Sunday, May 31, 2020

❖በልዑል መጠጊያ የሚኖር፦

ይህ የመዝሙር ክፍል አማኞች እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል ምን ያህል ዋስትና እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። እግዚአብሔር በአደጋዎች ሁል መጠጊያችን እንደሚሆን፣ ከዚህም የተነሣ መንፈሳዊና ሥጋዊ አደጋ ሲመጣ ቀድመን የእግዚአብሔርን ጥበቃ ልንፈልግ እንድምንችል የሚረጋግጥ ስንኝ ነው።

በእግዚአብሔር ለተወደድን ይኸውም ራሳችንን ለልዑል እግዚአብሔር ፈቃድና ጥበቃ አሳልፈን ለምንሰጥ፣ በእግዚአብሔር ሀልዎት ዕለት ዕለት ለመኖር ለምንፈልግ እጅግ ዋስትና ይሰጣል። 

 "በእጁ ጥላ ሰወረኝ፤ የተወለወለ ፍላጻ አደረገኝ፤ በሰገባውም ውስጥ ሸሸገኝ"።እንዳለው ነብዪ (ኢሳ 49፥2) እግዚአብሔር የእውነት መደበቂያችን ነው። ተሸጉጠን ክፉውን የምናሳልፍበት ምሽጋችን።

የዚህን መዝሙር ስንኞችን ሲያነብ ከነችግሩና መከራው አንብቦ የሚጨርስ ማነው? ስትጀምር የነበረው አደጋ ወይም መከራ ሁሉ ቁጥር አንድ ጋር አብቅቶ ሌላ ርዕስ ውስጥ ትገባላችሁ። እስኪ ከፋፍለን የእግዚአብሔርን ጥበቃ እንቃኘው

1) መዝሙሩ 91፥1-2 ፦
'' በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ። ''

ከሁሉ በላይ የሆነውንና የኃይሉን አምላክ መጠጊያው አድርጎ የሚኖር ሰው የሕይወቱ ዋስትና የሚያስተማምን በመሆኑ እግዚአብሔር መጠጊያዬና ምሽጌ የምተማመንበት ፈጣሪዬም ነው ብሎ ይመሰክራል።
   =} ምሳሌ:- አንድ ህፃን አባቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ እየወረወረ ሲያጫውተው ከሚተማመነው በላይ አደጋ ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር መተማመን። ይህንንም በእምነት መመስክር ያጋጠመን አደጋ ከእኛ ያሸሸዋል።

2) መዝሙር 91፥3-4፦
'' እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ''

እግዚአብሔር ሕዝቡን ከጠላት ይጠብቃል፣ በላባዎቹ ይጋርዳቸዋል፣ ጋሻ እና መከታ ይሆናቸዋል። ለእርሱ የአደጋውም ሆነ የችግሩ ግዝፈት እኛን ከመጠበቅ አያስቀረውም።
   =} አባባል:- ለእግዚአብሔር የችግርህን መጠን ከምትነግረው ይልቅ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለችግርህ ንገረው። የተባለውም ለዚህ ነው።

3) መዝሙር 91፥5-6፦
'' ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። ''

የእግዚአብሔር እንክብካቤ ጽኑና በቂ ነው ምክንያቱም ጥበቃው የተመሰረተው በማንነቱ ላይ ስለሆነ። እርሱ ሲጠብቅ ቀን አይል ሌሊት አይል ሁልጊዜ ነው። በጊዜ አይወሰን በስፍራም እንዲሁ በመዞር የተደረገ ጥላ የለበትምና። የእግዚአብሔር ጥበቃ በቀንና በሌሊት እንደ ሆነ ተፈጥሮአዊ በሆኑ ምክንያቶች ከሚመጣ ፍርሀትና ድንጋጤ ይጠብቀናል።
=} ሰባኪው:- እንኳን ሌሊት ተኝተን አይደለም ቆመንም አይተን ከምናልፈው አደጋ ሳናየው ጠብቆን ያሳለፈን እጅግ ብዙ ነው። ተውት ያስተዋልነውን!!!

4) መዝሙር 91፥7፦

'' በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። ''

እርሱ በምድር ላይ በሚሆኑ ነገሮች ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን ስላለው ለጥበቃው ወሰን የለውም። እንክብካቤውና ጥበቃው የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለማሳየት ሺህ እና አሥር ሺህ በማለት ይገልፀዋል። እግዚአብሔርን የሚያልፍ ችግር የለም።
   =} መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ:- ሕዝያስ እንዳጽናናቸው
(መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 32፥7-8 ) ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛም ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው ብሎ አጸናናቸው። ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።

5) መዝሙር 91፥8፦
'' በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። ''

ጻድቃን የእግዚአብሔርን ማዳን በእምነት ዐይን ማየታቸው ይበለጥ እንዲበረቱ ያደርጋቸዋል እግዚአብሔር ጻድቃንን ለመጠበቅና ለመባረክ ቃል ገብቷል ጻድቃን የእግዚአብሔርን ፍትሕና ታማኝነት እንዲሁም የክፉዎችን መቀጣት በዐይናቸው ይመለከታሉ።
=} አመለካከት:- ሰው በሚያየው ሳይሆን በሚያምነው ይኖራልና።

6) መዝሙር 91፥9-10፦
'' አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። ''

ልዑሉን መጠጊያችን በማድረግ የጥበብን መንገድ እንድንከተል ያበረታታል እርሱ መጠጊያችን ነው በምድር ላይ የሚሆነው ማንኛውም ነገር በእርሱ ቁጥጥር ሥር ነው ክፉ ነገር ወይም መቅሠፍት ቢሆን ያል እርሱ ፈቃድ አይሆንምና።
=} ሂሳባዊ ቀመር:- ይጠጌ አይነኬ (asymptote)፤ ቅርብ ቢመስልህም፣ ሊነካ የቀረበ ቢመስልም ሁሉን ማድረግ በሚቻለው ሀሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ በማይቸለው ተአምር አድራጊነት ሳይነካህ ያልፋል። ይታከክሃል አይነካህም ይቀርብሃል አይደርስብህም ይመጣብሃል አያገኝህም።

7) መዝሙር 91፥11-13፦
'' በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። ''

እግዚአብሔር እኛን አማኞችን በምንሄድበት ሁሉ ይጠብቁን ዘንድ መላእክቱን ያዛቸዋል። መላእክቱ እኛን ከአደጋ ለማስመለጥ እንዲጠብቁን ዘወትር እንዲታደጉን በተጠንቀቅ በዙሪያችን አሉ። እግዚአብሔር በልጆቹ ላይ ብዙ ነገር እንዲደርስ ሊፈቅድ ይችላል ይሁንና አንድም ኅይል ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ አንዳልሆነ ያውቃሉ።

8) መዝሙር 91፥14፦
'' በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ''

እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት እና ስሙም ለሚያውቁ ሁሉ የማዳኑን ንግር ያበሰረበት ክፍል ነው። መውደድ የሚለው ቃል እግዚአብሔርን ከልብ መናፈቅንና መሻትን ይሆንላቸዋል።
=} የጌታ ቃል:- ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ በታች እንደምትሰበሰብ እንዴት ይልቅ እርሱ እንደሚጋርደን።

9) መዝሙር 91፥15፦
'' ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። ''

ይህ ቃል የአማኝ የድምፅ ብክነትን የሚባል ነገር እንደሌለ ያሳያል። ሲጣር ደመና አይከለክለውም፣ የፀሐይ ግርዶሽ አይዘውም፣ ንፋስ አይወስደውም፣ ዝናብ አይመልሰውም። አቤት የሚል ብቻ ሳይሆን በመከራ የማይተወን አብሮን የሚሆን ደግሞም የሚያድነን ጌታ አለ።

10) መዝሙር 91፥16፦
'' ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። ''

ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ ሲገረም ''እንግዲህ ምን እንላለን'' ይላል ደግሞስ ምንስ ይባላል እኔም ከምናገር እጅህን አፍህ ላይ ጫን ይለኛል። ይህ ሁሉ ጥበቃ ለእኔና ለአናንተ ነው። እውን ከዚህ የቀረበ ደግሞም ህያው የሆነ ነገር ምን አለ?
      እግዚአብሄር ይክበር ይመስገን!!!

Wednesday, May 27, 2020

❖እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፦

  እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፦
        (ዮሐ 21፡17)
የክርስቶስ በጥብርያዶስ መገለጽ ሦስተኛው መገለጥ ነው። ጥብርያዶስ በባህር አጠገብ ያለ ቦታ ነው። ባህሩም የጥብርያዶስ ባህር ተብሎ ይጠራል። ክርስቶስ ዓሳ እያጠመዱ ሳሉ ተገልጾላቸዋል። 

በዚህች ሌሊት እነ ጴጥሮስ ምንም ዓሣ አልያዙም አለመያዛቸው የጌታ ፍቃድ አለመሆኑን ያስረዳል። ሰውን እንጅ ዓሣን እንደማያጠምድ አስቀድሞ የተናገራቸውን መዘንጋታቸው በዝህች ሌሊት ድካማቸው ከንቱ እንዲሆን ሆኗል። 

ያለ ጌታ ፍቃድ የሚሰራ ሥራና የሚደከም ድካም ውጤት እንደሌለው እንዲረዱ አድርጎአቸዋል። ሌሊት ያልተያዘው ዓሣ በንጋት በጌታ ቃል መረባቸውን ወደ ባህር በጣሉ ጊዜ ብዙ ዓሣ ተይዞአል። 

ይህም የጌታ ቃል ሁሉን እንደሚያደርግና ማድረግም እንደሚችል። እንዲያምኑ ረድቶአቸዋል። መታዘዛቸው ብዙ ዓሣ ለማግኘታቸው ዋነኛ ነው። ተስፋም አልቆረጡም። ሌሊቱን ሁሉ አልያዝንም ብለው መረባችንን አንጥልም አላሉምና። 

ጌታ መሆኑን ያወቁት ከታዘዙት በኋላ ነው በመታዘዛቸው ብዙ ዓሳ ሲያዝላቸው ነው። መታዘዝ የተሰወረውን ይገልጻል ያጡትንም ያስገኛል። 

ወደ ወደቡ ወይም ከባህሩ ከወጡ በኋላ የተጠበሰ ዓሳና የተዘጋጀ እንጀራ፤ የነደደ እሳት አግኝተዋል። ይህ ሁሉ ያልደከሙበት ነው፤ ታዘዙ በመታዘዝ የሰሩት ውጤታማ ሁነላቸው። የተዘጋጀ እንጀራና ዓሳ አገኙ።

ምስጢሩ ለሐዋርያነት ታዘው ዓለምን ሲያስተምሩ ሰውን እንደ ዓሳ ይስበስባሉ። በጌታ የተዘጋጀ ስማያዊ ጸጋንም ያገኛሉ። 

ተዘጋጅቶ የተገኘው እንጀራና ዓሳው እግዚአሔር የሚሰጠውን ጸጋ ያመለክታል።

ጴጥሮስን ትወደኛለህን? ብሎ ሦስት ጊዜ ጠይቆታል። እንደሚወደውም ባረጋገጠ ጊዜ በጎቼን፤ግልገሎቼን፤ጠበቶቼን ጠብቅ ብሎታል።  ጴጥሮስ የጌታን ፍቅር መግለጽ ያለበት እነዚህን በመጠበቅ ነው። ከዚህ የበለጠ ፍቅርም እንደማይኖር ደጋግሞ በመጠየቅና ከወደድከኝ ጠብቅ በማለት አስረድቶታል። በወደደው ልክ ምዕመናኑን መጠበቅ እንዳለበት ተረድቷል። 

ክርስቶስ ለጴጥሮስ ሲናገር ሽማግሌና ጎልማሳ ብሎታል። በጎልማሳነቱም ጊዜ የወደደውን የሚሰራበት ነበር ይህ ማለት ስሜቱን ተከትሎ ይኖር ነበር ማለት ነው። ሽምግልናው ግን የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ተከትሎ እንደሚሄድ ያስረዳል። 

ሽምግልና በአእምሮና በእውቀት በመንፈስ ቅዱስም ማደጉ ነው። ትጥቁም የመንፈስ ቅዱስ ነው። ሌላ ያስታጥቅሃል ወደ ማትወደውም ትሄዳለህ ተብሎአል። የማይወደውን ሞትና መከራ ለመቀበል እግጁ መሆኑን ያስረዳል። 
           ክብር ለስሙ ይሁን!!!

❖አርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወነበረ በየማነ አቡሁ፦

አርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ ወነበረ በየማነ አቡሁ፦
       (ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ 7)

    ዓለምን በሞቱ ና በትንሳኤው በፍቅሩና በኀይሉ ማርኮ ዐረገ። 

ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል።
ሰይጣንን የማረከው በሃያልነቱ ነው።
ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ መጥቶ ሲያሸንፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን ጋሻና ጦር ይወስድበታል ምርኮውንም ያካፍላል።    (ሉቃ 11፥22) 

ሰይጣን የሚታመንበት የክፋትና የጥላቻ ጋሻና ጦር ነበረው። በሁሉም ላይ በፍቅሩ መልቶ ለመኖር ከሰማይ ወረደ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው ። (ኤፌ 4፥8-10)
በዓለም ላይ ሃይሎ የነበረውን ሰይጣንን አስሮታል። ተቆጣጥሮት የነበረውን ሁሉ ወስዶበታል። 

"ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።" (ማቴ 12 .29 )

ጌታችን እንደተናገረው ኀይለኛው ባይታሰር ኖሮ ተቆጣጥሮት የነበረውን ሁሉ መማረክ አይችልም ነበር በኀጢአታችን ላይ በርትቶ የነበረው ታስሯል ።ጌታችን ድል አድርጎ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ዳግማኛም ይመጣል።
          ለርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን!!!