Friday, August 21, 2020

❖የክርስቶስ ራስነት:-

የክርስቶስ ራስነት:-

ራስ የሚለው ቃል በመፅሐፍ ቅዱስ ውሰጥ ያለው ትርጉም የነገሮች ዋና:የበላይ የሆነ:ከሁሉም ከፍ ያለ:ሁሉን ገዢ የሁሉ መሪ ማለት ነው።ታድያ ክርስቶስ ኢየሱስ የብዙ ነገር ዋናና የበላይ ነው።ይህን ስፍራ እንዲይዝ አሰቀድሞ መከራን መቀበል ቀጥሎም ወደ ክብሩ መግባት ነበረበት።

የብሉይ ኪዳን ነቢያት ይህን እውነት በአፅንዖት ተናግረዋል።ሉቃ 24:26 1ኛ ጴጥ 1:11 ይህን እውነት ሐዋርያት መሰክረዋል።ዕብ 2:18 12:2 13:12-13። እግዚአብሔር አንድያ ልጁ ኢየሱስን ያለ ልክ ከፍ ከፍ አድርጎታል።ፊሊ 2:9 በግርማዊ ዙፋን ቀኝም ጌታም ክርስቶስም አድርጎ የነገሮች ሁሉ ራስ አድርጎታል።የሐዋ 2:36 ይህ እንደ መደርደሪያ ካልን ኢየሱስ ራስ የሆነባቸው ጉዳዬች በጥቂቱ እንመልከት፦

1ኛ,ክርስቶስ ኢየሱስ የቤተክርትያን ራስ ነው።

ኤፌ 1:21-22"ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተክርስትያን ሰጠው።ክርስቶስ ሲሰቀል ሰይጣንና ዓለም ያላቸውን ኃይልና ብርታት አሳይተዋል።ያለ የሌለ ኃይል በመጠቀም ክርስቶስ ወደ መስቀለ ሞት ገፍተውታል።ይህን እንዲሆን የአይሁድ ሃይማኖትና የሮም የመንግስት ሰርዓት ተጠቅማል።ክርስቶስ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ስለ ፅድቅና የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ስለ ኃጢአት ሞተ።እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት በማስነሳት የኃይሉ ብርታት አሳዬ።ከጌትነት ከአለቅነት ከኃይላትና በዓለም ከሚጠራ ስም ሁሉ በላይ እግዚአብሔር አደረገው።ለአካሉ ማለትም ለቤተክርትያንም ራስ እንደሆን ሰጠው።ቤተክርስትያን አንድ ራስ ነው ያላት እርሱም ክርስቶስ ብቻ ነው።የቤተክርስትያን head office ክርስቶስ ነው።

2ኛ,ከዚህ የቤተክርስትያን ጉዳይ ጋር ክርስቶስ የማዕዘን ድንጋይ ራስ ነው።

ኤፌ 2:20"በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኅል።የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።አማኞች ሕያዋን ድንጋይ ናቸው።1ኛ ጴጥ 2:5 እነዚህ አማኞች በክርስቶስ የማዕዘን ድንጋይ ራስነት ይገጣጠማሉ።ክርስቶስ በአማኞች ላይ የበላይ ዋና የሆነ ብቻ ሳይሆን አማኞች ሚገጣጠሙበት ነው።በእርሱ ተገጣጥመው ቅዱስ መቅደስ ይሆናሉ።

3ኛ,ክርስቶስ የህይወት ራስ።

የሐዋ 3:14-15"እናንተ ግን,,,የሕይወት ራስ ገደላችሁት እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው።ሰው በበደል በኃጢአት ሙት ነው።ኤፌ 2:1ነገር ግን ሰው ህይወትን ለማግኘት ወደ ክርስቶስ መምጣት አለበት።ዮሐ 17:2 ስለዚህ በስሙ ለሚያምኑ ኢየሱስ ህይወትን ይሰጣቸዋል።ምክንያቱም የህይወት ራስ ነው።ዮሐ 3:36 1ኛ ዮሐ 5:12

4ኛ,ክርስቶስ የመዳን ራስ ነው።

ዕብ 2:10"ብዙ ልጆች ወደ ክብር ያመጣ ዘንድ የመዳናቸውንም ራስ በመከራው ይፈፅም ዘንድ ለእርሱ ተገብቶታልና።ሰው መዳን የሚችል ከፍጡር ዘንድ አንድም የለም።መዳን በማንም በሌላ የለም።የሐዋ 4:12 በእርሱ(በክርስቶስ) የሚመጡትን ፈፅሞ ያድናቸዋል።ዕብ 7:23 ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ሊያድን መጣ።1ኛ ጢም 1:15 ስለዚህ መዳንን በተመለከተ ክርስቶስ ብቻ ይመለከተዋል።ክርስቶስ የመዳናችን ዋና ነው።

5ኛ,ክርስቶስ የእምነታችን ራስ ነው።

ዕብ 12:3"የእምነታችን ራስና ፈፃሚውን ኢየሱስን ተመልከቱ።አንድ እምነት አለ።እርሱም ለቅዱሳን የተሰጠ ነው።ይሁዳ 1:3 የዚህ እምነት የበላይ ኢየሱስ ነው።ብዙ ሃይማኖቶች ራስ አላቸው። መፅሐፍ ግን ኢየሱስ የእምነታችን ራስ ነው ይለናል።አዎን ኢየሱስ ብቻ የሃይማኖት ራስ ነው።

❖በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር መስደድ:-

በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር መስደድ!
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች ምዕ. 2)
----------
6፤ እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።
7፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ።
በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ውስጥ ብቻ በፍልስፍና እና የሰው ስርዓት በሆነ ሃይማኖት እየተናወጡ ለነበሩት ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ድንቅ ምክር ተለግሷቸዋል። በክርስቶስ መመላለስ፣ በክርስቶስ ሥር መስደድ እና በክርስቶስ መታነፅ ወይም መገንባት ሶስቱ ቁልፍ ነገሮች ናቸው።
ለሁለቱ ነገሮች መሰረት ወደሆነው ቃል እንምጣ። ተክል፣ ሁሉ ነገሩ ያለው ሥሩ ላይ ነው። ሥሩ ለተክሉ ዋና ነገር ከሆነ ደግሞ በተመቻቸ ቦታ ሊተከል ይገባዋል። ጥሩ አፈር እና ውሃ ያለበት ቦታ ላይ ትንሽ የነበረው ሥር በሚገርም ሁኔታ አድጐ ይሰፋል። ተክሉም ያድጋል። ገና ሲተከል አካባቢ ህፃናት እንኳ በቀላሉ ሊጎዱት ይችላሉ። ከጊዜያት በኃላ ግን ጐልማሳም እንኳ አይደፍረውም።
እንዲህ ነው። እኛን በተመለከተ የተተከልንበት ቦታ ፍፁም፣ አስፈላጊው ሁሉ የሚገኝበት ውብ ስፍራ ነው። በዚያ የሕይወት ውሃ ምንጭ ሳያቋርጥ ይፈልቃል። ከእኛ የሚጠበቀው ዝም ብሎ የሚልቀውን ምንጭ እየጠጡ ሥርን ማስፋት ብቻ ነው።
ክርስቶስ የሕይወት ውሃ ምንጭ ነው። በእርሱ ዘንድ ሁሉም አለ። እርሱ ሁሉም ነው።
" ክርስቶስ ሁሉ ነው"
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3:11)
ነፍስ ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ ከክርስቶስ እየተመገበች፣ ከክርስቶስ ጋር በቃሉ በኩል ጊዜ እየሰጠች ስታሳልፍ፣ በክርስቶስ ውስጥ ስር ትሰድዳለች። ዕለት ዕለት ከቃሉ ጋር በፅሎት ስትጣበቅ ሥሯ ይሰፋል።
> የዚህም ውጤት ያች ነፍስ በሕይወቷ የምትመራው በክርስቶስ ሆኖ በእርሱ ትመላለሳለች፣ ደግሞ በዛው በክርስቶስ እየተገነባች በፍሬ ትታጀባለች።
" በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።"
(የዮሐንስ ወንጌል 15:5)
ያኔ ሙቀት ቢመጣ ድርቅ ማለትም የሰው ፍልስፍና ሆነ የሰው ሐይማኖት ሊያናውጧት እና ሊያሰጓት አይችሉም።
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕ. 17)
----------
7፤ በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8፤ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።