ሰው የለኝም፦
ዓበይተ ኃይላተ፣ ዓበይተ
ኃይላተ ገብረ ኢየሱስ በእለተ ሰንበት፣ እም ኩሉ ዘየዓቢ እነግር ዘገብረ ጽቡር ያአውር ህያወ ዓይነ ውእቱኒ ወረቀ ምድረ ወገብረ ጽቡረ ወአህየዎ ለዘእውሩ ተወልደ፡፡
“በሰንበት ቀን ኢየሱስ ታላላቅ ተአምራትን አደረገ፡፡ ከዚህ ሁሉ
የሚበልጥ ያደረገውንም እናገራለሁ፡፡ ጭቃ ደህናውን ዓይን ያጠፋል፣ እርሱ ግን በምድር ላይ ተፍቶ ጭቃ አድርጎ ዕውር ሆኖ
የተወለደውን አዳነ፡፡”
|
የዓቢ ጾም አራተኛው
ሳምንት መጻጉዕ ይባላል፡፡ ቅዱስ ያሬድም በዝማሬው ጌታ ድውያንን
መጎብኘቱንና መፈወሱን በማስተዋል ያነሳል፡፡
የስያሜው ዋና
ታሪክ፥በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ በምትባልና አምስት መመላለሻ በነበረባት አንዲት መጠመቂያ ሥፍራ
ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ ስለታመመ አንድ ሰው የሚተርክ ነው፡፡
ጌታ ወደዚህ ሥፍራ
የመጣው በሰንበት ቀን ነው፡፡ በዚያም የመጠመቂያውን ቦታ ውኃ የእግዚአብሔር መልአክ ባንቀሳቀሰው ጊዜ ቀድሞ በመግባት
ለመፈወስ፦ “በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር።”(ዮሐ.5፥2)
ይህ ሰው የነበረበት በሽታ ከፍ ሲል የሥጋ ደዌ ወይም የሰውነት መስለል ወይም ሽባነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከንባቡ
እንደምንረዳውም ሰውየው እጅግ በጣም ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም እንደእርሱ አይነት ሰዎች ውኃው በተንቀሳቀሰ ጊዜ
ፈጥነው ገብተው መፈወስ የሚያስችል አቅም ወይም ዘመድ ሲኖራቸው እርሱ ግን አልነበረውም፡፡
ጌታችን ወደዚህ ሰው
በመምጣት፦ “እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን? አለው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነጋሪ የማያስፈልገው ሁሉን አዋቂ ነው፡፡
በዚህ ክፍል አንድ ልዩ ነገር እናያለን፡፡ ጌታ ብዙ ጊዜ ሲፈውስ የምናየው ሰዎች እንዲያድናቸው በጠየቁት ጊዜ
ነው፡፡ በእርግጥ ሰውየው፥ “አድነኝ” ቢለው እንኳ የጌታ ኢየሱስ ጥያቄ ተገቢና ትክክል ነው፡፡ እርሱ መሻታችንን አስገድዶ
የሚገባ አይደለምና፡፡
ሰውየው፦ “ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው
ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።” (ቁ.7) ፡፡
ይህ ሰውዬ ሰው የለኝም ብሎ ተስፋ በመቁረጥ የሚኖር ሰው ነበር፡፡ ሰውየው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው 38 ዓመት በመጠበቁ
ይሆናል፡፡ በእርግጥ የዘመኑ ርዝመት ነፍስን ያዝል ይሆናል ፤ ነገር ግን ታማኙ ጌታ በዙፋኑ አለ፡፡ ለዚህ ሰው ዙርያው ሁሉ
ጨለማ ነው ፤ ጌታ ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ መጥቶ አጠገቡ ቆመ፡፡
የረዘመ መከራ ፣ እልህ አስጨራሽ ሙከራ ፣ ባለመድኃኒትቶች ሁሉ ያላወቁት
የሕመም እንቆቅልሽ ፣ ዳኛ ያጣመመው ፍርድ ፣ ደርሶባችሁ ዙርያው ሁሉ ገደል የሆነባችሁ አይዟችሁ አዳኙ በደጅ ነው፡፡
የሰውየው ናፍቆት ፈጥኖ ከውኃው በመግባት መፈወስ ነበር፡፡ ለዚያ ደግሞ የሚረዳው ሰው የለውም፡፡ ይህ እጅግ የሚያም ነገር
አለው ፤ ቀና ማለት ፣ ከሰው እኩል መቆም ፣ መፈወስ ፣ መዳን ፣ ከመከራ መውጣት መሻቱ ቢኖረውም ... በኢየሱስ ላይ ያለው
እምነት ደካማ ነበር፡፡ እንዲያው ከፈወሰውም በኋላ እንኳ ጌታን አላወቀውም፡፡ ጌታ ግን፦ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም
ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።”
ጌታ ብዙ በሽተኞች በዚያ ቢኖሩም የሄደው ግን ምንም ሰው ወደሌለው ወደዚህ አንድ ሰው እንደሆነ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
በእርግጥም
እርሱ፦“ለድሃ አደጉና ለመበለቲቱ ይፈርዳል፥ መብልና ልብስም ይሰጠው ዘንድ ስደተኛውን ይወድዳል።” (ዘዳግ.10፥18)
“ለድሀ አደግም
ረዳቱ አንተ ነህ።” ፤ “እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።” (መዝ.10፥14 ፤ 68፥5)
“መበለቲቱንና ድሀ
አደጉን በሚያስጨንቁ፥ የመጻተኛውንም ፍርድ በሚያጣምሙ፥ እኔንም በማይፈሩ ላይ ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት
ጌታ እግዚአብሔር፦” (ሚል.3፥5)
አዎ! እግዚአብሔር
ሰው ለሌላቸው ሰው ሆኖ በሥጋ የተገለጠ ነው፡፡ ሰው ለናቃቸውና ለገፋቸው ፣ ሰው ለሚጠየፋቸው ፣ ጐባጣና ድውይም ... እርሱ
የድሆች አምላክ ነውና ከመከራ ሁሉ ያድናቸዋል ፤ ይሟገትላቸዋልም፡፡ እኛም ይህን እውነት ከክርስቶስ ተምረናል፡፡
(1ጴጥ.2፥21)
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሰውየው ጌታን እንኳ ባያውቀውም ጌታ ኢየሱስ ግን በበሽታው ላይ ያለውን ፍጹም ሥልጣን
አሳይቶናል፡፡ ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ በሁሉም በሽታዎች ላይ ሥልጣን አለው፡፡ ሰውየው ባያውቀው እንኳ ጌታችን ከደዌው ሁሉ
ፈውሶታል፡፡ ውለታን ሳይጠብቅ ፈወሰው፡፡ እኛም ለሰዎች መልካምን ነገር ለማድረግ ምንም ዓይነት ቅድመ
ሁኔታ አይኑረን፤ ለተጠቃውና ለድኃው
፤ የሰው ያለህ እያለ ለሚጮኸው እንድረስለት፡፡ እንሟገትለትም፡፡
የእግዚአብሄር ጸጋና ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን//
No comments:
Post a Comment