንዘንጋ፡፡ለእርሱ ጀርባ አንስጥ፡፡ ሰላሙን ለመጠቀም ልባችንን ክፍት አድርገን እንጠብቀው፡፡