የእግዚአብሔር ጸጋ
የእግዚአብሔር ቃል "ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤" ይላል፡፡ወደ ቲቶ 2:11 የተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ፡-
1/ ዘር ሳይለይ ሰዎችን ሁሉ ያድናል!
2/ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ያስክዳል!
3/ የተባረከውን ተስፋችንን የኢየሱስን መገለጥ ያስጠብቃል!
4/ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንድንኖር ያስተምረናል!
የእግዚአብሔር ጸጋ የተገለጠው ኢየሱስ በሥጋ ሲገለጥ ነው፡፡ ቃሉ "ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።" እንደሚል፡፡ ዮሐንስ 1:14 የተገለጠዉ ጸጋ ለዓለም ህዝብ ሁሉ ይበቃል፡፡ ሁሉንም ለማዳን በቂ የሆነ ጸጋ ነዉ፡፡ በጸጋው ለመዳን ፈቃደኝነት እና እውነተኛ እምነት ያስፈልጋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” ይላልና፡፡ መዳን በነፃ ነው፤ ሰው ምንም ዋጋ አይከፍልበትም፡፡ ስላልከፈልንበት መዳናችን ዋጋ አልተከፈለበትም ማለት አይደለም፡፡ እርሱ ከፍሎልን ለእኛ ግን ስናምን እንዲያው (Freely) በነፃ ሰጠን፡፡ “"በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።" ሮሜ 3:24 እምነቱ እንኳን ከእኛ ነው ብለን እንዳንሞግት “የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” አለን፡፡ እንዲያው የእርሱ ሥራ ይደንቃል፡፡ አሜን ብለን እንስማማ!! እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ ሊያድን እጁን በጸጋ ዘርግቷል፤ እኛም የልባችንን እጅ በእምነት እንዘርጋ።
ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!!
No comments:
Post a Comment