Thursday, September 17, 2020

❖ቤተክርስቲያንና አዲስ ዓመት፦


መለወጥ የሌለበት፣ ጸንቶ የሚኖረው እግዚአብሔር ዘመናትን ያፈራርቃል።

ዳንኤል፦ "ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤.."እንዳለው( ዳን 2፥2) ትናንትን በዛሬ ተክቶ፥ ዛሬን ደግሞ በነገ ያስረጃል፡፡ በጊዜ ዑደትም ውስጥ ብዙ ዓመታት አልፈው ብዙ አዲስ ዓመታት መጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም እግዚአብሔር በባሕሪው ነበር፤ አለ ይኖራልም።

ዓመታት ሂደው ዓመታት ቢመጡም በእግዚአብሔር ዘንድ በየዓመቱ የሚቀያየር ሀሳብ የሚለዋወጥ አጀንዳ ፈጽም የለም፡፡ ዘላለማዊው እግዚአብሔር በዘላለም እቅዱ መሰረት ሁሉን ያከናውናል። በዕቅዱም መሰረት ይኼው በክርስቶስ ኢየሱስ በልጁ የመስቀል ስራ ሰዎችን ወደራሱ እያቀረበ ነው። በየዘመኑም ይኼን ለማድረግ ይተጋል። ይኼን ሃሳቡንም ለመደምደም በዘመን ፍጻሜ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማይም በምድርም ያለውን ሁሉ ሊጠቀልል አቅዷል። (ኤፌ 1፥10)።

ታዲያ ዘመናት ሲፈራረቁ ሁሉ ነገር ወደ እግዚአብሔር የዘመን ፍጻሜ ዕቅዱ ይፈጥናል። በዚህ መፈራረቅ ውስጥም ለዕቅዱ የወሰናቸው የመረጣቸው በተወሰነላቸው ዘመን እና ቦታ ሁነው ወደልጁ መንግስት ይፈልሳሉ። ለዚያም ነው የዘመናት መፈራረቅ ሰው የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዕቅዱን የሚከውንበት እንደሆነ እንዲያስተውል ዕድል የሚሰጥ እንዲሁም በልጁ የሠራውን እንዲያምን፣ እንዲያደንቅ እና መግቦቱንም እንዳይረሳ ያደርጋል የምንለው።

የሰው ልጆች አሮጌ የተባለው ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት ሲመጣ እና ከዚህ ጋር በማያያዝ በማቀዳቸው ሕይወታቸው እንደሚለወጥ ያስባሉ ። በእርግጥ የዓመታት መለዋወጥ የሰውን ሕይወት ይለውጣልን? በመሠረቱ ሰዎች ብዙ ነገሮችን ማቀዳቸው ክፉ አይደለም። ለስጋዊ ኑሯቸው ሊጠቅም ይችላል። ነገር ግን ሕይወታቸውን ሊለውጥ አይችልም። የሰውን ሕይወት የጌታ ኢየሱስ የመስቀሉ ስራ እንጂ የሚለዋወጥ ዓመትም ይሁን ይኼን ተከትሎ ሰዎች የሚያቅዱት ዕቅድ አይለውጠውም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የመስቀል ስራ አምነው ዳግመኛ የተወለዱትን ብልቶቿን ሁሉ የመንፈሳዊ ሕይወት መለወጥ መሻሻልና ማደግ መስራት አለባት፡፡ ይኼን ተግባራዊ ለማድረግም የአሮጌውን ሰው ባህሪ አውልቀው አዲሱን ሰው መልበስ እንዲችሉ በቃሉ አማኞችን ልታንጽ ያስፈልጋል፡፡

ለዚያም ነው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ፊተኛ ኑሯችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ። በአእምሯችሁ መንፈስ ታደሱ፤ ለእውነትም ለሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።» የሚለው። (ኤፌ 4፥22-24)።

በእርግጥ የአዲሱ ሰው ማንነት በውስጣችን አለ። ጳውሎስ በመልክቱ፦ «አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፍፋችሁታልና፤ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታልና» ብሏል። (ቆላ 3፥10)። ነገር ግን ይህ የአዲሱ ሰው ባህርይ ሊገለጥ ሊታይ ይገባል። ይህም ባህርይ ፍቅር፣ ጽድቅ፣ ቅድስና በአጠቃላይ እግዚአብሔርን መምሰል ነው። ቤተክርስቲያን ይኼን ስታደርግ እንደቃሉ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያለች።
ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!!!

No comments:

Post a Comment