አቤቱ ሞትህን እንናገራለን ድንቅ ትንሳኤህን እናወራለን፦
አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለ እርሱ እንደሚናገር ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መስክሮአል። « ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ….. እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።» (ሉቃ 24:27:44)
መላው መጽሐፍ ቅዱስ በአቀራረቡ ከፍጥረተ-ዓለም እስከ ኅልፈተ-ዓለም ያሉ ነገሮችን በአብዛኛው ጠቅለል አድርጎ ሲናገር የክርስቶስን ሕይወት ግን ከልደቱ እስከ ሞቱና ትንሣኤው በዝርዝር ዘግቧል። ከሚናገርለት የብዙ ሺህ ዓመታት ጉዳይ እና ብዙ ሰዎች አንጻር ስናየው ስለ ክርስቶስ ከሁሉም የበለጠ ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። በተለይም መከራና ሞቱን(ከትንሣኤው ጋር) በተለየ ሁኔታ በየሰዓቱ ማለት ይቻላል የነበረውን ዝርዝር ሁኔታ በመናገር ከሌላው የሕይወት ክፍሉ የላቀ ትኩረት እንደሰጠው እናስተውላለን።
ይህም የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አጀንዳ በልጁ ከልጁ ለልጁ ራሱ እንደሆነ፤ በልጁ ያደረገው እያደረገው ያለውና በልጁ ዳግመኛ መምጣትም የሚያደርገው የዘላለሙ አጀንዳው እንደሆነ ልብ ይሏል።
የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሞት እንዲሁም ትንሳኤ በአጠቃላይ የመስቀሉን ሥራ ሊተካ፣ ሊተካከል ወይም ሊወዳደር የሚችል አንዳች ነገር የለም አይኖርምም። ስለሆነም የአንድ ሰሞን አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የዘወትር ርእሳችን ነው። በየዕለቱ ዘወትር የክርስቶስን መከራና ሞት ልናስብ ልንናገር ይገባል።
ሞቱና ትንሳኤውን ማውራት ማለት ጲላጦስ ፊት ቆመ፣ ተገረፈ፣ ተቸነከረ፣ ...ወዘተ ማለት ብቻ አይደለም ይልቁንም በመስቀሉ ሥራ የተገኘውን ውጤትም ጭምር እንጅ። ጳውሎስ ስለጌታ ራት በጻፈበት መልዕክቱ የጌታ እራትን ዓላማ ሲገልጥ ሞቱን መናገር እንዲሁም ማሰብ እንደሆነ ነግሮናል። « ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና። » (1ቆሮ 11:26)
ቢጻፍ ዓለም የማይበቃው ቢወራ የማይ'ሰለቸውን የክርስቶስ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትኩረት፤ የእግዚአብሔር መልእክት እንደሆነ ሁሉ የኛም የስብከታችን ትኩረት፣ የመዝሙራችንና የጸሎታችን ማዕከል ነው። የቤተክርስቲያን የዘወትር ርእሷ፤ የሁልጊዜ መልእክቷ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ብቻ ነው ሊሆንም ይገባል። ጳውሎስ ወሬው ሁሉ እውቀቱ ሁሉ ኑሮውም ጭምር ለዚህ ነበር። (1ቆሮ 1:23 1ቆሮ 2:2 ፊልጽ 3:8-9)
ሰው የእግዚአብሔርን መልክ እየገለጠ እንዲኖር ቢፈጠርም ፈቃድ ያለው ፍጥረት ስለሆነ ፈቃዱን ተጠቅሞ ለእግዚአብሔር እንዲገዛ፣ እርሱን እንዲያከብር አትብላ የሚል ትዕዛዝ አግዚአብሔር ሰጥቶታል። (ዘፍ 2:16-17።)
ነገር ግን በሰይጣን ተንኮል በሔዋን መተላለፍ አዳም በመተላለፍ አትብሉ ከተባሉት ከዛፉ በላ። ከዛፉ በበሉ ጊዜ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ አመጹ። አዳም ትሞታለህ በተባለው መሠረት ወዲያው በስጋ አልሞተም ነገር ግን ከእግዚአብሔር በመንፈስ ተለየ (በመንፈስ ሞተ)።
የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ተለየ(ሞተ)። ከኤደን ገነት አባረራቸው። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ሕብረታቸው ተቋረጠ። በኋላም ዘጠኝ መት ሃምሳ ዓመት ኑሮ በስጋም ሞተ። ኃጢአት ሞትን አመጣበት። በዚህ ምንክያት ኃጢያት በአንድ ሰው ምክንያት ወደ ዓለም ገባ። ሞት የኃጢያት ውጤት ነውና በኃጢያትም ምክንያት ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ። (ሮሜ 5:12)
መጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ በሆነ መልኩ እንደሚነግረን፥ ከተካፈልነው የኃጢአት ተፈጥሮ የተነሳ፦ " ሁሉ ኃጢያትን ሠርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል" ይላል። (ሮሜ 3:23)
በአንዱ አዳም አለመታዘዝ ሁሉ ኃጢያተኛ ሆነ ከእግዚአብሔር ክብር ጎደለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ታላቅ ቁጣ ሥር ነው ያለው። የሰው ልጅ ሙት እና የእግዚአብሔር ጠላት ሆነ። (አፌ 2:1-3 ቆላ 1:20-21)
የኃጢያት ደመወዝ ሞት ነውና ለዘላለም የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ተለይቶ ቆዬ። (ሮሜ 6:23)
እግዚአብሔር ግን የምህረት አምላክ ሰለሆነ ለወደቀውና የዘላለም ፍርድ ለሚጠብቀው የሰው ዘር ሁሉ የምሕረት ዕድል ሰጠን። ስለዚህ በዘላለም ክብር የነበረው አምላክ እኛን ለማዳን በስጋ ተገለጠ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ መስቀል ላይ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ የሁላችንን ኃጢያት ተሽክሞ ምትክ ሆኖ ሊሞት ተሰቀለ። በኛ ላይ ሊያርፍ የነበረ የእግዚአብሔር ቁጣ በክርስቶስ ላይ አረፈ። እኛ መሞት የነበረብንን ሞት እሱ ሞተልን። በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን። አሁን የኃጢያት ስርየት አገኘን። (ሮሜ 3:25)
"እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥" ስለዚህ ክርስቶስ በሞቱ የኃጢያታችን ዕዳ ከፈለልን፤ እኛን ለማጽደቅ ደግሞም በአዲስ ማለትሜ በራሱ ሕይወት እንድንመላለስ ከሙታን ተነሳ። (ሮሜ 4:24-25 ኤፌ 2፣5)
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀራንዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለኃጢአታችን መስዋዕትን ሲከፍል የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተከናውነውልናል፡፡
የመጀመሪያው የኃጢአት ሥራ እና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ነው።
መስቀሉን ስንመለከት የኃጢአት ሥራ አስፈሪነትና አስቀያሚነት ይታየናል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአት ነው ክርስቶስን ከክብር ዙፋኑ ላይ ወደ እኛ እንዲመጣ ያደረገው፡፡ የሰው ኃጢአት ነው እርሱን የሀዘን ሰው ያደረገው፡፡ እኛን አሁን ባለንበት አሰቃቂ ክፋት እልቂት ጭከናና ጦርነት ሁኔታ ውስጥ የጣለን ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፣ ስለዚህ ኃጢአትን ይቀጣ ዘንድ ልጁ በመስቀል ተንጠለጠለ። ኃጢአት ለእግዚአብሔር ባህሪ የማይስማማው መሆኑን ኃጢአትን በክርስቶስ ስጋ ላይ ሲቀጣ እንገነዛባለን እናም እግዚአብሔር ጻድቅ ነው። ሮሜ 3:25-26
ሁለተኛው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው።
1ዮሐ 4:10 የታረደውን በግ በመስቀሉ ላይ ሆኖ ስናይ ሌላ የምናስተውለው ነገር የእግዚአብሔርን ፍቅር ነው። እኛ የሰው ልጆች በኃጢአት የቆሸሸ ሕይወት ያለን ነን፡፡ እኛ እራሳችንን ለኃጢአት ሸጠናል፣ በኃጢአት ውስጥ ዘቅጠናል፣ ጥላቻ፣ ነፍስ ግድያ፣ ስርቆት፣ ውሸት፣ አመንዝራ፣ ወዘተ ታሪካችንን ሞልቶታል፡፡ ከእነዚህ ከወደቅንባቸው ኃጢአቶች የተነሳ ንፁህና ፍፁም የሆነው እግዚአብሔር የዘላለም ፍርድ ሊሰጠን ይገባዋል፡፡
ነገር ግን በመስቀል ላይ የታረደውን በግ ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍቅርና የምህረቱን ብዛት እንገነዘባለን፡፡ ጻድቅ እግዚአብሔር ፍርዳችንን በንፁህ ጌታ ኢየሱስ ላይ አድርጎ እኛን ለማዳን እርሱ በእኛ ምትክ እንዲታረድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ይህ ከኛ የተነሳ ሳይሆን ከእርሱ ፍቅር ብቻ የተነሳ እንደተደረገ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ምን ዓይነት ፍቅር ነው፡፡ እኛን ጠላቶቹን እግዚአብሔር ወደደን። ይህንን ፍቅር በቃላት ለመግለፅ አይቻልም፡፡ ምን ማድረግ ይገባናል? መጽሐፍ ቅዱሳችን በውድ ልጁ እንዲያው የሠጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይኼን አደረገ ስለሚል በምስጋና እናወድሰው። (ኤፌ 1:6)
ሦስተኛ የእግዚአብሔር የዘላለም ዕቅድ ነው።
አንዳንዶች የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሞት እንደ ድንገተኛ አደጋ አድርገው ሊቆጥሩት ያስባሉ፡፡ በድንገት አዳምና ሔዋን ስለተሳሳቱ እግዚአብሔር እቅዱ እንዳይበላሽበት "በል እስኪ ሂድ ልጄ አድናቸው" ተብሎ የመጣ ድንገተኛ ሃሳብ አይደለም። ሲጀመርም ከዘላለም እግዚአብሔር ልጆቹ እንድንሆን ያሰበው በልጁ ስራ ነው። (ኤፌ 1:5)
ይኼን ሃሳብ ጴጥሮስ በመልክቱ ያጠናክረዋል። "ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ። (1ጴጥ 1:18-21)
ይህ የሚያሳየው የእርሱ የመስቀል ሞት በእግዚአብሔር ጥንት የታቀደ፤ የታሰበበት፣ ነገር ግን በድንገት ያልተፈፀመ መሆኑን ነው፡፡
በልጁ ሞት የኃጢአት ዕዳችን ተከፍሏል። ከእግዚአብሔር ቀጣ ተርፈናል። በልጁ ከሙታን መነሳት እኛም አብረን ከሞት መንደር ተነስተናል። የራሱን የእግዚአብሔርን ሕይወት ተካፍለናል፣ ጸድቀናል፣ ተቀድሰናል፣ ልጆች ሁነናል.....ወዘተ ይኼ ሁሉ በልጁ ሞት እና ትንሳኤ አግኝተን እንዴት ስለእርሱ አናወራ!
No comments:
Post a Comment