Wednesday, August 22, 2018

❖በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ (የምታርግ) ይህች ማን ናት?




በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ (የምታርግ) ይህች ማን ናት?”
                             (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 85)
                            **የድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት**

በክርስትና ስም ከሚጠሩ ቤተ እምነቶች በተለየ መልኩ፥ቀጥተኛ መንገድየሚል ትርጉም ያለው የኦርቶዶክስ እምነትን የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያን ለተቀደሰው ሐዋርያዊ ትውፊት (Holy Tradition) ትልቅ ቦታ አላቸው። ቅዱስ ትውፊት የምንለው ከቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ዘመን ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣውን አስተምህሮ እና ሥርዓተ አምልኮ ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስም እኛ ዘመን የደረሰው በዚሁ የተቀደሰ የትውፊት ሰንሰለት ነው። ለዚህም ነው ኦርቶዶክሳውያን አበው፦መጽሐፍ ቅዱስ፥ በተቀደሰው የትውፊት ዛፍ ላይ የበቀለ መልካም ፍሬ ነውየሚሉት።
የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፥ በምድረ ፍልስጥኤም 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን በዓለ ዕረፍት ወፍልሰት ማክበር እንደጀመረች የሚጠቁሙ ታሪካዊ መረጃዎች አሉ። በዚሁ ዘመን “The Dormition and the Assumption of the body of St. Mary into Heaven” በሚል ርእስ ዙሪያ የሚያትቱ ጽሑፎች በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይጻፉ እንደነበር በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ከነዚህ ጥናቶች መካከል ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ያተረፈው የሚከተለው መጽሐፍ ነው፦ Stephen Shoemaker, Ancient Traditions of the Virgin Mary’s Dormition and Assumption, Oxford University Press, 2006. በፍልስጥኤም (Palestine) የተጀመረውበዓለ ዕረፍታ ወፍልሰታ ለማርያምቀስ በቀስ ወደ ምዕራቡ ዓለም ደርሶ፥ 8ኛውና 9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዓለም አቀፋዊ በዓል ለመሆን ችሏል። ይህን በዓል ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያን August 15 ቀን ሲያከብሩት፥ ጥንታዊውን Julian Calendar የምትከተለው ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ነሐሴ 16 (August 22) ቀን በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች።
በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?” የሚለው የንጉሥ ሰሎሞን ዝማሬ፥ ሕይወቷን በሙሉ አምላኳን ያከበረች ነፍስ ከሥጋዋ ተለይታ ወደ፡ምትወደው ጌታ ስትሄድ የሚጠቀስ ጥቅስ ነው። ከዚህ በተሻለ መልኩ ግን፥ እመቤታችን ድንግል ማርያም በልጇ ኃይል ከሞት ተነሥታ፥ ንጽሕትና ቅድስት የሆነችውን ነፍሷን ውድ ልጇ በክብር ተቀብሎ ወደ መንግሥቱ ያሳረገበትን በዓል ለመዘከር ልንጠቀምበት እንችላለን። እንዲያውም የግእዙ ንባብ፦ መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ተዐርግ እም ገዳም አንተ ትትመረጐዝ በወልድ እኁሃ? - በውድዋ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምታርግ ይህች ማን ናት?” ያላትን፥ ሠናይት ከመ ወርኅ፥ ወብርህት ከመ ፀሐይ - እንደ ጨረቃ የተዋበች፥ እንደ ፀሐይም የምታበራበማለት ስለሚገልጻት፥ በፈቃድ ከሚሰራው የግል ኃጢአት ነጻ ለሆነችው ለቅድስቲቷ የእመቤታችን ነፍስ ዕርገት በእጅጉ የሚስማማ አገላለጽ ነው። ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሳብ በሥነ-ሥዕል (iconography) ለማመልከት፥ ኦርቶዶክሳዊ ሥዕል (icon) ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለመገነዝ አንደተሰበሰቡና ጌታ በሕፃን ልጅ አምሳል በነጭ መጎናጸፊያ የተጠቀለለችውን የብፅዕትና ቅድስት እናቱን ነፍስ ታቅፎ ያሳያል። ጌታን በሕፃንነቱ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ታቅፈው እንደነበር፥ እርሱ ደግሞ በተራው በዕረፍቷ ቀን የእናቱን ንጽሕት ነፍስ ታቅፎ ወደ መንግሥቱ ዘላለማዊ ክብር አገባት።
በሞቱ ሞትን ድል የነሣልን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ከሞት በኋላ የሚጠብቀን ትንሣኤ በኵር እንደሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጽፎልናል (1 ቆሮ1520) ይኸው ሐዋርያ ስለ ሙታን ትንሣኤ ሲጽፍ ሥጋዊ አካላችን ወደ አፈርነቱ ከተመለሰ በኋላ (በመበስበስ ከተዘራ በኋላ) መንፈሳዊ አካል ሆኖ በክብር አንደሚነሳ አስተምሮናል (1 ቆሮ 15 42-50) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ለፍርድ ሲመጣ፥በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸውእንደተባለ (ራእይ 1413) በምድራዊ ኑሮአቸው ክርስቶስን ለብሰው የኖሩ የእግዚአብሔር ልጆች የክብር ትንሣኤ ይነሳሉ። ለዚህም ነው ሐዋርያው፦ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” (ፊልጵ 321) ሲል ስለሚጠብቀን ዘላለማዊ ክብር የነገረን።
እንግዲህ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን፦ወላዲተ አምላክ ማርያም ሞትን ድል ባደረገው በልጇ ኃይል ከሞት ተነስታ ወደ ልጇ መንግሥት አርጋለችብላ ስታስተምረን፥ የአምላካችን ልጆች የሆንን ሁላችን በእግዚአብሔር መንግሥት የሚጠብቀንን ክብር እመቤታችን ቀድማ አግኝታለች ማለቷ ነው። ጌታ በትንሣኤው በኵር እነደሆነን፥ ቅድስትና ብፅዕት እናቱ ደግሞ ወደ ሰማያዊው መንግሥት በመግባት ቀዳሚት (በኵር) ሆነችን። ንጉሡ ጌታችን ኢየሱስ ከመንግሥቱ የተለየበት ጊዜ ፈጽሞ እንደሌለ እናውቃለን፤ መንግሥቱ ያለው ንጉሡ ባለበት ቦታ ነውና። ሁላችን ተስፋ የምናደርገውናወደ ጌታህ ደስታ ግባ” (ማቴ 2522) የሚለው፥ በእርሱ ሕያዋን ሁነን በመንግሥቱ ለዘላለም የመኖራችን እውነታ (eschatological fulfillment) ከሁላችንም ቀድሞ ለቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ተደረገ። ከመለኮት ባህርይ ተካፋይ የሆንበትን (2 ጴጥ 14) ምስጢር (theosis - ሱታፌ አምላክ) ከእግዚአብሔር በተሰጣት የተለየ ጸጋ በንጽሕና እና በቅድስና አጊጣ በሕይወቷ እውን ስላደረገችና ከቅዱሳን መካከል በንጽሕና የሚስተካከላት ስለሌለ፥ እመቤታችን ከቅዱሳኑ ሁሉ ቀድማ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ገባች ቢባል ጥያቄ ሊፈጥርብን አይገባም። ደግሞም አምላክን በድንግልና ወልዳ ላሳገደች እመቤት የሚገባት የክብር ሰማያዊ ፍጻሜ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም።
እግዚአብሔር ወልድ ከእመቤታችን የነሳው ሥጋ የእኛ ሥጋ እነደሆነ ግልጽ ነው፤ 318 የኒቂያ ጉባኤ አባቶች ስም የተደረሰው የቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴ፦ተዘከር ሥጋ እንተ ነሣእከ እምቅድስት ድንግል እንቲአነ ሥጋ አኮ እምሰማያት ዘአውረድከ - ከቅድስት ድንግል የነሣኸው ሥጋ የእኛ ሥጋ እነደሆነ፥ ከሰማይ ያወረድኸው እንዳይደለ አስብእንዲል (. 121) የመልአኩን ብስራትይኩነኒ በከመ ትቤለኒብላ ከተቀበለችበት ቅጽበት ጀምሮ እግዚአብሔር አብ በልጁ በኩል ያደርግ ዘንድ ላሰበው የማዳን ሥራ ድንግል ማርያምን መሣሪያ አድርጓታል። ልዑል ማደሪያውን ቀድሶ፥ቅድስተ ቅዱሳን - Holy of Holies” የተሰኘች የአንድ ልጁ ማደሪያ ትሆን ዘንድ መረጣት። ስለዚህ የድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት በዋነኝነት የሚያመለክተው፥ እነ ቅዱስ ኤፍሬም፦አንቲ ውእቱ ደብተራ እንተ ተሰመይኪ ቅድስተ ቅዱሳን . . . መቅደስ ዘይኬልሉኪ ኪሩቤልብለው ያወደሷት የጌታ ንጽሕት መቅደስ በመንግሥቱ መክበሯን ነው። ይህ የመንግሥቱ ክብር (glorification) ደግሞ የእኛም ክብር ስለሆነ በዚህ የተቀደሰ ትውፊታው አስተምህሮ ደስ ሊለን እንጂ፥ በጭራሽ ሊከፋን አይገባም።
አባቶቻችን፥ መሐሪው ጌታ እኛን የወደደበትን ዘላለማዊ ፍቅርንና ለእኛ ያደረገውን የማዳን ሥራ በመጽሐፈ ቅዳሴ፦ እንተ አፍቀርካ ለዛቲ ዘመድነ - ይህችን ባሕርያችንን የወደድሃት ሆይበማለት አድንቀዋል። እኛም ለእመቤታችን የተደረገው (ለአምላክ እናትነት መመረጧ፥ ዘላለማዊ ድንግልናዋ፥ ከፍጡራን ማንም የማይስተካከለው ቅድስናዋ፥ ከሞት ተነሥታ ማረጓ) ለድኅነታችን (ለመዳናችን) የተደረገና የእኛን ሰብዓዊ ባሕርይ ልዩ ክብር (glory) የሚያንጸባርቅ ስለሆነ በዚህ ሁሉ ደስ ይበለን፥ ሐሴትም እናድርግ። በሔዋን የተዋረደው ሰብዓዊ ባሕርያችን በዳግሚት ሔዋን (በድንግል ማርያም) ስለከበረ እንደ አባቶቻችን ትምህርት እመቤታችንን፦ትምክሕተ ኵልነ/ ትምክሕተ ዘመድነእንበላት። ይህን እውነት ሲያመሰጥር፥ በሶርያዊው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ስም የሚጠራው የኢትዮጵያውያን አባቶቻችን አኰቴተ ቊርባን፦ወካዕበ ተማኅፀነ በማርያም እምከ እንተ ይእቲ እግዝእትነ ወትምክሕተ ዘመድነ በወሊዶተ ዚአከ - ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናትይላል (. 99)
በመጨረሻም፥ ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አምላኩ እንደወሰደው (ዘፍ. 524) ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀናዒ የነበረው ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሰረገላና በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ አንደተነጠቀ (2 ነገ. 2 11) ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነበበ ሰው፥ የወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ወደ መንግሥተ ሰማያት መወሰድ ጥያቄ ሊፈጥርበት አይገባም።እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም” (1 ነገ. 827) የተባለለትን አምላክ፥ ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ተሸከመችው። ስለሆነምዳግሚት ሰማይ፥ ዳግሚት አርያም፥ ሰማይ ዲበ ምድር (በምድር ላይ ያለች ሰማይ)” ተባለች፤ ወንድሞቻችን ኦርቶዶክሳውያንም እንደ እኛ አባቶች፦ “O St. Mary, your womb is more spacious than the heavens” ብለው ዘመሩ። ስለዚህ የድንግል ማርያምን ወደ ሰማይ ማረግ (ዕርገት) እየተቃወሙ የትዕቢት ቃላትን ከመሰንዘር ይልቅ፥ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምሕሮ በትሕትና በመማር፥ ዳግሚት ሰማይ (ድንግል ማርያም) በዕለተ እሑድ ከተፈጠረው ሰማይ ጋር ኅብረት በማድረጓ እጹብ እያልን እናድንቅ፤ ይህን ሁሉ ላደረገ አምላካችንም የከንፈራችንን ፍሬ የምስጋና መሥዋዕት አድርገን እናቅርብለት (ዕብ. 1315)
ማደሪያ መቅደሱን ያከበረ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድስት እናቱ ጸሎትና ልመና በሰማያውያንና ምድራውያን በረከቶቹ ሁሉ ይባርከን፤ ለቅዱሳን አባቶቻችን የሰጠውን የእመቤታችንን የእናትነት ጣዕምና ፍቅር ያብዛልን።