Saturday, March 26, 2016

❖የመናፍስት ውጊያ

የመናፍስት ውጊያ፥

       ክፉ መንፈስ ሰዎችን በተለያየ ምክንያት ሊይዛቸው ይችላል። ለምሳሌም ከቤተሰብ በሚወረስ የባዕድ (የጣዖት) አምልኮ፣ የኃጢአት ሕይወትን በመምራት፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ባልተመሠረተና ባልጸና ክርስትና በመመላለስ፣ ለአጋንንት የተዘጋጁ መስዋዕቶችን በመካፈል (1ቆሮ. 10፣19-21)፣ … ሊሆን ይችላል። አጋንንትን ከሰው ውስጥ የማሰወጣት ሥልጣን በክርስቶስ ኢየሱስ ላመኑ ሁሉ የተሰጠ ስልጣን ነው (ማር. 16፣17)። እግዚአብሔር ያጎናጸፈን ክብር አጋንንትን ከማስወጣት የበለጠ ነው። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ (ሉቃ. 10፣19-20)። ሰይጣን እንግዳ የሆነ ጠላት ስለ ሆነ የእግዚአብሔር መቅደስ (ማደሪያ) በሆነው ሰው ውስጥ መኖር አይፈቀድለትምና ታዝዞ መውጣት አለበት። ሰይጣን ከሰው ሊወጣ የሚችለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ መሆኑን ግን አበክረን ለመግለጽ እንወዳለን። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት (ሉቃ. 10፣17፤ ፊል. 2፣9-10) ጳውሎስ ግን ዘወር ብሎ መንፈሱን፦ ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ (የሐዋ. 16፣18)።
ደግሞም ሰይጣን የተሸነፈ ባላጋራ መሆኑን፣ በእኛ ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንደሌለውና ዕድል ፈንታው ታዝዞ ወደ ዘላለም መኖሪያው ወደ ሲኦል መግባት እንደሆነ ልናውቅ ይገባል (ሉቃ. 10፣18፤ ራእ. 12፣10-11)። በእርግጥ አንዳንዱ የአጋንንት እስራት ብርቱ ጾምና ጸሎት ሊያስፈልገው ቢችልም አጋንንት በክርስቶስ ኢየሱስ ስም ሲታዘዙ ፈርተውናና ተንቀጥቅጠው ካልወጡና ከዚህ አልፈው ስለሚወጡበት ቀን ከተደራደሩ ያ የፈውስ አሰራር ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ማረጋገጥ ይቻላል። እስኪ እናስተውል የተሸነፈና የወደቀ ጠላት እንዴት ብሎ ዛሬ አልወጣም በመረጥኩት ቀን እንጂ ማለት ይችላል? ይህ በሚሆን ጊዜ እፈውሳለሁ የሚለውን ሰው ማንነት በሚገባ መመርመር ይገባል። ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚታለሉት እንፈውሳለን የሚሉት ሰዎች በሚጠቀሙት ሰይጣንን የማናዘዝ ክፉ ጥበብ በመወናበድ ነው። ሰይጣን እኮ ምንም እውነት የሌለው ጠላት ነው። ጌታ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና (ዮሐ. 8፣44)። ሰይጣን የተናገረውን ውሸት በመስማትና በማመን ስንት ቤተሰብ፣ ትዳር፣ ጓደኝነት፣ … ፈርሶአል። በቅርቡ አንዲት እህት ስናነጋግር በውስጧ ያደረው ጋኔን ሲለፈልፍ ድግምት ያደረገችብሽ ወላጅ እናትሽ ናት ብሎአት ከእናቷ ጋር መለያየቷን ነግራናለች። ሰይጣን ከሰው ከወጣ በኋላ ተመልሶ የሚገባበትን ምክንያት በተመለከተ፦ ዋናው ምክንያት ያ የተፈወሰው ሰው በእግዚአብሔር ቃል በመኖር ሕይወቱን መጠበቅ ሳይችል ሲቀር፣ በቀድሞ ሕይወቱ ከነበረው ልምምድ ያልተቆረጠ ነገር ሲኖረው … (ሉቃ. 11፣24-26፤ ዮሐ. 5፣14) ሊሆን ይችላል እንጂ ድግምቱ ታድሶበት፣ ከተፈወሰ በኋላ በመጣበት መንገድ ተመልሶ ስለ ሄደ፣ … የሚለው ሃሳብ ትክክል አይደለም። ደግሞም ሰዎችን ሳይፈወሱ በየጸበሉ ዘመናት እንዲቆጥሩ ማድረግ የሰይጣን ጥበብ ነው። በመጀመሪያ በመጎሳቆል ብዛት ጤናቸው ሊታወክና በበሸታ ሊሞቱ ይችላሉ። እንዲሁም መማር፣ መሥራት፣ ማግባት … የሚችሉበትን መልካም ጊዜ ያባክንና ጓደኞቻቸው በሕይወት አልፈዋቸው እንደሄዱ በማሳየት በተስፋ መቁረጥ ወደ ጥፋት ሁኔታ ሊመራቸው፣ ራሳቸውንም እንዲያጠፉ ሊያደርግም ይችላል። የዓምድ ጥበት ስለሚወስነን እንጂ ብዙ ነገር ለመግለጽ እንወድ ነበር። ለማጠቃለልም በመጀመሪያው ጥያቄሽ ላይ ያነሳሻቸው ሃሳቦች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆናቸውን አረጋግጠን ለመናገር እንወዳለሁ።
አንዳንድ ጊዜ ሴቶች ሱሪ አድርገው፣ ጥፍር ቀለም ተቀብተው፣ ፀጉራቸውን በዊግ (ሰው ሠራሽ ፀጉር) ተሠርተው፣ … ሲመጡ ርኩስ መንፈስ ያለባቸው ሰዎች እንዲህ ሆነሽ አትገቢም ብለው በድንጋይ ጭምር ሲደበድቡ አይቼአለሁ። አልፎ አልፎም በርኩስ መንፈስ የተያዙትም ሰዎች የሚገላግሉ መስለው ተመቺዋን ብቻ እጆቿን በመያዝ የሚያስደበድቡም አሉ። እኔ መጠየቅና ለምን? ማለት ስለሚቀናኝ፣ ሰይጣንን በእግዚአብሔር ቤት ሥርዓት አስከባሪ ያደረገው ማን ነው? ብዬ ስጠይቅ እመቤቴ፣ ሚካኤል፣ …መንፈሱን አዝዘውት ነው ይሉኛል። ይህስ በእግዚአብሔር ቃል እንዴት ይታያል? ሰይጣንስ ከቅዱሳን ጋር ምን ሕብረት አለው?
ይህ አሠራር ፈጽሞ ስሕተት ነው፤ ሰይጣን በምንም ዓይነት ሁኔታ የእግዚአብሔር ቤት ሥርዓት አስከባሪና ሕግ አስጠባቂ ለመሆን አይችልም። … ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? (2ቆሮ. 6÷14-15)። ብዙዎቻችን ስለ ሰይጣን ባሕርይና ስለ እግዚአብሔር የፈውስ አሰራር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳት ስለሌለን እንሳሳታለን። በተለይም በዘመኑ ያለው የፈውስ አሠራር የእግዚአብሔርን ክብር ከመግለጽ ይልቅ በአብዛኛው ሰይጣንን በማናዘዝ (ቃለ መጠይቅ በማድረግ)፣ እርሱን በማዳመጥና ሐሳቡን እንደ ትክክለኛ መልዕክት በማስተላለፍ ላይ ያተኮረ ነው። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ሰይጣናዊና አጥማቂ ነን የሚሉትን ሰዎች ዝና በመገንባት ላይ የተመሠረተና እንዲሁም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የስህተት ትምህርት በማስተላለፍ ሰዎችን ለበለጠ እስራት እየዳረገ ያለ ነው። መጽሐፍ ይህም ድንቅ አይደለም፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና። እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል (2ቆሮ. 11፣14-15) ይላልና ሰይጣን በሚናገረው ውስጥ ምንም ዓይነት መልካም ነገር እንደሌለ መረዳት ይገባናል፡ ሴቶች እንዲህ ሆነው አይገቡም፣ በዛሬው ዕለት አይሰገድም እያለ ሰላማዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት (ቃለ እግዚአብሔር መስማትን፣ ጸሎትና ምህላን፣ ስግደትን፣ …) ሲረብሽ ታዞ ነው ተዉት ማለት የሰይጣን ተከታይ ከመሆን የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። አንዲት እህት ለጸበል በሄደችበት ቦታ ልትጠመቅ ስትል ሰይጣን በአንዲት ሴት ውስጥ ተገልጾ ንስሐዋን አልጨረሰችምና ቀድማ ንስሐ ትግባ አለበለዚያ አትጠመቅም አለኝ። ኧረ እንዴት ይሆናል! እርሱ ከአምላኬ ጋር ያለኝን የንስሐ ጉዳይ የት ያውቅና ነው? ብል ሲገደድ እውነት ይናገራልና ንስሐ ካልገባሽ አትጠመቂም በማለት ሌሎች ተጠማቂዎች ለረብሻና ለድብድብ እንደተነሡባት መስክራለች።
ሰይጣን ዓላማው እኛን የነፍሳችን ድኅነት ብቸኛ መሠረት ከሆነው ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መለየት ነውና በመንፈሳዊ ልብ ማስተዋል አለብን። ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ … (2ቆሮ. 4፣3-6)። ለምሳሌም የቅዱሳን ስም ሲጠራበት ኧረ ተቃጠልኩ፣ ዕንባዋ አቃጠለኝ፣ … ስማቸውን አትጥሩብኝ ይላል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲሉት ግን ችግር የለብኝም ይላል። እንግዲህ ዓላማው የኃጢአት ዕዳችን ተከፍሎ ነጻ የወጣንበት፣ የገነት በር የተከፈተበት፣ ሰይጣን ለዘላለም የተሸነፈበት፣ ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣውን ፈራጅና የጌታን ስም አቃለን እንድንተው ለማድረግ መሆኑ ይግባን። ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና አዳኝና እንደሆነ የማይሰበክበት አጋንንትም በስሙ የማይታዘዙበት አገልግሎት ከእግዚአብሔር አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል (ፊል. 2፣6-11)። ከዚህ በላይ ለጠቀስናቸው ስሕተቶች በተለይ የሚጋለጡት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት የሌላቸው የእግዚአብሔር ጽድቅ የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማየት ይልቅ ምልክትና ድንቅ ፍለጋ የሚንከራተቱ ምስኪን ወገኖቻችን ናቸው።

No comments:

Post a Comment