Thursday, March 21, 2019

❖መጻጉዕ

 መጻጉዕ፦
( ፈዋሻችን ኢየሱስ ክርስቶስ)

መጻጉዕ የዐቢይ ጾም 4ኛ ሳምንት ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገለጠበት ዘመን የፈወሳቸውን ሕሙማን ማስረጃ በማድረግ ከፈወሳቸው ሕሙማን፥ ካነጻቸው ለምጻሞች፥ ቀን ካወጣላቸው ሰዎች፥ ከሰው ከቀላቀላቸው ግፉአን፥ ጋር በመቆም ቤዛችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናመሰግንበት ሳምንት ነው፡፡ ለአምልኮ የተመረጠው የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 5 ነው፡፡በወንጌሉ እንደተጻፈው ባለታሪኩ ሰውነቱ የሰለለ፤ ወደ መጠመቂያይቱ ተጋፍቶ የሚያስገባው ሰው የሌለው፤ ለብዙ ዘመናት ፈውሱን በተስፋ ሲጠብቅ የነበረ ሰው ነው፡፡ፈዋሹ ጌታ ኢየሱስ "ልትድን ትወዳለህን ? " ብሎ ጠየቀው፡፡እርሱም "ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።" ኢየሱስ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው።ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ዮሐ 5:7-12:: ክብር ለፈዋሹ!!

➊ ፈዋሽ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰዎች በተለያዩ ደዌዎች ሊያዙ ይችላሉ፤ ፈዋሹ ግን ሁሉን በሁሉ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው፡፡ ፈዋሹ በነፃ የሚፈውስ፥ ጤናን የሚመልስ አምላክ ነው"እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቁስልህንም እፈውሳለሁ" ኤር 30:17፡፡ በአንድም በሌላም በብዙም በጥቂትም ያድናል፡፡እኔ ፈዋሽህ ነኝ ያለ ቁስላችንን የማይፀየፍ አምላክ ነው፡፡ፈዋሹን የጠበቀ አንድ ቀን አልጋውን ተሸክሞ መሄዱ አይቀርም፡፡በዘመናችን ከእግር ጥፍራ እስከ ራስ ፀጉር ደዌ በሁሉ ሆኗል ፣ራስ ሁሉ ለህመም ልብም ለድካም ሆኗል ስሙን እየቀያየረ ደዌ ይመጣል፤ የስጋት ምንጭም ሆኗል፤ መፍትሔው ፈዋሹ ነው። ኢየሱስ ዛሬም በስሙ፣ በቃሉ እና በመንፈሱ ይፈውሳል። "እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝ" ዘጸ 15:26

➋ድኅነት የሰውን ፈቃድ ይፈልጋል፡፡ ፈውስ፣ ስጦታ እና ድኅነት የእግዚአብሔር የቸርነት ብልጽግና ፍሬዎች ናቸው፡፡እግዚአብሔር ለጥቅማችን የሆነን ነገር እንኳ አስፈቅዶ ያደርጋል፡፡ልትድን ትወዳለህ ብሎ ጠይቆ ነውና ያዳነው፡፡ጌታ ሲፈውስ ያለ ፈቃድ የፈወሳቸው በአጋንንት እስራት የተያዙትን ብቻ ነው፤ ይህን ያደረገው አእምሯቸው በሌላ አዛዥ ስለተያዘ ተናጋሪው ተከራዩ እንጂ ሕመምተኛው ስላልሆነ ነው፡፡እኛም የተያዝንበት ሕመም፥ ፈውስ ፍለጋ የወጣንበት ቁስል ይኖረናል። ፈዋሹ እግዚአብሔር ሊፈውሰን ፈቃዱ ነው፤ ምሕረቱ ግን ለሮጠ ወይም ለቀደመ ሳይሆን በእምነት ፈቃድ ለተከተለ ነው፡፡"እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ።"ሮሜ 9:16። በደዌ ሥጋ ወነፍስ ለተያዝን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ፈውስ ይሁን!!!

❖ምኩራብ


 ምኩራብ፦
~የቤትህ ቅናት...!
    (መዝ.68፥9)

የዐብይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኩራብ ይባላል፡፡ይህ ሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደሱን የጎበኘበት ነው፡፡ታሪኩ በማቴዎስ እና በዮሐንስ ወንጌል ተመዝግቧል፡፡ ጌታ፣ አምላክ፣ ሕይወት እና መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቅደስ ሲገባ መቅደሱ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ የንግድ ቤት ሆኖ አገኘ፡፡ እጅግ አዘነ፥ ጅራፍ አበጅቶ እንስሳትን ከመቅደሱ አወጣቸው፡፡ሰዎችን ገሰጸ፡፡ "ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።" (ዮሐ 2፥16)  ደቀመዛሙርቱ "የቤትህ ቅናት በላኝ" የሚለውን አሰቡ፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ የምናያቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦

1- መቅደሱ የጸሎት ቤት ነው፦
በጊዜው የነበረው መቅደስ የጸሎት ቤት ነበረ። ሰዎቹ ግን የገበያ አዳራሽ አድርገውት ነበረ። ወዳጆቼ ዛሬም ቢሆን በስሙ የተሰየሙ የጸሎት ቤቶች ለታሰበላቸው አላማ መዋል አለባቸው። ቤቱ መንፈሳዊ ነው ሥጋዊነት ሊነግስበት አይገባም፡፡ ቤቱ የዕረፍት ቤት ነው ሁከት መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ቤቱ የግለሰቦች ቤት አይደለም፤ ስለዚህ ማንም ማንንም የመንካት መብት የለውም፡፡ ቤቱ የሽፍቶች ዋሻ አይደለም፡፡ ቤቱ በንስሐ ለሚመለሱ እንጂ በዐመፅ ለሚቀጥሉት መደበቂያ አይደለም፡፡

 2- ሕያው እና ቅዱስ መቅደስ እንሁን፦
ሰውነታችን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው፤ (1ቆሮ 6፥19):: ስለዚህ ሰውነታችን የቅድስና መኖሪያ ብቻ ይሁን፡፡አመፅ፣ ግፍ፣ የክፋት አሳብ በውስጣችን መኖር የለበትም፡፡በእግዚአብሔር ላይ ያመጹ አጋንንት በኛ ልብ ሸፍተው ሊደበቁ አይገባም፡፡እኛ የልዑል ማደሪያ ብቻ ለመሆን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እንሰራ፡፡ሰውነታችን በመልካምነት አጊጦ በክርስቶስ ደም ተቀድሶ የአባቱ ቤት ይሁን፡፡ቤቱን ለታሰበለት መንፈሳዊ ዓላማ መጠቀም አለብን፡፡እግዚአብሔር ያያል፥ በቤቱ የሚሆነውን እና የምንሆነውን ያያል፡፡ "ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።" (ኤርምያስ 7፥11)። ስለዚህ ራሳችንን ቅዱስ፣ ሕያው እና እግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መስዋዕት አድርገን እናቅርብ።

3- ለቤቱ እንቅና፦
ቤቱ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ነው፡፡በዚህ ዘመን ዓይናችን እያየ ብዙ የሥላሴ ቤቶች እየፈረሱ ነው፡፡ትውልድ በሱስ ሲፈርስ፥ ተስፋ ቢስ ሆኖ ሲንከራተት፥ የአጋንንት ማደሪያ ሆኖ ሲሰቃይ፥ የትውልድ ዝንባሌ ወደ አመፃ ሲሆን እያየን ተደላድለን መቀመጣችን ለቤቱ እንደማንቀና ያሳያል፡፡ወልድ የተወለደው ቀንቶልን ነው፤ መዳናችን የተፈፀመው በእግዚብሔር ቅናት ነው፡፡ (ኢሳ. 9፥7) ኤልያስ ለእግዚአብሔር ክብር ቀንቶአል፡፡"ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።" (1ነገሥት 19፥10)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጅራፍ ያነሳው ለቤቱ ቀንቶ ነው፡፡በልባችን መሽገው የነበሩትን አጋንንት በደሙ ኃይል ጠራርጎ አስወጣ፥ ለአባቱ ቅዱስና ሕያው ቤት አድርጎ ሠራን፡፡እኛ በደም የተሠራን የሠው እጅ ያልሠራን የልዑል ማደሪያ ነን፡፡የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ነን፡፡ክርስቶስ ለሞተለት የደም ዋጋ ለተከፈለለት እንቅና፡፡

4- ቅጣት ከቤቱ እንደሚጀምር እናስተውል፦ እግዚአብሔር ፈራጅ ነው፤ ከብዙ ትዕግስት በኋላ ጅራፍ ያነሳል። ያኔ ቅጣቱ የሚጀምረው ከመቅደሱ ነው ሕዝብ ጋር ከመሄዱ በፊት ባለ አደራዎቹ ከሆኑት ከአገልጋዮቹ ይጀምራል፡፡መቼ ነው የምንመለሰው ? መቼ ነው በቤቱ ተገቢ ነገር ብቻ የምናደርገው ? ንግዱ ላይ በርትተን ቢመጣስ ? ነፍሳትን እየበተኑ ገንዘብ መሰብሰብ እስከ መቼ ?
ቅጣቱ ከእኛ ይጀምራል፡፡                                       
     ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!!
===●===●===●===