መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ምን ማለት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ እንደሚያመለክተው “መጽሐፍ” እና “ቅዱስ” የሚሉ የሁለት ቃላት ጥምረት ነው ፡፡ በግሪክ ቋንቋ ቢብሎስ
(byblos) ከደንገል በተሠራ ወረቀት ወይም በብራና ከተጻፈ በኋላ በሁለት በትሮች የሚጠቀለል መጽሐፍ ያመለክታል ፡፡ ቢብሎስ በእንግሊዘኛው ባይብል ተብሎ ሲተረጎም በአማርኛው ደግሞ መጽሐፍ በሚለው ቃል ተተረጐመ ፡፡ የግሪኩ ቃል ቢብሎስ
(byblos) እራሱ ቢብሎስ
(byblos) ከተባለ ከተማ ስም የተገኘ ነው ፤ እርሱም ከኒቂያ ወደቦች መካከል በቤይሩት
25 ማይል ያህል ርቆ የሚገኝ አገር ነው ፡፡ ለመጽሐፍ ያገለግል ዘንድ ፓፒረስ (ደንገል) የተባለውን ተክል እንደ ወረቀት አድርገው ይሠሩበት የነበረ ቦታ ነው ፡፡
ሁለተኛው ተጠማሪ ቃል “ቅዱስ” የሚለው ሲሆን ትርጓሜውም የተለየ ማለት ነው ፡፡ ሰው ወይም ማንኛውም ነገር ለእግዚአብሔር አገልግሎት ሲለይ ቅዱስ ይባላል ፡፡ ሰዎች (ዘጸ 28,
41) ፣ እንስሳት (ዘጸ13, 2) ፣ ቦታዎች (ዘጸ 3, 5) ቀኖች (ዘፍ 2, 3) ፣ ማናቸውም ነገር ቅዱስ ሊባል ይችላል (ኢያሱ 6, 19)
፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥምረት ወደሆነው “ቅዱስ” ወደሚለው ቃል ስንመጣ ደግሞ ይህ መጽሐፍ እንደማንኛውም ተራ መጽሐፍ የሚታይ ሳይሆን የተቀደሰና የተለየ መሆኑን ከማሳየቱም አልፎ የጻፉት ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተውና ተመርተው እንደነበር ያስገነዝባል ፡፡ በእርግጥም የጻፉት ሰዎች ከራሳቸው ልቦና ፈጥረው ወይም አንቅተው ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና በእግዚአብሔር እየተመሩና እየታዘዙ የጻፉት ነው (ዮሐ 14,
26) ፡፡
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ህልውናውንና ፈቃዱን ረቂቅ ባሕሪውን በተወሰነ መልኩ የምንረዳበትንና ፈቃዱንም ምን እንደሆነ ማወቅ የምንችልበት በእግዚአብሔር በራሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ለሰው ልጆች የተሰጠ(የተገለጸ) ቅዱስ ቃል ነው ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ እንደሚለው “ከመጀመሪያው ስለነበረው ስለ ሕይወት ቃል እንጽፍላችኋለን ፤ ይህ የሕይወት ቃል የሰማነውና በዐይኖቻችን ያየነው የተመለከትነውና በእጆቻችን የዳሰስነው ነው ፡፡ ይህ ሕይወት ተገልጦአል ፤ እኛም አይተነዋል ፤ እንመሰክራለንም ፡፡ በአብ ዘንድ የነበረውንና ለእኛም የተገለጠውን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን ፡፡ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተም እንነግራችኋለን ፡፡ ኅብረታችንም ከአብና ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው ፡፡ ደስታችንም ሙሉ እንዲሆን ይህን እንጽፍላችኋለን” (1 ዮሐ 1,
1-4) ፡፡
በአጠቃለይ መጽሐፍ ቅዱስ “ዘላለማዊ ሕግ” ሲሆን ዓላማውም ሰዎችን ለሰማያዊ መንግሥት ማብቃት ነው ፡፡ ስለዚህ ከሌሎች የሳይንስ ፣ የልቦለድና የፍልስፍና መጽሐፍት ፈጽሞ ይለያል ፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት ከመጻፉ አልፎ የሚያነቡትና የሚሰሙትን የሚመክር ፣ የሚገስጽ ፣ የሚያረጋጋና ወደ ደኅንነት ሊያደርስ የሚችል ጥበብ ያለው በመሆኑ ነው (2 ጢሞ 3,
14-17 ፣ ሐዋ 13,
16) ፡፡ ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ጣፋጭ የሆነ የሚበላ ሰማያዊ ስንቅ (ሕዝ 3,
1-3) ፣ ብርሃን ሆኖ የሚመራ (መዝ 119, ቁ. 105) ፣ አጽናኝና መካሪ መሆኑን በተለያዩ ቦታዎች ተገልጾ ይገኛል ፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የተገኘና እርሱ በመረጣቸው ቅዱሳን ሰዎች በራሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈና ከሰው ልጅም ጋር ቃል ኪዳን ያጸናበት ቅዱስ ቃል ነው ፡፡
በጥንት ዘመን ግን (እስከ 100 ዓ. ም ድረስ) የቅጠል ዓይነት መጽሐፍት (አሁን ያለው ዓይነት) ስላልነበር መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ቃል “ጥቅልል” በሚል ስም ይታወቅ ነበር ፡፡ የጥቅልል ርዝመት ዐሥር ሜትር ሊደርስ ይችል ነበር፡፡ ጽሕፈቱም በዐምዶች ላይ ነበር (ኢሳ 34, 4 ፣ ኤር 36, 2 እና 20-23 ፣ ሕዝ 3, 1-3
፣ ሉቃ 4,
17-19 ፤ 2ዮሐ 12 ፣ ራእ 5, 1 ፣ 2ጢሞ 5, 13)፡፡ ባጠቃለይ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዘመን በወረቀት ወይም በብራና የተጻፈውን ሲያመለክት የጥቅልል መጽሐፍ እንጂ በቅጠል ላይ የተጻፈ መጽሐፍ አልነበረም ፡፡
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳት መጻሕፍት መዝገብ ነው ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ናቸው ፡፡ ብሉይ ኪዳን ከ1400 -
400 ከክ.ል.በ በልዩ ልዩ ቦታዎች አርባ በሚያህሉ ልዩ ልዩ ጸሐፊዎች እንደተጻፈ ይነገራል ፡፡ አዲስ ኪዳን ከ45-96 ዓ. ም በስምንት ሰዎች ተጻፈ ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ የእግዚአብሔር መንፈስ ለምን አስፈለገ ?
የእግዚአብሔር መንፈስ ካስፈለገባቸው ጥቂት ምክንያቶች ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ፦
·
የሰው ልጅ አስቦ ሊደርስባቸው የማይችላቸውን እጅግ በጣም ጥልቅና ረቂቅ የሆኑ ነገሮችን የያዘ መጽሐፍ በመሆኑ
·
ያለ ስህተትና ምንም ዐይነት ልዩነት ሳያንጸባርቅ እንዲጻፍ (የዘር ፣ የቀለም ፣ የጎሳ ፣ የጾታ )
·
አንድ ዓይነት የሆነ የሃይማኖት የሥነ ምግባር ሥርዐት እንዲኖር ለማድረግ
·
እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች እንዲጻፉና የማይፈልጋቸው ጉዳዮች እንዳይጻፉ ለማድረግ ፤ ይህም ማለት በመንፈሱ በመመራት ትክክለኛውን ቃሉ መጻፍ እንዲቻል
·
የሰው እውቀትና ችሎታ እጅግ በጣም የተወሰነና የተገደበ ነው ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ምስጢራዊ ፣ ከሰው አእምሮና ጠቅላላ ችሎታ በላይ ስለሆነ ይህንን ቃል ለመጻፍ የእግዚአብሔር መንፈስ ድጋፍ እጅግ በጣም ያስፈልግ ነበር ፡፡
·
ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር “ለእኛ ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ አማካኝነት ምስጢሩን ገልጦልናል ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ዕቅድ እንኳ ሳይቀር ሁሉን ነገር ይመረምራል ፡፡ ስለ ሰው የሆነ እንደሆነ ከገዛ ራሱ መንፈስ በቀር በእርሱ ያለውን አሳብ የሚያውቅ ሌላ ማንም የለም ፤ እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔርን አሳብ የሚያውቅ ማንም የለም” (1 ቆሮ 2,
10-11) ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የተናገረውን ተረድቶ ለመጻፍ የራሱ መንፈስ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ፡፡
በምን ዐይነት መልክ ነው እግዚአብሔር ቃሉን ወደ እነሱ እንዲደርስ ያረገው?
እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ቃሉን ወደ ሚያደምጡት ቅዱሳኖች አስተላልፏል ፡፡ ቃሉ ለእነሱ ከመግለጹ በፊት ግን የእነሱ በጎ ፈቃደኝነት ይጠይቃል ፡፡ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ተገዶና ነጻነቱ ተነፍጎ አይደለም የሚጽፈው ፡፡ ጸሐፊው በበጎ ፈቃደኝነቱና በነጻነት ራሱን ያዘጋጃል ፤ ከዚያም እግዚአብሔር የገለጸለትን ቃል በራሱ ቋንቋ ፣ ባሕልና የአጻጻፍ ዘይቤ መሠረት ቃሉን ይጽፋል ፡፡ እግዚአብሔርም ቃሉን በሚከተሉት መንገዶች ለጸሐፊዎች ይገልጻል ፦
·
1/ ቃል በቃል በማነጋገር ፦ ሙሴን አንዳነጋገረው እግዚአብሔር ቃሉን በንግግር መልክ ይገልጻል ፡፡ ለምሳሌ “በድንገትም እግዚአብሔር ሙሴን ፣ አሮንና ሚርያምን እናንተ ሦስታችሁ እኔ ወደ ምመለክበት ድንኳን ኑ አላቸው ፤ እነርሱም ሄዱ ፤ እግዚአብሔርም በደመና ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ በመቆም አሮን ሚርያም ብሎ ጠራቸው ፤ ሁለቱም ወደ ፊት ቀረቡ ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለ እነሆ እኔ የምነግራችሁን አድምጡ…..እኔ ከእነርሱ ጋር ቃል በቃል በግልጥ እነጋገራለሁ” (ዘኁ 12,
4-8) ፡፡
·
2/ በሕልም በመግለጽ፦ (ዘፍ 37, 5)
·
በትንቢትና በራእይ ራሱን በመግለጥ ፦ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል “እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታሁ” (ዘኁ 12, 6)
፡፡ “የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈሕ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ” (ዮሐ 1,
10-11) ፡፡
·
ያዩትንና የሰሙትን ልብ ብለው አስተውለው ያንኑ እውነታ ብቻ እንዲጽፉ በማድረግ ፦ ቅዱስ ዮሐንስ እንደጻፈው “ገና የምነግራችሁ ብዙ ነገር አለኝ ፤ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል ፤ ምክንያቱም እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን አይደለም ፡፡ እርሱ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይነግራችኋል” (ዮሐ 16,
12) ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዋና ዓላማው ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉባቸው ዓለማዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል ፦
·
የእግዚአብሔርን ማንነት ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም እውነተኛና ዘላለማዊ አምላክ መሆኑን ተገንዝበን እንድናመልከውና ፈቃዱን ፈጽመን በሕይወት እንድንኖር (1 ዮሐ 1, 1-4
፣ ማቴ 28, 20
፣ ሮሜ 15, 4)
፡፡
·
ሥጋን ለብሶ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ጌ.ኢ.ክ እግዚአብሔር እንደሆነ አምነን በስሙም ዘላለማዊ ሕይወትን አንድናገኝ (ዮሐ 20,
30-31 ፣ 1 ዮሐ 5, 13)
፡፡
·
“እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚሰማና በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” (ዮሐ 5, 24)
እንዳለው በእግዚአብሔርና በልጁ በጌ.ኢ.ክ አምነን የዘላለም ሕይወት እንድንወርስ ፡፡
·
የሰው ልጅ በጥሩ ሥነ ምግባር ማደግ ወይም መታነጽ እንዲችል የተጻፈ ነው ፡፡ የሰው ልጅ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ሥነ ምግባራት በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ተገልጸዋል (ዘጸ 20,
7-17 ፣ ማቴ 5, 21)
፡፡ ባጠቃላይ የሰዎች ሥነ ምግባር ጥሩ መሆን ብቻ ሳይሆን ከክፋት መራቅና ፈተናን ማለፍ የሚችለው በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው እግዚአብሔርን በማወቅና እርሱን በመፍራት ላይ ሲመሠረት ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን እንዴት አድርጋ ነው እነዚህ መጻሕፍት ሁሉ አግኝታ በአንድ መጽሐፍ ውስጥ የሰበሰበቻቸው?
·
ከመጀመሪያ ጀምሮ ቤ∕ክ አይሁድ ያወቁአቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ተቀበለች፡፡ ቀጥላም በሐዋርያት ወይም በሐዋርያት ሥልጣን የተጻፉትን መጻሕፍት ሰብስባ እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቀበለቻቸው ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እየጠቀሱ አስተማሩ ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ በ367 ዓ.ም በጻፈው በፋሲካ ዕለት ቃለ በረከት ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሃያ ሰባት ብቻ መሆናቸውን ተናግሯል ፡፡ እንደዚሁም በ397 ዓ.ም በሰሜን አፍሪካ በካርታጎ (በካርቴጅ በቱኒዚያ) የተደረገው ሲኖዶስ ሃያ ሰባቱን መጻሕፍት አጸደቀ፡፡
·
በሌላ መልኩ በዕብራይስጥ የተጻፉ ብዙ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች የነበሩ ቢሆንም የመጀመርያው ቅጂ በ200 ከክ.ል.በ ገደማ ተጻፈ ፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት በጥንት ዘመን በጥቅልል እየተጻፉ በልዩ ልዩ ምኩራብና ቤ∕ክ ይሰበሰቡና ይነበቡ ነበር ፡፡ ቅደም ተከተላቸውም ልዩ ልዩ ነበር ፡፡ ለምሳሌ አትናቴዎስ ሰባቱን መልእክታት ከጳውሎስ መልእክታት አስቀድሟል ፡፡ የካርታጎ ሲኖዶስ ግን የመጻሕፍቱን ተራ እንደ አሁኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተራ አድርጎ አጽድቋል ፡፡