✔ የተባረከው ተስፋችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ ወደ ምድር ሲወርድ ተሞልቶ የመጣው ነገር ቢኖር ጸጋንና እውነትን ነው ዮሐ 1:14።ጌታ ከሰማይ ይዞት የመጣው ጸጋ አንድ የሚያድን ሁለት ደግሞ የሚረዳ ጸጋ ነው። በዚህ ጸጋ ፊት ቀርቦ ይቅር የማይባል ኃጢአት የለም። በዓለም ላይ ዋና የተባለው ኃጢአተኛ የተቀበለ እና ለጠላት ምህረት ያረገ ጸጋው ነው።
ምንአልባት ዛሬ ከኃጢአተኝኘታችን የተነሳ ሥጋችን ተፀይፈን ፣እኛነታችንን ጠልተን የምንኖር ልንሆን እንችላለን። እኔን እግዚአብሔር ይቅር አይለኝም የሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ያለን ፣ ባዶነት የሚሰማን፣ የበደል ሸክም የከበደን ፣ የኃጢአት ሞራ አይናችን ጋርዶን መሪ እንዳጣ ሰው እጃችንን ዘርግተን ብንዳብስ የምንይዘው አተን ዙርያው ሁሉ ጨለማ ሆኖብን ተቸግረን ይሆናል። በዚህ ውስጥ ካለን ዛሬ ግን ከእኛ የሚጠበቀው ነገር ቢኖር ፥ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ " ዕብ 4:16።
በዚህ ጸጋ ዙፋን ፊት የበደለ ይማራል፣ የደከመ ይበረታል፣ ያዘነ ይጽናናል። በእግዚአብሔር ዘንድ ለሁሉም የሚበቃ የትኛውንም ኃጢአት ይቅር የሚል የጸጋ ባለጸግነት አለ። ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል ቲቶ 2:11-13።
ከሞት ያዳነን ይህ ጸጋ ሦስት ነገርን ያስተምረናል።
1ኛ, ኃጢአተኝነትንና አለማዊ ምኞትን መካድ።
2ኛ, የተባረከውን ተስፋችንን መጠበቅ ።
3ኛ, ራሳችንን በመግዛት በጽድቅ እግዚአብሔርን በመምሰል መኖር ነው።
የተባረከ ተስፋ የተባለው የታላቁ የአምላካችንና የመዳኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ ነው። ጌታ ኢየሱስ ከነገረን ተስፋ መካከል አንዱ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ ዮሐ 14:3።
ክርስቲያኖች የምንጾናናበት ቃል አንዱ ጌታ ክፉ ከሆነው ከአሁኑ አለም ሊያድን ይመጣል የሚል ነው። እኛ እኮ ወዳጆቼ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች አይደለንም ። ከሰማይ ሊያድነን የሚመጣውን ጌታ የምንጠባበቅ የተባረከ ተስፋ ያለን ነን ስሙ ይባረክ። ጌታ ኢየሱስ እኛን ለመውሰድ በትዕዛዝ በመላእክት አለቃ ድምፅ ከሰማይ እስከ አየር ድረስ ሲወርድ ፦ በመጀመሪያ በክርስቶስ የሞቱ ይነሳሉ ከዚያ በኃላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ( ከሞት ከተነሱት ) ጋር በደመና እንነጠቃለን 1ተሰ 4:13-18።
ከመነጠቃችን በፊት እኛ ሕያዋን የሆነው እንለወጣለን ሙታን ደግሞ የማይበሰብሱ ሆነው ይነሳሉ 1ቆሮ 15:52። ይህ የክርስቲያኖች ንጥቀት ከክርስቶስ ጋር መሰወር ተብሎ ተገልጾአል። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ቆላ 3:3።
እኛ ከክርስቶስ ጋር ተሰውረን የምንቀር ብቻ አይደለንም ክርስቶስ በክብር በሚገለጥበት ጊዜ ክእርሱ ጋራ የምንገለጥ ነን። " ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ" ቆላ 3:4።
የተባረከው ተስፋችን በመጀመሪያ ለቅዱሳኑ ሲመጣ የተነጠቅነው ወይም ከእርሱ ጋራ የተሰወርነው እኛ ከቅዱሳኑ ጋር ሲመጣ ደግሞ ከእርሱ ጋራ በክብር እንገለጣለን እርሱ ሲነግስ አብረን እንነግሳለን። አሜን።
ክብርና ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን አሜን።
No comments:
Post a Comment