Wednesday, May 27, 2020

❖እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፦

  እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ፦
        (ዮሐ 21፡17)
የክርስቶስ በጥብርያዶስ መገለጽ ሦስተኛው መገለጥ ነው። ጥብርያዶስ በባህር አጠገብ ያለ ቦታ ነው። ባህሩም የጥብርያዶስ ባህር ተብሎ ይጠራል። ክርስቶስ ዓሳ እያጠመዱ ሳሉ ተገልጾላቸዋል። 

በዚህች ሌሊት እነ ጴጥሮስ ምንም ዓሣ አልያዙም አለመያዛቸው የጌታ ፍቃድ አለመሆኑን ያስረዳል። ሰውን እንጅ ዓሣን እንደማያጠምድ አስቀድሞ የተናገራቸውን መዘንጋታቸው በዝህች ሌሊት ድካማቸው ከንቱ እንዲሆን ሆኗል። 

ያለ ጌታ ፍቃድ የሚሰራ ሥራና የሚደከም ድካም ውጤት እንደሌለው እንዲረዱ አድርጎአቸዋል። ሌሊት ያልተያዘው ዓሣ በንጋት በጌታ ቃል መረባቸውን ወደ ባህር በጣሉ ጊዜ ብዙ ዓሣ ተይዞአል። 

ይህም የጌታ ቃል ሁሉን እንደሚያደርግና ማድረግም እንደሚችል። እንዲያምኑ ረድቶአቸዋል። መታዘዛቸው ብዙ ዓሣ ለማግኘታቸው ዋነኛ ነው። ተስፋም አልቆረጡም። ሌሊቱን ሁሉ አልያዝንም ብለው መረባችንን አንጥልም አላሉምና። 

ጌታ መሆኑን ያወቁት ከታዘዙት በኋላ ነው በመታዘዛቸው ብዙ ዓሳ ሲያዝላቸው ነው። መታዘዝ የተሰወረውን ይገልጻል ያጡትንም ያስገኛል። 

ወደ ወደቡ ወይም ከባህሩ ከወጡ በኋላ የተጠበሰ ዓሳና የተዘጋጀ እንጀራ፤ የነደደ እሳት አግኝተዋል። ይህ ሁሉ ያልደከሙበት ነው፤ ታዘዙ በመታዘዝ የሰሩት ውጤታማ ሁነላቸው። የተዘጋጀ እንጀራና ዓሳ አገኙ።

ምስጢሩ ለሐዋርያነት ታዘው ዓለምን ሲያስተምሩ ሰውን እንደ ዓሳ ይስበስባሉ። በጌታ የተዘጋጀ ስማያዊ ጸጋንም ያገኛሉ። 

ተዘጋጅቶ የተገኘው እንጀራና ዓሳው እግዚአሔር የሚሰጠውን ጸጋ ያመለክታል።

ጴጥሮስን ትወደኛለህን? ብሎ ሦስት ጊዜ ጠይቆታል። እንደሚወደውም ባረጋገጠ ጊዜ በጎቼን፤ግልገሎቼን፤ጠበቶቼን ጠብቅ ብሎታል።  ጴጥሮስ የጌታን ፍቅር መግለጽ ያለበት እነዚህን በመጠበቅ ነው። ከዚህ የበለጠ ፍቅርም እንደማይኖር ደጋግሞ በመጠየቅና ከወደድከኝ ጠብቅ በማለት አስረድቶታል። በወደደው ልክ ምዕመናኑን መጠበቅ እንዳለበት ተረድቷል። 

ክርስቶስ ለጴጥሮስ ሲናገር ሽማግሌና ጎልማሳ ብሎታል። በጎልማሳነቱም ጊዜ የወደደውን የሚሰራበት ነበር ይህ ማለት ስሜቱን ተከትሎ ይኖር ነበር ማለት ነው። ሽምግልናው ግን የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ተከትሎ እንደሚሄድ ያስረዳል። 

ሽምግልና በአእምሮና በእውቀት በመንፈስ ቅዱስም ማደጉ ነው። ትጥቁም የመንፈስ ቅዱስ ነው። ሌላ ያስታጥቅሃል ወደ ማትወደውም ትሄዳለህ ተብሎአል። የማይወደውን ሞትና መከራ ለመቀበል እግጁ መሆኑን ያስረዳል። 
           ክብር ለስሙ ይሁን!!!

No comments:

Post a Comment