Thursday, April 11, 2013

❖የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች ትርጓሜ


የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች፦
ምዕራፍ ዐሥራ ሁለት
ክፍል 5 : የክርስቲያን ኑሮ (የክርስትና ሕይወት ኑሮ)
v  ከምዕራፍ 12 - ምዕራፍ 14
Ø  ምዕራፍ 12 የክርስቲያን ኑሮ ክፍል መጀመሪያ ምዕራፍ ነው::
Ø  የክርስትና ሃይማኖት የእምነት ነገር ብቻ ሳይሆን በኑሮአችንም ውስጥ እንዴት እንደምንመላለስ የሚያስተምረን የኑሮ መመሪያችንም ነው (1ተሰ 4፥1፤ 1ዮሐ 2፥6)
Ø  ስለዚህ በሚከተሉት በእነዚህ ሦስት ምዕራፎች ጽድቅን በእምነት የተቀበለ ሰው በኑሮው እንዴት መመላለስ እንደሚገባው እንማራለን:: በዚህም መሠረት:-
·         የክርስቲያን ኑሮ በእግዚአብሔር ዘንድ በምዕራፍ 12፤
·         የክርስቲያን ኑሮ በምድራዊ መንግሥት ዘንድ በምዕራፍ 13፤
·         የክርስቲያን ኑሮ በወንድሞች ዘንድ በምዕራፍ 14 ተመልክቶልናልና በትኩረት እንማረው ዘንድ ይገባናል:: በመሆኑም:-
§  በምዕራፍ 12 ሊኖረን ስለሚገባ መልካም ኅሊና (በጎ ልብ)፣
§  በምዕራፍ 13 በኑሯችን ውስጥ ማድረግ ስለሚገባን ነገር፣
§  በምዕራፍ 14 ደግሞ ማድረግ ስለማይገባን ነገር እንመለከታለን::
Ø  እስከ አሁን በተመለከትናቸው 11 ምዕራፎች የእምነት ነገር ምን እንደሆነ እየተረዳን መጥተናል:: አሁን ደግሞ በዚህ በምዕራፍ 12  እና በቀጣዮቹ ምዕራፎች የእምነት ተከታይ የሆነው የመልካም ሥራ ነገር እናያለን::
Ø  ይህም የክርስትናው ሕይወትና የመንፈሳዊውን ኑሮ ቅደም ተከተል በሚገባ የሚያስረዳን ነው:: ይኸውም ሰው አስቀድሞ በእምነቱ ይጸድቃል፣ ቀጥሎም በእምነት የተቀበለውን የጽድቅ ሕይወት መልካም ሥራን በመሥራት ይገልጣል::
Ø  ይህም በአፅንኦት የሚያስገነዝበን የእግዚአብሔርን ጽድቅ በእምነት የተቀበለና በክርስቶስ የዳነ ክርስቲያን የመዳን ሕይወቱን የሚገልጥ መልካም አኗኗር ሊኖረው እንደሚገባ ነው::
v  ቁጥር 1- 2:-
Ø  “እንግዲህ” የተባለው ቃል ከምዕራፍ 3፥21 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 11 መጨረሻ ድረስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ርኅራሄ ይመለከታል::
Ø  በመሆኑም ሐዋርያው እስከዚህ ድረስ ባለው ትምህርት “የእግዚአብሔርን ርኅራሄ ከተረዳንና ከተቀበልን እንግዲህስ ራሳችንን ደስ የሚያሰኝና ሕያው መስዋዕት አድርገን ርኅራሄ ላደረገልን ለእግዚአብሔር እናቅርብ” በማለት ልመና አዘል ምክር ያቀርባል::
Ø  ይህም አቅርቦት መልካም ሥራችንን የተመረኮዘ ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ርኅራሄ ወረታ ወይም ምላሽ እንጂ ምህረቱን ለማግኘት የሚደረግ ሥራ አይደለም::
Ø  እናስተውል! ከምእራፍ 3፥21 ጀምሮ እስከ ምዕራፍ 11 መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነትና ርኅራሄ ከማዳን ሥራው ጋር ተመልክተናል::
Ø  አሁን ደግሞ ለዚህ ቸርነቱ የምናቀርብለትን ወረታ ወይም የምላሽ ስጦታ እየተጠየቅን ነው:: ለመሆኑ ምን ልንሰጠው ተዘጋጅተን ይሆን?
Ø  ብዙ ጊዜ ሲሆን የምናየው እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት በስጦታነት የምናቀርበው ያለንን ገንዘብ አልያም ከእኛ ውጭ የሆነውን ነገር ነው::
Ø  ሐዋርያው የሚነግረን ግን:-
·         እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መስዋዕት ወይም ስጦታ ከእኛ ውጭ የሆነ ነገር ሳይሆን የራሳችንን ሰውነት ማለትም ልባችንን እንድንሰጠው ነው:: እርሱም:-
1.      ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችን፣
2.     በልባችን መታደስ የተለወጠ ማንነት እና
3.     ይህንን ዓለም ያልመሰለ አኗኗራችን ነው::
ማስገንዘቢያ :-
Ø  ብዙ ጊዜ በክርስትና ኑሯችን ተመላልሰን የቤተክርስቲያንን ቅጥሮች ወይም በሮች ስመን እና ጥቂት ሳንቲም ዘርዝረን ለድሆች ሰጥተን መምጣት አልያም ጥቂት ሰዓት በጸሎትና በጾም ቆይተን መመለሱ ብቻ በቂያችን እንደሆነ ስንገምት እንታያለን:: ይህ ነገር ለክርስቲያን አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ነገር ግን አይደለም:: ዋናውና ቀዳሚው ያለንን ሳይሆን ራሳችንን ለቅዱሱ አምላካችን ለእግዚአብሔር በቅድስና መስጠት ነው:: ራስን መቀደስ፣ መለየት!
v  ቁጥር 3-8:-
Ø  ይህ የአካልና የብልቶች ምሳሌ ዓይነተኛው የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ሆኖ በ1ቆሮ 12፥12-27፣ በኤፌ 4፥15-16 እና በቈላ 1፥18 ደግሞ ቀርቧል ወይም ይገኛል::
Ø  በዚህ ትምህርት ውስጥ ሐዋርያው በተለይ ስለመንፈሳዊ ስጦታዎችና ስለቤተክርስቲያን ሥራ ይናገራል:: ስለሆነም:-
·         ትንቢት :- ተብሎ በቁጥር 6 ላይ የተገለጠው ቃል የወደፊትን ነገር መናገር ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚደረገውን የወንጌል ስብከትም የሚያመለክት ነው:: (1ቆሮ 14፥1-5) ይህም የቀሳውስትን ሥራ የሚያመለክት ነው::
·         አገልግሎት :- ተብሎ የተገለጠው የዲያቆናቱን የተልዕኮ ሥራ የሚያሳይ ነው (ሐዋ 6፥1-6)
·         መምከር :- ደግሞ የንስሐ አባት ሥራ ነው (ቁጥር 8)
·         መማር :- ደግሞ በሽተኞችን የሚጠይቀውና የሚንከባከበው ወገን ሥራ ነው::
·         መግዛት ወይም ማስተዳደር :-የዓለቃ ሥራ ነው::
Ø  እንግዲህ የክርስትና ማኅበር ወይም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እያንዳንዳቸው በተሰጣቸው ሙያ ሊተጉ ይገባል::
Ø  እያንዳንዳችን የተለያየ ስጦታ ተሰጥቶናልና (ኤፌ 4፥7)፤ ሁላችንም በተሰጠን ሥጦታ ሳንኮራ በመጨረሻው ቀን የጌታችንን ምስጋና እንቀበል ዘንድ በትጋት እናገልግል (ማቴ 25፥21-23)
v  ቁጥር 9-13
Ø  በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በቀዳሚነት የምንመለከተው ፍቅርን የሚያመለክቱ ሁለት ቃሎችን ነው
·         ፍቅር
·         መዋደድ የሚሉት ናቸው
Ø  ይህም አንደኛው እግዚአብሔር የሚያፈቅርበትን ከፍ ያለውን ነገር የሚገልጥ ሲሆን ሁለተኛው እርስ በእርስ ሊኖረን የሚገባውን መዋደድ የሚገልጥ ነው:: እነዚህ ቃሎች በ ዮሐ 21፥15-17 እየተፈራረቁ የተነገሩ ናቸው::
Ø  ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤
·         ይህ ቃል እግዚአብሔርን የምናፈቅርበት ፍቅር ሲሆን ምልክቱም :-
-       ክፉ ነገርን መጸየፍ እና ከበጎ ነገር ጋር መተባበር ነው
Ø  በወንድማማች መዋደድ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፤
·         ይህ ደግሞ የአንድ አባት ልጆች የሆንን (ዕብ 2፥10-11) ክርስቲያኖች ሊኖረን የሚገባውን መዋደድ የሚያመለክት ነው::: ምልክቱም:-
-       በ1ጴጥ 4፥8 ላይ የተገለፀው የሌላውን ኃጢአትና ድካም በመሸፈንና በመቻቻል እንዲሁም በመከባበር የሚገለጥ ፍቅር ነው::
Ø  ከ11-13 ባሉት ቁጥሮች የምናስተውላቸው ደግሞ ለመልካሙ የክርስትና ኑሯችን መሠረታዊ ሆነው የቀረቡትን ነገሮች  ነው:: እነርሱም:-
·         ለመልካም ሥራ አለመለገም /ዳተኛ አለመሆን/፤
·         በመንፈስ መቃጠል /ለመንፈሳዊ ነገር መቅናት/፤
·         ለጌታ መገዛት /ክርስቶስን ብቻ ማምለክ/፤
·         በተስፋ ደስ መሰኘት /የጌታን መምጣት መናፈቅ/፤
·         በመከራ መታገስ /የክርስትናውን ፈተና አለማማረር/፤
·         ቅዱሳንን መርዳት /ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ማገዝ/::
Ø  እዚህ ጋር ልብ ልንላቸው የሚገቡና በዓለም ሰዎችና በውጭ ባሉ ጠላቶች ዘንድ የምናደርጋቸው ሦስት ወሳኝ ነገሮች ናቸው::
1.      በተስፋ ደስ እንዲለን :- ተስፋ ምን እንደሆነ በምዕራፍ 8፥16-25 አይተናልና::
2.     በመከራ እንድንታገስ :- የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን በዚህ በሰይጣን ግዛት ውስጥ መከራ እንደሚገጥመን የታወቀ ስለሆነ  (1ዮሐ 4፥4-6፣ ገላ 4፥29፣ ዮሐ 15፥18)
3.     በጸሎት እንድንጸና :- ጸሎት ተስፋችን ላይ እንድናተኩርና በመከራችን እንድንበራታ ስለሚያደርገን
v  ቁጥር 14-21
Ø  በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ በዋናነት የሚከተሉትን ቁም ነገሮች እንማራለን
1.      መከራ ለሚያደርሱብን መጸለይ ከጌታ የተማርነውና የበለጠ ክብር የሚያመጣልን እንደሆነ (ሉቃ 23፥34)
2.     ከደስተኞች ጋር ደስታቸውን መካፈል፤ ከመከረኞች ጋር አብሮ መቸገር:: ይህም ሕይወት ከጌታችን የተማርነው ነውና:: ጌታችን እርሱ :-
§  “በመከራቸው ሁሉ ጨነቀው” (ኢሳ 63፥9)
§  በድካማችን ይራራል (ዕብ 4፥15)
§  የኃዘንተኞችን ሐዘን ተካፈለ (ዮሐ 11፥33-35)
§  በሠርግ ቤት ታደመ (ዮሐ 2፥1-2)
3.     የትዕቢትን ሐሳብ ትተን የትህትናን ነገር መሥራት:: ይህም ከጌታችን የተማርነው ስለሆነ እናስተውለው:: ጌታችን እርሱ:-
§  ከድሆች ተወለደ፤
§  ከተዋረዱት ጋር ተቀመጠ፤
§  የተማሪዎቹን እግር ሊያጥብ ተንበረከከ (ዮሐ 13፥4-5)
4.     ክፋትን በክፋት አለመመለስና በፈንታው መልካም የሆነውን ማሰብ:: ይህም:-
§  በዓለም ካሉትና ካልዳኑት ሰዎች የምንለይበት ብቸኛው የክርስቶስ ሕይወት ነው::
5.     በቀልንና ፍርድን ለእግዚአብሔር መስጠትን:: ይህም:-
§  በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፍርድ ማመንና መደገፍን የሚያመለክት ነው::
“እግዚአብሔር በእኔና ባንተ መካከል ይፍረድ” 1ሳሙ 24፥12-13

No comments:

Post a Comment