Saturday, June 15, 2019

❖መንፈስ ቅዱስ፦

መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

፩. መንፈስ ቅዱስ ማን ነው?

  ☞ ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል ነው፡፡

  ☞ የማይጨበጥ፤የማይታይ አካል ያለው መንፈስ ነው፡፡

  ☞ የሰረፀው (የወጣው) ከአብ ነው።

  ☞ ከአብ ከወልድ ጋር እኩል ምስጋና አምልኮ ይገባዋል

  ☞ እግዚአብሔር (አምላክ) ነው፡፡

  ☞ የአብ የወልድ እስትንፋስ (ሕይወት)ነው፡፡

  ☞ በነቢያትና በሐዋርያት አድሮ የተናገረ፥ሕይወትንም ያቀና : ምድርን ለክብሩ ያስጌጠ ነው፡፡

፪. የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ምን ምን ናቸው? ርግብ፣ እሳት፣ ውኃ፣ ዘይትና ነፋስ ናቸው። 

☞  ርግብ የዋህ ናት፡ መንፈስ ቅዱስም የዋህና ቂም የማያውቅ ነው፡፡ ርግብ በኖህ ዘመን የጥፋት ውኃ መድረቁን  ያወጀች  የሰላም ምልክት ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ክርስቶስ ሲጠመቅ የኃጢአት ባሕር መድረቁን በርግብ ምሳሌ ወርዶ የሰበከ የሰላም ጌታ ነው።

☞  እሳት ያበስላል፡ መንፈስ ቅዱስ ሕፃን የሆነውን አእምሮ በጥበብ ያጎለምሳል፡፡ እሳት የከበረ ማዕድንን ከአፈር ይለያል፥ መንፈስ ቅዱስም አምኖ የከበረውን ፡ ካላመነው ይለያል፡፡

☞  ውኃ ያነፃል፥ መንፈስ ቅዱስ ይቀድሳል፡፡

☞  ነፋስ፣ ነፍስና መንፈስ የሚወጡበት የግሪክ ቃል ኒዩማ የሚል ሲሆን ከነፋስ- ነፍስ፤ ከነፍስ- መንፈስ ይረቃል። ነፋስ በእንቅስቃሴው እንደሚታወቅ መንፈስ ቅዱስም በሥራው ይታወቃል፡፡

❖  በብሉይ ኪዳን የመብራት ዘይት ነበረ፥ በየዕለቱ በመቅረዙ ይጨመራል፡፡ ይህ የመብራቱ አለመጥፋት የመንፈስ ቅዱስን መኖር ያመለክታል፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ ለቅርፅ አልባዋ መሬት ውበት ያፈሰሰ፥ ውኆችን ለፍጥረት ጥቅም የቀደሰ ጌታ ነው፡፡ "ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።" ኦሪት ዘፍጥረት 1:2።

❖  መንፈስ ቅዱስ መሳፍንትን በምስፍና፥ ነገሥታትን በንግሥና፥ ካህናትን በክህነት ጸጋ፥ ነቢያትን በሀብተ ትንቢት፥ ዘማርያንን በዝማሬ ጸጋ፥ ፈዋሾችን በሀብተ ፈውስ ......የሾመ...ጸጋ የሰጠና ጸጋን ያደላደለ ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ ቅድስት ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም የሆነላትን እንድትረዳ አደረባት፡፡ ድንግል ማርያም በድንግልና እንድትወልድ ሁሉን አስቻላት፡፡ በክርስቶስ አገልግሎት ነበረ፡፡ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ መምጣት ተናግሯል፡፡

☞   "አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።" የዮሐንስ ወንጌል 14:26

☞  "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ስለ ፍርድም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው። የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።" ዮሐንስ 16:7-15::

☞   " ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤" የዮሐንስ 15:26።

☞  " ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" ዮሐንስ 14:15-16::

❖  በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአደራረጉ ምክንያት:- 

    ☞  የእውቀት መንፈስ፣ 

    ☞  የጥበብ መንፈስ፣ 

    ☞  የኃይል መንፈስ፣ 

    ☞  የእውነት መንፈስ፣ 

    ☞  የመገለጥ መንፈስ፣ ...ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በክርስቶስ አገለግሎት የነበረው ሱታፌ እንዳለ ሆኖ በክርስቶስ ትምህርት እንዴት እንደተገለጠ ከላይ ባሉት ጥቅሶች አይተናል፡፡ በክርስቶስ ትምህርት አጽናኝ(ጰራቅሊጦስ)፣ የእውነት መንፈስ እና ሁሉን የሚነግር መምህር ተብሏል፡፡ የሚመጣው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፡፡ የሚመጣበት አላማ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ነው፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የማያምኑትን ይወቅሳል፤ የዲያብሎስን መጣል ይናገራል፤ ጽድቅ ወደ አብ በሄደው በክርስቶስ እንደሆነ ይመሰክራል፤ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ይመራል፤ ምእመናንን ያጽናናል፤ ለበጉ ሠርግ ያዘጋጃል፤ አገልጋዮችን ያሰማራል፡፡ 

❖  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባረገ በአስረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም መጣ፤ በጽርሐ ጽዮን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተወለደችውን የክብርት ቤተክርስቲያን ልደት በእሳት ላንቃ በዓለም ቋንቋ አከበረ፡፡ ሐዋርያትን ለእውነት አስጨከነ፤ ምስጢር እና ብዙ ቋንቋዎች ገለጠላቸው፡፡ በጉዞቸው ሁሉ አብሮ ነበረ፡፡ ዛሬም የቤተክርስቲያን አገለግሎት ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ነውና ክብር ለመንፈስ ቅዱስ!!

❖  ላመነ ሰው ጥምቀት የሚፈጸመው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ይህም የክርስቶስ ትእዛዝ ነው፡፡ ማቴ 28:19:: በጥቅሉ ያለ መንፈስ ቅዱስ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አይፈጽሙም፡፡ የምስጢራቱ አፈጻጸም ሥርዓት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ 

በመግቢያዬ እንደጻፍኩት ቤተክርስቲያን ስለ መንፈስ ቅዱስ ጠንካራ አቋም አላት፦ "ማህየዊ በሚሆን በአንድ ጌታ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እርሱም ከአብ የሰረፀ ነው፡፡ በነቢያት እና በሐዋርያት ተናግሯል፡፡ ከአብ ከወልድ ጋር ምስጋና ይገባዋል።" ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ ፰.

መንፈስ ቅዱስ፦

☞  ሕይወት ሰጭ፤ ጥበብ ገላጭ መንፈስ ነው፡፡

☞  የጸጋ ምንጭ እና አደላዳይ ነው፡፡

☞  ለበጎ ሥራ ቀስቃሽ፤ከኃጢአት እንድንወጣ ወቃሽ ነው

☞  ልብን አይቶ የሚሾም፤ ትሁታንን የሚያከብር ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡

❖  መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ኃይል ነው፡፡ ብርታት የሆነን እርሱ ነው፡፡ ስንደክም ያግዘናል፡፡ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል(ሮሜ 8:26-27)፥ እንዴት ማምለክ እንዳለብን ይመራናል፥ ከዚያ ጸሎታችንን ይሰማል፤ አምልኮችንን ይቀበላል፡፡

❖  የመንፈስ ቅዱስ ነገር ለፍጥረታዊው ሰው ሞኝነት ነው፡፡ "ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም።" 1ቆሮንቶስ 2:14። የመንፈስ ቅዱስ ጉዳይ በእምነት መንፈስ እንጂ በሥጋ አይመረመርም፡፡ የጰራቅሊጦስ የተቀበልነው ይህን የእውነት መንፈስ ነው፡፡ "እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።" 1ቆሮንቶስ 2:12።

❖  መንፈስ ቅዱስ በፍጥረታዊ ሰው አይኖርም፡፡ እንዲያውም የክርስቶስ መንፈስ የሌለው የክርስቶስ ወገን አይደለም፡፡ "የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።" ሮሜ 8:9።

❖  ምክር፣ ጥበብ፣ ምስጢር፣ ትንቢት፣ ፈውስ፣ ዝማሬ፣ ሹመት፣ ኃይል .... ከመንፈስ ቅዱስ ይሰጣሉ፡፡ ደስታ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የዋሃት፣ ራስን መግዛት፣ ትዕግስት፤ በጎነት፣ ቸርነትና ሰላም የመንፈስ ፍሬ ናቸው፡፡ ገላ 5:23:: 

❖  መንፈስ ቅዱስ ከምንተነፍሰው አየር በላይ ያስፈልገናል፡፡ በሥራችን ዐመፃ የመንፈስ ቅዱስን አሠራር ልንቃወም እንችላለን፡፡ "መንፈስን አታጥፉ፤" 1ተሰሎንቄ 5:19። ንጉሥ ዳዊት በበደለ ጊዜ ይህ አጋዥ፣ አስተማሪ፣ መሪ እና አጽናኝ መንፈስ እንዳይወስድበት ለመነ፡፡ "ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።" መዝሙረ ዳዊት 51:11።

❖  መንፈስ ቅዱስ ከተለየን ሕይወት፣ ሰላም፣ ዕረፍት፣ መንፈሳዊነት ... የንስሐ ጸጸት...ይለዩናል፡፡ ስለዚህ "ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።" ኤፌ 4:30-32:: የሥጋ ሥራ ከመንፈስ አላማ ያወጣል፡፡ የሥጋ አሠራር መንፈስ ቅዱስን ይቃወማል፡፡ ደስታ የሰጠን ሀዘን ሊቀበል አይችልም፡፡ ባናከብረው ደስታ የምናጣው እኛ ነን፡፡ " ለአሠራሩ እንመች፡፡ በኖህ ዘመን ርግቧ በመጀመሪያው ጉዞዋ ማረፊያ አጥታ እንደተንከራተተች መንፈስ ቅዱስም ለአሠራሩ የሚመች ሰው አጥቶ በዙሪያችን አለ።" ለአሠራሩ እንመች፡፡ እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሰን፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ አንብቡ ፥ ዘምሩ፡፡ 

 ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይገባል!!! 

Sunday, June 9, 2019

❖የጠፋው ልጅ፦

✞📖የጠፋው ልጅና የእግዚአብሔር ፍቅር!

    💌በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከተዘገቡልን ድንቅ ምሳሌዎች አንዱ የጠፋው ልጅ ምሳሌ ነው። የጠፋውን ልጅ ታሪክ ስናነብ በእንባ እንሞላለን። ጽድቅ ሳለ ኩነኔ፣ ዕረፍት ሳለ ሁከትን መርጦ ለሚቅበዘበዘው የሰው ልጅ የፍቅር ዕንባ እንድናፈስ ያደርገናል። ከሁሉ በላይ ግን የጠፋው ልጅ አባት ፍቅር በዕንባ እንድንታጠብ ያደርገናል። ወደ እርሱ አንድ እርምጃ ሲመጡ አስር እርምጃ ወደ ጠፉት የሚመጣ፣ ሂሳብ ለመተሳሰብ የማይሻ፣ ተበደልኩ ሳይሆን ተጎዳችሁ ብሎ የሚያለቅስ ፣ ከነ ቆሻሻ የሚያቅፍ ፣ ልብስን ታሪክን የሚለውጥ ያ አባት ፍቅሩ ያስለቅሳል።

    📝 የጠፋው ልጅ ታሪክ የፈጠራ ድርሰት ወይም የሩቅ ዘመን ሀቅ አይደለም። የጠፋው ልጅ እኛ ነን። ወይ ጠፍተን እየተጎዳን ነው አሊያም የተገኘን ነን። በጠፋው ልጅ ታሪክ ላይ ደርበን ከመጻፍ ውጭ የግርጌ ማስታወሻ መያዝ አንችልም። የታሪካችን ማስታወሻ ምውትነት ነው። ለዚህ ነው ሐዋርያው፦ "በበደላችሁና በኃጢያታችሁ ሙታን ነበራችሁ" የሚለወ(ኤፌ.2፥1)።  ሞትን በነበር ያስቀረልን የሕይወት ራስ የሆነው ክርስቶስ ነው። የተፈቀረው ይህ ምውት ማንነት ነው። ምውትን ማን ይቀርበዋል? ቅድም ስንዳብሰው ቆይተን ሲሞት ሬሳው ብለን እንሸሸዋለን። እኛን የወደደ ቡሩክ ነው!

   "የጠፋው ልጅ ነበርኩ እጅግ ቀበዝባዛ፣
    የነፍሴ መድኃኒት ኢየሱስ ሆነኝ ቤዛ"
እያልን ከመዘመር ውጭ ሌላ ቃል የለንም።

     📝ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ስለ መጥፋት በብዙ ይጽፋል። የሉቃስ ወንጌል መሪ ጥቅስም፦ "የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና" የሚል ነው(ሉቃ.19:10)።  ሉቃስ ይባስ ብሎ ስለ ጠፋው ኢየሱስ ጽፏል(ሉቃ.2:41-51)።  ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ቀን መጓዝ እርሱን ለማግኘት ሦስት ቀን ያንከራትተታል። መጸለይን፣ ኅብረት ማድረግን ለአንድ ቀን መተው ሰላሙን ለመመለስ ሦስት ቀን ይፈጃል።

💌ወንጌላዊው ሉቃስ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣበትን ዓላማ ሲገልጥ፦ "የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና" ብሏል(ሉቃ.19:20)። ታዲያ በምዕራፍ 15 ላይ ስለ ጠፊዎች ወይም ስለ ጠፉ ወገኖች በሙሉነት ይተርካል።  የጠፋው በግ፣ የጠፋው ድሪም(ገንዘብ)፣ የጠፋው ልጅ።
የጠፋው በግ በደጅ፣ የጠፋው ድሪም በቤት፣ የጠፋው ልጅ በሩቅ አገር ነው። የጠፋው በግ በሞኝነት፣ የጠፋው ድሪም አለሁ እያለ በመሞት፣ የጠፋው ልጅ በምርጫ ነው። የጠፋው በግ አለማውያንን ይመለከታል። ባለ ማወቅና በሞኝነት ጠፍተዋል። መመለሻውን አጥተው የሚንከራተቱ ምስኪኖች ናቸው። የጠፋው ድሪም ግን ያለሁት እዚሁ ነው ብሎ መጥፋቱን ማወቅና ማሳወቅ አይችልም። የጠፋውም በደጅ ሳይሆን በቤት ውስጥ ነው። በእግዚአብሔር ቤት የጠፉ፣ አለን እያሉ ተበልተው ያለቁትን አገልጋዮችና ምዕመናንን ይመለከታል።

   "በአደባባይ ቆሜ ስምህን ከመስበክ
     መጀመሪያ ልቤ ለፍቅርህ ይንበርከክ
     ከአገልግሎት በፊት አንተን ልወቅህ
     መሥዋዕት ከማቅረብ ልታዘዝልህ"
ማለት ይሻላል።

     📖የጠፋው ልጅ የጌታን ሰላም ቀምሶ ፣ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተካፍሎ፣ በሰላሙ አርፎ የነበረ ምዕመንን ይገልጣል። ይህ ምዕመን ግን ትንሹ ሰላምን ዕረፍት ለዘላለም የሚኖር መስሎት በቃኝ ብሎ ሄዷል። ጸጋም ያልቃል። ጸጋው ቀጣይ የሚሆነው ባለጸጋውን ጌታ ስንይዝ ብቻ ነው። የጠፋው ልጅ እኛው ነን።

   📝 ሉቃስ ትረካውን በድንቅ ይጀምራል።

" እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ"
በማለት ይተርካል(ሉቃ.15:11-13)።

     💌ሁለት ልጆች ያሉት አባት እግዚአብሔር ነው። የመጀመሪያው ልጅ አይሁዳውያንን ይወክላል። የመጀመሪያዎቹ እድምተኞች፣ ደግሞም በኩር ፍሬ ናቸው። ሁለተኛው ልጅ ከአይሁድ ውጪ ያሉትን አማንያንን ያመለክታል። ሁለቱም ልጆች የየራሳቸው ጠባይ ቢኖራቸውም ለአባታቸው ግን አልተመቹትም። እንደ እርሱ አልሆኑም ታናሹ ልጅ አባቱን ሳይሆን ንብረቱን የሚወድ ነበር፣ ከዚያም ኮብልሎ የባከነ ነው። ታላቁ ደግሞ ንብረቱን ተካፍሏል፣ ግን በቤት ውስጥ ይኖራል። የቤት ውስጥ አቁሳይ ነው። ኋላ ወንድሙ ሲመለስም ደስተኛ አልነበረም። የወንድም ፍቅር የለውም። ግን በቤት የሚኖር ደግሞም ትጉህ ሠራተኛ ነው።  ፍቅር የሌለው ትጉህ ነው። የአባቱ ቤት ለእርሱ መሥሪያ ቤት ነው። ታናሹ ልጅ የተካፈለው ገንዘብ ምንድነው? ሰላም፣ ደስታ፣ ጸጋ፣ በረከት ነው። ከአባቱ ጋር ይኖር የነበረው ለእነዚህ ጉዳዮች ነው። እነርሱንም ተቀብሎ ቢኖር አባቱ አይከፋውም ነበር። ይባስ ብሎ ነጥቆት ሄደ።

       📖ሉቃስ ትረካውን ቀጠለ፦
" ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም።"(ሉቃ.15:14-16)

        📝ያ የጠፋው ልጅ የከሰረው አንዳንድ ነገሮችን አይደለም ሁሉንም ነገሮች ነው። ከእግዚአብሔር ስንርቅ ሁሉም ነገር ይከዳናል። ያለን ሁሉ የሚኖረን ከእግዚአብሔር ጋር ሳለን ብቻ ነው። የጠፋው ልጅ ቤተኛ ከሚሆንበት ኑሮ ወጥቶ ተዳበለ። የኮበለለ ምዕመን ኑሮው የደባል ነው። ደባል፦ ነጻነቱ የተገደበ፣ የማይፈልገውን ለማየት የተዳረገ፣ ጸጥታ የሌለው፣ ስድብ የሚጠግብ፣ የማይመለከተውን በግድ የሚያስተናግድ ነው። የጠፋው ልጅ ከራቡ የተነሣ የእርያ እረኛ ሆነ። እርያ ለአይሁዳውያን ርኩስ ነው። በረከሰ ተግባር ላይ ተሰማራ። ከእርያ ምግብም ለመጥገብ ይመኝ ነበር፣ ግን አልሆነለትም። የእርያ ምግብ እርያን እንጂ ሰውን አያጠግብም። የእሪያው ምግብ መጠጥ፣ ሲስ....ነው። መጠጥ፣ ዘፈን....ለዓለማውያን ይደልል ይሆናል፣ እውነትን ቀምሶ ለነበረ ግን በፍጹም አይሆንም። ማደንዘዣው እርሱ ላይ አልሰራ አለ። ዓለማውያን ኃጢያት ሠርተው የሚያገኙትን ጊዜያዊ ሣቅ ፣ ጊዜያዊ መዘናጋት እንኳ ማግኘት አቃተው። አካሉ ኃጢያት ስፍራ ልቡ ግን አባቱ ቤት ሆነ። እየጠጣ ያለቅሳል፣ ሱስ ላይ ተቀምጦ ዝማሬው፣ ቅዳሴው ይሰማዋል።

  " ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።" (ሉቃ.15:17-19)።

    💌ወደ ወደ ልቡ ሲመለስ የአባቱ ቤትና ክብሩ ታየው። እንኳን ልጅ ባሪያም የሚጠግብበት በረከት ታወሰው። የንስሐ መንስ ገዛው።  አባቱ ተራ አባት አይደለም። ሰማይን የሚገዛ ነው። ደግሞም ያየዋል። "በፊትህ በደልሁ" እለዋለሁ አለ። በእግዚአብሔር ቤት ትንሹን ድርሻ ናፈቀ። ትንሹም ትልቅ ነውና።

   📖ሉቃስም ቀጠለ፦

"ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ፦ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር።" (ሉቃ.15፥20-24)

      📝አባቱ ልጁን የተለየው በግድ ነው። ልቡ አላረፈም። ማዶ ማዶ እያየ ይጠብቀው ነበር። እስኪደርስ አላስቻለውም፣ መንገድ አጋምሶ ተቀበለው። አልተጸየፈውም፣ ከነ ቆሻሻው አቅፎ ሳመው። አልተበሳጨበትም አዘነለት። ልብሱን ቀየረለት፣ ታሪኩን ለወጠለት። ቀለበት አደረገለት፣ ቃልኪዳኑን አደሰለት። ፍሪዳ ሠዋለት አምልኮ ተጀመረ። ታላቅም ደስታ ሆነ።

     📖ሞት በሕይወት ፣ መጥፋት በመገኘት የሚተካው በመመለስ ነው። የሚፈርድብን ሳይሆን የሚምረን አባት ነው። ዛሬም ማዶ ማዶ እያየ ይጠብቀናል። ሉቃስ የጌታችንን ንግግር መጻፍ ይቀጥላል። በጠፋው ልጅ መገኘት ትክለኛ ወይም ኗሪ ነኝ የሚለው ልጅ ተበሳጨ። አባቱ ግን መልስ ሰጠ(ሉቃ.15፥25-32)።

     💌ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት የአባትና የልጅ ግንኙነት ነው። እርሱም አፍቃሪ አባታችን ነው። ስለ እኛ የሚቆጭ፣ በርህራሄ የሚቀበለን፣ ልብሳችንን የሚለውጥልን፣ ቃልኪዳንን ሊያድስልንና እንዴት መኖር እንዳለብን የሚመክረን አባት እርሱ ነው! እግዚአብሔር ዛሬም የፍቅር እጆቹን ዘርግቶ "ልጄ ሆይ" ና ይላል!
     መመለስ ይሁንልን!!!

Wednesday, June 5, 2019

❖እርገት፦

“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ”

“ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ፤ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ ➟በምሥራቅ በኩል ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣ [ላረገ] ለእግዚአብሔር ዘምሩ!” መዝ 67 (68)፥33
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው 9 የጌታ ዐበይት (ታላላቅ) በዓላት አንዱ  የዕርገት በዓል ነው።
የተቀሩት ስምንቱ፦
➠ በዓለ ትስብእት (ብስራት - Annunciation)
➟ ልደት
➟ ጥምቀት
➟ ደብረ ታቦር
➟ ሆሣዕና
➟ ስቅለት
➟ ትንሣኤ እና
➟ ጰራቅሊጦስ ናቸው።
የደብረ ታቦር በዓል በምሥራቅ አኀት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን (The Feast of Transfiguration) በመባል ይታወቃል። የመገለጥ/የመለወጥ በዓል ብለው ይጠሩታል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት 9 በዓላት በተጨማሪ ምሴተ ሐሙስን አካትቶ ፥ በ15ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር የነበረና በብዕር ስሙ “ርቱዓ ሃይማኖት - ሃይማኖቱ የቀና” በመባል የሚታወቀው ሊቅ “ድርሳናት ዘበዓላት ዐበይት” በሚል ርእስ ፥ የጌታችንን 9 ዐበይት በዓላት የተመለከቱ ድንቅ ድርሳናትን ደርሷል።

ቤተ ክርስቲያናችን የዕርገትን በዓል በማሕሌትና በቅዳሴ እንደምታከብረው እናውቃለን። ሊቃውንቱም፦ “ዮም ፍስሓ ኮነ በእንተ ዕርገቱ ለክርስቶስ እምድኅረ ተንሥአ እሙታን በ፵ ዕለት በይባቤ ወበቃለ ቀርን ፤ አማን መንክር ስብሐተ ዕርገቱ። ማለት ፦ ከሙታን ከተነሣ ከ፵ ቀን በኋላ በዝማሬና በመለከት ድምጽ ዛሬ ክርስቶስ ስላረገ ፥ [በዕርገቱ] ደስታ ሆነ” እያሉ በደስታና በሐሴት ያዜማሉ።
ነገር ግን አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ለምን ይህን የመዳናችን ክፍል የሆነውን ታላቅ በዓል እንደሚረሱትና ልብ እንደማይሉት ግልጽ አይደለም። ምናልባት ዕርገት የሚከበርበት ቀን ሐሙስን ስለማይለቅ የሥራ ቀን ሆኖባቸው ነው እንዳንል ፥ በሥራ ቀን የሚውሉ ሌሎች በዓላትን በድምቀት ሲያከብሩ እናያለን። ስለጌታ ዕርገት ያላስተዋልነውና ብዙ ልንማረው የሚገባ ነገር አለ።

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በይባቤ መላእክት በክብር ወደ ሰማያት ላረገው ጌታና አምላክ እንድንዘምር ያዘናል። አበው መተርጉማን “ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ፤ ሰማይ ዘመንገለ ጽባሕ” የሚለውን የዳዊትን መዝሙር ሲተረጉሙ፦ ለገነት ምዕራብ ከምትሆነው ከሲኦል ነፍሳትን አውጥቶ ወደገነት ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ፤ አንድም ➟ ለኢየሩሳሌም ምሥራቅ በምትሆነው በደብረ ዘይት በኩል ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ ማለት ነው ብለዋል። ይህ የድል ዝማሬ ነው ፤ በዚሁ በ67ኛው የዳዊት መዝሙር ቁጥር 18 ላይ “ዐረገ ውስተ አርያም ፄዊወከ ፄዋ - ምርኮን ማርከህ ወደ አርያም (ሰማይ) አረግህ” ተብሎ እንደተዘመረ ፥ ነፍሳትን ከሲኦል ግዞት ነጻ አውጥቶ በክብር ላረገው ጌታና መድኃኒት የአምልኮ ዝማሬ ይገባል።

መቼም ነቢይ ወንጉሥ የሆነው ዳዊት “እግዚአብሔር ዐረገ” “ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ” ሲለን እግዚአብሔር መውጣት መውረድ እንደሌለበት እናውቃለን። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ፥ ይህ ትንቢታዊ ቃል የተነገረው ቃልን ለተዋሐደው ሥጋ እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ። በድጋሚ ዳዊት በ46ኛው መዝሙሩ (ቁ.5 ላይ) ፦ “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ፥ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን ፥ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ - ጌታችን እግዚአብሔር በይባቤ መላእክት ፥ በቅዳሴ ፥ በሥልጣን ዐረገ ፤ ለአምላካችንና [ለንጉሣችን ለክርስቶስ] ዘምሩ (ምስጋና አቅርቡ)” ይለናል። ወረድ ብሎ ደግሞ (ቁ.8 ላይ) 

➟ “እግዚአብሔርሰ ይነብር ዲበ መንበሩ ቅዱስ - እግዚአብሔር ግን በቅዱስ መንበሩ ይቀመጣል” ሲል ይዘምራል። ይህም ከላይ እንደተገለጸው ፥ ሰማይ ዙፋኑ ምድርም ደግሞ የእግሩ መረገጫ ለሆነችለት ለእግዚአብሔር መውረድና መውጣት እንደሌለበት (ዐረገ ፥ ወጣ ፥ ወረደ እንደማይባል) ፤ ነገር ግን ከሦስቱ የሥላሴ አካላት አንዱ አካል (ወልድ) በተለየ አካሉ ከድንግል ማርያም የእኛን ባህርይ ወስዶ ሥጋን ስለተዋሐደ ፥ ያረገውም ከድንግል በነሣው በዚሁ ሥጋ ስለሆነ “እግዚአብሔር ዐረገ” ወይም ቃል በሥጋ ዐረገ ማለት እንደሚቻል ያመለክታል። በሌላ መልኩ ይህ ዝማሬ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ከሚያስረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች አንዱ ነው።

እንደ አባቶቻችን ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ትርጓሜ ፤ ቃለ እግዚአብሔርን የተዋሐደው ሥጋ በተዋሕዶ እንዳረገ የሚያስረዳው ተጨማሪ የዳዊት ዝማሬ፦ “ተፅዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሠረረ - በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ” የሚለው ነው (መዝ 17/18፥10)፡፡ ዳዊት ይህን ዝማሬ የሚዘምረው ➟ “አጽነነ ሰማያተ ወወረደ” (ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ወረደ) ካለ በኋላ ነው። “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ፥ መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም ፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” ሲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንደጻፈልን (2፥6-7) እኛን ያድነን ዘንድ በትህትና የተገለጠው ወልደ እግዚአብሔር ፥ የማዳኑን ሥራ ፈጽሞ ዐረገ። መድኃኒታችን ክርስቶስ ፥ ሰው የሆነ አምላክ ነውና “በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ (ዐረገ)” የሚለው የዳዊት ዝማሬ ሥጋ በተዋሕዶ ማረጉን ያመለክታል።

ከላይ የጠቀስነው “ርቱዓ ሃይማኖት” በሚል ስም እንደሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ በጌታችን ዕረገት ላይ ድርሳን (treatise) የጻፈው ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ዘሰግላ) ግሩም በሆነ ትርጓሜ “መጽሐፈ ምሥጢር” በተሰኘው መጽሐፉ ፦ “ያዕቆብ ሆይ ከኛ ጋር በዓልን ታደርግ ዘንድ ና! ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የወርቅ መሰላል ደብረ ዘይት ላይ ተተክሎ ጫፉ ሰማይ ደርሷል ፤ ይህ የወርቅ መሰላል ከደብረ ዘይት ተራራ ወደ ሰማይ ከወጣው የወልድ ሥጋ ዕርገት ሌላ ምንድን ነው?” ይለናል። በፊልጶስ ምክንያት ወደ መድኃኒታችን ክርስቶስ የመጣው ናትናኤል ከጌታ “ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” የሚል ቃል እንደሰማ እናውቃለን (ዮሐ 1፥52)፡፡ ለዚህ ነው አባ ጊዮርጊስ ፥ በፍኖተ ሎዛ ተኝቶ ከምድር እስከ ሰማይ በሚደርስ መሰላል ላይ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያየውን ያዕቆብን ፥ የህልምህ ፍቺ በጌታ ዕርገት ቀን ተፈጽሟልና ይህን ምሥጢር ታይ ዘንድ ፥ ከእኛም ጋር “በዓልን ታደርግ ዘንድ ና!” የሚለው።

በተመሳሳይ መልኩ ፥ በደብረ ታቦር ሙሴ የጌታችንን ግርማ-መለኮት እንዳየ ፥ ግሩምና ድንቅ የሆነውን ዕርገቱን ያይ ዘንድ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር እንዲህ ሲል ይዘክረዋል፦ “ሙሴ ሆይ! ሕዝብህን ቀን በደመና ፥ ሌሊት በእሳት ዐምድ የመራቸው ጌታ ፥ ወደ ላከው ወደ አብ በእሳት ዐምድ ዐረገ።” የምስጋና ንጉሥ ፥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪሩቤል ጀርባ ሆኖ በመላእክት ይባቤ ሲያርግ ፥ ለንጉሡ የሰማይ ደጅን ይከፍቱ ዘንድ የሰማይ መላእክት “አርኅዉ ኆኃተ መኳንንት” በሚል ቃል ታዝዘዋል። ንጉሡ ሲያርግ መላእክት ያጅቡት እንደነበር ፥ በሰው መልክ ተገልጠውና ነጫጭ ልብሶች ለብሰው ሐዋርያትን ካናገሯቸው መላእክት መረዳት እንችላለን።  ከወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምና ከሌሎች ቅዱሳት አንስት ጋር በአንድ ልብ ለጸሎት ይተጉ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ፥ በቢታንያ ተራራ ላይ እጆቹን አንሥቶ የባረካቸውን ጌታ እያዩት ከፍ ከፍ ሲል ደመናም ከአይናቸው ሰውራ ስትቀበለው ፈዝዘው ይመለከቱ ነበር። በዚህ ጊዜ ምስጋና ለሚገባው ንጉሥ ይባቤ እና ውዳሴ ያቀርቡ ከነበሩት መላእክት መካከል ሁለቱ፦ “የገሊላ ሰዎች ሆይ ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት ፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (የሐዋ ሥራ 1፥11)፡፡

ከሰማይ የወረደው እርሱ ወደ ሰማይ ሲወጣ ➟ “እናንተ መኳንንቶች ፥ በሮችን ክፈቱ ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ” የሚል ዝማሬ በሰማይ ተሰማ። (መዝ 23/24፥9) የሰማይ መኳንንት የሆኑት እነ ሚካኤል ፣ ገብርኤል ፣ ሩፋኤልና ሌሎችም ቅዱሳን መላእክት የሰማይን ደጆች አንዲከፍቱ ታዘዙ። ስለሆነም “ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ” የሚለው የጌታችን ትንቢታዊ ቃል ተፈጸመ። በሰማይ መከፈትና መዘጋት ባይኖርበትም ፥ ይህ አባባል በዕርገተ ኢየሱስ የተገለጠውን ታላቅ የሥጋዌ ምሥጢር ያመለክታል፤ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “ኦ አዳም ናሁኬ ተፈጸመ ዘይቤ እግዚአብሔር አመ ፀአትከ እምገነት አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ ➟አዳም ሆይ ከገነት በወጣህ (በተባረርክ) ጊዜ እግዚአብሔር “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ያለውን [ትንቢታዊ ቃል] እነሆ ተፈጸመ” ሲል አመስጥሮ እንደጻፈልን። አዳምን ካነሳ አይቀር ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ሔዋንንም፦ “ኦ ሔዋን ተፈሥሒ በሞገሰ ወለትኪ …ዝኩ ዘወለደቶ በአንቀጸ ሥጋሃ ኅቱም ተለዓለ ኀበ አቡሁ ሰማያዊ እንዘ ትኔጽሮ ቀዊማ ምስለ አርዳኢሁ ቡሩካን ➠ ሔዋን ሆይ በሴት ልጅሽ (በድንግል ማርያም) ሞገስ ደስ ይበልሽ ፤ . . . በታተመ ድንግልና የወለደችው እርሱ ፥ ከተባረኩ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆማ እያየችው ወደ ሰማያዊ አባቱ ዐረገ” ይላታል።

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ክርስቶሳውያን! መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዳነን ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ባደረገው አጠቃላይ (holistic) የማዳን ሥራ (እንደ አበው አባባል ፦ በሁሉ እየካሰልን) ስለሆነ ፥ የዕርገት በዓል የድኅነታችን (የመዳናችን) በዓል ነው። አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ በተሰበሰቡት 318 አባቶች ስም የተሰየመው የቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴ፦ “ተዘከር ሥጋ እንተ ነሣእከ እምቅድስት ድንግል ከመ ውእቱ ሥጋ ዘዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ➠ ወደ ሰማይ ያረገውና በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ከድንግል የነሳኸው ሥጋ እንደሆነ አስብ” ይላል። ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተነሳው ሥጋ ፥ የእኛ ሥጋ ነው። ስለዚህ ዕርገትን ስናከብር ፥ ሥጋችን ዐርጎ በኪሩቤል ጀርባ ፥ በአብ ቀኝ መቀመጡን ልብ እንበል። በእውነት ለተወደድንበት ዘላለማዊ ፍቅር ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ያለጥርጥር ታላቅ” እያለ ለሚያደንቀው በሥጋ ለተገለጠው ምሥጢር አንክሮ ይገባል! (1 ጢሞ 3፥16)፡፡ አባቶቻችን በቅዳሴ እንደነገሩንም፡- “ኦ እንተ አፍቀርካ ለዛቲ ዘመድነ ➠ አቤቱ ባህርያችንን የወደድሃት” እያልን የተወደድንበትን በሞት የተገለጸ ፍቅር እናድንቅ እናወድስም!

ከመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ ስለሆንን (2ኛ ጴጥ 1፥4) “ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአል” ተብሎ እንደተጻፈ (ሮሜ 8፥29) የልጁ መልክ በውስጣችን እስኪሳል ድረስ ኃጢአትንና ርኵሰትን ተጸይፈን የተጠራንበትን የቅድስና ሕይወት ልንለማመድ ይገባል! ሥጋችንን ያከበረው ፥ ከአእምሮ በላይ በሆነ ምሥጢረ ተዋሕዶ ከመለኮቱ ጋር ያዋሐደው አምላካችን ፥ ሰውነታችንን (ሁለመናችንን) እርሱን ደስ የሚያሰኝና ፥ ሕያው ፥ ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን እንድናቀርብ ያዝዘናል። (ሮሜ 12፥1) አገልግሎታችንንና “የምስጋና መሥዋዕት” የተባለው (መዝ 49/50፥14) የከንፈራችንን ፍሬ (ዝማሬያችንን) እግዚአብሔር ፊት ስናቀርብ ሥጋንና ነፍስን ከሚያስነውር ማንኛውም ዓይነት ርኵሰት ርቀን ፥ ኃጢአትንም ተጸይፈን መሆን አለበት።

የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን በዝሙት እያረከሰን ፥ መቅደሱን አፍርሰን እንዘምር ብንል በእግዚአብሔር ላይ መዘበት ይመስልብናል። የምናመልከው አምላክ ደግሞ ሽንገላን የማይወድ “እውነት ፥ መንገድና ሕይወት” ተብሎ የተጠራ ጻድቅ ነውና “አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ተብሎ ተጽፏል (ገላትያ 6፥7)፡፡ ቅዱስ ያሬድን በመከተል ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ስለጌታ ዕርገት ሲያስተምሩ፦ “ዐርገ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ➠ የጻድቃንን (የእውነተኛ ልጆቹን) ዕርገት ያጠይቅ ዘንድ ዐረገ” ይላሉ። እውነት ነው “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ . . . ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” (ዮሐ 14፥2-3) ሲል በማይታበል ቃሉ የነገረን አምላካችንና መድኃኒታችን ለእኛ ለልጆቹ ሰማያዊ ሥፍራ ያዘጋጅልን ዘንድ ዐረገ። በእርሱ ያመኑ ፣ እርሱን በፍቅር የተከተሉ ልጆቹ ቢሞቱ እንኳ ወደ ሕይወት ይሻገራሉ እንጂ ሞት የለባቸውምና: ነፍሶቻቸውን ቅዱሳን መላእክት በክብር ያሳርጋሉ። ጌታዋንና አምላኳን የምትወድድ ነፍስ ከሥጋዋ በሞት ተለይታ ወደ ሰማይ በምታርግበት ጊዜ ፥ “በውዷ ላይ ተደግፋ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?” የሚለው ፥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚበልጠው የሰሎሞን መዝሙር ይዘመርላታል (መሐልየ መሐልይ ዘሰሎሞን 8፥5)፡፡

በመጨረሻም ወገኖቼ፦ በመላእክት ቅዳሴ እና ይባቤ ላረገው ለንጉሡ ኢየሱስ (ለኢየሱስ ክርስቶስ) የተዘመሩ ዝማሬያትን ልብ እንበል። ስለ ዕርገቱ የተቃኙ የዳዊት ዝማሬያት በሙሉ “ዘምሩ” የሚል ትእዛዝ አለባቸው፦ “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ . . . ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ ፤ ዘምሩ ለንጉሥነ ዘምሩ ➠ አምላክ በእልልታ ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ ፤ ዘምሩ ፥ ለአምላካችን ዘምሩ ፤ ዘምሩ ፥ ለንጉሣችን ዘምሩ” (መዝ 46/47፥5-6)፤ “ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ➠ ወደ ሰማይ ላረገው ለእግዚአብሔር ዘምሩ” (መዝ 67/68፥33)፡፡ ስለሆነም የዕርገት ቀን የዝማሬና የይባቤ ቀን ነው ፤ ዛሬ ያልዘመርን መቼ ልንዘምር ነው? ጥምቀትን ደመቅ አድርገን ስናከብር ፥ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ . . .” የሚል አገርኛ አባባል አለን። ስለጌታ ዕርገት ከላይ የተዘረዘሩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ኦርቶዶክሳዊ ምልከታዎችን ልብ ብለን “ለዕርገት ያልሆነ መዝሙር . . .” የሚል አዲስ አባባል ልንፈጥር ይገባል።
አዎን! በይባቤ ፥ በመለከት ድምጽ ላረገው ጌታና ንጉሥ ከመላእክቱ ጋር አብረን እንዘምር።
ይህ የምስጋና ንጉሥ ስለኃጢአታችን የተሠዋ የእግዚአብሔር በግ ነውና። በሰማያት ለታረደው በግ የሚቀርበውን ዝማሬና ውዳሴ እኛም በምድር እንድገመው።
➦ ራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ 5፥8 . . . አራቱ እንስሶችና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
➦ 9-10 መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ፥ ታርደሃልና ፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው ፥ በምድርም ላይ ይነግሳሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።
➦ 11 አየሁም ፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር።
➦ 12 በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።
➦ 13 በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።
➦ 14 አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።
✟➫ ሥጋችንን ከመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ አድርጎ ላከበረን ፥ ከድንግል ማርያም በነሳው በእኛ ሥጋ ወደ ሰማያት ላረገው ፥ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ለተቀመጠው ፥ በክብር እንዳረገ ከደመና ጋር ዳግም ለሚመጣው ፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ ለእርሱ ፥ ከባሕርይ አባቱና ማሕየዊ ከሆነ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ፣ ኃይል ፣ እልልታ ፣ ይባቤና ሽብሸባ ፣ ምስጋናና ውዳሴም ይሁን።
   ~~~~~~||~~~~~~