Friday, June 5, 2020

❖ዘመኑን ማወቅ፦

   ዘመኑን ማወቅ፦
          (ሮሜ 13:11-14)

"ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤" (ሮሜ 13:11-13)

ሰላም ለእናንተ ይሁን። ጳውሎስ በወንጌል ስለተገለጠው የእግዚአብሔር ጽድቅ በሚያወራበት በሮሜ መልዕክት ውስጥ ሰው እንዴት እንደሚጸድቅ፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ጽድቅ በተለያየ አቅጣጫ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል ዘግቧል። በዚህ በመረጥነው ክፍልም ዘመንን ስለማወቅ ይነግረናል። እኛም በሚከተሉት ሁለት ንዑስ ርዕስ ከፍለን እንመለከታለን።

1. ዘመኑ ምንድነው?፣

ዘመንን ማወቅ ታላቅ ጥበብ ነው። ዘመንን ማወቅ ጥቅም እንደነበረው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ይነግረናል። ለምሳሌ ዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ ከሆነ በኋላ እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ሁለት መቶ ከይሳኮር ልጆች አለቆች ነበሩ። (1ዜና 12:32።) 

ዛሬም በአዲስ ኪዳን ዘመንን ማወቅ የሚገባውን እናደርግ ዘንድ አስፈላጊ ነገር ነው። ዘመንን ያለማወቅ ችግር የክርስትናችንን ሩጫ እንደሚገባ እንዳንሮጥ መሰናክል ከሚሆኑብን ነገሮች አንዱ እና ዋናው  ነው።

 መቼም ዘመኑ የተገለባበጠበት፥ ዘመኑንም  ማስተዋል የተሳነው ክርስቲያን እንደዚህ ዘመን የበዛ አይመስልም። 

ጳውሎስ በዚህ መልዕክቱ ዘመኑን እወቁ የሚለን ከእኛ አንጻር ነው። ዘመኑ ለእኛ ለአማኞች ምንድነው? ዘመኑስ ምን ዓይነት ነው? ይኼን ያላስተዋለ አማኝ ብዙ ነገሩን ይስታል። እግዚአብሔር አብ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሳ በልጁ ወንጌል ለጠራን በክርስቶስ የመስቀል ሥራ አምነን ለዳንን ለእኛ ለአማኞች ዘመኑ ምንድነው? ዘመኑን ማወቅ ካለብን በእርግጥም ለእኛ ለአማኞች ዘመኑ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ሰዓት ነው ይለናል።

ከእንቅልፍ መነሳት ማለት ምንድነው?

ይኼን ለማብራራት ጳውሎስ እንዲህ ይለናል። "ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል"። 

 የሌሊትን ማለፍ እና የቀንን መቅረብ ሁኔታ በአትኩሮት ስናጤን በርግጥም ጳውሎስ ምን ሊለን እንደፈለገ ይገባናል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ሦስት የተለያዩ ጊዜዎችን ይነግረናል። ጊዜዎቹም ሌሊት፥ ቀን እና በሌሊትና በቀን መካከል ያለ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ጊዜ ነው። ሌሊቱ የሚለው በክርስቶስ ከማመናችን በፊት የነበረውን በጨለማ ወይም በኃጢአት የነበርንበት ጊዜ ነው። ቀን የሚለው ደግሞ የክርስቶስ መምጣትና ከዚያ በኋላ ያለውን የዘላለም ዘመንን ነው። ሦስተኛው ደግም ከእንቅልፍ የምንሳበትን ወቅት ነው።

በእርግጥ ከእንቅልፍ የመነሻ ጊዜ በአሁኑ የሰለጠነው ዓለም የተለወጠ ቢሆንም ያኔ እዚያ መልክቱ የተጻፈበትን ዘመን ስንመረምር ሰዎች ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ከሌሉቱ 10:30 ጀምሮ እስከ 11:30 ባለው ውስጥ እንደሆነ ታሪካዊ ዳራዎች ያመለክታሉ። በእርግጥ አሁንም ራቅ ወዳሉ የገጠር የሃገራችን ክፍሎች ስንሄድ ሰዎች ከእንቅልፋቸው የሚነሱት ከላይ በጠቀስኩት የሰዓት ክልል ውስጥ ነው።

ይኼ ከእንቅልፍ የመነሻ ጊዜ የእኛን ከጨለማ ማለትም ከኃጢአት ባርነት ወጥተን አሁን በእምነት በክርስቶስ ድነን ያለንበትን ጊዜ ይወክላል።  አዎ!  አሁን በክርስቶስ አምነን ከዚያ ከጨለማ ከሌሊቱ ጊዜ ወጥተናል። 

መጽሐፍም "ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን.." ይለናል። (1ጴጥ 2:9።)  በጌታም ብርሃን ሁነናል ነገር ግን እንደዚህ የሮሜ ክፍል አውድ ወደሙሉ ቀን ወይም ሙሉ ብርሃን ገና አልደረስንም። ወገግታው ላይ ነን።  ለዚያም ነው "ቀኑ" ተብሎ የጠራውን የክርስቶስን ዳግመኛ መገለጥ "ቀኑ ቀርቧል" የሚለን ጳውሎስ።

2. ለምንድነው ዘመኑን እንድናውቅ የተፈለገው?

ጳውሎስ ለምንድነው ዘመኑን እንዲያውቁ ወይም እንድናውቅ የፈለገው ለሚለው ጥያቄ  መልሱ ለዘመኑ እንደሚገባ እንድንኖር ነው። ዘመኑን አውቀናል እርሱም ከእንቅልፍ መነሻ ነው። 

ከእንቅልፉ የሚነሳ ሰው ደግሞ የሌሊት ልብሱን አውልቆ የቀኑን ልብስ ይለብሳል። ለዚያም ነው ጳውሎስ "ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፤ " የሚለን። 

ሌሊቱ ስላለፈ ቀኑ ስለቀረበ የሌሊቱን ልብስ ማለትም የጨለማን ሥራ በማውለቅ የቀን ልብስ መልበስ አለብን። 

እኛም ሌሊቱ(በክርስቶስ ከማመናችን በፊት የነበረው ጊዜ) አልፎ ከእንቅልፍ የምንነሳበት ጊዜ ላይ ነን። "ቀኑ" ማለትም የክርስቶስን ምጻት ከፊት ለፊታችን ቀርቧል። ታዲያ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር ልንለብስ ይገባል። 

ጳውሎስም "በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤" ይለናል። ይልቁንም ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን እየቀረበ ስለሆነ (የስጋ ትሥሳኤ) ኢየሱስን ልንለብስ ይገባል። 
ኢየሱስን መልበስ ሲባል  የኢየሱስን ባህሪ ፍቅርን፣ ጽድቅን፣ ቅድስናን..በሕይወታችን መግለጥ ነው።

No comments:

Post a Comment