Sunday, December 27, 2020

❖ ያለ ክርስቶስ የሆነ ባለ ጠግነት፦

በክርስቶስና ያለ ክርስቶስ የሆነ ባለ ጠግነት፦

1ኛ/ ራዕይ 2:9፦ "መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ።
2ኛ/ ራዕይ 3:17፦ "ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ ጎስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ•••"

እግዚአብሔር ባለ ጠጋ የሆነ አምላክ ነው። ከእርሱ ባለ ጠግነት የተነሳ በጎ ስጦታውንና በረከቱን ለሚወዱትና ለሚፈሩት ይሰጣል። በዓለም ብዙ ባለጠግነት አለ። የዚህ ዓለም ባለጠግነት ከንቱ ነው። በባለጠግነቱም ብዛት ነፍሱ ሊያድን የሚችልና የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ የሚችል የለም።
(ማቴ 16:26 በማር 10:25)
ሁለት ዓይነት ባለጠግነት በአማኞች ዘንድ እናገኛለን፦
የመጀመሪያው ባለጠግነት በሰምርኔስ አማኞች የተገለጠ ነው። እነዚህ አማኞች በታላቅ መከራና በጥልቅ ድህነት ውሰጥ ሆነው ፍፁም መከራን እየተቀበሉ እሰከ ሞት ድረስ ይታመኑ ዘንድ የበረቱ ናቸው።ምንም መከራ ቢያገኙ ድህነት ቢፈትናቸውም እግዚአብሔር ግን ባለ ጠጎች ናችሁ ይላቸዋል።

ይህ ባለጠግነት፦
1ኛ/ የእምነት ባለጠግነት ነው።መከራና ድህነትን ተቋቁመው በእምነት እግዚአብሔርን እየመሰሉ በፅድቅ የሚኖርበት ነው። "እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግስት እንዲወርሱ የዚህ ዓለም ድሆች አልመረጠምን?(ያዕ 2:5)

2ኛ/ መንፈሳዊ በሆኑ ነገሮች ሁሉ ያለ ባለጠግነት ነው።አማኞች የመንፈሳዊ ፀጋ ተካፋዮች ናቸው። ክርስቶስ እሰኪ መጣ ድረስ አንድም የፀጋ ስጦታ አይገድልም። "በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጎችኋልና።(1ኛ ቆሮ 1:6)
በክርስቶስ የሆነ ባለ ጠግነት ስጦታ ነው።በእርሱ•••••ተደርገችኋል በማለት የሰውን ሰራና ልፋት ፋይዳ ቢስ ያደርገዋል።

3ኛ/ በማያልፍ በበጎ ስራ ያለ ባለጠግነት ነው።አማኞች በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ቤዛነት የፀጋ ሰራ የዳኑ ናቸው። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካም ስራ በጎ ስራ በእነርሱ ይገለጣል። "በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ,,,,,,,በበጎ ስራ ባለጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። (1ኛ ጢም 6:17-19)
እነዚህ ባለ ጠግነቶች በስምርኔስ አማኞች ታይተዋል።በዓለም ድሆች ሲሆኑ በመንፈሳዊ ነገር ብዙዎችን ባለ ጠጎች የሚያደርጉ ናቸው።2ኛ ቆሮ 6:8 ስለዚህ እግዚአብሔር በስጦታው በአማኞች በሚታየው ደስ ይለዋል።

ሁለተኛው ባለጠግነት ግን አማኞች ነን እያሉ በባለጠግነት አቆጥቁጠው ክርስቶስን ከቤቱ ወደ ደጅ የሚያወጡ ናቸው።

ይህ እግዚአብሔር ደስ አያሰኝም። በሎዶቅያ የታየው ይህ ነው።አንዳች አያስፈልገንም ባለጠጎች ነን በማለት ራስ የሆነውን ክርስቶስ አሰወጡ።ከደጅ ቆሞ ባለጠጋው ደጃቸውን ያንኳኳል። "እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ። (ራዕ• 3:20)
ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ ከየትኛው ባለጠግነት ዘንድ ነን? እግዚአብሔር ደስ ከሚያሰኘው በእምነት በመንፈሳዊና በበጎ ስራ የሆነ ባለጠግነት? ወይስ ክርስቶስን ወደ ውጭ የሚያደርግ የዚህ ዓለም ባለጠግነት?
ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!!

No comments:

Post a Comment