የመጨረሻው እራት፦
ዛሬ ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን እራት የበላበት እና እግራቸውን በትሕትና ያጠበበት ዕለት ነው፡፡ማቴ. 26፡20-29።ይህን እራት ጌታ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሊበላ በናፍቆት ይጠብቀው ነበረ፡፡ " እርሱም። ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤"ሉቃስ 22:15።
በሞት ዋዜማ ራት፡ በመከራ ዋዜማ ራት፡ ወዳጅ እንደሚሸሽ እየተረዳ ከወዳጅ ጋር ራት ይገርማል፡፡የመጨረሻ ነገር ትዝታ የሞላው ነው፡፡ልቡ ውስጥ ዘመናት የማያስረጁት ጥልቅ ፍቅር እና ክብር አለ፡፡ቃሉ እንዲህ ሲል አረጋገጠው፦ "ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።"ዮሐንስ 13:1 ይህ ሁላችንም እርግጠኛ ሆነን የምንናገረው ፍቅር ነው፡፡አምላክ አለን ወገን የሆነን፥ወዳጅ አለን ወገን ያደረገን፡፡ልባችን በዚህ ይታመን አጥብቆ ወዶናል፡፡አንስጋ የወደደን ለዘላለም ነው፡፡
ዛሬ ልዩ ነው፦ ደቀመዛሙርቱም እራት ከበሉ በኋላ የዘመሩበት የምስጋና ምሽት ነበር፡፡ ማቴ. 26፡30።
በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ- የሐዲስ ኪዳን ሥርዓት ሰርቷል፤አዲስ ኪዳን ስላደረገ ስለዚህ ዕለቱ የአዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ማቴ. 26፡26።
የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቧል፤ስለዚህ ዕለቱ ሕጽበተ እግር ሐሙስ ተብሏል፡፡ዮሐ. 13፡2-14።
በአረንጓዴው የአትክልት ስፍራ ጸልዮአል፤ስለዚህ ዕለቱን ጸሎተ ሐሙስ ተብሏል፡፡ማቴ. 26፡36-41
እስከ መጨረሻ ከወደዳቸው መካከል በችኮላ የሚታወቀው ጴጥሮስ፥ ተጠራጣሪው ቶማስ፥ አፍቃሪው ዮሐንስ፥ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ ይገኙበታል፡፡ይህን ሁሉ ችሎ እስከ መጨረሻው መውደድ እጅግ ይገርማል እኛ ሰውን ሳናውቀው ወደነው ስናውቀው እንጠላዋለን፡፡
ይህ ምን አይነት ፍቅር ነው? ስንደክምም ስንበረታም ስናጠፋም ስናለማም የማይለወጥ ፍቅር፡፡ይህ ፍቅር
በትህትና ሲገለጽ መምህሩ ተማሪዎችን፥ ጌታ ባሪያዎችን እግራቸውን ሲያጥብ አየን፡፡እሱ ያላጠበው አይነፃም፡፡እሱ ያላጠበው ከእርሱ ጋር እድል የለውም፡፡ከዘላለማዊ በደል በደሙ ያጠበን ይህ ትሑት ሊቀካህናት ነው፡፡ይህን የተደረገልንን እናስተውላለን?እርሱም በቃሉ ያደረኩላችሁን ታስተውላላችሁን ? ብሎናል።ልዑሉ በፍቅር ጎንበስ ማለቱ ይግባን፡፡ውለታ አናጥፋ፡፡ ዝቅ ብሎ ከፍ ማድረጉን አንርሳ፡፡በእውነት ፍቅሩን አስተዋይ ትውልድ መሆን አለብን፡፡መተጣጠቡን እርስ በእርሳችን እንዲሁ እናድርገው፡፡ለበዓሉ ብቻ ሳይሆን የዘወትርም ተግባራችን ይሁን፡፡ቃሉ ይህን ብታዉቁ ማወቅ ብቻ አይጠቅምምና ብታደርጉ ብፁዓን ናችሁ ይለናል፡፡ክርስትና የፍቅር ድርጊት እንጂ የአፍ ማስመሰል አይደለም፡፡ጌታ በሕይወት በድርጊት ነው ያስተማረን፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!
No comments:
Post a Comment