Thursday, March 16, 2017

❖ደብረ ዘይት

የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት ተብሎ ይጠራል።  የጌታችን ዳግም መምጣትና  የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተብሎ ተጠርቷል።  ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተባለ።  (ማቴ.24÷ 3) ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬሕይወት”
ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።”
ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24ን ነው፡ ጌታችን ሲመጣ ፍጥረት እንደማይፀና ኃጢአተኞች ደስታእንደማይሰማቸው ይገልጣል፡ በኃይሉ ፊት ፍጥረት፣ በፍርዱ ፊት ኃጥአን መቆም አይችሉምና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በብሉይ ኪዳን እመጣለሁ ብሎ መጥቷል፡ በአዲስ ኪዳንም እመጣለሁ ብሎ ቤተክርስቲያንን በተስፋ አስገዝቷታል።  ፍጥረት ሁሉ የሚጠብቀው አንድ ታላቅ እንግዳ ከፊታችን ባለው ባልራቀው ዘመን ይመጣል፡፡የሚመጣው በትሕትና ሳይሆን በልዕልና ነው።  በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል።  ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው ሆኖ አይመጣም፣  ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ይመጣል  ከእናቱ ጡትን እየለመነ አይመጣም፣ ለፍጥረት ሁሉ የሩጫውን ዋጋ ለመስጠት ይመጣል።  ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ አይመጣም።  ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ ይሰደዳሉ።  ለእኛ ለክርስቲያኖች መጣልን የምንለው እንግዳችን፣ ፈራጃችን እንጂ መጣብኝ የምንለው አይደለም፡፡

የጌታችን ዳግም ምጽአት፡-

1. የጸሎታችን መልስ ነው።
2. የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።
3. የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
4. የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
5. የእምነታችን ክብር ነው።
6. የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
7. የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡ 

              የጸሎታችን መልስ ነው
  ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ።  ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። ልበ ሙሉ ሆነው  ኃጢአት እንዳይሠሩ የመምጣቱ  ዜና ስለሚረብሻቸው ነው።  የጌታችን ዳግም ምጽአት በሚታሰብበት ቀን እንኳ ብዙ የኃጢአ ትመታሰቢያ ሲደረግ ይውላል።  ለብዙ ሰዎች እኩለ ጾም ከሥጋና ከስካር ከተላቀቁ አንድ ወር መሆኑን ለመገናኘትም ወር እንደሚቀራቸው የሚያስቡበት ቀን ነው።  በጊዜያዊ ጨዋነት የሰነበቱትም ሲሰክሩ የሚውሉበት የተውኔት ቀናቸው ነው።  ሃይማኖት የማይሞት ኃይል ነው።  ከሰው ልብ ግን ሊሞት የሚችለው ሰዎች እንደ ባሕል ቆጥረውት ሲኖሩ ነው።
 የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው።   የምንፈራውና ያርቅልኝ የምንለው ሳይሆን በየዕለቱ “መንግሥትህ ትምጣ”  እያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው።  የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው።  በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ.14÷17) ።  የክርስቶስ መንግሥቱ  የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ  ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው።  ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው።

የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው

ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” ይላል።  (ሮሜ.8÷19)ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” ይላል ቁ.22) ። በሰው ኃጢአት የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው። እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት እየተካፈሉ ነው። እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው። ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግ የሰውን ማረፍ ይናፍቃል።  የራሱም ዕረፍት ነውና።  ዛሬ በብዙ ነገር እናለቅሳለን።  ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን።  የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።

የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው
ማራናታ ማለት ጌታ ይመጣል ወይም ጌታ መጣ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 609) ።  ይህ ቃልዮሐንስ ራእዩን ሲዘጋ ተጠቅሞታል፡- “ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ.22÷20)።  ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው  የዘመናት ጣር ካየበኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌታ መምጣት እንደሆነ ተረዳ  ስለዚህም  ማራናታ አለ።  የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው።  በመጀመሪያ ምጽአቱ ሞት ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ መከራ ገደብ ያገኛል።

የተስፋችን ፍጻሜ ነው

የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡። የምንጠብቃቸው ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም።  ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እስከማያምረን ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “የተባረከውተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ.2÷12 13) ይላል።  ሰዎች ተስፋ ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ።   እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው። የክርስቶስ ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው።  ለቤተ ክርስቲያን የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው።
  
የእምነታችን ክብር ነው

ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡ የዘበቱብንና ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም።  የእግዚአብሔር ልጆች የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን በጉን እረኛችን አድርገን ወደ ፍስሐ ዓለም እንገባለን።

የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው
በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም” ይላል (ራእ.21÷1) ።  አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው።  ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው።  አሁን ፍጥረት አርጅቷል።  በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨመ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው።  ይህን አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣትነው።  ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል።

የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው

ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች።  ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያንበጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ።  ገነት ጊዜያዊ የነፍሶች ማረፊያ ናት። ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ። መንግሥተሰማያትና ገሀነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41) ።

የዘላለም ዘመንም ይከፈታል።  ዘወትር አዲስ የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን።

የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው።  ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው። ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል።

                 የእግዚአብሄር ጸጋና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን//
        



❖የአዲስ ኪዳን ጥናት በቅኝት መልክ

አዲስ ኪዳን ማለት አዲስ ውል አዲስ ስምምነት ማለት ነው፡፡ ለምን አዲስ ኪዳን ተባለ ስንል ፊተኛውን ኪዳን አስረጅቶ ስለገባና የዘላለም ኪዳን ስለሆነ ነው (ዕብ. 813 11-2)፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳን እንደሚገባ አስቀድሞ በነቢያት ተናግሯል (ኤር. 3131-34 ዕብ. 88-13)፡፡ ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን ሲነጻጸሩ አዲሱ ኪዳን ብልጫ አስገኝቷል፡፡ ብሉይ ኪዳን ባሰጣጡ ጊዜያዊ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን ዘላለማዊ ነው (ማቴ. 1113 ሉቃ. 1616)፡፡ ብሉይ ኪዳን የተሰጠው በሙሴ መካከለኛነት ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በእግዚአብሔር ልጅ መካከለኛነት ተሰጥቷል (ገላ. 319 1ጢሞ. 25)፡፡ ብሉይ ኪዳን ሕዝቡን ሊያድን ስላልቻለ የኲነኔ አገልግሎት ነበረ፤ አዲስ ኪዳን ግን የሕይወት አገልግሎት ነው (2ቆሮ. 37-11)፡፡ ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ላይ የተጻፈ የሕግ ግዴታ ሲሆን አዲስ ኪዳን ግን በልባችን ጽላት ላይ የተጻፈ የፍቅር ሕግ ነው (2ቆሮ. 33)፡፡

የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሰባት በሚያህሉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የተጻፈ የሃያ ሰባት መጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ እነዚህ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ እስኪያድርባቸው ጌታን ይከተሉ የነበረው ለምድራዊ ትልቅነት ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከተነሣና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ከምድራዊ የክብር አሳብ ተላቀው ሁሉን ጥለው ተከተሉት፡፡ ወንጌሉንም በማይመቹ ሁኔታዎች ለዓለም አደረሱ፡፡ መልእክቶቹን የጻፉት በርቀት የነበሩትን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ለማጽናት ነው፡፡ የመልእክቱ ባለቤት መንፈስ ቅዱስ ግን እኛን ጭምር በዚያ መልእክት ውስጥ ይመለከት ነበር፡፡
አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ የራሱ የሆነ አከፋፈል አለው፡፡ ስለዚህ በአራት ተከፍሎ ይጠናል፡፡ ወንጌል፣ ታሪክ፣ መልእክትና ትንቢት፡፡
                                ወንጌል

ወንጌል የሚባለው ከማቴዎስ እስከ ዮሐንስ ያሉት አራት ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መጸነስ፣ መወለድ፣ መኖርና መሞት፣ ትንሣኤና ዕርገት በሙሉነት ስለሚተርኩ ወንጌል የሚለውን ስያሜ አግኝተዋል፡፡ ወንጌል ማለት ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ መልእክት ነው (ሮሜ. 13-4)፡፡ ወንጌል ቃሉ ዩአንገሊዎን ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡ ትርጉሙም የምሥራች ቃል ወይም የድኅነት ዜና ማለት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ተወልዶ በመስቀል ላይ ስለ ኃጢአታችን ሞቶ ዓለምን ማዳኑን ስለሚናገርና ፍርድን የሚጠባበቁ ኃጢአተኞች ተስፋ ስለመጣላቸው ወንጌል ወይም የምሥራች ቃል ተብሏል፡፡

አራቱ ወንጌላት ቀጥተኛ ግባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ድኅነት የሚጠይቀውን ሙሉ መንገድ ተጉዞ የሰውን ዘር ከዘላለም ጥፋት ማዳኑ ነው፡፡ ፀሐፊዎቹም ሁለቱ ማለትም ማቴዎስና ዮሐንስ ከጌታ አሥራ ሁለት ደቀ መዛሙርት መካከል ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ማርቆስና ሉቃስ ከሐዋርያት ጋር በቅርበት የነበሩ ከእነርሱ የሰሙትን በጥንቃቄ የጻፉ ናቸው፡፡ የማቴዎስ፣ የማርቆስና የሉቃስ ወንጌላት ተመሳሳይ ትረካ ያላቸው ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው መሆኑን በመግለጥ እግዚአብሔር በሰውና በሰው ታሪክ መካከል ያደረገውን ይተርካሉ፡፡ ዮሐንስ ግን በተለየ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ክብር በመግለጥ አምላክነቱን ሰዎች እንዲቀበሉት ይጥራል፡፡ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተገልጦ ያደረገው ተአምርና የተናገረው ቃል ሰማይ ብራና፣ ዕፅዋት ሁሉ ብዕር፣ ውቅያኖስ ሁሉ ቀለም ቢሆኑ ተጽፎ አያልቅም (ዮሐ. 21252030)፡፡ ለመዳናችን የሚበቃን ግን ተጽፎልናል፡፡

                                     አራቱ ወንጌላት

የማቴዎስ ወንጌል- በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ምዕራፍ ካላቸው ሁለት መጻሕፍት አንዱ የማቴዎስ ወንጌል ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ለአይሁድ ስለሆነ የዘር ሐረግን፣ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ አይሁድ መሢሑን እንዲቀበሉ መሢሑ የአብርሃምና የዳዊት ዘር መሆኑን የሚገልጥ የዘር ፍሰትን ያወሳል፡፡ ለማስረጃም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በብዛት ይጠቅሳል፡፡ በዘር ሐረጉ ግን አይሁድ የማይጠቀሙበትን ስልት በመጠቀም አራት ሴቶችን ጠቅሷል (ማቴ. 14 . 5.6.16)፡፡ አይሁድ በዘር ሐረግ ውስጥ ሴቶችን አስገብተው አይቆጥሩም ነበርና፡፡ ክርስቶስ ግን የመምጣቱ አንዱ ዓላማ ይህን ልዩነት ለማስወገድ ነበር፡፡

የማርቆስ ወንጌል- ከወንጌላት ትንሽ ምዕራፎች ያሉት የማርቆስ ወንጌል ነው፡፡ የትምህርቱም ስልት የክርስቶስን የእጁን ተአምራት በመግለጥ በዘመኑ የነበሩ ሮማውያንን ለማሳመን ነው፡፡ ጌታችን በተያዘ ሌሊት እርቃኑን በነጠላ ሸፍኖ ይከተለው ነበርና በያዙት ጊዜ ነጠላውን ትቶ ራቁቱን የሸሸው ወጣት ማርቆስ መሆኑን ብዙ ሊቃውንቶች ይናገራሉ (ማር. 1451-52)፡፡ እናቱ ቤቷን ለአገልግሎት በመልቀቋ የማርቆስ እናት ቤት የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስያሜ አግኝታለች (ሐዋ. 1212-17)፡፡ ማርቆስ ከበርናባስ፣ ከጳውሎስና ከጴጥሮስ ጋር ብዙ ጊዜ አገልግሏል፡፡ የጴጥሮስም የመንፈስ ልጁ ነው (1ጴጥ. 513) ወንጌሉን የጻፈውም ከእነዚህ ሐዋርያት በጥልቀት በመጠየቅና በማዳመጥ ነው፡፡
የሉቃስ ወንጌል- ሉቃስ ከአሕዛብ ወገን የሆነና በክርስቶስ ያመነ የጳውሎስም ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው ነው፡፡ በሙያውም ሐኪም እንደ ነበረ ተጠቅሷል (ቈላ. 414)፡፡ ስለ ክርስቶስም ሙሉ ትረካ ያቀረበ ፀሐፊ ነው፡፡ ወንጌሉን የጻፈው ከአሕዛብ ወገን ለነበረና ላመነ ቴዎፍሎስ ለሚባል ወዳጁ ነው፡፡ ማቴዎስ ወንጌሉን ከዘር ሐረግ ይጀምራል፣ ማርቆስ ከጥምቀቱ ይጀምራል፣ ሉቃስ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኛ ከሆነው ከዮሐንስ መጥምቅ የጽንሰት ዜና ይጀምራል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሉቃስ ወንጌሉንና የሐዋርያት ሥራን ጽፎአል፡፡

የዮሐንስ ወንጌል- ዮሐንስ ወንጌላዊ ከሦስቱ ወንጌላት በተለየ ሁኔታ ወንጌሉን ጽፎአል፡፡ ሦስቱ ወንጌላውያን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆንና ሰብአዊ ቅርበቱን ተርከዋል፡፡ ዮሐንስ ደግሞ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር በማጉላት ጽፎአል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውነትና ፍጹም አምላክነት መቻቻል አለባቸው፡፡ ሰውነቱ አምላክነቱን ጋርዶብን አምልኮ እንዳንነፍገው፣ አምላክነቱ ሰውነቱን ሸፍኖብን እንዳናርቀው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የወንጌላውያኑም ጭንቀት ይህ ነው፡፡ ዮሐንስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ወንጌል፣ ሦስት መልእክታት፣ አንድ የራእይ መጽሐፍ ጽፎአል፡፡




                                      ታሪክ

በአዲስ ኪዳን የታሪክ ክፍል ተብሎ የሚጠራው አንድ ጥራዝ ብቻ ነው፡፡ እርሱም የሐዋርያት ሥራ ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ- የሐዋርያት ሥራን የጻፈው ሉቃስ ነው፡፡ የጻፈውም ወንጌልን ለጻፈለት ቴዎፍሎስ ለተባለው ወዳጁ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ሲናገር የሐዋርያት ሥራ ደግሞ ከዕርገቱ በኋላ ስላሉት ዐሥር ቀኖችና ስለ መንፈስ ቅዱስ መውረድ ይናገራል፡፡ የመጽሐፉ ሙሉ ይዘት ወንጌል ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ከዚያም እስከ መላው ዓለም በእንዴት ያለ ጸጋና ዋጋ መድረሱን የሚተርክ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት አድሮ የሠራው ሥራ በመሆኑ የሐዋርያት ሥራ ቢባልም ታሪኩን ስንዘልቀው ግንየመንፈስ ቅዱስ ሥራቢባል መልካም ነበር ያሰኛል፡፡ በዚህ መጽሐፍ በስፋት የተገለጠው የጴጥሮስና የጳውሎስ አገልግሎት ነው፡፡ መጽሐፉ እንደ ሌሎቹ መልእክታት በሰላምታ ወይም በምርቃት አይዘጋም፡፡ ይህ የሚያስረዳን የሐዋርያት ሥራ በትውልድ ሁሉ መቀጠሉን ነው፡፡

                                     መልእክት

የአዲስ ኪዳን ሦስተኛው አከፋፈል መልእክት ነው፡፡ መልእክት የሚባሉት ከሮሜ እስከ ይሁዳ ድረስ ያሉት 21 የመጻሕፍት ጥቅልል ናቸው፡፡ ፀሐፊዎቹም ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ናቸው፡፡ የተጻፉትም ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡

የጳውሎስ መልእክታት

ከሮሜ እስከ ዕብራውያን ድረስ ያሉት ዐሥራ አራት መልእክቶች ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ናቸው፡፡ ጳውሎስ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት መካከል አይደለም፡፡ ጌታ ካረገ ከስምንት ዓመት በኋላ ነው የተጠራው፡፡ ክርስትናን በብርቱ ይቃወም በነበረ ሰዓት በደማስቆ መንገድ በመብረቅ ብርሃን ጥሎት፣ ሦስት ቀን ዓይኑን አውሮት በወንጌል አመነ (የሐዋ. 918)፡፡ ከሁሉ ኋላ የተጠራ ቢሆንም ከሐዋርያት ይልቅ ሮጧል፣ ዋጋ ከፍሏል፣ አብያተ ክርስቲያናትን መሥርቷል፣ መልእክታትን ጽፏል፡፡ በመጨረሻም 67 . በሮም አደባባይ በሰይፍ ሞቷል፡፡ መልእክቶቹ ግን ከከዋክብት ደምቀው በዓለም ሁሉ በየዕለቱ ያበራሉ፡፡ መልእክታቱ የተጻፉት ለግለሰቦችና ለአብያተ ክርስቲያናት ሲሆን ምእመናንን ለማጽናት፣ ለመገሰጽ፣ ለማጽናናት፣ ቤተ ክርስቲያንን ፍሬያማ ለማድረግ ባጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመንና በማወቅ ለማደግ ተጽፈዋል፡፡ ጳውሎስ መልእክታቱን የጻፈው ከእስር በፊትና በእስር ዘመን ነው፡፡ መልእክታቱም አብያተ ክርስቲያናቱ በሚገኙበት አገርና ግለሰቦች ተሰይመዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የሮሜ መልእክት ሮም ለምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ሲሆን የጢሞቴዎስ መልእክት ደግሞ የጳውሎስ የመንፈስ ልጅ ለሆነው ለኤፌሶኑ ጳጳስ ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ነው፡፡

የጴጥሮስ መልእክታት

ጴጥሮስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱና የመጀመሪያው ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስን የእጁን ተአምራት፣ የቃሉን ትምህርት በቀጥታ የተቀበለ ነው፡፡ ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ሲሆን ጴጥሮስ የአይሁድ ሐዋርያ ነበር፡፡ 67 . በሮም አደባባይ የቊልቊሊት ተሰቅሎ እስኪሞት በብዙ ስደትና መከራ ወንጌልን ሰብኮአል፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት መልእክታትን ጽፎአል፡፡ የመጀመሪያው መልእክቱ በተለያዩ የእስያ አውራጃዎች ስለ ወንጌል ለተሰደዱ ክርስቲያን አይሁዶች የጻፈው ሲሆን በመታገሥ ያለውን ሰማያዊ ዋጋ በመግለጥ ሊያጸናቸው ጽፏል፡፡ ሁለተኛይቱ የጴጥሮስ መልእክት ደግሞ በክርስቲያኖች መካከል ሰርገው ስለገቡ የሐሰት መምህራን (መናፍቃን) ምእመናን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጽፎአል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የአረማውያን ነገሥታትን ያህል የሐሰት መምህራንም ጎጂዎቿ ናቸውና፡፡

የዮሐንስ መልእክታት

ዮሐንስ የክርስቶስን መለኮታዊ ክብር ለማጉላት ወንጌሉን እንደ ጻፈ  ዓይተናል፡፡ ደግሞም ሦስት መልእክታትንም አዘጋጅቷል፡፡ መልእክታቱንም ሆነ ወንጌሉን እንዲሁም ራእዩን የጻፈው በዕድሜው መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ የመጀመሪያይቱን መልእክቱን የጻፈው በዘመኑ ተስፋፍቶ የነበረውን የመናፍቃንን እንቅስቃሴ ለመጋፈጥና ምእመናን በፍቅር እየተባበሩ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛይቱን መልእክት ደግሞ የጻፈው ለአንዲት አማኝ ሴት ሲሆን ከስህተት ትምህርት እንድትጠበቅ ነው፡፡ ሦስተኛይቱ የዮሐንስ መልእክት በቤቱ እንግዶችን ለሚቀበል ጋይዮስ ለተባለ በጎ አማኝ ለምስጋና የጻፈለት መልእክት ነው፡፡

የያዕቆብ መልእክት

ያዕቆብ ከጌታ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነው፡፡ ይህ ያዕቆብ ይህችን ቀደምት መልእክቱን የጻፈው በስደት ለተበተኑት ክርስቲያን አይሁድ ሲሆን የመልእክቱ ዋና ዓላማ በመከራቸው እንዲፀኑና እምነታቸውን በምግባር እንዲገልጡ ለማነቃቃት ነው፡፡

የይሁዳ መልእክት

ባለ አንድ ምዕራፍ ከሆኑት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ የይሁዳ መልእክት ሲሆን ይሁዳም መልእክቱን የጻፈው በስም ላልተጠቀሱ አማንያን ነው፡፡ የመልእክቱም ዓላማ ክርስቲያኖች ሁሉ እምነታቸውን እንዲጠብቁ ለማስጠንቀቅ ነው፡፡

                                          ትንቢት

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የትንቢት መጽሐፍ ተብሎ የሚጠራው የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡

የዮሐንስ ራእይ- ዮሐንስ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ተግዞ /ታስሮ/ ሳለ በራእይ ያለፈውን፣ ያለውንና የሚመጣውን ተገልጾለት ጽፏል፡፡ የዮሐንስ ራእይ ክርስቲያኖችን ለማይቀረው የክርስቶስ ምጽአት ያዘጋጃል፡፡ አገላለጹም ሥዕላዊ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሥዕል ከብዙ ቃላት ይልቅ የመናገር አቅም ስላለውና ዳግመኛም መጽሐፉን ከአደጋ ለመከላከል ነው፡፡ ትንቢቶቹ በግልጽ ቢጻፉ ኖሮ አረማውያን ነገሥታት በቶሎ ይጠፉታልና ጠላት ለመቀነስ ነው፡፡

ይህንን ጥናት ስናጠና የመጽሐፍ ቅዱሳችንን ማውጫ እየተመለከትን ብናጠና ይበልጥ ይብራራልናል፡፡ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በምዕራፍ ይከፈላል፡፡ ምዕራፉ ደግሞ በቊጥር ይከፈላል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲጠቀስ በአጭሩ ይጠቀሳል፡፡ ለምሳሌ፡- ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አሥራ አምስት ቊጥር ስድስት ቀጥሎ ባለው መልኩ ይጠቀሳል፡- (ዘፍ. 15 6)፡፡