የዘላለም መኖሪያ
"ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥
በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም። መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤" ዘዳ 33:27
የሰው መሠረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፥ መጠለያ፥ ልብስ ናቸው።ልብስ እና ምግብ ኖሮን በኪራይ መኖሪያ ተጠልለን እንኖራለን።አንዳንዶች ይህንም ስላልቻሉ በየጎዳናው ያድራል።ቃሉ ለሁሉ የሚበቃ የዘላለም መኖሪያ እግዚአብሔር እንደሆነ ይነግረናል።ከእርሱ ርቃን በደጅ ያለን፥ ከፍቅሩ ተለይተን ራሳችንን በስቃይ የምንጎዳ፥ ያለ እርሱ ወጥታን ባክነን የምንመለስ፥ ያለእርሱ ዘምተን የተሸነፍን ፥ ያለ እርሱ ሮጠን ያልቀደምን ፥ ያለ እርሱ በልተን ያላማረብን፥ ያለ እርሱ ለብሰን የበረደን፥ ያለርሱ ሰብስበን የተበተነብን ሁሉ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር እንበል ብለን እንማልዳችኋለን።ወደ የዘላለም መኖሪያ ከተን ገብተን እንረፍ።ስለሚፈርስ ቤት፥ ዝናብ እና ነፋስ ስለሚያስገባ ቤት አይደለም የማወራችሁ።ከመከራ እና ከጉዳት የሚጠብቅ የዘላለም መጠለያ ስለሆነው አምላክ ነው።
ቃሉ እንዲህ ይለናል፦ "በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። እግዚአብሔርን። አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና።" መዝ 90:2 ይህ የዘላለም መኖሪያ የዘላለም አምላክ ነው።በመከራ ጊዜ መሸሸጊያ ነው።ከክፉ መዳኛ ነው።ወደ እርሱ የገቡ በውጭ ያለው የዓለም ነገር ያንስባቸዋል። እንደ እርሱ የለም።እግዚአብሔር ካለን ምንም አልጎደለን፥እርሱ ከሌለን ምንም የለንም፤ እኛም እንዳለን አንቁጠረው።ሕይወት በእርሱ መገኘት ውስጥ ስትሆን ነው በደስታ እና በባርኮት የምትጎበኘው።
የእስራኤል መኖሪያ ከነአን አይደለም።መኖሪያቸው የበረሀው ገነት እግዚአብሔር ነው።ዓለም ጭንቅ እየናጣት እኛ በደስታ የተሞሸርንበት የደስታ እልፍኝ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ትውልድ በርኩሰት ሲነድድ የእግዚአብሔር ልጆች መጠለያ መንፈስ ቅዱስ ነው።ተንከራታቾች ሆይ ወደ ዘላለም መኖሪያ ወደ ዘላለም አምላክ እንሰብሰብ።
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!
No comments:
Post a Comment