Thursday, September 17, 2020

❖ቤተክርስቲያንና አዲስ ዓመት፦


መለወጥ የሌለበት፣ ጸንቶ የሚኖረው እግዚአብሔር ዘመናትን ያፈራርቃል።

ዳንኤል፦ "ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤.."እንዳለው( ዳን 2፥2) ትናንትን በዛሬ ተክቶ፥ ዛሬን ደግሞ በነገ ያስረጃል፡፡ በጊዜ ዑደትም ውስጥ ብዙ ዓመታት አልፈው ብዙ አዲስ ዓመታት መጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም እግዚአብሔር በባሕሪው ነበር፤ አለ ይኖራልም።

ዓመታት ሂደው ዓመታት ቢመጡም በእግዚአብሔር ዘንድ በየዓመቱ የሚቀያየር ሀሳብ የሚለዋወጥ አጀንዳ ፈጽም የለም፡፡ ዘላለማዊው እግዚአብሔር በዘላለም እቅዱ መሰረት ሁሉን ያከናውናል። በዕቅዱም መሰረት ይኼው በክርስቶስ ኢየሱስ በልጁ የመስቀል ስራ ሰዎችን ወደራሱ እያቀረበ ነው። በየዘመኑም ይኼን ለማድረግ ይተጋል። ይኼን ሃሳቡንም ለመደምደም በዘመን ፍጻሜ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማይም በምድርም ያለውን ሁሉ ሊጠቀልል አቅዷል። (ኤፌ 1፥10)።

ታዲያ ዘመናት ሲፈራረቁ ሁሉ ነገር ወደ እግዚአብሔር የዘመን ፍጻሜ ዕቅዱ ይፈጥናል። በዚህ መፈራረቅ ውስጥም ለዕቅዱ የወሰናቸው የመረጣቸው በተወሰነላቸው ዘመን እና ቦታ ሁነው ወደልጁ መንግስት ይፈልሳሉ። ለዚያም ነው የዘመናት መፈራረቅ ሰው የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዕቅዱን የሚከውንበት እንደሆነ እንዲያስተውል ዕድል የሚሰጥ እንዲሁም በልጁ የሠራውን እንዲያምን፣ እንዲያደንቅ እና መግቦቱንም እንዳይረሳ ያደርጋል የምንለው።

የሰው ልጆች አሮጌ የተባለው ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት ሲመጣ እና ከዚህ ጋር በማያያዝ በማቀዳቸው ሕይወታቸው እንደሚለወጥ ያስባሉ ። በእርግጥ የዓመታት መለዋወጥ የሰውን ሕይወት ይለውጣልን? በመሠረቱ ሰዎች ብዙ ነገሮችን ማቀዳቸው ክፉ አይደለም። ለስጋዊ ኑሯቸው ሊጠቅም ይችላል። ነገር ግን ሕይወታቸውን ሊለውጥ አይችልም። የሰውን ሕይወት የጌታ ኢየሱስ የመስቀሉ ስራ እንጂ የሚለዋወጥ ዓመትም ይሁን ይኼን ተከትሎ ሰዎች የሚያቅዱት ዕቅድ አይለውጠውም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የመስቀል ስራ አምነው ዳግመኛ የተወለዱትን ብልቶቿን ሁሉ የመንፈሳዊ ሕይወት መለወጥ መሻሻልና ማደግ መስራት አለባት፡፡ ይኼን ተግባራዊ ለማድረግም የአሮጌውን ሰው ባህሪ አውልቀው አዲሱን ሰው መልበስ እንዲችሉ በቃሉ አማኞችን ልታንጽ ያስፈልጋል፡፡

ለዚያም ነው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ፊተኛ ኑሯችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ። በአእምሯችሁ መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም ለሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።» የሚለው። (ኤፌ 4፥22-24)።

በእርግጥ የአዲሱ ሰው ማንነት በውስጣችን አለ። ጳውሎስ በመልክቱ፦ «አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፍፋችሁታልና፤ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታልና» ብሏል። (ቆላ 3፥10)። ነገር ግን ይህ የአዲሱ ሰው ባህርይ ሊገለጥ ሊታይ ይገባል። ይህም ባህርይ ፍቅር፣ ጽድቅ፣ ቅድስና በአጠቃላይ እግዚአብሔርን መምሰል ነው። ቤተክርስቲያን ይኼን ስታደርግ እንደቃሉ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያለች።
ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!!!

Saturday, September 12, 2020

❖የባሕረ ሐሳብ ቊጥር፦

በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሠራጺ ብለን ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ስላልነ በባሕርይ በሕልውና አንድ አምላክ ብለን አምነን ጸሎቱ ልመናው በረከቱ ክብሩ ይደርብንና የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ድሜጥሮስ የተናገረውን የባሕረ ሐሳብ ቊጥር መጽሐፍን በእግዚአብሔር አጋዥነት እንጀምራለን፡፡


💥 እግዚአብሔር እንደዛሬው ኹሉ አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፍለው በአንድነት በሦስትነት ሳለ ክብሩ በብቻው እንደቀረ ዐውቆ ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፤ አስቦም አልቀረ ሰውና መላእክትን ስሙን ለመቀደስ ክብሩን ለመውረስ የቀረውን ፍጥረት ግን ለአንክሮ ለተዘክሮ ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ ፈጠረ። 

    “ወኲሉ ዘተፈጥረ ለመፍቅደ ነባብያን ቦ እምኔሆሙ ለምህሮ ወቦ እምኔሆሙ ለተገብሮ፤ ወእንዘ ኢየኀድግ ርእሶ ዘእንበለ ሰማዕት፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘንተ እምአፍአ ብከ ሰማዕት ወመምህር ዘይመርሐከ ኀበ ዝንቱ፤ ወዘኢያስተርኢ እግዚአብሔር እምፍጥረተ ዓለም ይትዐወቅ በፍጥረቱ” እንዲል።


💥 እግዚአብሔርስ የፈጠረው ፍጥረት እያንዳንዱ ቢቈጠር ፍጡር ተናግሮ ባልፈጸመውም ነበር፤ እየወገን እየወገኑ ግን ብዙውን አንድ ብዙውን አንድ እያሉ ቢቈጥሩ ከእሑድ እስከ ዐርብ የፈጠረው ሥነ ፍጥረት 22 ነው፡፡ እስከዚኽ አርዕስት ነው፤ ይኽንንም በሥነ ፍጥረት ይመለከቷል። 

የፀሓይ ጥንታት ሦስት የጨረቃን ዐምስት የሚል ነውና፤ ይኽ ዓለም የተፈጠረበት ዕለተ እሑድ ጥንተ ዕለት፤ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፀዋት የተፈጠሩበት ዕለተ ሠሉስ ጥንተ ቀመር፤ ብርሃናት የተፈጠሩበት ዕለተ ረቡዕ ጥንተ ዮን ይባላል፤ “እሑድ ወሠሉስ ወረቡዕ ዘውእቶሙ ሠለስቱ ጥንታት” እንዲል


💥 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ቢቈጠር በፀሓይ 7513 ዘመን፤  በጨረቃ 7743 ዘመን ከ7 ወር ከ16 ዕለት ነው፡፡ 


💥 ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ የነበረው በፀሓይ 5500 ዘመን፤ በጨረቃ 5668 ዘመን ከ10 ወር ከ9 ዕለት ነው፤ ይኽም  ዓመተ ኩነኔ፣ ዓመተ ፍዳ ይባላል፡፡


💥 ከልደተ ክርስቶስ ወዲኽ ያለው ግን በፀሓይ 2013 ዘመን፤ በጨረቃ 2074 ከ9 ወር ከ7 ዕለት ነው።  ይኽ ዓመተ ሥጋዌ፣ ዓመተ ምሕረት ይባላል፤ መላው ዓመተ ዓለም ነው፤ ዓመተ ዓለም ባለው ዓመተ ምሕረት የሚል ይገኛል፤ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድም ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል፤ ስለምን ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት አለው ቢሉ? ሰው በዚኽ ዓለም ሳለ ኀጢአት ሠርቶ ንስሓ ቢገባ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት የሚያገኝበት ስለኾነ ዓመተ ዓለምን ዓመተ ምሕረት ብሎ ተርጒሞታል “በዕለት ኅሪት እሰምዐከ ወበዕለተ መድኀኒት እረድአከ ወናሁ ይእዜ ዕለት ኅሪት ወናሁ ዮም ዕለተ አድኅኖት” እንዲል፡፡


💥 ለዚኹም መሥፈሪያ ሰባት አዕዋዳት አሉት፤ ምንና ምን ቢሉ? ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡ ከሊኹም ሦስቱ በዕለት አራቱ በዓመት ይቈጠራሉ፤ በዕለት የሚቈጠሩት ሦስቱ ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት ናቸው፤ በዓመት የሚቈጠሩ አራቱ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ፀሓይ፣ ዐውደ ማኅተም፣ ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡ ዐውደ ዕለት ከእሑድ እስከ ቀዳሚት ያሉ ሰባት ዕለታት ናቸው፤ እሊኽም አውራኅን ለማስገኘት በሰባት በሰባት ሲመላለሱ ይኖራሉ “እስመ ኊልቊ ሳብዕ ፍጹም ውእቱ በኀበ ዕብራውያን ” እንዲል። 


💥 ዐውደ ወርኅ በፀሐይ ዘወትር ፴ በጨረቃ አንድ ጊዜ 29፤ አንድ ጊዜ ፴ ይኾናል፤ እሊኽም ዓመታትን ለማግኘት በ፴ በ፴ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡


💥 ዐውደ ዓመት በፀሓይ 365 ዕለት በጨረቃ 354 ዕለት ነው፤ በፀሓይማ ምነው 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልኢት፤ በጨረቃ 354 ዕለት ከ22 ኬክሮስ ከ1 ካልዒት ከ37 ሣልሲት ከ52 ራብዒት ከ48 ኀምሲት አይደለውም ቢሉ “ወበውስተ ውሁድኒ ንብል አልቦ ወኢአሐዱ” እንዲል መጽሐፍ ትርፍን  ትቶ ጐደሎን  መልቶ መቊጠር ልማድ ነውና ፷ ካልመላ ብሎ እንዲኽ አለ እንጂ ቊጥሩስ አለ።  “እስመ ልማደ መጽሐፍ ይነግር ኊልቈ ምሉዓ ወፍጹመ ወየኀድግ ዘተርፈ ወይዌስክ ዲበ ሕፀፅ ካልዐ” እንዲል፤  ዕለታትን አዕዋድ አላቸው አውራኅን የሚያስገኙ ስለኾነ፤ አውራኅን አዕዋድ አላቸው ዓመታትን የሚያስገኙ ስለኾነ።  “ወበከመ ይትወለዳ አውራኅ እምዕለታት ወዓመታት እምአውራኅ ከማሁ ይትወለዳ አዕምሮታት እመከራት ወእምግባራት እንዲል፡፡


💥 ዐውደ አበቅቴ 19 ዓመት ነው።  በዚኽም  ፀሓይና ጨረቃ መንገዳቸውን ፈጽመው በተፈጠሩበት ኆኅት ይገናኙበታል፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ መምህራነ ወንጌል ሐዋርያት፣ ሊቀ ጳጳሳት ዲሜጥሮስ ከ፳ው አንድ ቀመር አንድ ተረፈ ቀመር፤ ከ፵ው ኹለት ቀመር ኹለት ተረፈ ቀመር፤ ከ፷ው 3 ቀመር 3ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፹ው 4 ቀመር 4ት ተረፈ ቀመር፤ ከ፻ው 5ቀመር 5ት ተረፈ ቀመር እያላችኊ ቊጠሩ ማለታቸው ከዚኽ የተነሣ ነው።  “ወእምዘተርፈከ እምዐሠርቱ ወተሰዓቱ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ እስመ ለዛቲኒ ዐሠርቱ ወተሰዓቱ ሙሴ ገብራ በጥበበ እግዚአብሔር ዘይገብሩ ባቲ ፍሥሐ አይሁድኒ ወክርስቲያንኒ” እንዲል። 


💥 ዐውደ ፀሓይ 28 ዓመት ነው፤ በዚኽ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ረቡዕ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ረቡዕ ማቴዎስ እንዲል፤ ዕለትን ፀሓይ አለው “ወበትእዛዝከ ይቀውም ዕለት” እንዲል፤ ወንጌላዊዉን ፀሓይ አለው “አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም” ካለው አንዱ ርሱ ነውና፤ በሰንጠረዥ ፀ፣ ደ ይላል፤ ዐውደ ፀሓይ ማለት ነው፡፡


💥 ዐውደ ማኅተም 76 ዘመን ነው፤ በዚኽ አበቅቴ ወንጌላዊ ይገናኙበታል፤ አበቅቴው 18 ወንጌላዊዉ ዮሐንስ ነው፤ ማኅተም አለው አበቅቴው ለአበቅቴ ወንጌላዊዉ ለወንጌላዊው ፍጻሜ ነውና፡፡ ዐውደ ቀመር 532 ዘመን ነው፤ በዚኽ ዕለት፣ ወንጌላዊ፣ አበቅቴ እሊኽ 3ቱ ይገናኙበታል፤ ዕለቱ ሠሉስ፣ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ ነው፤ ሠሉስ ማቴዎስ እንዲል አበቅቴው አልቦ ነው “ጥንቱ ለቀመር ዕለተ ሠሉስ ወንጌላዊ ማቴዎስ ወፍጻሜሁ ዕለተ ሰኑይ ወንጌላዊ ዮሐንስ” እንዲል።


💥 በዐውደ ፀሓይ ቦታ ዐውደ ማኅተም፤ በዐውደ ማኅተም ቦታ ዐውደ ፀሓይ የሚል ይገኛል፤ ከኹለቱ አንዱ ቢታጣ አንዱ ከቀመር ገብቶ ይቈጠራል፤ ቀመርን ለሦስቱ ስም በሰጡ ጊዜ ዐውደ ቀመር ዐቢይ ቀመር፤ ዐውደ ማኅተም ማዕከላዊ ቀመር፤ ዐውደ አበቅቴ ንዑስ ቀመር ይባላል፤ ዐቢይ ቀመር መደቡ 14 ቊጥሩ 532፣532፤ ማዕከላዊ ቀመር መደቡ 6 ቊጥሩ 76፣76፤ ንዑስ ቀመር መደቡ 3 ቊጥሩ 19፣19 ነው፡፡


💥 ከዚኽም ዓመተ አበቅቴን ለማግኘት 7513 ዘመን በዐቢይ ቀመር ቢቀምሩ 532፤ 532 የተፈጸመለት 14 ዐቢይ ቀመር፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኾኖ 8 ዓመት ይተርፋል፡፡ 


💥 መላውንም በማእከላዊ ቀመርም ቢቀምሩ 76፤ 76 የተፈጸመለት 98 ማእከላዊ ቀመር 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኹኖ 8 ዓመት ይተርፋል፡፡ 


💥 በዐውደ ፀሓይም ቢቀምሩ 28፤ 28 የተፈጸመለት 266 ዐውደ ፀሓይ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 3 ንዑስ ቀመር ኾኖ 8 ዓመት ይተርፋል፡፡ 


💥 መላውንም በንዑስ ቀመር ቢቀምሩ 19፤ 19 የተፈጸመለት 395 ንዑስ ቀመር ኹኖ 8 ዓመት ይተርፋል፡፡


💥 7513ኙን ዘመን በቀመረ ዐረብም ቢቀምሩ 228፤ 228 የተፈጸመለት 32 ቀመረ ዐረብ፤ 19፤ 19 የተፈጸመለት 11 ንዑስ ቀመር ኹኖ 8 ዓመት ይተርፋል፤ ስመ አቅማር ብዙ ነው አይቶ መተው ነው፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተጀመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ8ቱ አንዱን ቢያትቱ 7 ይተርፋል፤ 7 ወንበር (ዓመተ አበቅቴ)ወጣ ይሏል በዘመነ ማቴዎስ።

💥 አበቅቴን ለማግኘት ከ7ቱ ዓመተ አበቅቴ 11 ቢሄዱ፤ 77 ይኾናል፤ 60ውን በ2 ፴ ቢገድፉት 17 ይተርፋል፤ 17 አበቅቴ ወጣ በዘመነ ማቴዎስ፡፡ 


💥 መጥቅዕንም ለማግኘት ከ7ቱ ዓመተ አበቅቴ 19 ዕለት ቢሄዱ 133 ይኾናል፤ 120ውን በ4 ፴ ቢገድፉት 13 ይቀራል፤ 13 መጥቅዕ ወጣ በዘመነ ማቴዎስ፡፡ 


💥 13 መጥቅዕና 17ት አበቅቴ ፴ ይኾናሉ እንጂ ከ፴ አይወጡም ከ፴ አይወርዱም፤ “ዓዲ መጥቅዕ ወአበቅቴ ክልኤሆሙ እመ ይበዝኁ ወእመ ይውኅዱ ኢየዐርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወባሕቱ ወትረ ይከውኑ ፴” እንዲል። 

            

💥 ከዚኽም በዘመኑ የኾኑ አጽዋማትና በዓላትን ይናገሯል፤ መጥቅዕ 13 ነው።  መጥቅዕ ቢያንስ በጥቅምት ይውላልና፤ ጥቅምት እሑድ ይብታል፤ ከእሑድ እስከ እሑድ 8፤ ሰኞ 9፤ ማግሰኞ 10፤ ረቡዕ 11፤ ኀሙስ 12፤ ዐርብ 13፤ በዐለ መጥቅዕ ጥቅምት 13 ዐርብ ቀን ይውላል፤ የዐርብ ተውሳክ 2፤ 2 እና 13= 15 መባጃ ሐመር ይገኛል፤ በጥቅምት ሳኒታ የካቲት ሰኞ ይብታል፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 8፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 15፡፡ የካቲት 15 ሰኞ ነነዌ ይውላል፡፡


♦ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14፤ 14 ና 15 =29፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 8፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 15፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 22፤ ሰኞ እስከ ሰኞ 29 የካቲት 29 ቀን ዐቢይ ጾም፡፡


♦ የደብረ ዘይት ተውሳክ 11፤ 11 ና 15= 26፤ መጋቢት ረቡዕ ይብታል፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 8፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 15፤ ረቡዕ እስከ ረቡዕ 22፤ ኀሙስ 23፤ ዐርብ 24፤ ቅዳሜ 25፤ እሑድ 26፤ መጋቢት 26 ቀን ደብረ ዘይት፡፡


♦ የሆሳእና ተውሳክ 2፤ 2 እና 15=17፤ ሚያዝያ ዐርብ ይብታል፡፡ ዐርብ እስከ ዐርብ 8፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 15፤ ቅዳሜ 16፤ እሑድ 17 ይብታል፡፡ ሚያዝያ 17 ሆሳዕና 


♦ የስቅለት ተውሳክ 7፤ 7 እና 15=22፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 8፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 15፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 22፡፡ ሚያዝያ 22 ስቅለት፡፡ 


♦ የትንሣኤ ተውሳክ 9፤ 9 እና 15= 24፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 8፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 15፤ ዐርብ እስከ ዐርብ 22፤ ቅዳሜ 23፤ እሑድ 24፡፡ ሚያዝያ 24 ትንሣኤ 


♦ የርክብ ተውሳክ 3፤ 3 እና 15=18፤ ግንቦት እሑድ ይብታል፤ እሑድ እስከ እሑድ 8፤ እሑድ እስከ እሑድ 15፤ ሰኞ 16፤ ማግሰኞ 17፤ ረቡዕ 18፤ ግንቦት 18 ርክበ ካህናት፡፡


♦ የዕርገት ተውሳክ 18፤ 18 እና 15= 33፤ ፴ውን ገድፎ 3 ይቀራል፤ ሠኔ ማክሰኞ ይብታል፤ ማክሰኞ 1፤ ረቡዕ 2፤ ኀሙስ 3፤ ሠኔ 3 ዕርገት፡፡


♦ የጰራቅሊጦስ ተውሳክ 28፤ 28 እና 15= 43፤ ፴ውን ገድፎ 13 ይቀራል፤ ማግሰኞ እስከ ማግሰኞ 8፤ ረቡዕ 9፤ ኀሙስ 10፤ ዐርብ 11፤ ቅዳሜ 12፤ እሑድ 13፤ ሠኔ 13 በዓለ ጰራቅሊጦስ፡፡


♦ የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ 29፤ 29 እና 15=44፤ ፴ውን ገድፎ 14 ይቀራል፤ ማግሰኞ እስከ ማግሰኞ 8፤ ማግሰኞ እስከ ሰኞ 14፤ ሠኔ 14 ጾመ ሐዋርያት፡፡ 


♦ የጾመ  ድኅነት ተውሳክ 1፤ 1 ና 15= 16፤ ማክሰኞ እስከ ማክሰኞ 8፤ ማክሰኞ እስከ ማክሰኞ 15፤ ረቡዕ 16፤ ሠኔ 16 ጾመ ድኅነት ይውላል፡፡


💥 ዓመተ ወንጌላዊን ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዓመተ ወንጌላዊ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ለእመ ተርፈ አሐዱ ማቴዎስ ወክልኤቱ ማርቆስ ወሠለስቱ ሉቃስ ወለእመ ዐረየ ክፍል ዮሐንስ እንዲል፤ ዓመተ ወንጌላዊን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ አንድ ቢተርፍ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ መኾኑ፤ ኹለት ቢተርፍ ማርቆስ፤ ሦስት ቢተርፍ ሉቃስ ቢተካከል  መኾኑን በዚኽ ይታወቃል፤ 7513 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1878 ደርሷቸው 1 ይተርፋል፤ 1 ቢተርፍ ማቴዎስ ያለው ይኽ ነው፤ ዛሬ ወንጌላዊዉ ማቴዎስ መኾኑ በዚኽ ታውቋል፡፡


💥 ጥንተ ዮንንም ከዚኽ ይናገሯል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ጥንተ ዮን ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት ወትገድፎ በበሱባኤ ወዘተርፈከ እምሱባኤ ተአትት እምኔሁ አሐደ ዓመተ ወእምዝ ይከውን ጥንተ ዮን እንዲል፤ ጥንተ ዮንንም ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ 5ኛ መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን አትቶ 1 ቢተርፍ ጥንተ ዮን ረቡዕ መኾኑን መስከረም ረቡዕ መባቱን፤ 2ት ቢተርፍ ኀሙስ፤ 3 ቢተርፍ ዐርብ፤ 4 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 5 ቢተርፍ እሑድ፤ 6 ቢተርፍ ሰኞ፤ 7 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፡፡ አከፋፈል እንዳለፈው።


💥 7513 ዘመን ለአራቱ ወንጌላውያን ቢያካፍሉ 1878 ደርሷቸው 1 ይተርፋል፤ ይኽን በሱባዔ ይገድፏል፤ ከሺው 300 ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ ከ800ው አንዱን መቶ ነሥቶ 700 ግዱፍ፤ 400 ይተርል፤ ከ100ው 2፤ ከ400ው 8፤ ከ8ቱ አንድ፤ ከዚያም 1 እና 78= 79 ይኾናል፤ ከ79ኙ 70ውን በ11 ሱባዔ ቢገድፉ 2 ይተርፋል፡፡


💥 ከአንዱ ወንጌላዊ 2 ከ4ቱ ወንጌላውያን 8፤ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜን 1878 ዕለት ትኾናለች፤ ርሷ በዕለት፤ ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና ግድፈት እንዳለፈው፤ መጠነ ራብዒት  2= 10፤ ከዓመተ ወንጌላዊ የተረፈ 1 ና 10= 11 ይኾናል፤ ከ11ዱ 7ቱን በአንድ ሱባዔ ቢገድፉ 4 ይተርፋል፤ አሐደ አዕትት ለዘመን እንዲል ስለተዠመረ ተቈጠረ ስላልተፈጸመ ታተተ ብሎ ከ4ቱ አንዱን ቢያትቱ 3 ይተርፋል፤ 3 ቢተርፍ ዐርብ ያለው ይኽ ነው፤ የዐርብ ጥንተ ዮን 3 ነውና፡፡ ጥንተ ዮንም ማለት ጥንተ ፀሓይ፤ ጥንተ ጨረቃ፤ ጥንተ ከዋክብት ማለት ነው፤ ጥንተ ዮን ብሂል ጥንተ ተፈጥሮቶሙ ለፀሓይ፤ ወወርኅ ወከዋክብት እንዲል፡፡


💥 ዕለተ ቀመርንም ለማወቅ ለጥንተ ዮን ከወጣው አንዱን ሳያትቱ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ ማግሰኞ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 3 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 4 ቢተርፍ ዐርብ፤ 5 ቢተርፍ ቀዳሚት፤ 6 ቢተርፍ እሑድ፤ 7 ቢተርፍ ሰኞ መኾኑ በዚኽ ይታወቃል፤ ለጥንተ ዮን የወጣው 4 ነው፤ 4 ቢተርፍ ዐርብ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ቀመርም ማለት ቀመር የተዠመረበት ዕለት ማለት ነው፤ ቀመር የተዠመረው ማግሰኞ ነውና፡፡


💥 ዕለተ ዮሐንስንም ከዚኽ ይናገሩታል፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዕለተ ዮሐንስ ትከፍሎ ለዘመን ኀበ አርባዕቱ እድ፤ ወትዌስክ ቦቱ መጠነ ራብዒት፤ ወክልዔተ ዕለተ ጠቢባን ወትገድፎ በበሱባዔ ወዘተርፈከ እምሱባዔ ኢተአትት አሐደ ዓመተ፤ ወእምዝ ይከውን ዕለተ ዮሐንስ እንዲል ዕለተ ዮሐንስን ለማወቅ ዓመተ ዓለምን ከአራት ከፍሎ፤ 5ኛ መጠነ ራብዒት፤ 6ኛ ጳጉሜንን አክሎ 7ኛ 2ት ዕለተ ጠቢባንን ጨምሮ በሱባዔ ገድፎ ከሱባዔ የተረፈውን አንዱን ሳያትቱ አንድ ቢተርፍ ዕለተ ዮሐንስ እሑድ መኾኑ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት መኾኑ በዚኽ ይታወቃል።


💥 ለጥንተ ዮን የወጣ 4 እና 2 ዕለተ ጠቢባን= 6 ይተርፋል፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ ያለው ይኽ ነው፤ ዕለተ ዮሐንስም ማለት አሻቅቦ ወደ ላይ እስከ ፍጥረተ ዓለም፤ አቈልቊሎ ወደ ታች እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ቢቈጥሩ ለወንጌላዊዉ ዮሐንስ የሚደርሰው ቀን ማለት ነው፤ ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘኀለፈ ይመርሐከ ዝንቱ እስከ ፍጥረተ ዓለም ወለእመ ፈቀድከ ታእምር ዘይመጽእ ያበጽሐከ ዝንቱ እስከ ምጽአተ ክርስቶስ እንዲል፤ አንድም ሠርቀ ቲቶን ዕለተ ዮሐንስ ይለዋል፤ ቲቶ የተባለው መስከረም ነው፤ የመጥምቁ ዮሐንስ በዓል የሚውልበት ቀን ማለት ነው፤ ርዕሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ እንዲል፡፡


💥 ዕለተ በዓል ዘኀለፈ ዕለተ በዓል ዘይመጽእ የእሑድ አሚሩ ሰንበተ ክርስቲያንን ለማወቅ በዘመኑ የወጣውን ጥንተ ዮን፤ ሠርቀ መዓልት፤ 2 ዕለተ ጠቢባን በየወሩ የሚገኘውን አጽፈ ወርኅ እሊኽን 4ቱን አንድ አድርጎ ቈጥሮ በሱባዔ ገድፎ 1 ቢተርፍ እሑድ አሚሩ፤ 2 ቢተርፍ ሰኞ ሰኑዩ፤ 3 ቢተርፍ ማግሰኞ ሠሉሱ፤ 4 ቢተርፍ ረቡዕ ረቡዑ፤ 5 ቢተርፍ ኀሙስ ኀሙሱ፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ ሰዱሱ፤ 7 ቢተርፍ ቀዳሚት ሰቡዑ፤ 8 ቢተርፍ በሱባዔ ገድፎ እሑድ አሚሩ የሚያሰኘው ይኽ ነው፡፡ 


💥 አጽፈ ወርኅም ማለት የወርኁ ከወርኅ የሚደረብ ማለት ነው፤ ይኽስ ከምን ይገኛል ቢሉ? ወሩን በሱባዔ ቢገድፉ 4 ሱባዔ ኾኖ 2 ይተርፋል፤ የወርኁ 2 የዓመቱ 24፤ እንዲኽ ግን ስለኾነ ለመስከረም አጽፈ ወርኅ የለውም በጥንተ ዮን፤ በሠርቀ መዐልት በኹለት ዕለተ ጠቢባን ይቈጠራል፤ በእሊኽ በ3ቱ ይቈጠራል፤ ጥንተ ዮን 3፤ ሠርቀ መዐልት 1=4፤ ኹለት ዕለተ ጠቢባን 2፤ 6 ይኾናል፤ 6 ቢተርፍ ዐርብ ሰዱሱ ያለው ይኽ ነው። 


💥 ዕለተ ጠቢባንም ማለት ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም የፈጠሩበት፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን የሚያመሰግኑበት ቀን ማለት ነው፤ (ዬ) ጠቢባን ሥላሴ ይኽነን ዓለም ከእሑድ እስከ ዐርብ ፈጥረዋል፤ ጠቢባን መላእክት ሥላሴን ዘወትር ያመሰግናሉ ብሎ የቊጥር መጽሐፍን የተማሩ መምህራን ዕለተ ሰንበትን፤ 6ቱ ዕለታትን፤ ያለፉትን የሚመጡትን በዓላት የሚያውቁባቸው የሚያሳውቁባቸው ማለት ነው፤ ዕለተ ጠቢባንም የተባሉ እሑድና ሰኞ ናቸው፤ ከቀመር ገብተው አልተቈጠሩም፡፡


💥 ዕለተ ምርያ አዕዋዲትንም ለማወቅ የፀሓይ ዐውደ ዓመት 365 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ነው፤ ይኽነን በሱባዔ ቢገድፉት 52 ሱባዔ ኾኖ 1 ዕለት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይተርፋል፤ ይኽቺውም አንድ ዕለት የተባለችው ዐምስተኛዪቱ ጳጒሜን ናት፤ ዕለተ ምርያ አዕዋዲት ይላታል፤ ዕለተ ምርያ ማለት ዕለተ መድኀኒት ማለት ነው፤ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን የምታሳውቅ ማለት ነው፤ ርሷ በዋለች ልደት ይውላልና፤ አዕዋዲትም አላት ዘመኑን የምታዘዋውር የምታለዋውጥ ማለት ነው፤ እሑድ የዋለውን ሰኞ፤ ሰኞ የዋለውን ማግሰኞ እንዲውል የምታደርግ ርሷ ናትና፡፡


💥 መጠነ ራብዒት 6ኛ ጳጉሜንም ለማወቅ የአንዱ ዓመት ኬክሮስ 15፤ የ2 ዓመቱ 30፤ የ4 ዓመቱ 60 ኬክሮስ ነው፤ 60ው ኬክሮስ 1 ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም በሉቃስ መጨረሻ ዮሐንስን ተጠግታ የምትውል ስድስተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ መጠነ ራብዒት፣ ሠግረ ዮሐንስ ይላታል፤ መጠነ ራብዒት አላት ርሷ በዕለት ወንጌላዊ በዓመት ይተካከላሉና፤ ሠግረ ዮሐንስም አላት ዮሐንስ ተራምዶ የሚውልባት ስለኾነ፡፡


💥 ዕሪና መዓልትና ዕሪና ሌሊትን ሰባተኛዪቱን ጳጉሜን ለማወቅ የአንዱ ዓመት ካልዒት 6፤ የ5ቱ ዓመት 30፤ የ10ሩ ዓመት 60 ይኾናል፤ 60ው ካልዒት 1 ኬክሮስ ይኾናል፤ የ100ው ዓመት 10 ኬክሮስ፤ የ600 ዓመት 60 ኬክሮስ፤ 60ው ኬክሮስ አንድ ዕለት ይኾናል፤ ይኽቺውም ሰባተኛዪቱ ጳጉሜን ናት፤ ዓለም በተፈጠረ በ600 ዘመን ዕሪና መዓልት ዕሪና ሌሊት ኾኗል፤ ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እስከ ዛሬ ድረስ 12 ዕሪና መዓልት 12 ዕሪና ሌሊት ኾኖ 13ኛው ከተዠመረ 313 ኾኖ በዘመነ ማቴዎስ ይኸውም ሊመላ 287 ይቀራል፡፡

ከዚኽ በኋላ እንዲኽ ብሎ ባሕረ ሐሳብ አውጪው እንዲኽ ብሎ አሥርቆት ያውጣ፡፡


💥 በዘንዜከር ሐሳባተ ሕጉ ወትእዛዙ ለእግዚእነ ወአምላክነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዘ ሀሎነ በዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ዘመነ ማርቆስ ዜናዊ፤ ወንጌላዊ አለው ማቴዎስን ባለዘመን ነውና፤ ዜናዊ አለው ማርቆስን የሚመጣ ነውና ወረኛ ንጉሥ እንዲሉ፡፡ በሰብዐ ወኀምስቱ ምእት ዐሡሩ ወሠሉሱ ዓመተ ዓለም፡፡ በኀምሳ ወኀምስቱ ምዕት ዓመተ ዓለም፤ በዕሥራ ምዕት ዐሡሩ ወሠሉሱ ዓመተ ምሕረት፤ ሠረቀ ለነ ወርኀ መስከረም ቡሩክ ያብጽሐነ እስከ ወርኀ ጥቅምት በሰላመ እግዚአብሔር አሜን፤ አበቅቴ 17 ሠርቀ መዓልት 1፤ ሕጸጽ 1= 19፤ ዐሡሩ ወተሱዑ ሠርቀ ሌሊት፤ ዕሥራ ወሡሉሱ ሠርቀ ወርኅ፤ አሚሩ ሠርቀ መዓልት፤ ሰዱሱ ሠርቀ ዕለት፤ ዮም በዛቲ ዕለት ዘአቅረብነ ለከ አምኀ ስብሐት ያዐርጉ ለነ መላእክት ተወከፍ ለነ እግዚአ ስብሐት። 

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!


Saturday, September 5, 2020

❖የ2013 ዓ.ም አጽዋማትና በዓላት ቀመር፦


የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር (ባሕረ- ሐሳብ )


“በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ” [መዝ.64(65)፥11]

▰▰▰▰▰▰▰▰▰
ዓመተ ዓለም = ዓመተ ምህረት + ዓመተ ኩነኔ (ፍዳ) = 2013 + 5500 =7513
ወንጌላዊ፦ በዓመቱ የሚሾም ወንጌላዊ ማለት ነው፡፡
ዓመተ ዓለም፥4
7513 ÷ 4 = 1878
1878 ፦ መጠነ ራብዒት ይባላል፡፡
7513 - 4×1878 = 1
ቀሪው ' 1 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ
ቀሪው ' 2 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ማርቆስ
ቀሪው ' 3 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ሉቃስ
ቀሪው ' 0 ' ከሆነ ዘመኑ ዘመነ ዮሐንስ ይሆናል።
ስለዚህ ቀሪው '1' ስለሆነ የዘንድሮው ወንጌላዊ ማቴዎስ ሲሆን ዘመኑ ዘመነ ማቴዎስ ይባላል።
•••
ዕለተ ቀመር፦ መስከረም አንድ የሚውልበት ቀን ነው፡፡
ዕለተ ቀመር= ዓመተ ዓለም+መጠነ ራብዒት÷7
= 7513 + 1878 =9391
= 9391 ÷ 7 = 1341 ቀሪ 4
ቀሪው '0 'ከሆነ ሰኞ
ቀሪው '1' ከሆነ ማክሰኞ
ቀሪው '2 'ከሆነ ረቡዕ
ቀሪው '3 'ከሆነ ሐሙስ
ቀሪው '4 'ከሆነ ዓርብ
ቀሪው '5 'ከሆነ ቅዳሜ
ቀሪው '6 'ከሆነ እሁድ መባቻ ይሆናል። በመሆኑም ዘንድሮ ቀሪው '4'ስለሆነ ዕለተ ቀመር ዓርብ ይሆናል።
•••
መደብ = ዓመተ ዓለምን በ19 በመግደፍ እናገኛለን። = 7513፥19=395 ደርሶ 8 ይቀራል። ስለዚህ መደብ 8 ይሆናል፡፡
•••
• ወንበር = ከመደብ አንድን ለዘመን በመተው ወንበርን እናገኛለን።
ወንበር =8 - 1= 7 ይሆናል።

• አበቅቴ ፦ጥንተ አበቅቴን በወንበር አባዝተን በ30 ገድፈን እናገኛለን።
አበቅቴ =11*7=77
77፥30= '2' ደርሶ ቀሪው '17' ሲሆን ዘንድሮ አበቅቴ '17'ይሆናል።

• መጥቅዕ፦ ጥንተ መጥቅዕን በወንበር አባዝተን ለ30 በመግደፍ(በማካፈል) እናገኛለን።
መጥቅዕ = 19×7 = 133
133 ÷ 30= 4 ቀሪው '13 'ስለሆነ መጥቅዕ ዘንድሮ '13 'ይሆናል።

“አበቅቴ ወመጥቅ ክሌሆሙ ኢይበዝሁ እም30 ወኢይኅዱ እም 30 ወትረ ይከዉኑ 30 ፤ አበቅቴ ቢበዛ መጥቅ ቢያንስ መጥቅ ቢበዛ አበቅቴ ቢያንስ ከ30 አይበዙም አያንሱም” ይህም ማለት በሌላ አገላለጽ መጥቅዕና አብቅቴ ተደምረዉ ዉጤቱ ከ30 መብለጥና ማነስ የለበትም፤ ሁሌ 30 ይሆናል፡፡ የዘንድሮዉ የ2013 ዓ.ም = 17+ 13 = 30

መጥቅዕ ከ14 በላይ ከሆነ በመስከረም ይዉላል፤
መጥቅዕ ከ14 በታች ከሆነ በጥቅምት ይዉላል፤

መጥቅዕ በመስከረም ቢዉል ጾመ ነነዌ በጥር፣ መጥቅዕ በጥቅምት ቢዉል ጾመ ነነዌ በየካቲት ይብታል።
ስለዚህ በዚህ ዓመት መጥቅዕ 13 ሲሆን ከ14 ያንሳል፤ ስለዚህም መጥቅዕ በጥቅምት ይዉላል፤
•••
ስለዚህ የ2013 መጥቅዕ ጥቅምት 13 ነው ሲሆን ዕለተ መጥቅዕ አርብ ይሆናል፡፡
•••
መባጃ ሐመር፦ መጥቅዕንና የባለመጥቅዕን ተውሳክ በመደመር በ30 በመግደፍ እናገኛለን፡፡ ከዕለተ መጥቅዕ ጀምረን እስከ ነነዌ ጾም መግቢያ ስንቆጥር 128 ቀን ይሆናል፡፡ በ30 ብንገድፈዉ 4 ቀሪ 8 ይሆናል፡፡ ይህም የቅዳሜ ተውሳክ ነው። ልብ ይበሉ የዕለት ተውሳክ ከቅዳሜ ይጀምራል፡፡
• ቅዳሜ፡ 128፥30=4 ቀሪ 8
• እሁድ፡127፥30=4 ቀሪ 7
• ሰኞ፡126፥30=4 ቀሪ 6
• ማክሰኞ፡125፥30=4 ቀሪ 5
• ረቡዕ፡124 ፥30=4 ቀሪ 4
• ሐሙስ፡123፥ 30= 4 ቀሪ 3
• ዐርብ፡122፥ 30= 4 ቀሪ 2

መባጃ ሐመር=13+2=15
መባጃ ሐመር ከ30 ስለሚያንስ ራሱ 15 ይያዝና መጥቅዕ በጥቅምት ስለዋለ ጾመ ነነዌ በየካቲት 15 በዕለተ ሰኞ ይውላል ማለት ነው።

• ጾመ ነነዌ፦ መጥቅዕና የዕለቱን ተውሳክ
በመደመር በ30 ገድፈን እናገኛለን፡፡ይህ ጾም ሕጸፅ የለውም፡፡ ሌሎችን አጽዋማት ተውሳኩን ከነነዌ ደምረን ከ30 ከበለጠ ለ30 እያካፈልን እናገኛለን።
•••
፩፥ ከነነዌ ጾም እስከ ዐቢይ ጾም 14 ቀናት አሉ። ስለዚህ የዐቢይ ጾም ተውሳክ 14 ይሆናል፡፡
፪፥ ከነነዌ እስከ ደብረዘይት 41 ቀኖች አሉ፡፡
41 ÷ 30 = 1 ደርሶ ቀሪው 11 የደብረዘይት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፫፥ ከነነዌ እስከ ሆሣዕና 62 ቀኖች አሉ፡፡
62 ÷ 30 = 2 ደርሶ ቀሪው 2 የሆሣዕና ተውሳክ ይሆናል፡፡
፬፥ ከነነዌ እስከ እስከ ስቅለት 67 ቀኖች አሉ፡፡
67 ÷ 30 = 2 ደርሶ ቀሪው 7 የስቅለት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፭፥ ከነነዌ እስከ ትንሣኤ 69 ቀኖች አሉ፡፡
69 ÷ 30 = 2 ደርሶ ቀሪው 9 የትንሣኤ ተውሳክ ይሆናል፡፡
፮፥ ከነነዌ እስከ ርክበ ካህናት 93 ቀኖች አሉ፡፡
93 ÷ 30=3ደርሶ ቀሪው 3 የርክበ ካህናት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፯፥ ከነነዌ እስከ ዕርገት 108 ቀኖች አሉ፡፡
108 ÷ 30 = 3 ደርሶ ቀሪው 18 የዕርገት ተውሳክ ይሆናል፡፡
፰፥ ከነነዌ እስከ ጰራቅሊጦስ 118 ቀኖች አሉ፡፡ 118 ÷ 30 = 3 ደርሶ ቀርው 28 የጰራቅሊጦስ ተውሳክ ይሆናል፡፡
፱፥ ከነነዌ እስከ ጾመ ሐዋርያት 119 ቀኖች አሉ፡፡ 119 ÷ 30 =3 ደርሶ ቀሪው 29 የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ ነው፡፡
፲፥ ከነነዌ እስከ ጾመ ድኅነት 121 ቀኖች አሉ፡፡ 121 ÷ 30 = 4 ደርሶ ቀሪው 1 ሲሆን የጾመ ድኅነት ተውሳክ 1 ይሆናል፡፡
•••

ከዚህ ተነስተን አጽዋማትንና በዓላትን ተውሳኮቻቸውን ከነነዌ ጋር እየደመርን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የ2013 የነነዌ ጾም መገቢያ የካቲት 15 ይሆናል፡፡
13+2=15 ስለሆነ ነው፡፡
★ ዓብይ ጾም ተውሳኩ 14 ነው
= 14 +15= 29 ሲሆን ስለዚህ ዘንድሮ በዘመነ ማቴዎስ ዓብይ ጾም በየካቲት 29 ይገባል ማለት ነው፡፡
* ደብረ ዘይት፡ ተውሳኩ 11 ነው፡፡
11+15 =26 ይሆናል፡፡ 26 ከ 30 ስለሚያንስና በየካቲት ስላለፍን ቀጣዩን በመጋቢት እናገኛለን። ስለዚህ በመጋቢት 26 እሁድ ደብረዘይት ይሆናል።
★ ሆሣዕና ተውሳኩ 2 ነው፡፡
= 2+15 =17 ሲሆን ከ30 ስለሚያንስና በመጋቢት ስላለፍን ቀጣዩን ሚያዚያን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ ሚያዚያ 17 እሁድ ይሆናል፡፡
★ ስቅለት ተውሳኩ 7 ነው፡፡
7+15= 22 ሲሆን ዘንድሮ በሚያዝያ 22 ዓርብ ስቅለት ይሆናል፡፡
★ ትንሣኤ ተውሳኩ 9 ነው፡፡
9 +15 = 24 ሲሆን ሚያዝያ 24 በዓለ ትንሣኤ ይውላል።
★ ርክበ ካህናት ተውሳኩ 3 ነው፡፡
3 +15 = 18 ሲሆን 18ን በሚያዝያ ስላለፍን በግንቦት 18 ረቡዕ ርክበ ካህናት ይሆናል።
★ ዕርገት ተውሳኩ 18 ነው፡፡
18 +15 = 33 ሲሆን ዘንድሮ ሰኔ 3 ሐሙስ በዓለ ዕርገት ይሆናል።
★ ጰራቅሊጦስ ተውሳኩ 28 ነው፡፡
28 +15= 43 ዚህ ሰኔ 13 እሁድ በዓለ
ጰራቅሊጦስ ይውላል።
★ ጾመ ሐዋርያት ተውሳኩ 29 ነው፡፡
29 +15=44
44 ን በ30 ገድፍን ቀሪው 14 ሲሆን ሰኔ 14 ሰኞ የሐዋርያት ጾም ይገባል።
ፆመ ድህነት ተውሳኩ 1 ነው፡፡
= 1 + 15 =16 በመሆኑም ጾመ ድህነት(የረቡዕና ዓርብ ጾም) ሰኔ 16 ይገባል።

▰▰▰▰▰▰▰▰▰
የአጽዋማትና የበዓላት ኢይወርድ ኢይዓርግ(ገደብ)
➛ጾመ ነነዌ ከጥር 17 በታች አይወርድም ፤ ከየካቲት 21 በላይ አይወጣም።
➛ ዐቢይ ጾም ከየካቲት 1 በታች አይወርድም ፤ ከመጋቢት 5 በላይ አይወጣም።
➛ ደብረዘይት ከየካቲት 28 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 2 በላይ አይወጣም።
➛ ሆሣዕና ከመጋቢት 19 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 23 በላይ አይወጣም።
➛ ስቅለት ከመጋቢት 24 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 28 በላይ አይወጣም።
➛ ትንሣኤ ከመጋቢት 26 በታች አይወርድም ፤ ከሚያዝያ 30 በላይ አይወጣም።
➛ ርክበ ካህናት ከሚያዝያ 20 በታች አይወርድም ፤ ከግንቦት 24 በላይ አይወጣም።
➛ ዕርገት ከግንቦት 5 በታች አይወርድም ፤ ከሰኔ 9 በላይ አይወጣም።

▰▰▰▰▰▰▰▰▰
# ልብ_በሉ
• ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ አይወጡም።
• በዓለ ደብረዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤና ጰራቅሊጦስ ከእሁድ አይወጡም፡፡
• ዕርገት ከሐሙስ
• ስቅለት ከዓርብ አይወጣም።
• ርክበ ካህናትም ከረቡዕ አይወጣም።