❖ ምኩራብ፦
~የቤትህ ቅናት...!
(መዝ.68፥9)
የዐብይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኩራብ ይባላል፡፡ይህ ሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተመቅደሱን የጎበኘበት ነው፡፡ታሪኩ በማቴዎስ እና በዮሐንስ ወንጌል ተመዝግቧል፡፡ ጌታ፣ አምላክ፣ ሕይወት እና መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቅደስ ሲገባ መቅደሱ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ የንግድ ቤት ሆኖ አገኘ፡፡ እጅግ አዘነ፥ ጅራፍ አበጅቶ እንስሳትን ከመቅደሱ አወጣቸው፡፡ሰዎችን ገሰጸ፡፡ "ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።" (ዮሐ 2፥16) ደቀመዛሙርቱ "የቤትህ ቅናት በላኝ" የሚለውን አሰቡ፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ የምናያቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦
1- መቅደሱ የጸሎት ቤት ነው፦
በጊዜው የነበረው መቅደስ የጸሎት ቤት ነበረ። ሰዎቹ ግን የገበያ አዳራሽ አድርገውት ነበረ። ወዳጆቼ ዛሬም ቢሆን በስሙ የተሰየሙ የጸሎት ቤቶች ለታሰበላቸው አላማ መዋል አለባቸው። ቤቱ መንፈሳዊ ነው ሥጋዊነት ሊነግስበት አይገባም፡፡ ቤቱ የዕረፍት ቤት ነው ሁከት መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ቤቱ የግለሰቦች ቤት አይደለም፤ ስለዚህ ማንም ማንንም የመንካት መብት የለውም፡፡ ቤቱ የሽፍቶች ዋሻ አይደለም፡፡ ቤቱ በንስሐ ለሚመለሱ እንጂ በዐመፅ ለሚቀጥሉት መደበቂያ አይደለም፡፡
2- ሕያው እና ቅዱስ መቅደስ እንሁን፦
ሰውነታችን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው፤ (1ቆሮ 6፥19):: ስለዚህ ሰውነታችን የቅድስና መኖሪያ ብቻ ይሁን፡፡አመፅ፣ ግፍ፣ የክፋት አሳብ በውስጣችን መኖር የለበትም፡፡በእግዚአብሔር ላይ ያመጹ አጋንንት በኛ ልብ ሸፍተው ሊደበቁ አይገባም፡፡እኛ የልዑል ማደሪያ ብቻ ለመሆን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እንሰራ፡፡ሰውነታችን በመልካምነት አጊጦ በክርስቶስ ደም ተቀድሶ የአባቱ ቤት ይሁን፡፡ቤቱን ለታሰበለት መንፈሳዊ ዓላማ መጠቀም አለብን፡፡እግዚአብሔር ያያል፥ በቤቱ የሚሆነውን እና የምንሆነውን ያያል፡፡ "ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።" (ኤርምያስ 7፥11)። ስለዚህ ራሳችንን ቅዱስ፣ ሕያው እና እግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መስዋዕት አድርገን እናቅርብ።
3- ለቤቱ እንቅና፦
ቤቱ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ነው፡፡በዚህ ዘመን ዓይናችን እያየ ብዙ የሥላሴ ቤቶች እየፈረሱ ነው፡፡ትውልድ በሱስ ሲፈርስ፥ ተስፋ ቢስ ሆኖ ሲንከራተት፥ የአጋንንት ማደሪያ ሆኖ ሲሰቃይ፥ የትውልድ ዝንባሌ ወደ አመፃ ሲሆን እያየን ተደላድለን መቀመጣችን ለቤቱ እንደማንቀና ያሳያል፡፡ወልድ የተወለደው ቀንቶልን ነው፤ መዳናችን የተፈፀመው በእግዚብሔር ቅናት ነው፡፡ (ኢሳ. 9፥7) ኤልያስ ለእግዚአብሔር ክብር ቀንቶአል፡፡"ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ አለ።" (1ነገሥት 19፥10)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጅራፍ ያነሳው ለቤቱ ቀንቶ ነው፡፡በልባችን መሽገው የነበሩትን አጋንንት በደሙ ኃይል ጠራርጎ አስወጣ፥ ለአባቱ ቅዱስና ሕያው ቤት አድርጎ ሠራን፡፡እኛ በደም የተሠራን የሠው እጅ ያልሠራን የልዑል ማደሪያ ነን፡፡የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ነን፡፡ክርስቶስ ለሞተለት የደም ዋጋ ለተከፈለለት እንቅና፡፡
4- ቅጣት ከቤቱ እንደሚጀምር እናስተውል፦ እግዚአብሔር ፈራጅ ነው፤ ከብዙ ትዕግስት በኋላ ጅራፍ ያነሳል። ያኔ ቅጣቱ የሚጀምረው ከመቅደሱ ነው ሕዝብ ጋር ከመሄዱ በፊት ባለ አደራዎቹ ከሆኑት ከአገልጋዮቹ ይጀምራል፡፡መቼ ነው የምንመለሰው ? መቼ ነው በቤቱ ተገቢ ነገር ብቻ የምናደርገው ? ንግዱ ላይ በርትተን ቢመጣስ ? ነፍሳትን እየበተኑ ገንዘብ መሰብሰብ እስከ መቼ ?
ቅጣቱ ከእኛ ይጀምራል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!!
===●===●===●===
No comments:
Post a Comment