☞መንፈስ ቅዱስ የሕይወት ውኃ ወንዝ ነው፦
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲስተምር፦
"በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ ይላል "ቅዱስ ወንጌል
(ዮሐ 7፥38)
❖ ይህን የተናገረው ለማን እንደሆነ ሲገልጽ፦
"ይህን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስላላቸው ስለ መንፈስ ተናገረ፤ ኢየሱስ ገና ስላልከበረ [ስላልተሰቀለ ማለት ነው] መንፈስ ገና አልወረደም ነበርና" ብሏል።
ወንዝ ሳያቋርጥ የሚፈስ ነው የመንፈስ ቅዱስ ፀጋና በረከትም ለሚቀበሉት ሁሉ ያለማቋረጥ ሲሰጥ ይኖራል።
❖ ቅዱስ ጴጥሮስ በሃምስኛው ቀን ለደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ መውረዱን ሲያስረዳ፦
እግዚአብሔር ይላል፦
"በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ"።
(የሐዋ 2፥17-18)
☞ ወንዝ የፈሰሰበት ሁሉ ይለመልማል ያፈራል። መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሁሉ በእግዚአብሔር ፀጋ ይለመልማል የእግዚአብሔር የሆነውን ያፈራል ።
☞ ሕዝቅኤል የመንፈስ ቅዱስን ፀጋና በረከት ከመቅደሱ የሚፈስ የሕይወት ውኀ መሆኑን ገልጿል።
ከመቅደሱ የሚወጣ ዉሃ ወደ ምስራቅ ሲፈስ ይመለከታል፡፡
ሰውየው (የሚያሳየው መልአክ ማለት ነው) ገመዱን በእጁ ይዞ 1000 ክንድ ለካ፡፡
☞ በዉሃው ውስጥ አሻገረኘ ዉሃው እስከ ቁርጭምጭሚት ደረሰ።
☞ ሁለተኛ ሲሻገረው እስከ ጉልበት።
☞ ሶስተኛ እስከ ወገብ ።
☞ አራተኛ እጀግ ጥልቅና ሰፊ ወንዝ በመሆኑ ማንም ሊሻገረው የማይችል ወንዝ ሆነ፡፡
❖ ወንዙ የእግዚአብሔርን በረከትና ፀጋ ዘልዓለማዊ ሕይወትን ይገልጻል፡፡
☞ እስከ ቁርጭምጭሚት በዘመነ አበው የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ፣
☞ እስከ ጉልበት በዘመነ መሳፍንት የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ፣
☞ እስከ ወገብ በዘመነ ነቢያት የነበረውን የእግዚአብሔር በረከትና ፀጋ ደህንነት፣
☞ ማንም ሊሻገረው የማይችለው ዉሃ በጌታችን በኢየሱስ ክረስቶስ የተሰጠውን በረከትና ፀጋ ዘልዓለማዊ ሕይወት የሚገልጽ ነው፡፡
ማንም ሊሻገረው የማይችል ታላቅ ወንዝ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና የሚለውን ያረጋግጣል።
☞ መሲህ የሕይወት ዉሃ መሆኑን ተናግሯል፡፡
☞ መንፈስ ቅዱስም የሕይወት ውሃ መሆኑን ተናግሯል።
☞ በርሱ የሚያምን የሕይወት ዉሃ ከርሱ እንደሚመነጭ አስተምሯል፡፡
❖ በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።
❖ ዉሃው ወደ ምስራቅ ባሕር በገባ ጊዜ የምስራቁ ባሕር ሙት ባሕር ነው፡፡ ዉሃው ይፈወሳል።
☞ ዉሃው የሚወክለው የረከሰውን ሕዝብ ሰለሆነ በመሲህ ያመነ ሁሉ ፈውስንና የዘልዓለም ሕይወትን ማግኘቱን ያረጋግጣል፡፡
❖ ዉሃው ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ በሕይወት የሚኖርበት መሆኑን ይናገራል፡፡
☞ ወንዙ በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል፡፡
ዉሃው የሚፈሰው እጅግ በበረሃማነት ወደሚታወቀው ወደ ይሁዳ ምድረበዳና ወደ ጨው ባሕር ነው፡፡ መራራው የጨው ባሕር የብዙ ዓሳዎችና ተንቃሳቃሽ ሕያዋን ፍጥረታት መኖርያ ይሆናል፡፡ ይህም የሆነው ጨዋማው ዉሃ በመቅደሱ ውሃ ስለተፈወሰ ነው፡፡
ረግረግና እቋሪው ግን ጨው እንደሆነ ይኖራል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመኑትን ይመለከታል፡፡ በወንዙ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ቅጠሉ የማይረግፍ ፍሬው ለሁልጊዜ የሚያፈራ አለ፡፡ ፍሬው ለመብል ቅጠሉ ለመድኀኒት የሕይወት ዛፍ ነው የሚወክለውም ዘልዓለማዊ ሕይወትን ነው፡፡
(ሕዝቅኤል 47፥1-12)
እግዚአብሄር ይክበር ይመስገን!!!
No comments:
Post a Comment