Thursday, September 16, 2021

❖ዘመኑን ዋጁ፦

ዘመኑን ዋጁ፦
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ምእመናን መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከገለጠላቸው በኋላ አያይዞ እንዴት መኖር እንዳለባቸው መክሮአቸዋል፡፡ ስለመጪው ጊዜ ሲነግራቸው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና›› ብሏቸዋል፡፡
እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሲመክራቸው ደግሞ ‹‹እንደጥበበኞች›› በጥበብ መመላለስ እንደሚገባቸው፤ ዳግመኛም ‹‹በጥንቃቄ›› እና ‹‹በመጠበቅ›› እየኖሩ ዘመኑን እንዲዋጁ አሳስቧቸዋል፡፡ (ኤፌ5፥15-16) እነዚህ ቁም ነገሮች ለጊዜው በኤፌሶን ላሉ ምእመናን ቢጻፉም ለሁላችን ምክር እና እዝናት የሚሆኑ ናቸውና በየተራ እንመለከታቸዋለን!
‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› ማለት ምን ማለት ነው? የቀን ክፉ አለን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ ክፋት አስቦና ፈቅዶ በሚበድል በሰው ልጅ ዘንድ እንጂ በቀናት ዘንድ ክፋት የለም፡፡ ዕለታትን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነው›› (1ጢሞ4 ፥ 4) ስለዚህ ዕለታት በሙሉ በተፈጥሮ አንድ ናቸው፤ እንዲሁም ሁሉም መልካም ናቸው፡፡ የዕለታት መልካቸው የሰው ልጅ ምግባር ነው፡፡ የሰው ሥራ ክፉ የሆነ እንደሆነ ዕለታትም ይከፋሉ፡፡ ሰው መልካም ሲሆን ዘመናቱ መልካም ይሆኑለታል፡፡ ሐዋርያው በዕለት አንጻር የሰውን ክፉነት ሲነግረን ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች›› ናቸው አለን፡፡ በጸሎተ ቤተ ክርስቲያን ‹‹እግዚኦ አድኅነነ እምዕለት እኪት ወባልሃነ እምኩሉ መንሱት›› - ‹‹አቤቱ ከክፉ ቀን ከፈተናም ሁሉ ፈጽመህ አድነን፡፡›› የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ አበው ካህናት ሲያሳርጉ ‹‹ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን!›› የሚሉት እነዚህን የቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለ ቃላት መሠረት አድርገው ነው፡፡ የሰው ልጅ ምግባር ሲከፋ ዘመናቱ ክፉዎች የሚሆኑት ዕለታት የተፈጠሩት ለሰው ልጆች ጥቅም ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም›› እንዲል፡፡ (ማር2 ፥ 27) ሐዋርያውም ቀኖች ለሰው የተፈጠሩ መሆናቸውን በሚጠቁም ቃል ‹‹ቀኖቹ›› ማለቱን ልብ እንበል፡፡ ‹‹ቀኖቹ›› ያለው የሰው ልጅ ቀኖች ለማለት ነውና፡፡ ስለዚህ ዕለታት ለሰው ልጅ መጠቀሚያነት እስከተፈጠሩ ድረስ ሰው ሲያበላሻቸው ይበላሻሉ ማለት ነው፡፡ ሰው ምግባሩን ሲያከፋ ዕለታት እየከፉ የሚሄዱት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሰው መልካም ሲሁንም ‹‹ቀኖቹ›› መልካም ይሆኑለታል፡፡
መጪው ጊዜ፦
ነቢዩ ዳንኤል እንደተናገረው ዘመን እየገፋ በሄደ ቁጥር ዕውቀት ይበዛል፡፡ ሥልጣኔም ይሰፋል፡፡ (ዳን12 ፥ 4) ይሁን እንጂ በሥነ ምግባር ደረጃ የሰው ልጆች ክፋት እየጨመረና በምድር ላይ ኃጢአት በምልዓት እየተፈጸመ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ይህን እውነት በትንቢት መነጽር የተመለከተው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› ማለቱ የሚገባ ነው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነገር አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ በመጨረሻዎቹ ዘመናት እምነት በሰው ልጅ ዘንድ ጎደሎ እንደሚሆን በተጠየቅ መንገድ ‹‹ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?›› ሲል ተናግሯል፡፡ (ሉቃ18 ፥8) እንዲሁም በሰው ልጆች መካከል ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ‹‹ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡›› በማለት ከነምክንያቱ አስቀምጦልናል፡፡ (ማቴ24 ፥ 12) ይህ በግልጥ የሚታይ እውነት ስለሆነ ምስክርም አያስፈልገውም፡፡ እንግዲህ በመጪዎቹ ዘመናት እምነትና ፍቅር በሰው መሃል ካልተገኙ የሰው ልጅ ለበጎ ምግባር ምን መነሻ ይኖረዋል? ከፍቅርስ የሚበልጥ ምን ምግባር ይኖረዋል? እንዲህስ ከሆነ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› መባሉ ተገቢ አይደለምን?
ቀኖቹ ክፉዎች መሆናቸው እና የሰው ልጆች መንፈሳዊ ደረጃ እየዘቀጠ የሚሄድ መሆኑን ከራሳችን የግል ሕይወት በመነሣት መረዳት የምንችለው ነው፡፡ አብዛኞቻችን ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ትጋት ስንጀምር እንደነበረን አይሆንልንም፡፡ ስንጀምር የነበረን ለጸሎት ማልዶ መነሣት፣ ዘወትር ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ ቃለ እግዚአብሔርን በመመሰጥና በድስታ ማዳመጥ፣ ንስሐ መግባት፣ ሥጋ ወደሙ መቀበል፣ ወይም ከመንፈሳዎ ምሥጢራት ስለ መራቃችን መቆጨት ከውስጣችን ሙጥጥ ብሎ ያለቀ ይመስላል፡፡ በምትኩ ተስፋ መቁረጥ፣ ድንዛዜ ስንፍና እና ልዩ ልዩ የኃጢአት ልምምዶች ልባችንን አጣበውታል፡፡ ታዲያ በእኛ ውስጥ የምንመለከተው ይህ ሁኔታ በብዙ ሰዎች ዘንድ መኖሩን በተደጋጋሚ ስንሰማ ዘመኑ እየከፋ መምጣቱን አይነግረንምን?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸው›› በማለት ብቻ አላበቃም፡፡ በሌላ ክፍል ‹‹ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንደሚመጣ ዕወቅ፡፡›› እያለ መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ከነምክንያቱ ጽፏል፡፡ (2ጢሞ3.፥ 1) መጪው ጊዜ አስጨናቂ የሚሆነው ሰዎች ‹‹ራሳቸውን የሚውዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ ፣ ቅደስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ›› ሰለሚሆኑ እንደሆነ አያይዞ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው የቀኖቹን ክፉነት ብቻ ሳይሆን እኛ ከዚህ ሁሉ ለመዳን ምን ማድረግ እንዳለብንም ጠቁሟልና ያንን ቀጥለን እንመለከታልን፡፡
1ኛ. ዘመኑን መዋጀት:-
ሐዋርያው ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ›› ብሎናል፡፡ ዘመንን መዋጀት ማለት ምን ማለት ነው ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመኑን መግዛት፣ ድል ማድረግ፣ ማሸነፍ፣ የራስ ማድረግ፣ ዘመኑን መቅደም እንጂ በዘመን አለመቀደም… ወዘተ ማለት ነው፡፡ ዘመን ዘመናት የሚባሉት የሚመጡት አዳዲስ ዓመታት ብቻ አይደሉም፡፡ ያለፈውም ጊዜ የዘመን አካል ነው፡፡ ስለዚህ ዘመንን መዋጀት ስለሚመጣው ብቻ ሳይሆን ስላለፈውም መመርመር፣ ታሪክን በሚገባ ማወቅ፣ ካለፈው መማርና ለወደፊቱ መጠንቀቅ ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ካልመረመርነው ዘመንን ዋጀን አይባልም፡፡ የሚመጣውን ብንዋጅ ያለፈውን ዘመን ካልዋጀን ዘመኑን ዋጀን ሊባል አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ዘመኑን መዋጀት ማለት ዘመን ያፈራውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማወቅና መጠቀም ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም የሚሰፋ ሐሳብ ያለው ነው፡፡
ዘመኑን መዋጀት ማለት በእያንዳንዱ ቀን ፈተናዎችን እንደየአመጣጣቸው እየለዩ መመከት ማለት ነው፡፡ የሰው ልጆች ጥንተ ጠላት ሰይጣን ዓለምን ማርኮ ለመግዛት ብዙ አሳሳች መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ አዳምንና ሔዋንን የፈተነው አምላክነትን እንዲመኙና ዕፀ በለስን እንዲበሉ በማድረግ ነው፡፡ ኢዮብን የፈተነው ያለውን ሁሉ በማውደም እና በሽታ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ነው፡፡ እስራኤልን የወርቅ ጥጃ እንዲያመልኩ ስቧቸዋል፡፡ ክብር ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ የፈተነበት መንገድ ግን ከተዘረዘሩት በእጅጉ ይለያል፡፡ ስለዚህ ሰይጣን የሚፈትነን እንደዘመናችን ስለሆነ ዘመኑን ካልዋጀን ፈተናውን ማለፍ አንችልም፡፡ስለዚህ ሐዋርያው እንደመከረን ‹‹መጠንቀቅና›› ራሳችንን ‹‹መጠበቅ›› አለብን፡፡ ‹‹መጠንቀቅ›› ካላወቅነው፤ ነገር ግን ሊሆን ይችላል ብለን ከምንገምተው ክፉ ነገር ሁሉ ራስን ለማዳን መሽቀዳደም ሲሆን ‹‹መጠበቅ›› ደግሞ ክፉ መሆኑን ከተረዳነው ነገር ሁሉ እንዳይጎዳን የምናደርገውን ጥረት ያመለክታል፡፡ (ኤፌ5፥5)
2ኛ. በጥበብ መመላለስ:-
ጥበብ ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ይመደባል፡፡ ወይም በቅዱስ ያዕቆብ ገለጻ መሠረት ሰማያዊ እና ምድራዊ ጥበብ ይባላል፡፡ (ያዕ3፥ 15-17) የመንፈሳዊ ጥበብ መነሻው ሃይማኖት ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ይላልና፡፡ (መዝ1)0፥0) እግዚአብሔርን መፍራት ደግሞ በሃይማኖት ይተረጎማል፡፡ ምክንያቱም በዓይነ ሥጋ ያላዩትን እግዚአብሔርን ኃጢአት ብሠራ ይፈርድብኛል ብሎ መፍራት ራሱ እምነት ነውና፡፡ ስለዚህ የጥበብ መጀመሪያ እምነት መሆኑን በዚህ እናውቃለን፡፡ እንዲህ ከሆነ በጥበብ መመላለስ ማለት ደግሞ በእምነት መመላለስ ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም በጥበብ መመላለስ ማለት በዚህች ዓለም ማታለልና ክፉ አሠራር እንዳይያዙ በዘዴ፣ በዕውቀት፣ በማስተዋል፣ በብልሃትና በፈሊጥ መመላለስ ማለት ነው፡፡ በሃይማኖት መመላለስ ከክፉ ሁሉ ይሰውራል፡፡ እውነተኛ የልብ እምነት ክፉውን ሁሉ ይመክታል፡፡ ‹‹ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ እምነት ያለው ሰው በምንም በማንም አይሸነፍም፡፡ (1ዮሐ5፥4) ስለዚህ በዚህ ዘመን ሃይማኖታችንን ጠበቅ አድርገን መያዛችን ለአሸናፊነታችን ዋስትና ነው፡፡
3ኛ. ከክፉ መሸሽ:-
አብዛኞቻችን በጎ ዘመን ላይ ደርሰን በሰላምና በደስታ ለመኖር የምንጓጓውን ያህል ለዚህ የሚያበቃውን መስፈርት ግን ለማሟላት ስንደክም አንገኝም፡፡ ወደፊት በመልካም ለመኖር የሚጠበቅብን ነገር አለ፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዳዊት የተናገረውን ልብ እንበል፡፡ አስቀድሞ ‹‹ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማነው? በጎንም ዘመን ለማየት የሚወደድ?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ መቼም ለዚህ ጥያቄ እኔ እፈልጋለው ብሎ መልስ የማይሰጥ አይኖርም፡፡ ቀጥሎ ማሟላት የሚገባን ነገር መኖሩን ‹‹አንደበትህን ከክፉ ከልክል፡፡ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም›› ሲል ይጠቁመናል፡፡ (መዝ33፥ 12-14) ስለዚህ በአጭሩ ከክፉ መሸሽና መልካም ማድረግ የወደፊት መንገዳችንን እና መጪውን ዘመን ብሩህ ያደርግልናል፡፡ መልካም አኗኗር ከውስጣችን የሚፈልቅ እንጂ በግዢ የሚገኝ ቁስ አይደለምና፡፡ ደስተኛና ሰላማዊ ኑሮ መኖር ከፈለግን ምግባራችንን እናስተካክል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን?›› ብሎአልና፡፡ (ዘፍ4 ፥ 7) መልካም ከሠራን ፊታችን ይበራል፡፡ ዘመኑም መልካም ይሆንልናል፡፡ እንጂ መልካም አዲስ ዓመት ስለተባባልን ብቻ ዘመኑ መልካም እንደማይሆንልን እንረዳ! በጎ መመኘታችን እንደተጠበቀ ሆኑ በጎ ለመሥራት አሁኑኑ እንነሣ!
ከዕለት እኪት ከዘመን መንሡት ይሰውረን! አሜን!
መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን!

Monday, August 9, 2021

❖መንፈሳዊ እድገት፦

#መንፈሳዊ እድገት፦
መንፈሳዊ ዕድገት በማይታየው ቅዱስ መንፈስ የተደገፈ የሚታይ ኑሮ ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት ያመነ ሰው እምነቱን በሥራ የሚገልጥበት ሂደታዊ(ዘላቂነት ያለው) አኗኗር ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት የመንፈሳዊ ሰው የከፍታ ምስጢር ነው፡፡
መንፈሳዊ እድገት መንፈሳዊ ሰው በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ በመንፈስ ፍሬዎች የሚያጌጥበት የሕይወት ውበት ነው፡፡ይህ ኑሮ ሰው እንዲጠቀምበት፥ እግዚአብሔር እንዲከብርበት በመለኮት ዕቅድ ቀድሞ የታሰበ ኑሮ ነው፡፡

መንፈሳዊ ዕድገት የቅድስና መንገድ ነው፡፡
መንፈሳዊ ዕድገት በግንዱ በክርስቶስ በመሆን ፍሬ የምናፈራበት አኗኗር ነው፡፡ከግንዱ ተለይቶ ማፍራት አይቻልም፡፡"እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።"ዮሐንስ 15:5
በመንፈሳዊ ሕይወት የገጠመን ዝለት እና ስልቹነት ከግንዱ ጋር አለመተባበር ነው፡፡በግንዱ ካልሆነ ድርቀት እንጂ እድገት አይኖረንም፡፡የመንፈሳዊ እድገት መሠረቱ በግንዱ ሆኖ ማፍራት ነው፡፡መንፈሳዊ እድገት ሰሞነኛነት አይደለም፡፡መንፈሳዊ ሕይወት የማይቋረጥ ኑሮ ነው፡፡በየጥቂቱ የሚያድግ አኗኗር ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ኑሮ በሚገባ ተርኮታል፦
"ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።" 2ጴጥ 1:5-10፡፡
እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ መንፈሳዊ ሕይወታችን እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ ነው? በቦታ እና በሁኔታዎች አይወስንም ??? በጊዜ ሂደት አልቀነሰም ??? መንፈሳዊ ሰው በመጨመር በማብዛት እና በመብዛት ፍሬው ይገለጣል፡፡መንፈሳዊ ዕድገት ክርስቶስን ወደመምሰል የምናደርገው ጉዞ ነው፡፡

1. የመንፈሳዊ ዕድገት መሠረት፦
ሕንፃ ያለ መሠረት እንደማይመሠረት መንፈሳዊ ዕድገትም ያለ መሠረት አይወጠንም፡፡የመንፈሳዊ ሕይወት ጽኑ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ጥሩ መሠረት ያለው ቤት ሞገድ እና ነፋስ እንደማይነቅለው በክርስቶስ ላይ ሥር ሰዶ በመታነጽ የመንፈሳዊ ዕድገት ጉዞ የወጠነ አማኝም በምንም ሁኔታ በፍጹም አይናወጽም፡፡መሠረቱ ላይ ያልተተከለ፥ ራስ በሆነው ያልተጋጠመ ይህን ክፉ ዘመን አያልፍም፥ ነፋስ አቅጣጫ ያስቀይረዋል፡፡ተወዳጆች ሆይ፦ እምነት እና አላማችንን መሠረቱ ላይ እናድርግ፡፡የሁሉም መነሻ እና መድረሻ እርሱ ነውና፡፡ "የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ።" ዕብ 12:1-2
መሠረቱ አንድ ነው፥ ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም፡፡ "ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።"
1ኛ ቆሮንቶስ 3:11 ይህ መሠረት ላይ የቆመ ዕድገቱ አስተማማኝ ነው፥ አይንሸራተትም፥ አይሰነጠቅም፥ መከራ ወደ ኋላ አይመልሰውም፡፡ከተመሠረትን በኋላ ጸንተን በብዙ ፍሬ ለማደግ የሚከተሉትን መንፈሳዊ ተግባራት ሳናቋርጥ እናድርግ፦
1. ቃሉን መመገብ
2. ጸሎት
3. ጾም
4. መንፈሳዊ እውቀት መጨመር
5. ትጋት
6. ቅዱስ ቁርባን

1.ቃሉን መመገብ፦
በተፈጥሮ ህግ የማይመገብ ሰው ይራባል ፣ይደክማል፣ ይታመማል ፣ባለመመገቡ ከጸና ይሞታል።ቃሉን የማይመገብ ክርስትያን መንፈሳዊ ረሃብ (የፍቅር፣የትህትና ፣የበጎነት ፣የቅንነት ወዘተ… ረሃብተኛ)፣ ድካም( ለፀሎት ፣ለአገልግሎት ፣ለፆም ወዘተ… ደካማ)፣ ህመም ( ቃሉ ምንድነው ? መንፈሳዊነት ምንድነው ? ቤተክርስትያን ምንድናት ወዘተ… የሚል ህመምተኛ )፣ሞት( ያለእግዚአብሔርና ያለቃሉ የሚኖር ስም ያለው ነገር የሞተ ማንነት ያለው ይሆናል) ።
"ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።"
1ኛ ጴጥሮስ 2:2-3። እንደተባለ ቃሉ ለእድገታችን ጠቃሚ የሆነ ዋና ምግብ ነው፡፡በቃሉ በኩል እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የፈቃዱን ምስጢራት እናውቃለን፡፡ስለዚህ እንደ ፈቃዱ የሆነ እድገት ይኖረናል፡፡የቃሉ ወተት የሚያስፈልገን አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ነው፡፡ወተት አሁን ለተወለዱ ሕፃናት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ካደጉ በኋላ ግን ብዙ አማራጭ ይኖራቸዋል፡፡መንፈሳዊ ሰው በዋናነት ሁልጊዜ የቃል ወተት ያስፈልገዋል፡፡ቃሉ የልጅነት ትዝታችን፥ የጉልምስና ትጥቃችን፥ የሽምግልና ወራት ኃይላችን ነው፡፡ቃሉ የማያስፈልግበት ጊዜ የለም፡፡ስለዚህ ሁልጊዜ የቃሉ ወይን ጠጅ የማይጎድልባቸው ማድጋዎች እንሁን፡፡ያለ ቃሉ ድጋፍ መንፈሳዊ እድገት አይከናወንም፡፡ሕፃናት ከእናታቸው የሚያገኙት ወተት ጤናማ እንደሚያደርጋቸው ሁሉ የጌታ ምክርም ጤናማ ዕድገት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

2. ጸሎት፦
ለምን እንጸልያለን?
-ፈቃዱን ለማወቅ ዘፍ 24:11-14
-ለማመስገን መዝ 12:6
-ወደፈተና እንዳንገባ ማቴ 26:41
-ከክፉ ለመጠበቅ ማቴ 6:13
-ዲያብሎስን ለመርታት ማቴ 17:21
እኛ መሥራት ያልቻልነውን እግዚአብሔር እንዲሠራልን የምንጠይቅበት መሳሪያ ጸሎት ይባላል፡፡ነገር ግን መጸለይ ባለመቻላችን የጸሎትን ኃይል መጠቀም አልቻልንም፡፡ባለመጸለያችን ከነችግራችን እንኖራለን።ጸሎት የሕይወታችን እንቅስቃሴ በጌታ ፈቃድ እንዲመራ ፈቃደኝነታችንን የምናሳውቅበት መንገድ ነው፡፡"ከልብ የሆነ ጸሎት ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ያለው መብአ ነው" እንዳለ ቅዱስ አግናጥዮስ ጸሎት የአምልኮ መገለጫ ነው፡፡ለመንፈሳዊ ዕድገት እጅግ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ጸሎት የማይቋረጥ ድርጊት ነው፡፡ጸሎት በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ የግንኙነት መስመር ነው፡፡መጸለይ ካቆምን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጭ እንሆናለን፡፡በብዙ ጉዳዮች ስለተያዝን የጸሎት ጊዜና አቅም አጥተናል፡፡ስለዚህ ለመጸለይ እንኳ ጸሎት ያስፈልጋል፡፡ጸሎት የመንፈስ ብልጽግና ያመጣል፤ ኃይል ያጎናጽፋል፤ በጸጋ ያሳድጋል፡፡<ጸሎት ለነፍስ ሰላምና እርጋታን ያመጣል፡፡> ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡ጸሎታችን፦ በእምነት፥ በመንፈስ፥ በስሙ፤ እንደ ፈቃዱ መሆን አለበት፡፡ያለ ጸሎት የመንፈሳዊ ዓለም ተጋድሎ አይቻልም፡፡ድል የኛ እንዲሆን፥ እንድናድግ ጸሎት ያስፈልገናል፡፡ጸሎታችን ምስጋናን፥ የኃጢአት ይቅርታን፣ምልጃን እና ልምናን ማካተት አለበት፡፡ 1ጢሞ 2:13፡፡

3 ·ጾም፦
ጾም በራስ ፈቃድ ለጊዜው ከምግብ፤ ለዘላለም ከኃጢአት መከልከል ነው፡፡ጾም የክርስቲያን ሕይወት አካል ነው፡፡ ጾም የአዲሱ ሰው ኑሮ ማሳያ ነው፡፡<ጾም የሥራ መጀመሪያ ነው፡፡>ጾም ለመንፈሳዊ ዕድገት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ጾም ስለ እግዚአብሔር ክብር የሥጋ ፍላጎትን መተው ነው፡፡በሁለቱም ኪዳናት መልካም ታሪክ ያላቸው አባቶች የጾም ሕይወት ነበራቸው፡፡ሙሴ፥ ኤልያስ፥ አስቴር፥ ዳንኤል፥ ዕዝራ ከብሉይ ኪዳን ይጠቀሳሉ፡፡በአዲስ ኪዳን ሐዋርያት እና ሌሎች ለእግዚአብሔር ያደላ ኑሮ ያላቸው በጾም ይታወቀሉ፡፡የክርስትና አርአያ ጌታችን ኢየሱስ ጾሟል፡፡የእርሱን ፍለጋ የምንከተል በጾም ላይ ጠንካራ አቋም ሊኖረን ይገባል፡፡በመብል የሠሩባት አልተጠቀሙምና፡፡ዕብ 13:9:: በመንፈሳዊ እድገት ከፍ ለማለት፥ለመንፈስ ቅዱስ አሠራር ለመመቸት ሥጋችንን መጎሰም አለብን፡፡
ለምን እንጾማለን?
-ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳችንን ለማስገዛት መዝ 35:13 ዕዝ 8:21
-ለንስሐ ዮናስ 3:10
-ለአገልግሎት ጥንካሬ እና ለበረከት ማቴ 6:17-18
እንዴት እንጹም፦
-በደልን በመናዘዝ ኢሳ 58:8 ሉቃስ 18:11
-ፍትሐዊ በመሆን ኢሳ 58:3
-ራስን በመግዛት 1ቆሮ 7:5
-ሥጋን ከነመሻቱ በመስቀል ገላ 5:24
-የዲያብሎስን ማታለያ በመናቅ ማቴ 4:1-11
-ታይታ ባለመፈለግ ማቴ 6:16-18
-ሌላውን ባለመንቀፍ ሮሜ 14:41.

4 ·እውቀት፦
መንፈሳዊ እውቀት ለዕድገት ወሳኝ ነው፡፡ ለማደግ የጥበብን ደጅ ማንኳኳት አለብን፡፡እውቀት በትምህርት፣ በልምድ፣ በምንባብ፣ በጥናት እና ምርምር ይገኛል፡፡ቅዱስ አትናቴዎስ <ለእግዚአብሔር ራሱን የሰጠ ሰው ፀሐይ ንጋት ላይ ስትወጣ በእጆቹ ላይ ቅዱስ መጽሐፍ መገኘት አለበት>እንዳለ ከመጻሕፍት ጋር መዛመድ አለብን፤ መንፈሳዊ እውቀት ግን የልብ ቅንነት እና እምነት ይፈልጋል፡፡መንፈስ ቅዱስ ለሚያስተምረን ልባችን ክፍት መሆን አለበት፡፡ዕድገትን የሚያቀጭጩ ከንቱ ፍልስፍናዎችን መራቅ አለብን፡፡ብዙ ማብራሪያ የሚያገላብጥ፥ ጥንታዊ ቋንቋዎች አመሣክሮ ቃሉን የሚያጠና አማኝ በኑሮም ምስክር መሆን አለበት

5. ትጋት፦
ትጋት የፍሬ መሠረት ነው፡፡ ትጋት የመንፈሳዊ ዕድገት ትጥቅ ነው፤ ያለ ትጋት ዕድገት የለም፡፡የተሰጠንን ጸጋ እና ኃላፊነት በማክበር ለተፈጠርንበት አላማ እንድንታመን መትጋት አለብን፡፡ትጋት በስም ሳይሆን በሥራ የሚገለጽ ጥንካሬ ነው፡፡ስንፍና፥ ዳተኝነት፥ ግዴለሽነት፥ ዝለት፥ ቅምጥልነት የዕድገት ፀር ናቸውቅ.ጳውሎስ "በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።"ዕብ 6:11—12፡፡መንፈሳዊ ሰው የዕድገቱ ቀጣይነት የሚረጋገጠው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ባለው ድጋፍ ሲሆን ትጋት የከበረ ሀብቱነው፡፡ይህ ትጋት የዘመን ሙሉ ኃይል ነው፡፡ያለ ትጋት ምንም ለውጥ አናመጣም፡፡በእምነት የተስፋ ቃል ተቀብለናል፤ በትዕግስት ለመቀበል ትጋት ትልቁ መሳሪያ ነው፡፡ሥራ ጀምረን ለመጨረስ ኃይል፥ መንፈሳዊ ኑሮ ለመቀጠል አቅም፥ ለመበልጸግ ሀብት፥ ለማሸነፍ አቅም ትጋት ነው፡፡ "ለሰው የከበረ ሀብት ትጋት ነው"ምሳ 12:27።

6· ቅዱስ ቁርባን፦
የክርስቶስ ሥጋና ደም/ ቅዱስ ቁርባን/ ሞቱን የምንመሰክርበት አንደበት ነው፡፡"ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና።" 1ቆሮ 11:26፡፡ቅዱስ ቁርባን የኪዳን ምልክት፥ የምስክርነት ራስ፥ የኅብረት ማህተም፥ የግንኙነት መሠረት ነው፡፡ለመንፈሳዊ ዕድገት እጅግ በጣም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሰበብ ማብዛቱን ትተን ቁርባንን የመንፈሳዊ ሕይወታችን አካል እናድርግ፡፡መንፈሳዊ ሕይወት ቀጣይነት ያለው የክርስትና ፍሬ ነው፡፡ ክርስትና ለእግዚአብሔር የተለየ አኗኗር በመሆኑ ቃሉን በማጥናት፥ እውቀት በመጨመር፥ በጸሎት እና በጾም በመጽናት፥ መልካሙን ሁሉ በትጋት በማድረግ፥ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል አለብን፡፡
የእግዚአብሔር ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን !!!

Tuesday, March 2, 2021

❖አቢይ ጾም፦

የአቢይ ጾም ሦስቱ ክፍሎች፦

1. ዘወረደ (ጾመ ሕርቃል)፤ ይህም ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሑድ ያረስ ያለው 7 ቀን ነው።

2. የጌታ ጾም፤ ይህም ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሣዕና ዋዜማ ዓርብ ድረስ ያለው 40 ቀን ነው።

3. ሕማማት፤ ይህም ጌታችን በአልዓዛር ቤት ለማዕድ ከተቀመጠበት የሆሳዕና ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ሥዑር ቅዳሜ ያለው መከራን የተቀበለበት 8 ቀን ሕማማት ነው።

ይህም 7+40+8 = 55 ቀን ማለት ነው።

«ዘወረደ» ማለት «የወረደ» ማለት ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን የሚያዘክር፤ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት ፣ የሚታወስበት፣ የሚነገርበት የዐቢይ ጾም አንደኛው ሳምንት ነው፡፡ዮሐ.3-13፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም በገባዉ ቃልኪዳን መሰረት “ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ” እንዳለ ሐዋርያዉ ቅዱስ ጳዉሎስ የጠፋዉን አዳም ፍለጋ ከአባቱ እሪና ሳይጎድል ሳይለይ ከሰማይ መዉረዱን የምናዘክርበት በዓል ነዉ።

ይህ ጾም የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም “ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅየ አድንኃለሁ” ብሎ ለአዳም ቃል ገባለት ፡፡ ዘፍ. ፫ ፥ ፲፭ ይህ ኪዳነ አዳም ይባላል ፡፡ የቃል ኪዳን ሁሉ መሠረት ነው ፡፡ ሁለቱን ኪዳናት (ብሉይ ወሐዲስ) በፅኑዕ ተስፋ ያስተሳሰረ የረጅም ዘመናት የድኅነት ሰንሰለት ነው ፡፡ ዘወረደ እርቀ አዳም ፤ ተስፋ አበው ፤ ትንቢተ ነቢያት ፤ ሱባኤ ካህናት መፈፀሙ ፤ ኪዳነ አዳም መሲህ መወለዱ የሚነገርበት የፍቅር አዋጅ ነው ፡፡

ዘወረደ ማለት?

 የምስጢረ ሥጋዌ ትምህርት ነው
 ዘወረደ ስንል አምላክ መጣ ፤
 ወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ፤
 በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆነ ማለታችን ነው ፡፡
 ዘወረደ በአምላክ ትህትና ክብረ አዳም የሚነገርበት ነው ፡፡
 አምላክ ሰው በመሆኑ ሰው አምላክ ሆነ ፤ ከበረ ፤ ገነነ ፤ ነገሠ ፡፡
 ሕያው አምላክ ክርስቶስ በቅድስት ሞቱ ሟቹን አዳም ዘላለማዊ ሕያው አደረገው ፡፡
 አምላክ ወልደ አምላክ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ሞቶ ለአዳም ያለውን ታላቅ ፍቅር ገለጸ ፡፡
 የተጣላውን አዳምን በፈቃዱ ታረቀው ፡፡
 ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን ፥ ይልቁንም ከታረቅን በኃላ በሕይወቱ እንድናለን ፡፡ ሮሜ. 5 ፥ ፲ ፡፡ በዚህም ትህትናን ፍቅርን አስተማረን ፡፡

የመጀመሪያ የአቢይ ጾም መግቢያ እሁድ ዘወረደ ይባላል ደግሞም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ስያሜውም፤ በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡

በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡

በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡

እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡

የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ በ

ጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡

የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡

ጾም ስጋችንን ለነፍሳችን የምናስገዛበት ከፈጣሪ ጋር የምንገናኝበት የጽድቅ መንገድ ለስጋ ጤንነትም ቢሆን አስፈላጊያችን የሆነ አንዱና ዋነኛዉ የጽድቅ እቃ ጦራችን ነዉ፡፡

ሆኖም የጾም ወቅት ሲመጣ አቀበት የሚወጡ ይመስል የሚፈሩትና የሚያማርሩት ሳይሆን እንኳን መጣልን ተብሎ በጉጉት የሚናፈቅ መሆን አለበት፡፡ስለሆነም ማንኛዉም ሰዉ ጾሙን ሲጀምር የሚከተሉትን ጉዳዮች በደንብ ሊያጤናቸዉ ይገባል፡፡

የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅም በፆም ድል ማድረግን ለእኛ አስተምሮናል። እኛምበዚህ በአብይ ፆም የለመነውና የጠየቅነው ነገር ሁሉ ከኃጢአት በስተቀር እንዲከናወንልን ፆምን ገንዘባችን እናድርግ።


ጾም ጸሎታችን የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይቀበልልን አሜን።
  ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!