Friday, August 21, 2020

❖በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር መስደድ:-

በክርስቶስ ኢየሱስ ሥር መስደድ!
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች ምዕ. 2)
----------
6፤ እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ።
7፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ።
በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ውስጥ ብቻ በፍልስፍና እና የሰው ስርዓት በሆነ ሃይማኖት እየተናወጡ ለነበሩት ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ድንቅ ምክር ተለግሷቸዋል። በክርስቶስ መመላለስ፣ በክርስቶስ ሥር መስደድ እና በክርስቶስ መታነፅ ወይም መገንባት ሶስቱ ቁልፍ ነገሮች ናቸው።
ለሁለቱ ነገሮች መሰረት ወደሆነው ቃል እንምጣ። ተክል፣ ሁሉ ነገሩ ያለው ሥሩ ላይ ነው። ሥሩ ለተክሉ ዋና ነገር ከሆነ ደግሞ በተመቻቸ ቦታ ሊተከል ይገባዋል። ጥሩ አፈር እና ውሃ ያለበት ቦታ ላይ ትንሽ የነበረው ሥር በሚገርም ሁኔታ አድጐ ይሰፋል። ተክሉም ያድጋል። ገና ሲተከል አካባቢ ህፃናት እንኳ በቀላሉ ሊጎዱት ይችላሉ። ከጊዜያት በኃላ ግን ጐልማሳም እንኳ አይደፍረውም።
እንዲህ ነው። እኛን በተመለከተ የተተከልንበት ቦታ ፍፁም፣ አስፈላጊው ሁሉ የሚገኝበት ውብ ስፍራ ነው። በዚያ የሕይወት ውሃ ምንጭ ሳያቋርጥ ይፈልቃል። ከእኛ የሚጠበቀው ዝም ብሎ የሚልቀውን ምንጭ እየጠጡ ሥርን ማስፋት ብቻ ነው።
ክርስቶስ የሕይወት ውሃ ምንጭ ነው። በእርሱ ዘንድ ሁሉም አለ። እርሱ ሁሉም ነው።
" ክርስቶስ ሁሉ ነው"
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3:11)
ነፍስ ከትላንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ ከክርስቶስ እየተመገበች፣ ከክርስቶስ ጋር በቃሉ በኩል ጊዜ እየሰጠች ስታሳልፍ፣ በክርስቶስ ውስጥ ስር ትሰድዳለች። ዕለት ዕለት ከቃሉ ጋር በፅሎት ስትጣበቅ ሥሯ ይሰፋል።
> የዚህም ውጤት ያች ነፍስ በሕይወቷ የምትመራው በክርስቶስ ሆኖ በእርሱ ትመላለሳለች፣ ደግሞ በዛው በክርስቶስ እየተገነባች በፍሬ ትታጀባለች።
" በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።"
(የዮሐንስ ወንጌል 15:5)
ያኔ ሙቀት ቢመጣ ድርቅ ማለትም የሰው ፍልስፍና ሆነ የሰው ሐይማኖት ሊያናውጧት እና ሊያሰጓት አይችሉም።
(ትንቢተ ኤርምያስ ምዕ. 17)
----------
7፤ በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
8፤ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።

No comments:

Post a Comment